የራእይ አልባ፣የጥፋት አመራር አነሳስ

ፈይሳ ነግሪ 7-23-19

ኢትዮጵያ አገራችን ከደርግ ውድቀት በኋላ ከምዕራቡና ከምስራቁ ዓለም ምህዋር ውጭ በራሷ መንገድ መሽከርከር መጀመሯ የሚታወቅ ነው። ከፖሊሲ ጥገኝነት ወጥታ በራሷ አገራዊ ፖሊሲ መመራት ከጀመረችም ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ተቆጥሯል። ከተመፅዋችነት የምትወጣበትን ሐዲድ በመከተልና በህዝቦችዋ ዓቅም በመተማመን በለኮሰችው የለውጥና የህዳሴ ጉዞ በከፍተኛ ፍጥነት በመገስገስ ላይ የምትገኝ አገር ሆናለች። ከዚህ የተነሳም የአፍሪቃ የለውጥ ተምሳሌት መሆን ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃ ያበረ ድምፅ መሪ ወደ መሆን ተሸጋግራ፣ በዓለም ያላት ተሰሚነትና ተቀባይነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

ይህ አዲሱ የአገራችን ገፅታ ግንባታ እውን የሆነው ኢህአዴግ ወደ መድረክ መንበረ-ስልጣን ብቅ ማለቱን ተከትሎ ነው፡፡የዛሬ አያድርገውና ኢህአዴግ በጣም ጠንካራ ከሚባሉ የዓለማችን ፖለቲካዊ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ የኢህኣዴግ ጥንካሬም የኢህአዴግ አስኳል ከሆነው ህወሓት የመነጨ እንደሆነ ድፍን አገር ያወቀው ጉዳይ ነው፡፡ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ግን እስከ 1970ዎቹ መጨረሻ ኢህኣዴግን ወደ እንዲህ ዓይነቱ ጥንካሬና ውጤት ያደረሰው ህወሓት በጥልቀት የተገነዘቡበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ከ1966ቱ ህዝባዊ ዓመፅ በኋላ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የጎላ ቦታና ተሰሚነት የነበራቸውኢህአፓ እና መኢሶን የተባሉቱ ፖርቲዎች ነበሩ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ከታጣቂዎች ደግሞ ታዋቂየነበሩት የኤርትራዎቹ ሁለቱ ድርጅቶችን [ጀብሃና ሻዕቢያ] መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዛን ጊዜ ህወሓት በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መድረክ ብዙ ቦታ የሚሰጠውና እምብዛም የሚታወቅ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ደርግን ሲቃወሙ የነበሩ ኃይሎች ህወሓትን ከቁብ የሚቆጥሩት አልነበሩም፡፡ አንዳንዶቹም ሲበዛ ንቀት ነበራቸው፡፡ ደርግ ራሱ በህወሓት ላይ በጣም ከፍተኛ ንቀት እንደነበረው ከአነጋገሩም ሆነ ከድርጊቱ ይስታውቅ ነበር፡፡ በዛን ወቅት ደርግ ህወሓትን በስሙ ሳይሆን የገጠር፣ የጓሮ ኣይጥ ወዘተ… እያለነበር የሚጠራው፡፡ ፀረ­­‑ህወሓት በአካሄዳቸው የመጀመሪያዎቹ መጠነ‑ሰፊ ዘመቻዎቹም በአብዛኛው መፈክሩ ትግራይን በመዳሰስ ኤርትራን መደምሰስ የሚል እንደምታ ነበረው፡፡

የኋላኋላ ግን ደርግና የቀኝ እጁ የነበረው የልዕለ ኃያሏ ሶቭየት ሕብረት የስለላ ድርጅት [ከይ.ጂ.ቢ.]በህወሓት የሚመራው የትጥቅ ትግል ለእንቅስቃሴያቸው ትልቁ እንቅፋትና አደጋ መሆኑን ደርሰውበታል፡፡ ከዚህ የተነሳም ሶቭየት ሕብረት ለደርግ ዘመናዊ የጦር መሳርያና ሎጂስቲክስ አቅርቦት በገፍ በማቅረብ፣ የስለላና የውግያ ስልትና ጥበብ ስልጠና በመስጠት፣ በጣም የተራቀቁ የዘመቻ ስምሪቶችን ፕላን በማዘጋጀት ህወሓትን ለማጥፋት እጅግ ብዙ ጥረቶች አድርጋለች፡፡ ከ1970ዎች አጋማሽ ጀምሮ በተለይ በ70ዎቹ መጨረሻ ዓመታት ደርግ በትግራይ ያካሄዳቸው ዘመቻዎች ይህንኑን በግልፅ የሚያሳዩ ነበሩ፡፡ ህወሓት እነዚህ በሶቭየት ሕብረት ከፍተኛ የፖለቲካና ወታደራዊ አመራር የተካሄዱበትን ዘመቻዎች በሚያስገርም ቆራጥነትና የአላማ ፅናት በመመከት፣ ደርግ ከሶቭየት ሕብረት በገፍ የታጠቀውን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በመማረክ ይበልጥ እየፈረጠመ ናበድል እየተራመደ ወደ ስትራተጂያዊ ማጥቃት መሸጋገር ችሏል፡፡ ህወሓት ወደዚህ ከፍታ በደረሰበትና በደርግ ውድቀት ዋዜማ ወቅት ሶቭየት ሕብረት በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተመታ መሰነጣጠቅ የጀመረችበት ክስተት ስለተፈጠረ ደርግን ልታግዝ ቀርቶ ራሷን መታደግ ተስኗት የመፈራረስ ፈተና አጋጠማት፡፡ በዚህም የምስራቁ ልዕለ ኃያል ካምፕመናድ ሲጀምር የምእራቡ ዓለም ሙሉ በሙሉ የበላይነቱን ለመያዝ በቃ፡፡

በሌላ በኩል ልዕለ ኃያሏ ኣሜሪካና ምዕራባውያኑ ሸሪኮቿ የህወሓት ዓላማና ጥንካሬ የማይጥማቸው ቢሆንም ከሶብየት ሕብረት ጋር ተጣብቆ ለስትራተጂያዊ ጥቅማቸው እንቅፋት ነው ብለው ከፈረጁት ደርግ ጋር ሲያነፃፅሩት ለህወሓት ትልቅ ትርጉም ሰጥተው በአጀንዳቸው የያዙት አልነበረም፡፡ በሂደትም ደርግን በማዳከምና በማሸነፍ ስልጣን ይዘው የኛን ዓላማ ያስፈፅማሉ ያልዋቸውን በአብዛኛው የትምክሕት ኃይሎችን በተለያዩ ድጋፎች ሲያጠናክሩ ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ምዕራባውያኑና የዓረብ አገራት ህወሓትን ኮሚኒስት በሚል ጥርጣሬ የተነሳ ከሌሎች ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚደርሳቸውን ኢንፎርሜሽን መሰረት በማድረግ በህወሓት የውጭ ጉዳይ እንቅስቃሴ ላይ ቀላል የማይባል ጫና ሲፈጥሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ይሁንና በአንድ በኩል ምዕራባውያኑ ተስፋ የጣሉባቸው ተቃዋሚ ኃይሎች በደርግ እየተንኮታኮቱ የመጡበት፣ የኤርትራ ታጣቂ ድርጅቶችም ሳይቀር ብዙ ተስፋ የማይጣልባቸው የሆኑበትና ራሳቸውን ከደርግ ጥቃት ወደ መከላከል የገቡበት ሁኔታ  ሲታይ በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ፍጥነት ያድጋል ተብሎ ያልተገመተውና የተናቀው ህወሓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ ፈርጣማ ሆኖ የወጣበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በዚህም በደርግ ላይ ከፍተኛ ጫናና ምት ሊያሳርፍ የሚችል ህወሓት ብቻ እንደሆነ ለሁሉም ግልፅ እየሆነ መጣ፡፡ በዚህ ምክንያት የምዕራቡ ዓለም የህወሓት ዓላማና ጥንካሬ የማይዋጥለት ቢሆንም ቅሉ የመጀመሪያ እንቅፋት አድርጎ ከሚያየው ደርግ አንፃር ሲመዝነው ግን ከህወሓት ጋር ቅራኔ መፍጠር ተመራጭ ሆኖ አላገኘውም፡፡ ለጊዜውም ቢሆን ህወሓትን ችላ ብሎ በማለፍ በደርግ ላይ ትልቅ ጫና እንዲያሳርፍለት ይፈልግ ነበር፡፡ ይህ አጋጣሚ በሁለቱ ልዕለ‑ኃያላን ያለውን ቅራኔ የመጠቀም ስልት ለሚያራምደው ህወሓት በተነፃፃሪ የተመቸ የትግል ሁኔታ እንደፈጠርለት ይታመናል፡፡ ህወሓት በበኩሉ በስልታዊ መድረኩ በቅድሚያ መታየት ያለበት የሶቭየት ሕብረት ጣልቃ ገብነት ነው ብሎ ያስቀመጠ ስለነበር ከምዕራቡ ዓለም ጋር ወደ አላስፈላጊ አታካራ እንዳይገባ በጥንቃቄ ይጓዝ ነበር፡፡ ሁለቱም ኃይሎች [ህወሓትና ምዕራባውያን] ልዩነታቸውን በይደር በማቆየታቸው ለትጥቅ ትግሉ የተመቸ ሁኔታ እየፈጠረ ሄደ፡፡ በሂደትም የሁለቱ ስልታዊ ግብ [ደርግንና የሶቭየት ሕብረት ጣልቃ ገብነትን ማስወገድ]ለማሳካት አስቻለ፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ምዕራባውያኑ ስለ ህወሓት ምንነትና የአመራር ጥንካሬ ከቅንጭብጭብ ኢንፎርሜሽን በዘለለ የረባ መረጃና እውቀት የነበራቸው አይመስልም፡፡ ከደርግ መደምሰስ በፊት ስለ ህወሓትና አመራሩ ጥልቅ ጥናት እንዳልነበራቸውም ይነገራል፡፡ ህወሓት በዓውደ‑ውግያ የማሸነፍ ዕድል ሊኖረው እንደሆነ እንጂ ድሕረ-ደርግ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፣ አገር በመምራትም ተዋናይ ይሆናል የሚል ግምት የነበራቸው አይመስልም፡፡ የህወሓት ሚና ደርግን በመደምሰስ እንደሚያበቃ አድርገው የሚያስቡ አንደነበሩ በዛን ጊዜ ከነበራቸው አመለካከትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመገንዘብ የሚከብድ አይደለም፡፡ የደርግ ውድቀት ሲረጋገጥ በተለመደው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሴራቸው [በሌሎች አገሮች ተግባራዊ እንዳደረጉት ሁሉ] ህወሓትን ከጨዋታ ውጭ እንደሚያደርጉት እምነት የነበራቸው ይመስላል፡፡ ደርግ ሊወድቅ በተቃረበበትና በወደቀ ማግስት ሲያደርጉት የነበረ እንቅስቃሴ ሲታይም ይህንን የሚያረጋግጥ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከደርግ ወድቀት ማግስት ኢትዮጰያን ሊያስተዳድር የሚችል አማራጭ ያሉት የግለሰቦች ስብስብ በጥናት ይዘው እንደነበርም ከታማኝ ምንጮች ይነገራል፡፡

የውግያ ጡንቻው ከማሳየት ባለፈታላቋን ሀገረ‑ኢትዮጵያ በብቃት በመምራት የማረጋጋት፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችንፈር በማስያዝ ውጤት የማስመዝገብ ተልእኮ ብዙም የሚሳካለት አይሆንም ተብሎ በብዙዎቹ ዘንድ የታሰበው ህወሓት በአጭር ጊዜ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር [ኢህአዴግ] በመመስረት የትጥቅ ትግሉን ለመሰረታዊ አገራዊ የፖለቲካ ስኬት አደረሰው፡፡ግንባሩ ከተመሰረተ አጭር ዕድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም በህወሓት ፊታውራሪነት ከዕድሜው በላይ ተፅእኖ ፈጣሪ ለመሆን በቃ፡፡ የካበተ ልምድ አላቸው ከሚባሉት የዓለም የገንዘብ ተቋማት ሳይቀር በሽግግሩ ወቅትና ማግስት ያጋጠሙትን ተግዳሮች በብቃት ለመመከት ያደረገው እንቅስቃሴና እያደረ ያስመዘገበው ውጤት ብዙዎችን ያስደመመ ነበር፡፡ እንደ ዩጎዝላቭያና ሞንሮቪያ ትበታተናለች ተብሎ የተተነበየላት አገር በብቃት አረጋግቶ ማስቀጠል መቻሉ፤ የተሳካ የሽግግር መድረኽ መርቶ፣በሰፊ የህዝብ ተሳትፎ ሕገ-መንግስት ማስፀደቅና በህዝብ ምርጫ የተሰየመ መንግስትን ለማቋቋምና የአገሪቱ ኢኮኖሚ የቁልቁለት ጉዞ በመግታት የእድገት ዜና ለማብሰር መብቃቱ ኢህአዴግ ቀላል ኃይል አለመሆኑን በኃያልያኑ መንግስታት ዘንድ ትልቅ ሓሳብ ጫረ፡፡ ብዙዎች ያልተገነዘቡት የኢህአዴግ የንድፈ-ሓሳብ፣ የፖለቲካና የአመራር ብቃትም ጋሃድ ሊሆን ቻለ፡፡

ግንባሩ የልማታዊ መንግስታትን ተሞክሮ በመቀመር በነደፈው የልማታዊ መንግስት ፖሊሲም በአገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ ባለ ሁለት አሃዝ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ቻለ፡፡ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ እድገቱ የሀብት ትሩፋት ክፍፍሉም ከማንኛውም አገር የተሻለና ፍትሃዊነት ያለው እንዲሆን የሚያደርግ የፖለሲ አቅጣጫ ተከተለ፡፡ በዚህም ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ሲወጣበ 1983 ዓ/ም ከድህንነት ወለል በታች የነበረው ዜጋ 60.5% ሲሆን ይህ አሃዝ በ1993 ዓ/ም ወደ 53.6% በ2008 ዓ/ም ደግሞ ወደ 23.5% ዝቅ ብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ተርታ ላይ ከሚገኙት 10 የዓለም አገራትአንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡ በዲፕሎማሲው መስክም ከጊዜ ወደ ጊዜ አበረታች ለውጥ በመታየቱ የአገሪቱ ተሰሚነት በአፍሪቃ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃም ከፍ ሊል ችሏል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከሁሉም ዓይነት ጥገኝነት ደረጃ በደረጃ እየተላቀቀች በራሷ መዘውር ብቻ የምትሽከርከር አገር መሆንዋ ለምዕራባውያኑ [ኒዮ‑ሊበራሊስቶች] የሚዋጥላቸው አልሆነም፡፡ ቀደም ሲል የናቁት ኃይል ባልተገመተ ፍጥነት የመጓዝ ዓቅም እያሳየ በመምጣቱ ኒዮ­­­­‑ሊበራሊስቶቹ ፈፅሞ ሊቀበሉት የሚችሉ አልነበረም፡፡ ይህንን ጉዞ የተለያዩ መሰናክሎች በማጥመድ ለማኮላሸትም ሙከራዎች አድርገዋል፡፡ ኢህአዴግ በበኩሉ የእነዚህ መሰናክሎች ባህርይ በሳይንሳዊ መንገድ እያጠና መፍትሄዎችን በማስቀመጥ ሊሻገራቸው ችሏል፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ እነሱ ካሰቡትና ካስቀመጡት በላይ ዓቅም ያለው መሆኑን ሳይወዱ ለመረዳት ተገደዋል፡፡ ከዚህ የተነሳ አንድ ብለው ኢህአዴግ እንዴት ማንበርከክ እንዳለባቸው ለሁለት አስርት ዓመታት በስለላ ድርጅታቸው ሲ.ኣይ.ኤ. አማካኝነት ጥናት ሲያደረጉ ቆይተዋል፡፡ ከጥናታቸው በመነሳትም ኢህአደግን ሊያዳክምና ሊያንበረክክ ይችላል ያሉትን በተለያየ ጊዜያት ሴራ ከማቀነባበር አልቦዘኑም፡፡ በአገር ውስጥ ለዚሁ ሴራቸው የተመቻቸ ሁኔታ ስላልነበራቸው፣ ይህ እስኪመቻች ድረስ በዋነኛነት በኢህአዴግ ላይ ካኮረፈው የዲያስፖራ ማሕበረሰብ ውስጥ ይታዘዘናል ያሉትን ኃይል በመጠቀም ከአገር ቤቱ ፀረ‑ኢህአዴግ እንቅሰቃሴ ጋር በማስተሳሰር ሲሸርቡ ኖረዋል፡፡ በተለያየ ጊዜም ይብዛም ይነስ የቀለም አብዮት ሙከራዎች አድርገዋል፡፡

ኒዮ‑ሊበራሊስቶችና የኢትዮጵያ እድገት ብሄራዊ ጥቅማችንን ይጎዳል ብለው ሁሌም የሚያስቡ አንዳንድ አገራት የኢትዮጵያን ፈጣን እድገት እንቅልፍ ሲነሳቸው ታይቷል፡፡ በዚህ የተነሳም ይህንኑን ለመቀልበስ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ ብዙ ነገር ሞክረው አልሳካ ሲላቸውም ለዚህ እድገት ዋና አንቀሳቃሽ ሞተር የሆነው ኢህአዴግን በማዳከም ሽባ ለማድረግ ቆርጠው ተነሱ፡፡ ለዚህም የመጀመሪያ እርምጃቸው ያደረጉት የኢህኣዴግን ጠንካራ አመራር ማዛባት ነበር፡፡ የኢህአዴግ “የስበት ማእከል’’ [1] የሆነውን ህወሓት ላይ ጠንካራና የማያቋርጥ ምት ማሳረፍ ላይ ያለ የሌለ ኃይላቸውን በመጠቀምም ተረባረቡ፡፡ ለዚህ ዓላማቸው ትግበራ የጠንካራውና ታዋቂው መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ያልተጠበቀ ህልፈተ‑ህይወት አመቺ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ይታመናል፡፡ የአቶ መለስ ድንገተኛ ሞት በብዙዎች ዘንድ እንቆቅልሽ የሆነና እስካሁንም ጥያቄዎችን እያጫረ ያለ ክስተት ነው፡፡ የተለያዩ መላምቶች በማስቀመጥ በአሜሪካና የግብፅ የስለላ ድርጅቶች ተቀነባብሮ የተፈፀመ ድርጊት እንደሆነ የሚያምኑ ጥቂቶች አይደሉም፡፡የአሟሟቱ ጉዳይ በዚሁም ይሁን በሌላ ክስተቱ ግን በኢህአዴግ ውስጥ የተለየ ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ይህ ፍላጎታቸው በመሳካቱ ደግሞ እነዚህ ኒዮ‑ሊበራል የቀለም አብዮቶኞች የተቀረውን የኢህአዴግ ኮር ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ብዙም ከባድ ሆኖ አልታያቸውም፡፡ስለሆነም ኢህአዴግን በማዳከም የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ በሁሉም መስክ ለማሽመድመድ በተለያዩ ጊዜያት ሲሞካክሩት የነበረውን የቀለም አብዮት እቅዳቸው በነውጥ መስመር ይበልጥ በማጠናከር ወደ መረባረብ ገቡ፡፡ ይህ ደግሞ የተሳካላቸው ይመስላል፡፡በመሆኑም፣ አሁን ኢትዮጵያ ከህዳሴው የልማታዊ ዴሞክራሲ ሐዲድ ወጥታ በነውጥ መስመር [shock doctrine] እየተመራች ያለች መሆንዋ ጋሃድ እየሆነ ነው፡፡

Full Website