ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ቀውስ አፋፍ ላይ እንደደረሰች የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ለውጥ ደጋፊዎች የሆኑት ፈረንጆችም ካመኑበት ሰነባብተዋል። ከ 3 ሚልዮን በላይ ህዝብ በብሄር ጥቃት ምክንያት   በአገር ውስጥ ተፈናቃይ (IDP) ያለባት እና  ከ 8 ሚልዮን በላይ  የአስቸካይ ምግብ እርዳታ የሚፈልግ ህዝብ አደጋ ውስጥ ያለባት አገር የሚያስተዳድረው በዶክተር አብይ የሚመራው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በነሃሴ በመጀመርያው ሳምንት ውስጥ ስብስበዋን ማጠናቀቁ በአቶ ፍቃዱ ተሰማ የድርጅቱ ፅህፈት ቤት ሃላፊ በኩል መግለጫ ሰጥቷል። ይሁን እንጂ መደበኛው የተለመደው መግለጫ እስካሁን ድረስ አልተሰጠም።

ምነው? ምነው? ዶክተርየ! ፓርላማ ፊት ቀርበው ከአሁን በኃላ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ሳንሸፋፍን በግልፅ እንዳለ  ይቀርባል ብለው እንዳስጨበጨቡን ረስተዉት ነው፡፡ በቀጥታ ይተላለፋል የታበለውስ እሺ ይቅር መደበኛውና የተለመደው መግለጫ ለምን ይቀረናል? እንዴት ይባስ ብለው ተሸፋፍኖ በስብሰባው በነበረ አንድ አባል በተሰጠው አቅጣጫ ልክ ይገለፃል?

ከስብሰባው በፊት የነበሩትን ሁኔታዎች እስቲ በአጭሩ እንይ። የክልል ሃላፊዎች በጠራራ ፀሓይ በአዴፓ ማ/ኮሚቴ አባል በሆነ ሰው በቢሯቸው ተረሸኑ። የዚህ ድርጊት ፈፃሚዎችን በመከታተል የነበሩ የአገራችን ኤታማዦር ሹም ከድሮ የስራ ባልደረባቸው ከነበሩት ጄነራል አብረው በጠባቂያቸው በቤታቸው ውስጥ ተገደሉ። በዚህ ጉዳይ በተነሳ ምክንያት በህወሓትና በአዴፓ እንዲሁም በፌደራል መንግስት መካከል ልዩነት ተፈጠረ፡፡  በደቡብ ህዝቦች የራስ በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በማቅረባቸው  በአፈታት ችግርና ጊዜ መገተት ምክንያት ህውከት ተፈጠረ፡፡  ለፓርላማ ተጠሪነት የሌለውና ህጋዊነት የሌለው ኮማንድ ፖስት ታወጀ፡፡ ክልሉ የራስ በራስ የማስተዳደር ስልጣኑ በወታደሮች ስር እንዲቆይ የለውጡ መሪ፣ ጠቅላይ ሚኒስቴርና የኢህአዴግ ሊቀመበር ዶክተር አብይ ከስልጣናቸው ውጭ ወስነው በደቡብ ህዝቦች ወረራ ፈፀሙ። ይህ ባዘዙበት ቅፅበት ዓላማው ምንም ግልፅና ይፋ ያልተደረገ ድንገተኛ ጉብኝት በኤርትራ አደረጉ። የእሳቸው መውጣት ተከትሎ በደቡብ ህዝቦች ከልክ ባለፈና ያልተመጣጠነ እርምጃ የፌደራል መንግስት ወስዶ በሞቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገደሉ። ቆሰሉ። ተፈናቀሉ።

ከዚህ በኃላ ዘግይቶ ቢሆንም  የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ሲቀመጡ የጠበቅነው፣ በአገራችን ኢትዮጵያ ለምን ተከታታይ ቀውስ ገጠመ? ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው? ተጠያቂው ማን ነው? መፍትሔውስ? ከአፋርና ትግራይ ክልሎች በስተቀር በሁሉም ክልሎች በኮማንድ ፖስት ወታደራዊ አገዛዝ ስር እስከ መቼ ይቆያሉ? ብሎ ለውጥ ያደርጋል ብለን ነበር። ስብሰባው ግን ጭራሽ ሽፍንፍን በማድረግ አሁንም እንደጨለመን፣ ተስፋ እንደቆረጥን፣ መዳረሻው ወደ ማይታወቀው የጥፋት ጎዳና በደመነፍስ እየቀጠልን ነው። ጎዳናው አገራችንን ወደ ሚያፍረስ ወደ የመን፣ ሊብያ፣ ሶርያና ሶማሊያ ዓይነት ነው። ለዛውም ዕድለኞች ከሆን ነው።

ዶክተር አብይ ከቅድመ ጥልቅ ተሃድሶ በባሰ ደረጃ ከወሰዱን ፓርላማ ላይ የተጨበጨላቸውን ንግግራቸው በሾርት ሞመሪ ችግር ህዝቡ አያስታውሰውም ብለው ከደበባበቁ ያለን አማራጭ ሹክ ብለን ህዝባችንን ማሳወቅ ነው።

አንደኛ ሹክ። የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ አጀንዳዎች ሁለት ነበሩ። ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ግምገማና ቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች። ሁለተኛው አጀንዳ ስለ ፓርቲ ውህደት ነበር።

ሁለተኛ ሹክ። አቶ ለማ ከረዥም የአሜሪካ አገር ጉዞ በኃላ በስብሰባው ተገኝተዋል። ዶክተር ደብረፅዮን ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት በስብሰባው አልተገኙም። ሌሎች ሁሉም ነበሩ አቶ ሚሊዮን ጭምር።

ሦስተኛ ሹክ። ስብሰባው እንደተጀመረ የአዴፓ አመራሮች በህወሓት ላይ ፕሮስጀር በተደጋጋሚ እያፈረሳቹሁ … ብለው ምሬት በተሞላበት መንፈስና ሁኔታ ጥቃት ጀመሩ። ሌሎችም ተከትለው በህወሓት ላይ የተጀመረውን ጥቃት ተቀላቀሉ።  የኢህአዴግ ዲሲፒሊናዊ የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሰራር ጣሳቹህ ብለው አምርረው ወቀሱ። መርህ በማፍረስ ህወሓት የውስጥ ገበናችንን ወደ ውጭ ማጋለጡ ትክክል አይደለም አሉ። ነገሩን ስብሰባ እንዲጠራ ጠይቆ በዝግ ስብሰባ እንዲታይ ማስደረግ እየተቻለ መግለጫ ማውጣት አልነበረበትም አሉ። የፀረ-ህወሓት ቃል ኪዳን ግንባር አሁንም እንደጠበቀ ይመስላል። ህወሓት ዛሬ ጉድ ሆኑ አለቀላቸው ብሎ አድፍጦ ምንም ቃል ሳይተነፍስ የሚያዳምጥም ቀላል ያልሆነ አባል አለ። አጎንብሶ መልሶ የማያየውና የማያነበውን ማስታወሻ ላይ የሚቸከችክ እንደዛው። ህወሓት ተራው ደርሶ ቀጠለ። አምርረው ግን ቀስ ብለው በትዕግስት ጉዳዩ በመካከላችን ያለው ችግር ልዩነት ፕሮስጀራል ቢሆን ነሮ ምንኛ በታደልን ብለው ጀመሩ። ግን ባለመታደል ሆኖ ልዩነታችን ከፕሮሲጀር በላይ ነው። እኛና እናንተ የተለያየንው በመስመር ነው። የአብዮታዊ ዲሞክራሲን መስመር አሽቀንጥራችሁ የኒዮ-ሌበራሊዝም አቀንቃኝ ነን ከምትሉ ጋር ምንም አንድ የሚያደርገን ነገር የለም አሉ። ፕሮሲጀር ይከበር የምትሉት መጀመርያ ፕሮሲጀሩ የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የፓርቲ እስርቤት አሰራር ነው ብሎ አሽቀንጥሮ የጣለው ማን ሆኖ ነው? ብለው ሞጎቱ። ህገ መንግስቱን በአደባባይ የሚቃወምና በተግባር እያፈረሰ ካለ የኢህአዴግ ፓርቲ አባላት ጋር ችግርና ልዩነት እንጂ እንዴት ተብሎ ፕሮሲጀራዊ አንድነት ይኖረናል። የትኛው ነው እንዴ የሚቀድመው? በይዘት ተለያይተን በፕሮሲጀርና በዲሲፒሊን እንዴት እንጠያየቃለን? ፈደራሊዝም አልሰራም አሃዳዊ እንመለስ ብላቹሁ ይህን መፈክር ከሚያሰሙ የፋሽስት ደርግ ርዝርዦች ግንቦት ሰባትና ሌሎች አሰላለፋቹህን ካሳመራቹህ ጋር እንዴት አንድ እንሆናለን? ይህ ሁኔታቹህ ደግሞ አገራችን አሁን ለደረሰችበት ፈታኝ የመበተን አደጋ አፋፍ ላይ እንድትሆን ዳረጋት በማለት እንደሁሌም ህዋሕቶች ያላቸውን ፅኑ አቃምና ልዩነታቸውን ሲያቀርቡ አዲሱ ቤት ፀጥ ረጭ ብሎ ተሰብሳቢዎቹ በድንጋጤ ክው ብሎው ያዳምጡ ነበር አሉ።

አራተኛ ሹክ። ማፈግፈግ አይሉት ሽወዳ የህወሓትን መልስ ያልጠበቁት የኢህአዴግ የለውጥ መሪ ነን ባዮች ፈጥነው ልዩነት የለንም አሉ። አብዮታዊ ዲሞክራሲ መመርያችን ነው። ህገ መንግስቱን በተለይ ፌደራሊዙም አማራጭ የሌለው ስርዓት ነው። ምርጫም ማን አባቱ ያስረዝመዋል በወቅቱ ይካሄዳል ተባለ። ለአንድ ዓመት ተኩል ያልተናገርዋቸውና ሲፀየፏቸው የከረሙትን አብዮታዊ ዲሞክራሲና ፌደራሊዝም የኛ ነው አሉ። ቀጠሉ ምንም ልዩነት የለንም። ምርጫውም በህገመንግስቱ እንጂ እኛ የምንወስነው አይደለም አሉ። አሁን ጥቃቱ ከህዝብ አልፎ ወደ ፖለቲካ አመራሩ እያነጣጠረ ነው፣ ጎበዝ በአንድነት እንመክተው እንጂ በሌለን ልዩነት አንሟገት አሉ። የለውጥ መሪውቹ ነን ባዮችም ዶክተር አብይ ለጥቀው አለቃህን ተከተል ይመስል ምክትል ሊቀምበሩ ደመቀ መኮነን እንደሁሌም አይናቸውን አፍጥጠው የግምባራቸውን ቆዳ ሰብሰብ ዘርጋ እያደረጉ አንድ ነን ልዩነት የለንም አሉ። ምን ግድ አላቸው በቀጥታ ስርጭት አይተላለፍ። እዚህ አደራሽ ውስጥ ውሸት ይደሰኩሩና በኃላ በመግለጫ ይሸፋፉንታል። ህወሓት እንደዛ አልነበረም ብሎ መግለጫውን ሲቃወም ደግሞ ጆሮ ዳባ ይሉታል።

አዴፓዎች የሰጠንነው መግለጫ አሳፋሪ ነው። በስሜት ተገፋፍተን ነው። አንድ ላይ የታገለን ድርጅት እንደዛ ማለታችን እኛንም አርባ ዓመት እንደበግ ለምን እየተጎተትን ቆየን የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው አሉ። ገሚሶቹ የአዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የአዴፓ መግለጫን ስንሰማ ደነገጥን ይላሉ። መግለጫው የጋራ እንዳልነበረ ፍንጭ በሚሰጥ አነጋገር።

የህወሓት አባላትም መግለጫ ማውጣታችን በይዘትም በፕሮሲጀርም ትክክልና ወቅታዊ ነው አሉ። በአዴፓ ውስጥ የተፈፀመ መገዳደል ራሱን ያጥራ ማለታችን ትክክል ነው። የደቡብ ህዝቦችም በፓርላማ ጭምር በሃይል እንፈታዋለን የሲዳማ የክልል ጥያቄ ሲባል ትክክል አይደለም በሰላምና በህገመንግስት ይፈታ ማለት ጣልቃ መግባት አይደለም ይመለከተናል። ለሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የሚመለከት ነው ብለው እምነታቸውን ገለፁ።

አምስተኛ ሹክ። ክረምት አይደለ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ትልቅ ያልታሰበ ነጎድጋድ ድምፅ ተሰማ። አትደንግጡ። በኢህአዴግ ስብሰባዎች ለረዥም ጊዜ ድምፃቸው አሰምተው የማያቁት አቶ ለማ በድንገት ተናገሩ። ከሳቸው የለውጥ መሪ ያልተጠበቀ ንግግር ቤቱን በሁለት የከፈለ ሃሳብ አቀረቡ። ንግግራቸውን የጀመሩት በሊቀምበሩ ዶክተር አብይ በተዘጋጀው መወያያ ፅሑፍ አርእስትን በመቃወም ነበር። ‘ሁለተኛ ጥፋት ቆሞ ማንቀላፋት’ የሚለው አርእስት ተቀይሮ ሁኔታችን የሚገልፀው ‘አገር አጥፍተን እኛም እየጠፋን ነው’ ቢሆን ነው የሚሻላ አሉ። ኢህአዴግ ፈርሷል። የለም። ከአሁኑ የፈራረሰው  ኢህአዴግና አገር ከለውጡ በፊት የነበረው ኢህአዴግና አገር ከነችግሮቹ ይሻላል አሉ። ከለውጡ በኃላ እየታዩ ያሉ ችግሮች በአገራችን ታሪክ ተከስተው ታይተው የማያቁ ናቸው። አገር የሚያጠፉ ናቸው። ዋናው ችግራችን ኢህአዴግ ባለመኖሩ ነው። ለውጡ ስለተጠለፈ (hijacked ስለ ተደረገ) ነው ችግር ላይ የወደቅ ነው። መዳን ከፈለግን ኢህአዴግ ወደ ነበረበት ቁመና እንመልሰው። ወይም በሰላማዊ መንገድ እንለያይ አሉ።
Full Website