የትግራይን ህዝብ የሚጎዳ ፓለቲካ ይቁም

ዮሃንስ  አበራ (ዶር) 8-14-19

የትግራይ ህዝብ መልስ ያጣለት ነገር ቢኖር ያም ያም እየተነሳ ለምን እንደሚዝትበት ነው እንጂ ዋናው ማንነቱ የሆነው ኢትዮጵያዊ መሆን አለመሆን አይደለም። በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ ሰፍኖለት ሳይበደልና ሳይጨቆን የኖረ ህዝብ የለም። ትግራይን የጨቆነ መንግስት በሌላው ላይ ደግ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። ዴሞክራት ህዝብ አይመርጥም አምባገነንም እንዲሁ። የሚያዳላ ቢሆንም እንኩዋን የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱን የጨበጠው ተፈጥሮአዊ ስለሆነ እንጂ በመደራደሪያነት አይደለም። ማስታወስ የሚገባን ነገር ቢኖር በራሱ ልጆች እጅ ሆኖ በነበረበት ሰላሳ አመትም ቢሆን መልካም አስተዳደር እንዳልታደለ ይታወቃል። መገንጠል ከልጆቹ እንኩዋን አጥቶት የኖረውን መልካም አስተዳደር አያስገኝለትም። ከሌላ ስለመጣ አይደለም ጭቆና ጭቆና የሚሆነው። የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊነትን ሲመረው የሚጥለው ሲደላው የሚያነሳው አይደለም። ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ ያህል አድርገው የሚሰድቡትን የሚያስፈራሩትን የሚታገላቸው ኢትዮጵያዊነቱን ጠንካራ ክንድ አድርጎ በመጠቀም እንጂ ዋናው ማንነቱን ጥሎ በመሸሽ አይደለም። ጀግናው የትግራይ ህዝብ ፈሪ የሚሆነው ማንነቱ የሆነውን ኢትዮጵያዊነትን ጥሎ የሄደ ቀን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ችግር ላይ የወደቀው የትግራይ ህዝብ ብቻ ነውን; የሚለው ጥያቄ ታዛቢና የደረሰበት ሁሉ የሚመልሰው ነው። የጋራ ችግር የጋራ ትግል ያስፈልገዋል። አሁን ያለው የኢትዮጵያ ችግር የፓለቲከኞች ቁርቁስ ያመጣው እንጂ ህዝቡ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። ተራው ህዝብ በሰላም እንደወትሮው አብሮ እየኖረና እየሰራ ነው። ለዚህ በቂ ማስረጃ የሚሆነው ከሰማንያ በላይ ብሄር የተወከለባት ትንሽዋ ኢትዮጵያ የሆነችው  አዲስ አበባን አንድ ቀን ወስደን ብንዘዋወር የህዝቡ መተሳሰብና መከባበር አገር ፈረሰ እያሉ ሽብር የሚነዙትን ፓለቲከኞች የሚያሳፍር ነው። የት ላይ እንደሚጠቀሙበት ማወቅ ያቃታቸው ግን የፓለቲካ ሳይንስ ምሁራን ነን ባዮች ከፈረኝጅ የተዋሱትን ፌይልድ ስቴት የሚለው ቃል ኢትዮጵያ ላይ አምጥተው ይለጥፉታል። ኢትዮጵያ ፌይልድ ስቴት አይደለችም መቸም አትሆንም። የብዙ ዘመናት የመንግስታዊ ስርአት ባህል ያላት አገር መንግስት ሊሳሳባትና ሊዳከምባት ይችላል እንጂ አትፈርስም። በኢትዮጵያ ታሪክ የመንግስት መዳከም አዲሰ ነገር አይደለም፡፡ ረብሻና መካረር በተፈጠረ ቁጥር የሚፈርስ አገር እኮ ድሮም በሙጫ ተጣብቆ የነበረ ከሆነ ነው። ህዝብን የሚያለሙትና የሚያጠፉት ፓለቲከኞች ናቸውና መቶ ሚልዮን ህዝብ ምን እየተፈጠረ እንደሆነ ሳይገባው በፓለቲከኞች የብተና ሽብር እየተነዛበት ነው። እንዲህ እንደቀላል ነገር የሚደጋግሙት ብተና ለፓለቲከኞቹ ስጋት ነው ወይስ መልካም አጋጣሚ ለመለየት ይቸግራል። ለትግራይ አንዳንድ ፓለቲከኞች ግን የአዝናኝ ጨዋታ ያህል የተመቻቸው ይመስላሉ። ካልሆነ የትግራይ ነፃ መንግስት መመስረት ነው! የሚለው አባባል በትግራይ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ንቀት ማንፀባረቅ ነው።  ህዝበ ውሳኔ አካሂደውና መቶ ፐርሰንት እንገንጠል የሚል የትግራይ ህዝብ ድምፅ አገኝተው ለጋዜጠኞች ሪፓርት የሚያደርጉ ይመስላሉ። እነዚህ ዝና ፈላጊና ሃላፊነት የማይሰማቸው ፓለቲከኞች የሚናገሩትን የመገንጠል አስፈላጊነት ትርክት ከትግራይ ስድስት ሚልዮን ህዝብ ውስጥ ምን ያህሉ እየሰማ ይሆን; እንኩዋንና የብዙ ዘመናት ታሪክ ያለው የትግራይ ህዝብ ቀርቶ ወላጅ ስለልጁ ውሳኔ ሰጪ የሚሆነው አስራ ስምንት አመት እስኪሞላው ብቻ ነው። የመገንጠል ጥቅምና ጉዳት በሚገባ ያልተገነዘበን ህዘብ በስሜት አነሳስቶ ጀሮው ውስጥ እንደ ጣፋጭ ሙዚቃ ማንቆርቆር ወንጀል ነው፡፡ መገንጠልን እንደቀላል መውጫ በር አድርገው የሚቆጥሩት የትግራይ አንዳንድ ፓለቲከኞች እየጎረሱ ያሉት ሊውጡ ከሚችሉት በላይ ነው። የመገንጠል ግብ እኮ መገንጠል አይደለም። የመገንጠል ግብ ራስን የሚሸከም ጠንካራ አንገት ያለው ነፃ አገር መፍጠር TKƒ ነው። ይህ ስራ ነብዩ እንዳለው ጎጆ የመቀለስ ያህል ቀላል አይደለም። መራራ እውነትን መቀበል ያስፈልጋል። አንዳንድ የትግራይን የኢኮኖሚ አቅም ማቃለል የሚወዱ ግለሰቦች ስለሚናገሩት ብቻ አሳፍሮን የምንደብቀው ነገር አይደለም። ትግራይ በአሁኑ ሁኔታዋ ራስዋን ችላ መቆም የምትችል ነፃ መንግስት ልትሆን አትችልም። በሌላ በኩልም እነዚህ የመገንጠል ፓለቲካ የሚያራግቡ ፓለቲከኞች ጨርሶ የዘነጉት አብይና ወሳኝ ነገር አለ። ስለ ትግራይ መገንጠል ሲናገሩ ሽግግሩ ሰላማዊ ይሆናል ብለው ማሰባቸው ነው። መገንጠልን የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ የማይደግፉ ግን ዝም ያሉት አብዝሃዎቹ እንደበግ ወደማይፈልጉት ነገር ተጎትተው መሄድን አሻፈረን ይሉና የማያባራ ግጭት ይፈጠራል። ሌላው የቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ስሜት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ፈቃደኛ ካልሆነ የትግራይ የመገንጠል ውሳኔ በሰላማዊ መንገድ ይጠናቀቃል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። አንቀፅ ሰላሳ ዘጠኝ ተግባራዊ የሚሆነው እኮ በመግባባት እንጂ በፀብ አይደለም። በፀብማ ሲሆን አንቀፁም ቁጥር ብቻ ህገ መንግስቱም የተረት መፅሃፍ ይሆናሉ። ህግ እኮ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን አስፈፃሚም ያስፈልገዋል። ትግራይ የምትገነጠለው አገሪቱ ልትበተን ስለሆነ ነው ይላል መሓሪ ዮሃንስ። ኢትዮጵያ ልትበተን ከሆነ አንቀፅ ሰላሳ ዘጠኝ እንዲተገበር ውሳኔ እንዲሰጥ በህገ መንግስት ስልጣን የተሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህልውና ይኖረዋል; ምስጋና ስላልተቀበልን ኢትዮጵያ እንዳትበተን ጥረት አናደርግም የሚለው የመሓሪ አባባል በሰላም ጊዜ ቢሆን ኖሮ በአገር ክህደት ወንጀል (ትሪዝን) ያስከስሰው ነበር። ማንም ዜጋ የሃገሩን ደህንነትና የግዛት አንድነት የመጠበቅ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ አለበት።  ይህ እንኩዋን ከፓለቲካ ሳይንስ ምሁር ትምህርት ካልነካ ሰውም አይጠበቅም። አገርን ከአደጋ መጠበቅ ተመስጋኙ ማነው፣ አመስጋኙስ ማነው? ይህን እያሰቡ አልነበረም ኢትዮጵያን ለመጠበቅ በየጦር ሜዳው ስንት ጀግኖች የወደቁት። የምስጋና ነገር ሲነሳ የትግራይ ፓለቲከኞች ሌላውን ከመውቀሳቸው በፊት መጀመሪያ ራሳቸው ምስጋናን መማር አለባቸው። ምስጋና ማለት ውድ የሆነ ሃውልትና አዳራሽ ገንብቶ ስም ዝርዝር መለጠፍ አይደለም። ምስጋና ማለት በሺዎች ደም የተገኘውን ለግል ቅንጦት መጠቀም አይደለም። ምስጋና ማለት በህይወት ያሉት የጦር ጉዳተኞችና የስውአን ቤተሰቦችን እንደ መብታቸው ሳይሆን ምፅዋት ተቀባዮች እንዲሆኑና አሁን ከበርቴ የሆኑት የቀድሞ የትግል ጉዋዶቻቸው በጎ አድራጎት እንዲጠብቁ ማድረግ አይደለም፣ ምስጋና ማለት በትግሉ የመከራ ገፈት ቀማሽ ሆኖ የቆየውን የትግራይን ህዝብ ችላ በማለት ሃብት ከማጋበስ በስተቀር ህዝባቸውን የማገልገል ችሎታና ፍላጎት ለሌላቸው አስተዳዳሪዎች ትቶ አዲስ አበባ ላይ የድሎት ኑሮ መመስረትና ትግራይን ዘንግቶ በፌደራል የስልጣን ሽኩቻ ላይ መጠመድ አይደለም። እንዲደረግብህ የማትሻውን በሌላው ላይ አታድርግ ይላል ታላቁ መፅሓፍ። ሰሞኑን አዲስ አበባ የሚኖሩ ትውልዳቸው ትግራይ የሆኑ የትዳር ጉዋደኞች የገቡበት ውዝግብ  ላጫውታችሁ። እነ መሃሪ፣ ኪዳኔና የመሳሰሉት ስለትግራይ ራስን መቻል ሲናገሩ አዲስ አበባ የሚኖረውና አንድ ሚልዮን ሊሆን የሚችለው የትግራይ ተወላጅ ሽብር እየገባው መሆኑ የተረዱ አይመስለኝም። የባልና ሚስቱ ጭቅጭቅ የተቀሰቀሰው ለትግራይ ተወላጆች አስጊ የሆነ ጊዜ እየመጣ ነውና ወደ ትግራይ ሄደን እንኑር በሚለው አጀንዳ ነው። መቀበል የሚገባን ሃቅ አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖረው የትግራይ ተወላጅ ህዝብ የኢኮኖሚ አቅሙ ፈርጣማ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለትግራይ ክልልም የኢኮኖሚ ምሶሶ ነው። ትግራይ ላይ በግዴለሽነት የሚለፈፈው የመገንጠል ፓለቲካ ግዙፍ የኢኮኖሚ ድርሻ ያለውን አዲስ አበባ ነዋሪ የትግራይ ተወላጅ ተረጋግቶ እንዳይኖር እያደረገው ነው። ይህ ለትግራይ ክልል ኢኮኖሚ ከፍተኛ አደጋ አለው። በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ!! መቐለ ላይ ተቀምጦ መፈላሰፍ አዋቂ አያሰኝም። አዋቂነት የሚባለው አንዴ ለመናገር አስር ጊዜ ማሰብ ነው። ትግራይ የሰፈሩት ምሁራን መላ ኢትዮጵያ ተዘርቶ ስለሚገኘው የትግራይ ትውልድ ያለው ህዝብ መናገር የሚቻላቸው ቢሆንም መወሰን ግን አይችሉም። የህዝብ ይሁንታ ሳያገኙ በህዝብ ስም የሚደረሰው ድምዳሜ የአምባ ገነንነት አደገኛ ዝርያ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች የሚኖረው የትግራይ ትውልድ ያለው ህዝብ አገሬ ነው፣ የኔ ቀየ ነው፣ የልጆቼ የትውልድ ስፍራ ነው እያለ ነው በመኖር ላይ ያለው። የትግራይ ፓለቲከኞች ሲፅፉም ሆነ ሲናገሩ ወደ ውስጣቸው ብቻ ሳይሆን ራቅ አድርገው ዙርያ ገባውን ቢያስተውሉ ይመከራል። የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ የአዲስ አበባ ህዝብን ጨዋ ኢትዮጵያዊነት ማድነቅና ማመስገን እወዳለሁ። አዲስ አበባ ውስጥ እኮ በሰላም እየኖሩ ያሉት ትግራይ የሚገኙት ከፍተኛ የህወሓት ባለስልጣናት ቤተሰቦችም ጭምር ናቸው። የህወሓት አመራሮች ንብረቶችና ድርጅቶችም ቢሆኑ የነካቸው የለም። ፌደራል የትግራይ በጀት ቀነሰ፣ የሃራ ገበያ መቐለን ባቡር ፕሮጀክት ዘጋው የሚል ምሬት ይሰማል። በርግጥ ሆን ተብሎ ህዝብን ለመጉዳት ከሆነ የሚወገዝ ነው። በሌላ መአዝን እንደ ፌደራሉ ሆነን ብናየው ግን ክልከላው የትግራይ ፓለቲከኞች አስተዋፅኦ አለበት። ካልሆነ እንገነጠላለን የሚል ግልፅ መልእክት ከክልሉ እየተንፀባረቀ ባለበት ሁኔታ፣ በየስብሰባው የሚነገረው መረር ያለ ቁዋንቁዋ ሞባይል ጥርቅም አድርገው ቢዘጉትም መሃል አገር መድረሱ አልቀረም። የበጀት ድጎማው ሆነ የባቡሩ ፕሮጀክት ከመላ ኢትዮጵያ ግብር ከፋይ የሚገኝ እንደመሆኑ እገነጠላለሁ እያለ ለሚዝት ክልል አቅም ግንባታ ማዋል ፌደራል መንግስቱን ሊያስጠይቀው ይችላል። ክፉ አያሳስበው እንጂ የመቐለ ውሃ ፕሮጀክት የብድር እዳ ውስጥ የገባው እኮ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። ፍቺ ሲኖር ሰብአዊነት አይኖርም። የመቐለና አክሱም ህዝብ እኮ ውሃ እንዲያጠጣው የጠየቀው ፌደራል መንግስትን ነው። ነገር ማለባበስ ምን ይፈይዳል;
Full Website