yordimassa@yahoo.com

እኛ ኢትዮጵያውያን ላለፉት ሶስት ሺ ዘመናት ከሰማንያ በላይ ብሄርና ብሄረሰቦች ይህችን ሃገር ሃገራችን ብለን፣ እንዲሁም በተለያዩ የሃይማኖትና የዕምነት ተቋማት እንደየዕምነታችን ተከባብረን በኖርባት ምድር ላይ ካባቶቻችንና ካለፉት መሪዎች በውርስነት የተቀበልናቸው በርካታ መልክምና አንዳንድ ቁርሾዎች መኖራቸው አይካድም። ካለፈው ታሪካችን ተምረን ብዙ ተአምራት የምንሰራበትና ከመጥፎ ታሪኮቻችን ደግሞ ትምህርት ወስደን እነዚህን መጥፎ ቅርሶች ወደ መልካም በመቀየር ከሰው በታች ሆነን እንድታይ እያደረገን ያለውን ድህነት ታሪክ ሆኖ እንዲቀርና በዓለም መድረክ ላይ ቀና ብለን እንድንቆም የሚያስችል ተግባር በመፈፀም ፈንታ ሊፈቱ የማይችሉና መልስ የሌላቸው ጥያቄዎች ላይ እራሳችንን በማድከም፣ ታሪክን እንደ አንድ መማሪያ ሃሳብ ሳይሆን እንደ ኑሮአችን በመውሰድ የመልካም ታሪክ ሃገር እያልን ያቆየናትን ሃገር በመጥፎ ታሪክ ተክተን ሃገሪቱን ለማሻሻል ሳይሆን ሁላችንም በየፊናችን አኩራፊና ነቃፊ ብቻ ሆነ ሃገራችንን ወደ መጨረሻ እርከን እየገፋት እንገኛለን። አንዳንዴ መንግስት የወጣበትን ህዝብ ይመስላል ሲባል ዕውነት አይመስለኝም ነበር ወይም ከነማሻሻያው ልቀበለው የሚል ዕምነት ነብረኝ። አሁን ሳየው ግን ነገሩን ደግሜ ደጋግሜ እንዳጤነው እገደዳለሁ። ባሁኑ ሰኦእት በሃገራችን የፈጠጡ የሰላምና የፍትህ፣ የኢኮኖሚ፣ የዜጎች በሰላም ወጥቶ በሰላም መመለስ መብቶች ወዘተ ከባባድ ህገመንግስታዊ ጥያቄዎች ፈጠው የሚታዩበት ልዩ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ይሁን እንጂ መንግስት እነዚህን አንገብጋቢ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን ለራሱ በሚመቸው መንገድ ብቻ በመተርጎም ለራሱ የፖአልቲካ ፍጆታነት ሲያውላቸው ማየት እጅጉን የሚያሳዝን ቢሆንም በሃገራችን ውስጥ ያለ ዕውነታ ነው። አሁን ሃገራችንን እየመሩ ያሉ ልሳናቸውን እንጂ ህሊናቸውን ባግባቡ ያልገሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን በመጡ በመጀመሪያዎቹ ወራት “ካሁን በኋላ ወደፊት እንጂ ወደኋላ ማየት የለም፣ ትናንት ለትናንት መተው አለበት። ያለፉት በደሎችን ሁሉ ይቅር ብለን ሁላችንም ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደ ብልፅግና ከፍታ እንወጣለን። ወዘተ ” ሲሉ ህዝቡ እንደ አንድ መሪ ሳይሆን ከፈጣሪ መልእክተኛ ወይም ነቢይ ጋር እስከ ማነፃፀር የሄደ ከፍተኛ ድጋፍና ተቀባይነት አስገኝቶላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ቃላቸው ከቃል በላይ ሳይሆን ቅርቶ በተለይም ህወሓትን ያጠቁ እየመሰላቸው የትግራይ ህዝብ ላይ ከፍተኛ የሆነ የስነ ልቦናና የኢኮኖሚ ጦርነት አወጁበት፣ በየአከባቢው በብሄራቸው ምክንያትየሚታረዱ አማሮች፣ ትግራዮችና ሌሎች ብሄረሰቦችንም እንዳልተበደሉ በተለያዩ መንገዶች ድምፃቸው ወደ ዓለም ህብረተሰብ እንዳይደርስ የራሳቸው ሚዲያዎችን በማደራጀትና በመክፈል፣ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በማስነዛትና የሰዎችን ዕልቂት እንደ አንድ ተራ ክስተት በማቅረብ በሃገርና በወገን ላይ ይህ ነው የማይባል ኪሳራ አድርሰዋል። በተልይም ደግሞ የራሱን ዜጎች በየምድረበዳውና በየባህሩ እየጠፋ እንዲቀር ያደረገና ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ስልጣን ላይ በጉልበት ተቀምጦ የተቃወመውን በመግደልና በማጥፋት የሚታወቀው ፋሺስቱ የኤርትራ ፕረዚደንት እንደ ዋነኛ አማካሪውና ወዳጅ አድርጎ መንቀሳቀሱ ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢያንስ ስለኢትዮጵያ ደንታ የሌለው እንዲሁም በተገኘ መንገድ ሁሉ የፈሰሰ ደም ፈሶ የሱ ስልጣን ማስቀጠል የሚሻ መሆኑን በህዝቡ ዘንድ እየታወቀ መጥቷል። ሃገራችን ኢትዮጵያ ካልተበታተነች በስተቀር ኤርትራ ሰላም አታገንም እንደፈለግነውም ኢትዮጵያን መበዝበዝ አንችልም ብለው የሚያምኑና በፅናት የሚታገሉ ጠላት እንደ አንድ አማካሪና መሪ አድርጎ መቀበል በራሱ የሚናገረው ከባድ የሆነ ምስጢር አለ። ከዚያም በላይ እኝህ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰዎች በግፍ ተገደሉ ሲባሉ አስከሬንን በብሄር በመከፋፈል ከዚህ ብሄር ይህንን ያህል ሰው ሞተ ከማለት በስተቀር እነዚህ ንፁሃን ዜጎች በሳቸው አመራር ልፍስፍስነት አሊያም ለዜጎች ጥበቃ ለማድረግ ካለመፈለጋቸው የተነሳ መሞታቸውን እንኳ ለማሰብ አይፈልጉም። በተለዩ ጊዜያ በሃገራችን ከተራ አርሶ አደር ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የመንግስት ባልስልጣናት በተለያዩ ጊዜያት ሲገደሉ መንግስት ዜጎቹን በሰላም የማኖር አቅሙ የመከነና መጣልን ተብሎ የተዘመረለት የዶክተር ዓቢይ ለውጥም መጨንገፉ በግልፅ ታይቷል። ከዚህ በኋላ ሌላ ተአምር መጥቶይህንን የበሰበሰና የወደቀ ስርዓት ያነሳዋልየሚል ተስፋ ባይንርም እንኳ አሁንም ሃገሪቱ ሙሉ በሙሉ ከመበታተኗ በፊት ዶክተሩ ተፀፅተው ሃገሪቱን ብቃት ላላቸው ሽማግሌዎችና የሽግግር መንግስት ማስረከብ ቢችሉ ቢያንስ ላለፈ ይቅርታ የሌለው ጥፋታቸው ማካካሻ ሆኖ ያገለግላል። ሃገራችን በየትኛውም ዘመኗ እንደ ዶክተር ዓቢይ ያለ ግብዝና በሃሰት ላይ ሃሰት እየተናገረ የሚመራ መሪ አጋጥሟት አያውቅ። ዶክተር ዓቢይ በመቶዎች የሚቆተሩ የማይፈፀሙ ውሸቶችን ለህዝቡ በመንገር ለጊዜው ሲያደናግሩት ቢቆዩም አሁን ግን ሁሉም ነገር ኮለል ብሎ የታየበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
Full Website