አቶ ጌታቸው፦በመሰረቱ አንድ ድርጅት አለ የሚባለው የቆመለት ፕሮግራም ካለ ነው፤ ኢሕአዴግ የቆመለት ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ የሚባልና ሁሉም ድርጅቶች ከሞላ ጎደል እናምንበታለን የሚሉት ፕሮግራም አለ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የድርጅቱ ሕገ ደምብ ነው ድርጅቱን ድርጅት የሚያደርገው፡፡ አለ? የለም? ለማለት እነዚህን ጥያቄዎች getachew-reda-zemen.jpg በአዎንታዊ መመለስ ተገቢ ነው፡፡ ድርጅት አለ፤ የኢህአዴግ ጽ/ቤት የሚባል አለ፤ እኔ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ነኝ፡፡ ዋናው ነገር ፕሮግራሙ እየተከበረ ነው? ፕሮግራሙን ለማስፈጸም የሚያስችሉት የድርጅቱ ሕገ ደንቦች በስራ ላይ እየዋሉ ናቸው ወይ የሚለውን ጥያቄ መመለሱ ነው ተገቢ የሚሆነው፡፡
ከዚሕ አንጻር ፕሮግራሙን ከሞላ ጎደል ባለፈው ጉባኤ ላይ ተስማምተን የወጣንበት ሁኔታ አለ፡፡ እርግጥ አዝማሚያዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ ድርጅቶች በይፋ የኢሕአዴግ ፕሮግራም አይመለከተንም ብለው የሚናገሩበት ጊዜ አለ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ባለፈው ጉባኤ ላይ የተጠቃለለው ፕሮግራማችን ለውጥ አያስፈልገውም የሚል ነው፡፡ በእኛ በኩል ዋናው መሰረታዊ ነጥብ ፕሮግራሙን በተግባር ላይ ለማዋል ምን ያህል ዝግጁነት አለ የሚለው ነው፡፡ ኢህአዴግ በጉባኤው እስካረጋገጠው ድረስ ፕሮግራሙ አለ ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ሕገ ደንቡን ከመተግበር አንጻር ውስንነቶች አሉ፤ በተግባር ማየት ያለብን ግን ኢህአዴግ ለፕሮግራሙ፣ ለሕገ ደንቡስ ምን ያህል ታማኝ ነው? ሁሉም ድርጅቶች ፕሮግራሙን ማእከል ያደረገ አንድነታቸው በምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚሉት ጥያቄዎች ናቸው ወሳኝ የሚመስሉኝ፡፡

ዘመን፦በኢሕአዴግ ውስጥ ክፍፍል አለ የሚል አስተያየት ይሰነዘራል፤ እውነት ነው?

አቶ ጌታቸው፦ስራ ብንሰራ ኖሮ እኮ ነው ወጥነት የሚኖረው፡፡ ለምሳሌ ‹‹ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ ፕሮግራማችን ነው አንድ የሚያደርገን›› ስንል በዲሞክራሲና በሰላም ጉዳይ ላይ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ አቋም ይዘን እንቀሳቀሳለን ማለት ነው፡፡ አሁን የዚህች ሀገር ሰላም ጠንቆች ምንድናቸው ብለህ ስትጠይቅ አንዱ ድርጅት የሚሰጠው ምላሽና ሌሎቹ ድርጅቶች የሚሰጡት ሁኔታ የተለያየ ነው፡፡ ለዚህች ሀገር ሰላም መደፍረስ ምክንያቱ የሆነ ከሩቅ የሚዳሰስ የማይዳሰስ ወገን ነው ብሎ የሚያስብ አለ፡፡ የወጣት ስራ አጥነት ነው መሰረታዊ ችግሩ፡፡ የልማት፣ የሰላምና የዲሞክራሲ ጥያቄአችንን ለመፍታት በሚደረገው እንቅስቃሴ ኢህአዴግ በግልጽ ያስቀመጠው ወጣቶቻችንን፣ ሴቶቻችንን ተጠቃሚ ማድረግ የሚል ነው፤ ትልቁ አቅማችን ሕዝባችን ስለሆነ ሕዝቡን እንደ ልማት ኃይል ተጠቅሞ መንቀሳቀስ የሚለው ስራ ላይ ያለው ድክመት ግልጽ ነው፡፡ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ዐይን ለዐይን እንተያያለን ማለት አይደለም፤ ከዚህ አንጻር ነው የኢሕአዴግ ሕልውና መጠየቅ ያለበት፡፡ ዘመን፦በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ሰላም ሲደፈርስ፣ ሰዎች ሲገደሉና ሲፈናቀሉ ‹‹ከችግሩ ጀርባ ሁሌም የሕወሀት እጅ አለ›› የሚል ሰፊ ክስ ይሰማል፤ ምን መልስ አለዎት? አቶ ጌታቸው፦ ሕወሐት በጣም ስራ በመስራት ነው ጊዜውን የሚያሳልፈው፡፡ እንኳን ሌላ ጉዳይ ውስጥ ገብተን ልንፈተፍት ሙሉ ትኩረት ሰጥተነውም ቢሆን ሙሉ በሙሉ አልፈታነውም እንጂ የወጣቶችንን ችግር ለመፍታት እየተንቀሳቀስን ነው ያለነው፤ ሕወሀት ለበርካታ አስርት አመታት የሕዝብን አቅም ተጠቅሞ ለውጥ እያስመዘገበ የመጣ ድርጅት ነው፡፡ ለሰላም፣ ለዲሞክራሲ፣ ለልማት አርአያ መሆን የሚችል ተግባር ያከናወነ ድርጅት ነው፡፡
የሀገሪቱ ሰላም መጠበቅ አለበት ብቻ ሳይሆን እንዲጠበቅም ምናልባትም ከማንም የተሻለ ሚና የተጫወተ ድርጅት ነው፡፡ በዚህ ሰዓት የወንድም ሕዝቦችን ሰላምና መረጋጋት የሚረብሽበት የሚያናጋበት ምክንያት የለም፡፡ይሄንን ክስ የሚያቀርቡት ሰዎች ጠበቅ ያሉ ፖለቲከኞች ናቸው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ጠበቅ ያለ ፖለቲከኛ በወጣትና በሴቶች አቅም አካባቢን መለወጥ መቻል ላይ ነው ትኩረት አድርጎ መስራት ያለበት፡፡ ሕወሐት የሰራው ይሄንን ነው፡፡ሩቅ ሳንሄድ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ይሄ አካባቢ በጦርነትና በተፈጥሮም የተጎሳቀለ ስለሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰውን ጉልበት በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን ያተረፉ በርካታ ስራዎችን የሰራ ነው፡፡
በዚህ መልኩ ወጣቱን አንቀሳቅሶ ስራ እንደመፍጠር ጠመንጃ እያወዛወዙ ‹‹ጥራኝ ጫካው ጥራኝ ዱሩ›› እያሉ ጊዜ ለመግዛት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው ይሄን ሀገር አደጋ ላይ እየጣለ ያለው፡፡ ቀበቶን ጠበቅ አድርጎ ስራ መስራት ነው ጥሩ የሚሆነው፡፡ የወጣት ጥያቄ በብዙ መዝሙር በብዙ ፉከራ ሊድበሰበስ አይችልም፤ መመለስ መቻል አለበት፡፡ ለመመለስ ደግሞ እኛ የምናደርገው እንቅስቃሴ አለ፡፡ በኢህአዴግም ደረጃ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አሉ፡፡ ሌላ አዲስ ተአምር መፍጠር አይጠበቅብንም፡፡ ያንኑ መልሰህ በማየት እዚህ ላይ ነው ያጠፋሁት፤ እዚህ ላይ ነው መልስ መስጠት ሲገባኝ መልስ መስጠት ያልቻልኩት ብለህ አስተካክለህ ለመንቀሳቀስ መሞከር ነው እንጂ የምክንያቶች መብዛት አወዳደቅህን አያሳምርም፡፡
ዘመን፦በቅርቡ ጠ/ሚሩ በሰጡት መግለጫ ኢህአዴግ ወደ አንድ ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲነት ይለወጣል ብለዋል፤ በሕወሀት በኩል ደግሞ ያልተሟሉ ሁኔታዎች ስላሉ ውህደቱን አንቀበልም የሚል ሀሳብ እንዳለ ተሰምቶአል፤ እርስዎ ምን ይላሉ? አቶ ጌታቸው፦ ውሕደት የመቀበል ያለመቀበል ጉዳይ አይደለም፡፡ ይሄ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በሕወሀትም ሆነ በሁሉም ድርጅቶች ዘንድ አደረጃጀታችንን እንፈትሸው፤ ተብሎ የቆየ ነው፤ አደረጃጀት ታክቲክ ነው እንጂ የመጨረሻ ግብ አይደለም፡፡ እንደገለጽኩት ፕሮግራም ነው የሚያገናኘን ካልን ፕሮግራሙን ለማስፈጸም በምናደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ አሁን ያለው አደረጃጃት እንቅፋት ይሆንብናል ወይ የሚለውን ማየት ይጠይቃል፡፡ ይሄ ተፈትሾ በጥናት ላይ ተመርኩዞ ይደረጋል፡፡ የዓላማ አንድነት ሊኖር ይገባል፡፡ በተለይ ድርጅት /ፓርቲ የሚባለው ዝም ብለህ አላፊ አግዳሚው በሙሉ የያዘውን ያምጣ ብለህ የሚቀመጥ አይደለም፡፡ ቆሜለታለሁ የምትለውን ማህበራዊ መሰረት ጥቅሞች በሚመለከት በደምብ የተዘረዘረ፣ በደምብ የተተነተነ አቋም መኖር አለበት፡፡ ይሄን ይዘህ ያንን ጥቅምን ለማስከበር የሚያስችሉ አቅጣጫዎች እነዚህ እነዚህ ናቸው፤ ይሄ ፕሮግራም እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ያስችላል፤ ፕሮግራሙ ለይቶ ያስቀመጣቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ደግሞ ስትራቴጂዎችን፣ ፖሊሲዎችንና፣ ደንቦችን ቀርጸን መንቀሳቀስ ይኖርብናል ብሎ ማሰብን ይጠይቃል፤ የሀሳብ አንድነትን ይጠይቃል፡፡ ምስራቅ አውሮፓ ውስጥ በተለይ ከሶቭየት ሕብረት መፈራረስ በኋላ ወደ ስልጣን የመጡ ፓርቲዎች ምን ያደርጉ ነበረ? ኮሚኒስት ፓርቲው ብቻውን ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለው እድል ስለማይኖር ከሌሎች ስልጣን በትንሽ በትልቁ መቀራመት ከሚፈልጉ ወገኖች ጋር በመሆን እነሱ ‹‹ፓርቲ ኦፍ ፓወር›› የሚሉት ስልጣን ላይ ለመቆየት ያሰበ ፓርቲ የመመስረት አዝማሚያ ነበራቸው፡፡ እሱ ፓርቲ በየሶስት ሳምንቱ የሚታመስ ኃይል ከመሆን ውጭ የፈየደው ነገር አልነበረም፡፡ አሁን ዋና ትኩረት ማድረግ ያለብን የጋራ ብለን ያስቀመጥናቸውን ፕሮግራሞቻችንን የሚያሰሩ የማያሰሩ ብለን መፈተሽነው፤ ይሄ ቀኖና አይደለም፤ እስከጌታ መምጫ ድረስ ይኸው ነው ፕሮግራማችን ተብሎ የሚቀመጥ አይደለም፤ በየጊዜው መለወጥ ያለበት ነገር ካለ እየተፈተሸ ይሄዳል፡፡ ከኢሕአዴግ አንጻር ሕብረብሄራዊ አደረጃጀት ማለት የብሄር ድርጅቶችን ማጥፋት ማለት አይደለም፡፡የብሄር ድርጅቶችን ለማጥፋት ማሰብ ራሱ የኢትዮጵያን ሁኔታ አለማገናዘብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባለው እውነታ የብሄር ቅራኔ የሚባል በመሰረታዊ ደረጃ ተፈትቷል የሚባል ቢሆንም ብሄሮች ከአሁን በፊት ያነሷቸው ጥያቄዎች በተሟላ መልኩ ተፈትተዋል ተብሎ አይወሰድም፡፡ ስለዚህ በቋንቋ የመጠቀም፤ ባሕልን የማበልጸግ፤ በራስ የመዳኘት፤ በራስ የመተዳደር ጥያቄዎች በተሟላና ሁላችንም እኩል ነን ብለን በምናምንበት መልኩ እስኪረጋገጡ ድረስ የብሄር አደረጃጀትን በህግ የምታጠፋውም አይደለም፡፡ አንዳንዱ ዝምብሎ ፋሽን መስሎት አይ በዚህ በዚህ መደራጀት አይፈቀድም የሚል አስተሳሰብ ይኖራል፡፡ ፓርቲዎቹ ግን ሲራኮቱ የምታያቸው በብሔር ዙሪያ ነው፡፡ ለምሳሌ ኬንያን የወሰድን እንደሆነ የብሔር ወይም የጎሳ አደረጃጀት ተከልክሏል ከሚባሉት መሰለኝ፡፡ ምርጫ በቀረበ ወቅት የምታየው መራኮት በጎሳ ዙሪያ ነው፡፡ አለባብሶ የማረሱ ጉዳይ በአረም ከመመለስ አያስቀርምና ዋናው ትኩረታችን መሆን ያለበት የዓላማ አንድነት ፈጥረናል ወይ ነው፤
የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች አንዱ ሌላውን እየከሰሰ፤ አንዱ የራሱን የቤት ስራ መስራት ሲያቅተው በሌላው ላይ ጣት እየቀሰረ፤ በፍጥነት ተጠፍጥፈን በድንገት አንድ እንሆናለን ማለት አይቻልም፤ መሆን ያለበት የራሳችንን ጠባብ ልዩነትና ጠባብ ጥቅሞች ያመጧቸውን ልዩነቶች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየጫንን፤ እርስ በእርስ ለማጋጨት እንቅስቃሴ ማድረግ ባልቆመበት ሁኔታ ኢሕአዴግ በፈለገው ስሌት አንድ ሆኜአለሁ ቢል ቀልድ ነው የሚሆነው፡፡ የሕወሀት አቋም አንድ መሆን አያስፈልግም የሚል አይደለም፤ የሕወሀት አቋም የታይታ አንድነት አይደለም የሚያስፈልገን፤ ፕሮግራማችን ለማስፈጸም የሚያስችል ስለሆነ ቅድሚያ የሕዝባችንን ጥያቄ መመለስ የሚያስችል እንቅስቃሴ ማድረግ አለብን የሚል ነው፡፡
ከዚህ ውጭ ተሰባስበን ስልጣን ላይ ለመቆየት፣ ድምጽ ለማግበስበስ በሚያመች መልኩ ፓርቲ ማቋቋም ነው የሚል ሀሳብ ካለ እንዲህ አይነት አስተሳሰብ አይኖርም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ካለ ግን የጥፋት መንገዱን ከማራዘም በዘለለ እዚህ ግባ የሚባል ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለንም፡፡ ዘመን፦ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መሪ ርእዮተ ዓለም ሆኖ እንዲቀጥል ሕወሀት ይፈልጋል፤ ሌሎች የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ደግሞ እየተቃወሙ መሆኑ ይሰማል፤ ስለሁኔታ ቢገልጹልን? አቶ ጌታቸው፦ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ስሙ ላይ ከሆነ ጠባችን መቀየር እንችላለን ተብሎ እኮ በ2003 ዓ.ም አቶ መለስ በነበሩበት ወቅትም ‹‹የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማሕበራዊ እንቅስቃሴአችንን በደምብ የሚገልጸው ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመር የሚለው ስለሆነ ይሄኛው ተመራጭ ነው›› ከሚል ነጥብ ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ ያ ሲባል ‹‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ›› የሚለው ቃል አርጅቶ አፍጅቶ ተቀባይነት አጥቶአል ማለት አልነበረም፡፡ ቃሉ በደርግ ጊዜም ስለነበረ ብዙ የረከሱ ቃሎች አሉ፤ ‹‹አብዮት›› ሲባል ከግርግርና ከቀይሽብር ጋር የማያያዝ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከስሙ ሳይሆን ከይዘቱ አንጻር ነው መመዘን ያለበት፡፡ አስተሳሰቡ ሰላምና ዲሞክራሲ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕልውናና ቀጣይነት ማረጋገጫ ምሰሶዎች ናቸው የሚል ነው፡፡

ዘመን፦በአንድ ድርጅት ውስጥ ሁለት አይነት ርእዮተ ዓለም ሊኖር ይችላል?

አቶ ጌታቸው፦ምን ርእዮተ ዓለም ያስፈልገዋል? ስለዲሞክራሲና ልማት መግባባት ካልቻልን በምንም መግባባት አንችልም፡፡ ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ አይደለም የሚያስፈልገኝ ሌላ ነው የሚል ካለ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ሊበራል ዴሞክራሲ ምን እንደሆነ አንድም ቀን ሰምቶ የማያውቅ ሰው ሊበራል ዴሞክራቲክ አስተሳሰብ ነው የሚሻለኝ ይላል፡፡ ሊበራል ዴሞክራሲ ምንድነው ብንል ሊበራል ዴሞክራሲ የሚባለው አንድ ወቅት ብርና ንብረት ላላቸው ሰዎች ብቻ የመምረጥ መብትን ማጎናጸፍ የፈለገ ሀብታሞችን ከድሆች ለመከላከል ተብሎ ሲራመድና ሲቀነቀን የነበረ ስርዓት ነው፡፡ በሂደት መታገል የጀመሩ ድሀ ነጮች ትንሽ ንብረት ሲቋጥሩ ምርጫ ውስጥ መግባት አለብን ማለት ጀመሩ፤ ሴቶችም እኛም ተምረናል ዲሞክራሲ ይመለከተናል ማለት ጀመሩ፡፡ ጥቁሮች በተሟላ ደረጃ የሰብአዊ መብት አዋጅ የሚባለው እስኪወጣ ድረስ የመምረጥ ነጻነት መብት አልነበራቸውም፡፡ አሁንም ቢሆን የተሟላ ነጻነትና መብት አላቸው ተብሎ አይገመትም፡፡ አስተሳሰቡ ምን እንደሆነና ከየት ተነስቶ ምን እንደደረሰ በወጉ የማይረዳ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ የቋንቋ የቡድን መብት በተሟላ ደረጃ መረጋገጥ አለበት ብሎ የሚያምን ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ባለበት ሀገር አይ የግለሰቦችን መብት ማረጋገጥ ብቻ ነው የኢትዮጵያን ችግር የሚፈታው ማለት አስገራሚ ነው፡፡
የሙስሊሞች፣ የሴቶችና የብሔሮች መብት በቡድን ደረጃ መረጋገጥ አለበት፡፡ ብዝሀነታችንን በወጉ ማረጋገጥ ስንችል ፌደራል ስርአታችንን እናጎለብታለን ነው፡፡ እነዚህን ጉድለቶች መቀበል አለብን፡፡
Full Website