On Dec 18, 2019 204

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚውል የመራጮች ምዝገባ ሰነዶች ህትመትና የቁሳቁሶች ግዥ መጀመሩን አስታውቋል።

https://fanabc.com/wp-content/uploads/2019/12/tyuuiio-750x430.jpg ምርጫ ቦርድ ለቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ከሚያደርጋቸው ዝግጅቶች መካከል አንዱ የሆነውን የመራጮችን ምዝገባ ዘመናዊ እና ተአማኒ የሚያደርግ የህትመት ስራ እንዲጀመር በትላንትናው እለት በዱባይ ስምምነት ተፈራርሟል።

በዚህ መሰረትም ህትመቱ የመራጮች መመዝገቢያ መዝገቡም ሆነ የምዝገባ ማረጋገጫ ካርድ የራሳቸው የደህንነት ማረጋገጫ ያላቸውና ሊጭበረበሩ እና ሊባዙ የማይችሉ መሆናቸው ነው የተገለጸው።

የመራጮች ካርድ ቀሪ ያለው ሆኖ የሚዘጋጅና መራጮች ጋር ያለው ካርድ ቀሪ የምርጫ አስፈጻሚዎች ጋር የሚቀር መሆኑ በምዝገባ ወቅት ሊፈጠር የሚችል ማጭበርበርን ማስቀረት እንደሚያስችልም ተጠቁሟል።

ከዚህ ባለፈም እያንዳንዱ መራጭ በመራጮች ካርር አማካኝነት የራሱ የሆነ ልዩ መለያ ቁጥር ያለው ሲሆን፥ሁሉም ሰነዶች በአምስት ቋንቋ ማለትም፣ በአማርኛ፣ በአማርኛ/ትግርኛ፣ በአማርኛ/አፋን ኦሮሞ፣ በአማርኛ/ሶማሊኛ እንዲሁም በአማርኛ/ አፋርኛ የሚታተሙ ይሆናል።

ህገ ወጥ የሆነ የምርጫ እቃዎች አግባብ ባልሆነ እጅ እንዳይወድቁ እቃዎቹ የሚታሸጉበት ልዩ ቁሳቁስ ለመራጮች ምዝገባም ሆነ ለድምጽ መስጫ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪም የህትመት ሂደቱ ጋር አብሮ የሚከናወነው ግዥ ጥቅል የሆነ ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልግ ቁሳቁስ፣የማጭበርበር ሙከራ ካለ ሊያጋልጥ የሚችል የፕላስቲክ ቦርሳ እና የአጠቃቀም ስልጠናን እንደሚያካትት ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ይህንን ህትመት የሚያከናውነው ድርጅት ለኬንያ ፣ ለኡጋንዳ፣ ለማላዊና ለዛምቢያ የምርጫ ሰነዶችን በማተም የሚታወቅና የምርጫ ስራዎችን በልዩ ሁኔታ የሚሰራ ተቋም መሆኑ ተጠቁሟል።

Full Website