(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡2009 እና

የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

ዛሬ ዛሬ ዕውን በዓለማችን በተለይ በሀገራችን ስለኾኑና እየኾኑ ስላሉ ኹለንተናዊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኹነቶች በትክክል እንደውሃ በጠራ መንገድ - ለኹሉ በሚስማማ - ለኹሉ በሚገባ - በሃሰት አይደለ በዕውነት፤ በስፋት አይደለ በልኬት፤ በድብቅ አይደለ በግልጽ፤ በልዩነት አይደለ ያለልዩነት፤ ከክፋት አይደለ በቅንነት፤ በሴራ አይደለ በሥልጣኔ፤ በባርነት አይደለ በነጻነት፤ በድንቁርና አይደለ በዕውቀት፤ በፍርሃት አይደለ በድፍረት፤ በመቀያየር አይደለ በወጥነት፤ በጥላቻ አይደለ በፍቅር፤ ለማራራቅ አይደለ ለማቀራረብ፤ በውግንና አይደለ ያለውግንና - በንጹህ መንገድ ሊናገር የሚችል ማነው? ሊጽፍ የሚችል ከቶ ማን ሊኾን ይችላል? በጋራ ስለጋራ ለጋራ በሚጠቅሙን ሰብዓዊና ሀገራዊ ኹለንተናዊ ጉዳዮቻችን ዕውነት አንዲትና ዘላለማዊት ብትኾንም በመረጃና በማስረጃ መለያየት - እኛ እጅጉን ተራርቀናል፤ አንዳችን ሌላችንን ለማወቅ፣ ለመረዳትና ለማስተዋል እጅጉን ተቸግረናል፡፡ አንድ እንዳንኾን እጅጉን እንቅፋት በዝቶብናል፡፡ ባንለያይም ትርጉም ባለው መንገድ ከተመለከትነው በእምነት (በአስተሳሰብና አመለካከት)፣ በእውቀት (በመረጃ፣ በስልት፣ በስትራቴጂና በተልዕኮ) እንዲሁም በተግባር (በድርጊት) እጅጉን ተለያይተናል፡፡ ተራርቀናል፡፡ ለምን ይኾን? ማን እንዲጠቀም? ስለምንስ እስከዛሬ መንቃት አቃተን? ማስተዋልስ ተሳነን? አስቀድመን መረዳት እንኳ ባንችል ከኹለንተናዊ አስከፊ ጉዳቶች በኃላ እንኳ ለምን መረዳት አቃተን? ዛሬ ዛሬ እጅግ በሚያሳዝን፣ በሚያሳፍርና በሚያሳቅቅ ኹኔታዎች - በተነገሩን፣ ባነበብነውና በምናየው ኹለንተናዊ ነገር የተደነባበርን ብዙዎች አይደለንምን? በአንድ ፍጻሜ ላይ እጅግ የተለያየ ኸረ እንዲያውም እጅጉን በተቃርኖ ውስጥ ባለ ጽንፍ የቆምን ብዙዎች አይደለንምን? ዕውን ከዚህ ኹለንተናዊ መዘበራረቅና መደነባበር ብሎም ከዛ ውጤት ከሚታዩ ገጽታዎች የሚያላቅቀን ማን ይኾን? ዕውን ጉዳቱ አልተሰማን ይኾን? የዕውነት መታጣት አልጎዳንም ይኾን? ለዚህ ትክክለኛ ወጥ፣ ያልተዛባና ቀናኢ መረጃና ማስረጃ ሊሰጠን የሚችል ማን ነው? ኹሉን ያለ ልዩነት በመያዝ አጥርቶ የተመለከተንና የሚመለከተን ማን ይኾን?

ምድር ተናገሪ

ብሶትሽን አውሪ!’

አንቺ የሰው ልጅ መገኛ - ፈጣሪ የተገኘብሽ - ሰው መምጣት ብቻ ሳይኾን የሚመላለስብሽ፤ ከፍ ቢል ወደ ላይ ካንቺ አንጻር የሚታይ - ወደ ታች ቢወርድ ማንጸሪያው የኾንሽ ክብርት መለኪያ ዕውን ካንቺ ያልወጣ ማነው? ከፍጡር እስከ ፈጣሪ ካንቺ የተገኘብሽ አይደለሽምን? ማን ነው አስገኚውን ያስገኘ? አንቺ አይደለሽምን? አንቺ የማትጠቢና የማትሰፊ - አንቺ ውለታ የማትረሺ - ለተጉብሽ በታሪክ ብዙ ዘመን እንዲኖሩ የምታደርጊ - አንቺ እልፍ አላፎች ያለፉብሽና መሰሎቻቸው የሚኖሩብሽ - ትውልዶችን አሳልፈሽ በትውልዶች ውስጥ የምትኖሪና የምታኖሪ ከሰው በፊት የነበርሽ - ከሰው ጋርም ያለሽ ብዙ የሰው ኹለንተናዊ ኹነቶችን ያሳለፍሽና በማሳለፍ ላይ ያለሽ አንቺ አይለሽምን?

ምድር ተናገሪ

ብሶትሽን አውሪ!’

ሰውን ያህል ክፉ - ሰውን ያህል ደግ፤ ሰውን ያህል ጨካኝ - ሰውን ያህል ሩህሩህ፤ ሰውን ያህል ትዕቢተኛ - ሰውን ያህል ትሁት፤ ሰውን ያህል ታማኝ - ሰውን ያህል ከሃዲ፤ ሰውን ያህል ሥልጡን - ሰውን ያህል ስይጡን የተሸከምሽ አይደለሽምን? አሸናፊንም ተሸናፊንም የተሸከምሽ አይደለሽምን? ያለፈንም ኾነ ያለንስ የምትይዥ አይደለሽምን?

ምድር ተናገሪ

ብሶትሽን አውሪ!’

ዕውን ካንቺ የተሰወረ - ሊሰወርስ የሚችል ከቶ ምን አለ? ሰው ተፈጠርኩ ቢል ካንቺ ላይ - ኖርኩ ቢል ባንቺ ላይ - ሠለጠንኩ ቢል አሻራውን ባንቺ ላይ በማኖር አይደለምን? አንቺ የህልውናው መሠረትስ አይደለሽ? አንቺ ዘርን ካልሰጠሸው - ፍሬን ካላፈራሽለት ማን ይሰጠዋል? ሠለጠንኩ ብሎ ቤት ቢሰራ መሠረቱ አንቺ አይደለሽ? አንቺ ካልፈቀድሽለት ከቶ እንደምን ሊቆም ይችላል? ተራባው ቢል ባንቺ ላይ ቆሞ፤ አፈራው ቢል አንቺን ተንተርሶ፤ ሀብት አለኝ ቢል አንቺንና ባንቺ ላይ ያሰፈረውን ተማምኖ አይደለምን? ያለ ስስት ቢረግጥሽ - አምኖብሽ አይደለምን? ምንስ አማራጭ አለው? ቢታመም መድህኑ ካንቺ የሚገኝ አይደለምን? ማንነቴ ቢል አንቺን ሰፍሮና ቆጥሮ አልያም ለክቶ በማስቀመጥ አይደለምን? ቢዋጋ - ከሱ በፊት ለነበርሽው በባለቤትነት አይደለምን? ሰው አፈቀርኩ ብሎ በንጹህ ልቦና ቢኖር ታውቂዋለሽ፤ በማፍቀሬ እርግጠኛ አይደለሁም ብሎ የክህደትን ሥራም ቢሰራ ታውቂዋለሽ፤ ሰው ከሰው ተደበቅኩ ብሎ ቢልከሰከስ ታውቂያለሽ፤ ሰው ከናትና ካባቱ ተደብቆ - አደረግኩ ቢል አንቺ በቦታው አለሽ፤ ሰው ሴራ ቢጎነጉን ታውቂያለሽ፤ ሰው በጎ ለመስራትም ቢማከር ታውቂያለሽ፤ የጦር ጀግና ነኝ ብሎ ቢፎክር ሲወድቅ ማረፊያው አንቺ ነሽ፡፡ ሰው ያላንቺ መኖር የማይችል ፍጡር አይደለምን? ሰው ከሰው ሊሰውር ይችላል - ካንቺ ግን ሰው ሊሰውር እንደምን ይቻለዋል? ታድያ ምድር ስለሰው የማታውቂው፣ ያልሰማሽውና ያልተመከትሽው ምን አለው? አንቺ የማታወቂውስ አንዳች ነገር እንደምን ሊኖረው ይችላል? በዕውነት ስለዕውነት ምድር ኾይ ጆሮሽ እንደምን ያለ ታላቅ ቻይ ነው? ምድር ኾይ አይኖችሽ እንደምን የማያንቀላፉ ናቸው? ምድር ኾይ ስሜትሽ እንደምን ያለ ጠንካራ ነው? ምድር ኾይ ማሕጸንሽ እንደምን እጅጉን የሰፋ ነው? ምድር ኾይ ትከሻሽ ምን ያክል ቻይ ይኾን? አንቺ የቻልሽውን ማን ይችላል? ማንስ ይሸከማል?
Full Website