ለፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የሆኑ ፀጥታ አደፍራሽ ሀይሎች መንግስት ቢያውቃቸው እንጂ የኢትዮጵያ አያውቅም ። ህዝብ ካላወቀ ደግሞ ከመንግሥት ጋር መተባበር አይችልም ። በመሆኑም ማህበራዊ ችግሮች ከመቀነስ ይልቅ እየተባባሱ የመሄድ አጋጣሚ መፈሩ አይቀርም ። መንግስት ወቅታዊ እንዲሁም በቂ መረጃ ለህዝብ አይሰጥም ። ህዝብ መረጃ የማግኘት መብቱ ሲነፈግ የፀጥታና መረጋጋት ችግር ይስፋፋል ። መንግስት ባለቤት የሌለው አጀንዳ እያናፈሰ የህዝብ ሰላም ያውካል ። በምዕራብ ሆነ በምስራቅ ፣ በሰሜን ሆነ እንዲሁም በደቡብ የአገርና የህዝብ ደህንነት ስጋት ለይቶ ለህዝብ የማሳወቅ የመንግስት ሀላፊነት ነው ። ህዝብ በአገሩ የሚፈፀሙ የፀጥታ ስጋቶች የማወቅ ሙሉ መብት አለው ። ህዝብ ሰለ አገሩ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ይበልጥ ባወቀ ቁጥር  ሰላሙን የማስጠበቅ ሀላፊነቱ ይወጣል ። ጠቅላይ ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ በለውጥ ሰም የታሰሩ እና የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በቀላሉ የሚገመት አይደለም ። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ከመሬት ይዞታ እንዲሁም የንግድ ስርአትና ዝውውር ጋር በተያያዘ በትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሰ እስራትና መንገላታት ተገቢ አልነበረም ። አህያውን ፈርቶ ዳውላው  እንደሚባለው መሬት ሲሸጡ ሲለውጡ የነበሩ ባለስልጣናት ተጠያቂ ሳይሆኑ የግለሰቦች ንብረትና ሐብት እንዲታገድ መደረጉ ተገቢ አልነበረም ። በምዕራብ ኢትዮጵያ የመንግስት ሆነ የግል ባንኮች በኦነግ ታጣቂዎች ሲዘረፍ ፣ ንፁሃን ሰዎች ሲገደሉ መንግስት እንዳልሰማ ማለፉ ከትዝብት በላይ ነበር ። ዜጎች በአገራቸው ተፈናቃይ እንዲሆኑ መሆን ከመንግሥት አልባ አገር እንኳን የማይጠበቅ ድርጊት ነበር ። በኮዮፈች የጋራ መኖሪያ ቤቶች የቤት ባለቤት እጣ እድለኞች በጃዋር መሐመድ አማካይነት እደላው እንዲቆም መደረጉ እንዲሁም ጉዳዩ በጠቅላይ ሚኒስትር የዘር የፖለቲካ ድርጅት መደገፉ አሰገራሚም አሳዛኝም ነበር ። ያ ክሰተት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የህዝብ መሪ ለመሆናቸው አጠያያቂ ነበር ። የአማራ እና የትግራይ አገናኝ መንገዶች በስርአት አልባ የመንግስት ሀላፊዎች ሆኑ ግለሰቦች ሲዘጉ የጠቅላይ ሚኒስትር አሰተዳደር ምንም የማስተካከያ እርምጃ ያለመወሰዱ የመንግስት የማስፈፀም አቅም መሽመድመድ የሚያመላክት ነበር ። ኢትዮጵያ እንደ አገር እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ህዝብ ከመበልፀግ ይልቅ መደህየት ፣ ከመደጋገፍ ይልቅ መጠላለፍ ፣ ከመከባበር ይልቅ መጠላላት ፣ ከአንድነት ይልቅ መነጣጠል ፣ ከመተሳሰብ ይልቅ ፣ መጎዳዳት እንዲያቆጠቁጥ አንዱ ምክንያት ለሴራ ፖለቲካ ተገዢ መሆን ይመስለኛል ። የፖለቲካ ሰልጣን ለመያዝ መገዳደል ለምን አስፈለገ ? ። ወንድም ወንድሙን አጥፍቶ የመንግስት ስልጣን ለመጨበጥ ማሰቡ በራሱ አብይ ስህተት ነው ። የመንግስት ስልጣን የህዝብ መሆኑ የሚያምኑ ፖለቲከኞች የሴራ ፖለቲካ ስንክሳር ውሰጥ መነከር ኪሳራ ቢሆንም እንጂ ትርፍ አይኖረውም ። የሴራ ፖለቲካ አገር አፍራሽ ፣ ትውልድ ጨራሽ ፣ ህዝብ በታኝ ፣ የአገር ልማት አውዳሚ ፣ የድህነት መነሻ ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግጭት ምክንያት ፣ የኋላቀርነት ማሳያ ምልክት ነው ። በሀሳብ ልዕልና ተከራክሮ ፣ በህዝብ ይሉኝታና ተቀባይነት አግኝቶ የመንግስት ሰልጣን ከመያዝ በጠበንጃ አፈሙዝ ስልጣን ላይ ለመውጣት ማሰብ የዋህነት ብቻ ሳይሆን አገራዊ ወንጀል ነው ። በሴራ ፖለቲካ የመንግስት ሰልጣን የሚጨበጥ መንግስት በህዝብ ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም ። የፖለቲካ ስልጣነ የህዝብ አሰተዳደር በመሆኑ የህዝብ ይሉኝታ ያሰፈልጋል ። የሴራ ፖለቲካ መጠንሰሰ የህዝብ ውሳኔ መግታት በመሆኑ በምንም መልኩ ተቀባይነት የለም ። ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ የተፈፀመው በጅምላ የክልሉ ባለስልጣናት የመረሸን ተግባር የተወገዘ ሲሆን መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ያስቆጣ አሳዛኝ ድርጊት ነው ። ድርጊቱ በምንም ማሳያ ኪሳራ እንጂ ትርፋማ አልነበረም ። በእኔ አተያይ በባህርዳርና አዲስ አበባ የተፈፀመው የግድያ ወንጀል የመፈንቅለ ሰርአት እንደነበር ስምምነት የለኝም ። የሰኔ 15 ቀን በአማራ ክልል በህዳር ከተማ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ላይ የተፈፀመው አሳፋሪና አሳዛኝ የሴራ ፖለቲካ ወንጀል በገለልተኛ አጣሪ ኮምሽን መመርመር እና መጣራት አለበት የሚል እምነት አለኝ ። የጠቅላይ ሚነስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር የ 2011 የበጀት አመት ዝርዝር የሥራ አፈፃፀም ለኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባቀረቡበት ወቅት ወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከምክር ቤቱ በጥያቄ መልክ ተነስቶ ነበር ። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመንግስት ትዕግሥት እሰከ አገራዊ አንድነት ድረስ እንደሆነ ነገር ግን የአገር ልዕልና እንዲሁም የህዝብ ደህንነት የሚፃረር ሁሉ አሰፈላጊ መንግሰታዊ እርምጃ ይወሰዳል ሲሉ ተደምጧል ። በክልሎች ከተሞች ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ሰዎች በገፍ እየታሰሩ እንደሆነ የሰማል ይታያል ። በእኔ እምነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ህግን መሠረት ያደረገ እርምጃ ለመውሰድ ዘግይቷል የሚል እምነት አለኝ ። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ጠበንጃ አንግበን እንዋጋለን ሲሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ሀሳቡን በጭብጨባ ሲደግፉት ማየቴ በሁሉም ባይሆን ደጋፍ በሰጡ የምክር ቤቱ አባላት ላይ አዝኛለሁ ። ለምንና እንዴት ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ ግደል ብሎ ድጋፍ መሰጠት ከምክር ቤት አባላት የሚጠበቅ አልነበረም ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ ሳለ ምክርቤቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እስኪመስል የወረደ የልጅ ጨዋታ ነበር የታዘብኩት ። መንግስት ህግን መሠረት አድርጎ ወንጀል መከላከል ሲቻል ሀይል እጠቀማለሁ ሲል ማጨብጨብ ለምን አስፈለገ ። የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር መቶ በመቶ በኢህአዴግ የተያዘ ነው ። በመሆኑም የሀሳብ ልዩነት ፍጭት የማይታይበት ደካማ ምክርቤት ነው ። ህዝብ ከህግ ውጭ በሐይል ማስተዳደር ሰላምና መረጋጋት አያመጣም ። ህዝብ ለህግ ካልተገዛ ለሐይል አይገዛም ። በመሆኑም የተረጋጋ አገር ለመፍጠር ህግን መሠረት በማድረግ ወንጀል መከላከል ይቻላል ። ችግሩ የፍትሕ ተቋማት ገለልተኛ ካለመሆን ጋር በተያያዙ የሚፈጠሩ ማህበራዊ ችግሮች ውስብስብ ከመሆናቸውም በላይ ፍትሀዊ የህግ አሰራር እንዳይኖር ምክንያት ይሆናል ። ለህዝብ ታማኝ ያልሆነ መንግስት አገራዊ ችግሮች በቀላሉ መፍታት አይችልም ። የህዝብ ደህንነት የማያስጠብቅ መንግስት በትናንሽ አጀንዳዎች ጊዜ ከማጥፋት ውጭ የህዝብ ፍላጎት አያሟላም ። በመሆኑም መንግስት ህዝብ በማያምንበት ጉዳይ ጊዜ ማባከን የለበትም ። የህዝብ ፍላጎት ሰላምና መረጋጋት መስፈን ነው ። የህዝብ ፍላጎት የመንግስት ፍላጎት ከሆነ ህዝብ የሚጠይቀው መንግስት ማስተካከል አለበት ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር የኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ጀሮ መሆን ላይ መሸራተት ይታይባቸዋል ። የህዝብ ድምፅ በአግባቡ አይሰማም ፣ አይመዘንም ፣ ተግባር ላይ አይውልም ። በኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች ላይ ለተፈፀሙት ከፍተኛ የግድያ ወንጀሎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቀጥታ ሆነ በሌላ ከተጠያቂነት ውጭ አይሆንም ። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሐንዲስ በግፍ መገደል ገና ያልተጣራ ጉዳይ ነው ። የአማራ ክልል አሰተዳደር ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች የጭካኔ ግድያ ከአማራ ዲሞክራሲ ፖርቲ ካድሬዎች አሰተያየት ውጭ በቂና ገለልተኛ መረጃ አልተገኘም ። የኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦር አዛዥ በግፍ መገደል ከገለልተኛ አካል መረጃ ገና አልተገኘም ። በግድያ ሴራ ላይ የመንግስት እጅ ይኑር አይኑር በገለልተኛ የተጣራ መረጃ የለም ። ጉዳዩ በገለልተኛ ካልተጣራ መንግስት በሚሰጠው መረጃ ብቻ ተመሥርቶ ትንታኔ ለመስጠት የሚቻል መስሎ አልታየኝም ። ምክንያት እውነት ከቤተመንግስት ይገኛል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው ። ? ። የኢትዮጵያ መከላከያ የበላይ ሀላፊ ጀነራል ሰዐረ መኮነን እንዴት በቅርብ ጠባቂው ይገደላል ? ። የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳድር ለመግደል ሴራ ሲጠነሰሰ የኢትዮጵያ የደህንነት መሥሪያ ቤት ጉዳዩ እንዴት ሳያውቀው ቀረ ? ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ የሐሳብ ልዩነት ምክንያት መገዳደል ማብቃት ያለበት ጊዜ ይመስለኛል ። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ባለቤት አልባ አጀንዳዎች እንዲሁም ውጤት አልባ የሴራ የፖለቲካ አካሔድ ማቆም ፍትሀዊነት ነው ። ክብር ነክ የትንኮሳ ንግግር አለፍ ሲልም የዘር ፖለቲካ ማራመድ ማቆም ፍትሐዊነት ነው ። ህዝብ የሚያከብር ፣ለህዝብ ደህንነት ጥብቅና የሚቆም ሀቀኛ የፖለቲካ ድርጅት እንዲያቆጠቁጥ ፣ የዲሞክራሲ መርህ ተኮር የፖለቲካ ሰርአት እንዲያብብ ከተፈለገ በህግ ልዕልና የሚመራ ህዝብና መንግስት መኖሩ የግድ ይሆናል ። መንግስት ህዝብ ገዳይ ፣ ህዝብ ደግሞ መንግስት ገዳይ ከሆነ አገርም ህዝብም አይኖርም ። በመሆኑም ለህግና ሰርአት ልዕልና የቆመ መንግስት ያሰፈልጋል ። ህዝብና መንግስት መናበብና መግባባት ካልቻሉ የችግር መነሻ ይሆናሉ ። አገር በህግ የበላይነት እንጂ በአድርባይ የፖለቲካ ድርጅት ካድሬዎች አይመራም ። የፖለቲካ ድርጅት ካድሬዎች ከህግ በላይ ሆኖ ዜጋ ሲበድሉ እርምጃ የማይወስድ መንግስት ለህዝብ አስተዳደር አይደለም የሞተ እሬሳ ለመቅበርም ብቁ አይደለም ። መንግስት የሚወስዳቸው የእርምት እርምጃዎች ለህዝብ አይገልጽም ። በመሆኑም በኢትዮጵያ ወንጀለኛና ንፁህ መለየት አይቻልም ። አውራ ጎደና የጭነት መኪና አስቁሞ የሚዘርፉ የተደራጁ ስርአት አልባ ሰዎች መንግስት ተከታትሎ ለህግ ማቅረብ ሥራው ነው ። ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ተቀዳሚ የመንግስት ሰራ ነው  ። ልማት ማፋጠን ፣ የአገር አንድነት ማስጠበቅ ፣ የህዝብ ድህነት ማስከበር ፣ ሥራ አጥነት መቀነስ ፣ ሁሉም አይነት ወንጀሎች አሰቀድሞ መከላከል መንግስት ከህዝብ የተቀበለው ሀላፊነት ነው ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሰተዳደር በበርካታ ችግሮች የተከበበ ቢሆንም የችግሮች መፍትሔ ደግሞ ራሱ መንግስት ነው ። ያለአግባብ በአዲ አበባ ከተማ የታሰሩ በርካታ የትግራይ ተወላጆች በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው ። የአማራ ህዝብ እና የትግራይ ህዝብ በጠላትነት እንዲተያይ ጥላቻ የሚሰብኩ የኢህአዴግ ካድሬዎች ከድርጊታቸው መታቀብ የግድ ይላቸዋል ። የአማራ አሰና የትግራይ ህዝብ ወንድም ህዝብ እንጂ የቆየ ቅራኔም ሆነ ቂም በቀል ያልተላበሰ ህዝብ ነው ። የሁለቱም ህዝብ የፖለቲካ ካድሬዎች ህዝብ የሚያቀራርብ ተግባራት ከመፈፀም ይልቅ አሉባልታ ላይ ተሰማርቶ ይታያል ። ይህ አስነዋሪ ድርጊት እንዲቆም ይፈለጋል ። በውይይት እንጂ በጉልበት የሚፈታ ጉዳይ የለም ። የአማራ ክልል ሆነ የትግራይ ክልል አመራሮች እየፈፀሙት ያለ የተሳሳተ የፖለቲካ ቁማር ተገቢነት የለውም ። መሬት የሰው ህይወት አይተካም ። የሐይል አሰራር ማንንም አያስተምርም ፣ ምንንም አያሰወግድም ። ትርፉ ትርምስና መተላለቅ ብቻ ነው ። ችግሮች ከጥላቻ በራቀ መንፈስ ለመፍታት መትጋት የአንድ መሪ ብልህነት ነው ። በቅርቡ የአማራ ክልል ምክርቤት ያስተላለፈው አስቸኳይ ውሳኔ በሚገባ የተሞከረበት ሳይሆን ከስሜታዊነት የመነጨ ውሳኔ ይመስለኛል ። የትግራይ ልዩ ሐይል ከአማራ አዋሳኝ ቦታዎች እንዲለቅ የሚል ሲሆን መቀሌ የመሸገው አጥፊ ሐይል ብሎ መፈረጅ አግባብነት የለውም ። በአንድ አገር እየኖሩ ፣ በአንድ አይነት ቋንቋ እየተግባቡ ፣ እንደ ባላንጣ መተያየት አግባብነት የለውም ። መስክን ያሰፈልጋል ። ከክብር ነክ የጥላቻ ንግግሮች መቆጠብ ያሰፈልጋል ። መቀሌ የመሸገው ሐይል ለኢትዮጵያ አንድነት ችግር መስሎ አይታየኝም ። ምክንያቱም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በመሆናቸው ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጋ የሚያስበው መሳብ የሚችሉ ሰዎች ናቸው ። የፖለቲካ ልዩነት ቢኖራቸውም ክፋት የለውም ። ሀሳብን በሐሳብ መሞገት ተፈጥሯዊም ህገ መንግሰታዊም ነው ።
Full Website