ፀጋዬ በርሔ (ዶ/ር)  4-12-19

እኔ ፀጋዬ በርሄ /ዶ/ር/ የተባልኩ ኢትዮጵያዊ በትግራይ ክልል በአድዋ ከተማ ተወልጄ በወላጆቼና በኅብረተሰቡ እንክብካቤ አግኝቼ ያደኩና በአገር ውስጥና በውጭ አገር ትምህርቴን በማጠናቀቅ በተለያዩ ዓለምአቀፍ እና አገር አቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች፣ በተለያየ ደረጃ እና ኃላፊነት ማለት በኢትዮጵያ እና በተለያዩ አፍሪካ አገራት አገለግያለሁ፡፡

በነዚህ የአገልግሎት ዘመኔ ሁሉ በትምሕርት፣ በጤናና በተለያዩ የማኅበራዊ ጉዳዮች ለኢትዮጵያ ሀገሬና ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች የምችለውን አስተዋፅዎ አድርጌአለሁ፡፡

1ኛ/ በትምሕርትና በሕፃናት አስተዳደግ

ሀ/ በሕፃናት አስተዳደግ ጉባኤ የድርጅቱ መሥራችና የመጀመሪያ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ለ30 ዓመታት አገልግያለሁ፡፡ በነዚህ ዘመናት በተለያዩ የሀገሪቱ ከተማዎች 37 የሕፃናት ማሳደጊያ ማዕከላት በመክፈት፣ በአንድ ግዜ ከ 8000 ያላነሱ ወላጅ አሳዳጊ ያጡ ሕፃናት በየሕፃናት ማሳደጊያው ተቀብለን በማሳደግ በድርጅቱ በቆየሁባቸው ዘመናት በ37ቱ ሕፃናት ማሳደጊያዎች ከ36.000 ሕፃናት በላይ አድገውና ተምረው በተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊነቶች አገራቸውንና ወገናቸውን እያገለግሉ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ከ37 ሕፃናት ማሳደጊያዎች መካከል 9ኙ ሕፃናት ማሳደጊያ በትግራይ ክልል ውስጥ በተለያዩ ከተሞች ተቋቁመው ከ12.000 ሕፃናት በላይ አሳድጎ ለሀገር ልማት አበርክተዋል፡፡ከነዚህ የሕፃናት ማሳደግያ ውስጥ አንዱና ፈለገሕይወት ሕፃናት ማሳደግያ ተብሎ በአድዋ ከተማ የተቋቋመው ድርጅትም ከ1000 ሕፃናት በላይ አሳድጎ ለቁምነገር አድርሰዋል፡፡ በዚህ ድርጅት በቆየሁባቸው አመታትም የድርጅቱ ዳሬክተር ከመሆኔ በላይ በምስራቅ አፍሪካ የእርዳታ ሰጪው /የK.N.H/ የኪንደርኖት ሂልፈ ለተባለው ድርጅት ተወካይ በመሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ 5 የአፍሪካ ሀገራት ሳስተባበር ቆይቻለሁ፡፡

ለ/ በኢ.ት.ኦቤ የልማት ኮምሽን

በዚህ ድርጅት ለ8 ዓመታት ኮምሽነር በመሆን ያገለገልኩኝ ሲሆን በተለይም በትግራይና በወሎ ክፍላተ ሃገራት በየግዜው በሚፈጠረው የአየር መዛባት ምክንያት ለተቸገሩት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ወገኖችን ከተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች እርዳታ በማሰባሰብ ቋሚና ዘላቂ እርዳታ በመስጠት የብዙ ሰው ሕይወት ከሞት አትርፈናል፡፡

ሐ/ ዋይድ ሆራይዘን ፎር ችልድረን WHFC

ከላይ ከተጠቀሰው ድርጅት ጋርም ለ12 ዓመታት የሰራሁ ስሆን በመጀመሪያው 4ቱን አመታት የኢትዮጵያ ፕሮግራም የሀገር ተወካይ በመሆን ሲሆን ሌላው 8 ዓመታት ግን የድርጅቱ የአፍሪካ ፕሮግራም ዳሬክተርና በአሜሪካ በማሳቹሰስ ከተማ የሚገኘው ዋናው ጽ/ቤት የሚመራውን አስተዳደር ኮሚቴ ከ6 አባላት አንዱ በመሆን በአፍሪካ ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ የ8 ሃገራት በፕሮግራም ዳሬክተርነት ሥራውን ስመራና ሳስተባብር ቆይቻለሁ፡፡ በእነዚህ አመታት ውስጥ የዋይድ ሆራይዘን እርዳታ ሕፃናት ከቤተሰብ ጋር በማገናኘት፣ ሕፃናት ከወላጅ ወይም ከዘመድ ጋር ሆነው እርዳታ እያገኙ እንዲማሩ በማድረግና በቤተሰብ ራስን በማስቻል ፕሮግራም በጠቅላላው ከ50.000 ሰዎች በላይ ሕይወት የቀየረ ሲሆን በጤናና በትምሕርትም በተለያዩ  ቦታ በመሰማራት የሚከተለውን አኩሪ ሥራዎችን ሰርተዋል፡-

እነዚህም፡-

1/ በጤና ጉዳይ፡-

ይህንን ድርጅት ወደ ደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን እና ወደ ትግራይ ክልል ማእከላይ ዞን በጤና ጉዳይ እንዲሰማራ በማድረግ በሲዳማ ዞን ሸበዲኖ ከተማ አንድ ታዋቂ ሆስፒታል ከማሰራታችን ሌላ ለ12 ተከታታይ አመታት በየ 3 ወሩ ታዋቂ የሆኑ ሀኪሞችን ከአሜሪካ በቡድን በማስመጣት የአካባቢውን ሕዝብ የነጻ ሕክምና በመስጠት በሆስፒታሉ ለሚገኙ ሃኪሞችም ከፍተኛ የሕክምና ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

የትግራይ ማዕከላዊ ዞን አድዋ ከተማም በተመሳሳይ በየሶስት ወሩ የሕክምና ቡድን በማስመጣት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ጠቅላላ የነፃ ሕክምና ከመስጠት ባሻገር እንኳንና በወረዳ ደረጃ በሀገር ደረጃም ማድረግ የማይቻለውን ቀዶ ጥገና በማድረግ የብዙ በሽተኞች ሕይወት አድነዋል፡፡

ይህ ቡድን ከሚሰጠው ሕክምና ባሻገር በአድዋ፣ በአክሱም፣ በሽሬና በአዲግራት ሆስፒታል የሚገኙት ሃኪሞችንም በማሰልጠን ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡ ድርጅቱ ሕክምና በመስጠት ብቻ ሳይወሰን የአድዋ ሆስፒታል የነበረውን የአልጋ፣የስትሪቸር፣ የማዋለጃ አልጋና ጠቅላላ የመሳሪያ እጥረት ከማሟላቱ ሌላ ተጨማሪ የሕክምና ክፍሎች በመስራትም በሆስፒታሉ የነበረውን የክፍል ጥበት አቃልለዋል፡፡ ከሁሉም በላይ አንድ ትልቅ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ጤና ጣቢያ ሰርተን ከነሙሉ ዝግጅቱ ለሕዝቡ አስረክበናል፡፡ ከዚህም ሌላ በአድዋ አካባቢ ባሉት ገጠሮች በሚገኙና በወሊድ ምክንያት ለሚሞቱ እናቶች ለመታደግ አንድ ዘመናዊ የተሟላ አምቡላንስ ለዚህ ጤና ጣቢያና ከተማ ሰጥተናል፡፡ ከዚህ የተነሳም ከከተማው በስተደቡብ ያሉት ገጠሮች ውስጥ የሚገኙ እርጉዞች በወሊድ ግዜ ቤተሰቦቻቸው በቃሬዛ ተሽክመው በከተማው በስተሰሜን ጥግ ወዳለው ሆስፒታል (10 ኪ.ሜ ያህል) ሲጓዙ የነበረውን ጉዞ ቀርቶ በቅርባቸው ባለው የተሟላ ጤና ጣቢያ ከመገልገላቸው ሌላ እናቶች ምጥ በሚያዙበት በማንኛውም ሰዓት የጤና ጣቢያውን አምቡላንስ ከነአዋላጁ በመጥራት አስቸኳይ እርዳታ ስለሚያገኙ በየግዜው በወሊድ ምክንያት የነበረውን የእናቶች ሞት ሙሉ በሙሉ አስቀርተናል፡፡ ለዚሁ የከተማውም ሆነ የገጠር ሕዝብ ሕያው ምስክር ነው፡፡

2/ በትምሕርትና በተማሪዎች እርዳታ

ቀደም ሲል በጽዮን ት/ቤት የነበረውን የክፍል ጥበት "ከዳስ ወደ ክላስ" የሚለውን የት.ል.ማ መርህ በመከተል አራት ትልልቅ ክፍል የያዙ ሁለት ብሎክ ሰርተን ከነመማሪያ ዴስክና ጥቁር ሰሌዳ አሟልተን ከማስረከባችን በላይ ከ300 በላይ ችግረኛ ተማሪዎችንም ለእያንዳንዱ በየወሩ ብር 500 እና ሌሎች እርዳታዎች በመስጠት ላለፉት 12 አመታት ረድተናል፡፡ በቅርቡም በወርዒ ለኸ እና በመረብ ለኸ ትምሕርታቸውን አቋርጠው በከብት ጥበቃ ለቆዩ ሕፃናት በእያንዳንዱ ወረዳ 3 ከፍሎች በመክፈል በ1 ዓመት ውስጥ ከ1ኛ-3ኛ ክፍል እንዲማሩ በማድረግ ለ200 ሕፃናት የመማር እድል ሰጥተናል፡፡ ለ150 ድሃ ቤተሰብም አስፈላጊውን እርዳታ በመስጠት ራሳቸው እንዲያቋቁሙና ራሳቸውን እንዲችሉ አድርገናል፡፡ ለዚህም ድርጅታችን ከክልሉ የተለያዩ መ/ቤቶች በተደጋጋሚ የምስጋና ደብዳቤዎችና ሽልማቶች አግኝተናል፡፡

ከላይ የተዘረዘረው ሥራ በ42 ዓመታት የሥራ ዘመኔ ለሀገሬና ላሳደገኝ ኅብረተሰብ የሀገር አቀፍና የአለም አቀፍ ድርጅቶችን ወደ አገሪቱ በማስመጣትና በማስተባበር  የሰራሁት ሥራዎች ናቸው፡፡

ከ2 ዓመታት በፊት በገዛ ፈቃዴ ጡረታ ወጥቼ ማረፍ እንዳለብኝ የወሰንኩ ቢሆንም፡-በጡረታ ዘመኔም እግዚብሔር ጤናው ሰጥቶ በሕይወት እስካኖረኝ ድረስ በተለያዩ ቦታዎች የበጐ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት፤የመቀዶንያ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ድርጅት በቦርድ ሊቀመንበርነት ከማገልገልና የኢትዮጵያ ወወክማ ፕሬዚዳንት ከመሆን በተጨማሪ የአድዋ ልማት ማሕበርን ጨምሮ በ6 የተለያዩ ድርጅቶች የቦርድ አባልና አማካሪ በመሆን የነጻ አገልግሎት በመስጠት ላይ እገኛለሁ፡፡ከዚህም ሌላ የዋይድ ሆራይዘን አለም አቀፍ ፕሮግራም ከ6 የአመራር ኮሚቴ አባላት አንዱ በመሆን ከማገልገሌ ሌላ በየሶስት ወሩ ወደ አዋሳና አድዋ የሚመጡት የሕክምና ቡድን በመምራትና በማስተባበር የነጻ አገልግሎት እየሰጠሁ እገኛለሁ፡፡ በተለይ የሕክምና ቡድኑ ወደ አድዋ በሚመጣበት ግዜ በመኖሪያና በቢሮ እጦት እንዳይቸገሩ በግሌ የሰራሁትን ቤት ከነሙሉ ዝግጅቱ በነጻ እንዲጠቀሙበት ሰጥቻለሁ፡፡ ከዚህም ሌላ በአድዋና አካባቢው ተወልደው በየቦታ ለሚጣሉ ሕፃናት አንስቶ ለመንከባከብ ዋይድ ሆራይዘን ፈቃደኛ ሲሆን በእኔ በኩልም ቀደም ሲል ከአባቴ በውርስ ያገኘሁትን ቤት ለዚህ አላማ በነጻ እንዲጠቀሙበት ሰጥቻለሁ፡፡ አሁን ካለኝ የጡረታ ገቢዬም 32 ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋዊያን እናቶችን በየወሩ ገንዘብ በመስጠት እረዳለሁ፡፡ ይህ ሁሉ በጡረታ ከወጣሁ ግዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የምሰጠውን አገልግሎት ሲሆን ለወደፊቱም እግዚብሔር እድሜና ጤናው እስከሰጠኝ ድረስ በገንዘቤ በእውቀትና በጉልበቴ ያሳደገኝን ኅብረተሰብ የበለጠ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡፡

በጡረታ ተገልዬ ወደ እ ረፍት ከመሄዴ በፊት ላሳደገኝ ኅብረተሰብ የሚጠቅም በስሜ አንድ ሥራ ሰርቼ ማለፍ እንዳለብኝ ለብዙ ዘመናት ሳስበው የነበረ ሕልሜ ነው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖም በግዜው የአድዋ ከተማ ከንቲባ የነበሩት በአካባቢው የነበረውን የት/ቤት ጥበትና የትምህርት ጥራት መጓደል የፈጠረውን ችግር በመዘርዘር በዚህ ዘርፍ የተለመደውን ድጋፍ እንዳደርግ ከመጠየቃቸው ሌላ የትግራይ ልማት ማሕበርም "ልምዓት ዓዲ ብወዲዓዲ" በሚል መርህ ማንም ተወላጅ በስሙ የሚጠራ የትምህርትም ሆነ የጤና ተቋም እንዲሰራ ባደረገው ጥሪ መሠረት እኔም ጥሪውን በመቀበል የነበረኝን የብዙ ግዜ ሕልም ወደ ተግባር ለመተርጐም ቀደም ሲል ከአድዋ ከንቲባ ጽ/ቤት ቀጥሎም ከትግራይ ልማት ማኅበር የተለያዩ ስምምነት ፈፅምኩኝ፡፡

በተደረገው ስምምነት መሠረት የዋናው ሕንጻ መሥሪያ ገንዘብ ግማሹ በእኔ በኩል እንዲሸፈን ሌላው ግማሽ ደግሞ ወረዳው ሕዝቡን አስተባብሮ እንዲሸፍንና በተጨማሪም በተመፃሕፍትና ላብራቶሪ፤ የት/ቤቱ ቢሮዎች፤ የግቢው አጥርና የወንድና የሴት ሽንት ቤቶች እንዲሁም የኳስ መጫወቻ ሜዳ ወረዳው እንዲያሰራ በስምምነቱ ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም ሕዝቡም ሆነ ወረዳው ጽ/ቤቱ ለዚህ ሁሉ ወጪ የመሸፈን አቅም እንደሌለው በመገንዘብ የወረዳውና የአካባቢውን መዋጮም ራሴ መቶ በመቶ በመሸፈን በ5 አመታት እንዲሰራ የታቀደውን ት/ቤት በ10 ወራቶች አጠናቅቄ ት/ቤቱ ለአገልግሎት እንዲውል አድርጌአለሁ፡፡

በስምምነቱ መሠረትም ለትውልድ በስሜ የሚጠራ፣ የትምሕርት ጥበትን የሚያቃልልና የትምሕርት ጥራትን የሚያረጋግጥ አንድ ዘመናዊ ሁሉንም ያሟላና ከየቦታው የተመረጡ ጎበዝ ተማሪዎች የሚማሩበት ልዩ 2ተኛ ደረጃ ት/ቤት ለመስራት በመወሰን፤ የነበረኝን ንብረት በመሸጥና ቀሪውን ደግሞ ከልጆቼ ከቤተሰቦቼና ከጓደኞቼ በማሰባሰብ፤ ለልጆቼም ቢሆን ንብረት ከማውረስ ይልቅ መልካም ሥራና መልካም ስም ማውረስ እንዳለብኝ በማሳመን፤ በ5 ዓመት ሊሰራ የታቀደውን ሕንፃ ሥራውን በእግዚአብሔር ቸርነት እና እርዳታ ጀምሬ በ10 ወር ውስጥ ሁሉንም አሟልቼ በመስራት የአባቢው ኅብረተሰብ ልጆች ላለፉት 9 ዓመታት እንዲጠቀሙበት አድርጌአለሁ፡፡ ይሁን እንጂ የአድዋ ከተማ ጽ/ቤት ትምሕርት ቤቱ እንደታቀደውና እንደተስማማንበት እንዲሁም በመጀመሪያ 4/አራት/ ዓመት እንደነበረው ባለመጠቀሙ ባልደሰትበትም አሁንም ቢሆን የ2ተኛ ደረጃ መሰናዶ ት/ቤት ሆኖ በማገልገል ብዙ ተማሪዎችን እያስተማረና ለከፍተኛ ደረጃ እያደረሰ ያለ ትምህርት ቤት ነው፡፡

ሆኖም ት/ቤቱ በታቀደለት ዓላማ መሠረት ልዩ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ሆኖ እንዲያገለግል በምሯሯጥበት ሰዓት እኔ ፍፁም ያልጠበቅኩትና ከስምምነታችንና ከዓላማው ውጭ የሆነ ለማንም ሰው የሚያስደነግጥ እና የሚያስገርም  ክስተት ተፈጠረ፡፡ ይኸውም የት/ቤቱ ግቢ ሊሠራ ወደታቀደው ፓን አፍሪካ ዩንቨርስቲ እንዲካተት እንደተፈለገ ሰማሁ፡፡

በእኔ በኩል የአፍሪካ ኩራት የሆነውን የአድዋ ድል የሚዘክር ዩንቨርስቲ በአድዋ ከተማ  መሠራቱ የምመኘውና ከልቤ በግንባር ቀደም የምደግፈው ነው፡፡ ይህንን እውን ለማድረግም በጉልበቴ በእውቀቴና በገንዘቤ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ፡፡ ይህንን ልማትም በምንም ቢሆን በማንም እንዲደናቀፍ አልፈልግም፡፡

Full Website