1. ታሪካዊ መንደርደሪያ

ጤሶ በንቲ ( / ) የተባሉ የኦሮሞ ተወላጅ ምሁር ‘‘ Oromo Indigenous Religion and Oromo Christianity: Contradictory or Compatible?’’ በሚል አርእስት እ . . . 2018 ጀርመን ሀገር በሚገኘው የሐይልድሸም ዩኒቨርሲቲ ባሳተሙት የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ የጥናት ድርሳናቸው፤ በወቅቱ የወለጋ ጠቅላይ ግዛት ተብሎ በሚጠራው የኢትዮጵያ ግዛት ክፍል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ መንፈሳዊ አገልግሎት ጅማሬ ምን ይመስል እንደነበር እንዲህ ገልጸውታል፡፡

. . . 1898 . . ከኤርትራ ወደ ወለጋ ጠቅላይ ግዛት የመጡት መምህሬ ገብረ ኤዎስጣቴዎስ የተባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ / ክ ካህን የአፋን ኦሮሞ መጽሐፍ ቅዱስ ከተረጎመው ከአናሲሞስ ነሲብ / ከአባ ገመችስ ዘንድ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋን በሚገባ አጠንተው ነበር፡፡ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋን በግላቸው ያጠኑት እኚህ ካህን በወቅቱ የነቀምት ገዢ ከነበሩት ከፊታውራሪ ዲባባ ፊት ለመቅረብ ዕድሉን አግኝተው ነበር፡፡

መምህር ገብረ ኤዎስጣቴዎስ ከፊታውራሪ ዲባባ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከሐዲስ ኪዳን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በአፋን ኦሮሞ ካነበቡላቸውና መዝሙር ከዘመሩላቸው በኋላ ፊታውራሪ ዲባባ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ቃለ - እግዚአብሔርን በመስማታቸው እጅግ ከመደስተቻውም በላይ፤ ‘‘ለካ በአፋን ኦሮሞ ወንጌል መስበክ፣ መቀደስ፣ መዘመር፣ እግዚአብሔርን ማወደስ ይቻል ኖሯል ?!’’ በሚል ከፍ ባለ አድናቆትና አግራሞት ተመልተው እኚህን ካህን የቦጂ ቃርቃሮ ማርያም ቤተክርስቲያን አገልጋይ እንዲሆኑ ሾሟቸው፡፡

መምህሬ ገብረ ኤዎስጣቴዎስ በወለጋ ጠቅላይ ግዛት በግእዝና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ለአካባቢው ሕዝብ ወንጌልን የሰበኩና መንፈሳዊ አገልግሎት የሰጡ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ካህን መሆናቸውን ዶ / ር ጤሶ በንቲ በዚሁ ጥናታዊ ድርሳናቸው ያትታሉ፡፡

ይህን ከመቶ ዓመታት በላይ ባስቆጠረ ታሪክ መሠረትነት ከሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያናችን የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪ አገልጋዮችና ምእመናን ዘንድ ‘‘የኦሮሞ ቤተክህነት ጽ / ቤት ይቋቋምልን !’’ በሚል የተነሳውን ውዝግብ መነሻ አድርጌ፤ ጥቂት ለውይይት መነሻ የሚሆነን ሐሳብ ለመሰንዘር ነው፡፡

በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳዩ ከመግባቴ በፊት ግን ለመግቢያ ያህል እንዲሆነኝ ስለአፍ መፍቻ ቋንቋን በተመለከተ አንድ ታሪካዊ ክስተትን በአጭሩ ለማስታወስ እወዳለኹ፡፡

Full Website