ትግራይን መገንጠል፣ ለምን? ለማን?

ዮሃንስ አበራ (ዶር) 6-16-19

በባለፀጋ አገሮች በማንኛውም ህዝባዊ ጉዳይ ላይ የህዝብ ስሜት ይህ ነው ያ ነው እያሉ ከኪስ እየመዘዙ መናገር ያስወግዛል ሊያስቀጣም ይችላል። የህዝብን ስሜት የሚያውቀው ህዝቡ ራሱ ብቻ ነው። ህዝብን የሚያከብርና የወሳኝነት ሚናውን አምኖ የሚቀበል ማንም አመራር ሰጪ ሆነ ግለሰብ ፓለቲከኛ በማንኛውም ጉዳይ ላይ የህዝብን አስተያየት በበቂ ሁኔታ ጠይቆ ሳያጣራ ወክሎ የመናገር ፍላጎት አይኖረውም። ቢናገርም ከታዘባቸው ነገሮች መነሻነት በመላምትነት የማቅረብ ጉዳይ ይሆናል። ይህ ድርጊት ስፔኩሌሽን በሚል የኢንግሊዝኛ ቃል ይገለፃል። ለዚህም ነው መላውን ህዝብ ጠይቀው ሳያጣሩ በእርግጠኝነት ከመናገር ይልቅ ባደጉት አገሮች የህዝብ አስተሳሰብ መጠየቅያ ስርአት ያደራጁት። ለዚህም ሳይንሳዊ ዘዴ በመጠቀም ወካይ ናሙና መርጠው ባሉት የመገናኛ ዘዴዎች አማካይነት አስተያየት ይጠየቃል። ናሙናው በፓለቲካም፣ በዘርም፣ በሃይማኖትም፣ በገቢም የተዛባ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረጋል። ይህ ሲጠናቀቅ ነው ፓለቲከኛ ይሁን ጋዜጠኛ ህዝብ እንዲህ አለ፣ ይህን ይወዳል፣ ያንን ይጠላል፣ ይህን ይደግፋል፣ ያንን ያወግዛል፣ ወዘተ በማለት አፉን ሞልቶ ቢናገር ተቀባይነት የሚያገኘው። ይህን ጉዳይ በተመለከተ ስለ ሌሎች ታዳጊ አገሮች ሁኔታ በቂ እውቀት የለኝም። በኢትዮጵያ የፓለቲካና ማህበራዊ መድረኮች ግን ትልቁም ትንሹም ፓለቲከኛ፣ በየደረጃው ያሉ መሪዎች ሆኑ ተራ ሰዎች ከቀላል ማህበራዊ ጉዳዮች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የፓለቲካ ክስተቶችና ሂደቶች ድረስ የህዝብ ምንነትን የሚገልፁ እንዲሁም የህዝብ አስተያየትን ይወክላሉ የተባሉ መግለጫዎች መስጠት ሃይ የሚለው ዳኛ ያጣ ጎጂ ባህል ከሆነ በርካታ አመታትን አስቆጥሯል። በማህበራዊው ህይወት ረገድ ስለተለያዩ ብሄር ህዝቦች የሚነገረው ጥሩም ሆነ መጥፎ፣ የተጋነነ ይሁን የተቃለለ ሃብትን፣ ችሎታን፣ እውቀትን፣ ጀግንነትን፣ ዘርን የመሳሰሉ ባህርያተ-ህዝብ አንዱ ላይ ባዩት ሚልዮኖች ላይ አጠቃሎ መናገር የተለመደ ነው። አንዱን ህዝብ ጀግና ሌላውን ፈሪ፣ አንዱን አስተዳዳሪ ሌላውን ሁሉ መዝባሪ፣ አንዱን ህዝብ አንበሳ ሌላውን ጅብ፣ አንዱን ህዝብ መሰሪ ሌላውን ጅል አድርጎ መሳልና በአደባባይ መናገር ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልገውም። አድማጩም ምንም ለማጣራት ሳይሞክር የባሰ ሲያራባው ይገኛል። ከዚህ የተነሳ አንዳንድ ህዝብ ላይ በአንዳንድ ግለሰቦች የሚለጠፉ ባህርያተ-ህዝብ ቋሚ ይሆኑና ህዝቡ ለእርስ በርሱ የሚኖረውን አመለካከትና አፈራረጅ ሲመሩ ይኖራሉ። መንግስቱ " ህዝቡ ወርቅ ሲሉት ፋንድያ..." ያለውም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። እንዲህ የሚለው የኢትዮጵያ ህዝብ ያለው እሱ ጭንቅላት ውስጥ ብቻ ነው። ፋንድያን ከወርቅ የሚያስበልጥ ህዝብ በአለም ውስጥ ይኖራል? በፓለቲካው ረገድ ስናየው ቁጥሩ አምሳ እያለ አምሳ፣ ሰባ እያለ ሰባ፣ አሁን ደግሞ መቶ በሆነበት "መቶ ሚልዮን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲህ ብሏል፣ ይህንን ተቃውሟል፣ ያንን ደግፏል፣ ወዘተ እያሉ በየመድረኩና በየሚድያው መግለጫ መስጠት ጭብጨባን ያስገኛል እንጂ "ከየት አመጣኸው?" የሚል ጥያቄን አያስከትልም። ይህ የሚሆነው አንድም ባህል እየሆነ በመምጣቱ፣ ሁለትም ጠያቂ ሲኖር እንደ አፍራሽ ተቃዋሚ ስለሚቆጠር፣ ሶስትም በሚድያውና በአዳራሹ የሚታደመው አንድ አይነት አመለካከት ያለው ስለሚሆን፣ ሌላም ሌላም። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የፓለቲካ መድረኮች ላይ የሚታየው ችግር የመፃፍና የመናገር መብቱ ከመስመር አልፎ ወሳኝ የሆኑ ግን የህዝብን ሙሉ ይሁንታ ሳያገኙ፣ ያለው የፓለቲካ ሁኔታም ለዚህ አይነት ድምዳሜ፣ ንግግርና ፅሁፍ የሚያበቃው ደረጃ ላይ ደርሶ ነወይ ተብሎ በቅጡ ሳይመረመር፣ እንዲሁ የሚፃፉና የሚነገሩ ነገሮች አሉ። ከነዚህ ሁሉ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው "የትግራይ ከኢትዮጵያ የመገንጠል" ሃሳብን የሚመለከት ነው። የመገንጠል ጥያቄ የኢትዮጵያን የፓለቲካና ማህበራዊ ህይወትን ሲንጥ የኖረ ከባድ ጥያቄ ነው፦ የኤሪትርያ ጥያቄ፣ የኦሮሞ ጥያቄ፣ የኦጋዴን ጥያቄ። ሁሉም የየራሳቸው የሆኑ ታሪካዊ መነሻዎች ያሏቸው ቢሆኑም መቶ በመቶ የህዝብ ጥያቄዎች ለመሆናቸው ግን ምንም ማረጋገጫ የለም። የተለመደው አካሄድ እንዲህ ነው፦ ህዝቡ ከፍተኛ በደል ስለደረሰበት መፍትሄው ከጨቋኙ መንግስት ብቻ ሳይሆን "ከጨቋኙ ህዝብ"ም መለያየት አለበት ብለው ድምዳሜ ላይ የደረሱ የተወሰኑ ግለሰቦች ተደራጅተው ይታገላሉ። ጭቆናው እየጠነከረና በተደራጀው ተቃውሞ እየተሳበበ የሚፈፀመው ግፍ የተደራጀውን ተቃውሞ የበለጠ አቅም እንዲያካብት ያደርገዋል። ይህ "ህዝባዊ" ጥያቄ እውነትም ህዝባዊ መሆኑ ለማረጋገጥ የሚሞከረው ግን ትግሉ ከተጠናቀቀ በኋላ በሚካሄደው ሬፈረንደም ነው። ትክክለኛ ህዝባዊ በሆነ አስራር ግን ህዝብ መጠየቅ ያለበት ቀደም ብሎ ትግሉ ሳይጀመር ነው። ህዝቡ እንገነጠላለን ብሎ ከወሰነና መንግስት አልፈቅድም ካለ ትግል ይጀመራል። መጨረሻ ላይም ያለሬፈረንደም ነፃነትን ማወጅ ነው። በኤሪትርያ የተፈጠረው ነገር ይህንን ይመስላል። የነፃነት ትግሉ በኤሪትርያ ህዝብ የመገንጠል ፍላጎት ላይ ተመስርቶ አልተጀመረም። ከላይ እንደተገለፀው ትግሉ የተጀመረው ዒድሪስ ዓዋተ በሚባል በእንድ ግለሰብ መሆኑ ይታወቃል። የኤሪትርያ ህዝብ ፍላጎቱን የተጠየቀው 30 አመት ሙሉ የጦርነት አውድማ ሆኖ ከቆየ በኋላ ነው። ከጦርነት፣ ከዚህ ሁሉ ግፍና እልቂት በኋላ የሚጠየቅ ጥያቄ መልሱ ሳይታለም የተፈታ ነው። ጉዳዩ ከዚህ ቀደም ሲነሳና ሲደበዝዝ የቆየ ቢሆንም፤ ህወሓት በምስረታ አመታት ላይ "ሪፑብሊክ" የሚል ቃል አሰፈረች በሚል ለብዙ አስርት አመታት ስትወቀስ የቆየች ብትሆንም፣ የትግራይ "የመገንጠል ጥያቄ" እንደ አሁኑ ጎልቶ የወጣበት ዘመን የለም። በማህበራዊ ሚድያዎች ላይ ከሚቀርቡት ትንተናዎች ይልቅ ትኩረቴን የሳበው የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶር. ደብረፅዮን የተናገሩትና በሪፓርተር ጋዜጣ ላይ ታትሞ የወጣው መግለጫ ነው። ጠቅለል ሳደርገው ዶር. ደብረፅዮን ያሉት እንዲህ ነው፦ "የትግራይ ህዝብ እየደረሰበት ካለው ዘርን ካማከለ ጥቃት የሚያስጥለው በማጣቱ እኛ(ህወሓት) ልናረጋጋው ብንሞክርም የመገንጠል ስሜቱ እየጨመረ ሄዷል።" ይህ አባባል እውነትም በአስተያየት ሰጪዎች እንደተባለው "አስደንጋጭ" ነው። የአስደንጋጭነቱ አንዱ ምክንያት መምጣት ከማይገባው አቅጣጫ መምጣቱ ነው፤ ከርእሰ መስተዳድር። ሁለተኛው አስደንጋጭነቱ ትግራይና ኢትዮጵያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ሆነው እንጂ፣ ሌሎች ስለራሳቸው እንደሚያምኑት ውህደታቸው የድርድር ውጤት ባለመሆኑ፣ ትግራይ የምትገነጠለው ከራሷ ነው? የሚል ገራሚ የሆነ ጥያቄ ስለሚያስነሳ ነው። በርግጥ በትግራይ ህዝብ ላይ ካቅም በላይና ትእግስት አስጨራሽ የሆነ ብዙ በደልና ማግለል እንዳለ እሙን ነው። ሆኖም ግን ጫፍ ወደ ረገጠና መመለሻ ወደሌለው "መፍትሄ" ከመኬዱ በፊት የዚህ ችግር ትክክለኛ መንስኤው ምንድነው? ሌላ መፍትሄ የለውም ወይ?  መገንጠል የተሻለ መፍትሄ የሆነለትና በሰላምና ብልፅግና የዜጎቹን መብት ከበፊቱ አስበልጦ ያስከበረበት አጋጣሚ በየትኛው የአፍሪካ አገር ታይቷል? መገንጠል መልካም መፍትሄ የሚሆነው የሚገነጠለው ግዛት ውስጥ ያለው ህዝብ በፍቅርና አንድነት ለመኖር የሚያስችሉት ጠንካራ ማህበራዊ እሴቶች መኖራቸው ማረጋገጥ አያስፈልግም ወይ? የሚገነጠለው ግዛት የዘር ሃረጋዊና የአምባገነናዊ አገዛዝ ሳይሆን የነፃና አሳታፊ ዴሞክራሲ ባህል ባለቤት መሆኑ መረጋገጥ የለበትም ወይ? ይህ ካልሆነ መገንጠል የሚያመጣው ልዩነት የቤትና የጎረቤት ጅብ የመምረጥ ጉዳይ አይሆንም ወይ? ይህ መገንጠል የሚባለው የህዝብ ኢኮኖሚያዊና  ማህበራዊ ትስስሮችን ያላገናዘበ ውሳኔ ዳቦ የመቁረስ ያህል ቀላል ሳይሆን ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎች የሚያስከትል ከሞት ለመዳን ካልሆነ ለሌላ ምንም ነገር እንደ መፍትሄ የማይወሰድ መሆኑ በቂ ግንዛቤ አለ ወይ? ኤሪትርያንና ደቡብ ሱዳንን ያየ በመገንጠል እሳት አይጫወትም። ከዚህ በላይ የገልፅኳቸው ስጋቶች ህዝብ በፓለቲከኞች ተገፋፍቶ፣ ሊያልፉ በሚችሉ ችግሮች ተገፋፍቶ የመገንጠል እርምጃን መውሰድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ለማለት እንጂ ከፓለቲካ ሴራ ነፃ ሆኖ መገንጠልን ከሚወስን ህዝብ የበለጠ አውቅልሃለሁ ማለቴ አይደለም። በርግጥ ህዝብ በጊዜያዊ ችግር ተነሳስቶ ስለወደፊቱ ኑሮው በቂ መረጃ ሳይኖረው መሪዎቹ በሚቀዱለት አደገኛ ቦይ ሊፈስ መቻሉ ታሪክ በተደገጋሚ ያረጋገጠው ነው። የደርግ ቦምብ ሲፈነዳባት የኖረች ኤሪትርያዊት እናት መገንጠልን እልል እያለች በካርድ ከመረጠች በኋላ ልጇ ኑሮ ፍለጋ ሜዲትራንያን ባህር ውስጥ ሰምጦ ሲሞትባት የማይራራ "የራሷ" መንግስት ይኖረኛል ብላ እያሰበች አልነበረም፤  ከምታውቀው ሰይጣን የማታውቀውን መላክ መምረጥዋ ነበር። የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር የክልሉ ገዢ ፓርቲ አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ እየመሩ መሆናቸው ይታወቃል። የሚመሩት ድርጅት አንዳንድ አባላት በህግ የሚፈለጉበት ሁኔታ ባለበትና "ህግ አይደለም አድልዎ ነው" በሚል አተካሮ ከማእከላዊው መንግስት ጋር በተካረሩበት ወቅት ሌሎች የፓለቲካ ሃይሎች ይህን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመው በህወሓትም ሆነ ህወሓትን በማቀፉ መቀጣት አለበት ብለው በሚያምኑት የትግራይ ህዝብ ላይ ጭንቀት እየፈጠሩበት ነው። አብረው በኢህዴግ ማእቀፍ ውስጥ ሲመሩም ሆነ ሲያደናብሩ የቆዩት ድርጅቶት እንደ ጲላጦስ እጃቸውን ታጥበው "ሌባ አስጠጋችሁ፣ ለወንጀለኛ ከለላ ሰጣችሁ" እያሉ ትግራይ ህዝብ ላይ አመልካች ጣታቸውን የሚያዛውዙት ግለሰቦችና ቡድኖች አላማ ስላልገባው ህዝቡ ህወሓትን አሳልፎ መስጠት ትርጉም የለሽ ጥያቄ ሆኖበታል። እነዚህ ድርጅቶችና ግለሰቦች ግን ከትግራይ ህዝብ የሚያንሱና ጊዜያዊ ከመሆናቸው የተነሳ የትግራይ ህዝብ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመወሰን ሊያበቁት አይችሉም።
Full Website