“የጭፍን ጥላቻ ማማ!”

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ 7-27-19

"All we have to decide is what to do with the time that is given us."

The Lord of the Rings

በጽንሰ ሀሳባዊም ኾነ በተግባራዊ ኹለንተናዊ መለኪያዎች ጥላቻ በአሉታ እንጂ በአዎንታ በግልጽ ሲነገር፣ ሲጻፍና ሲሰበክ መስማት ያልተለመደ ቢኾንም የተለያየ ፍላጎት፣ ዓላማና ግብ የነበራቸውና ያላቸው ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ተቋማቶች ጠላትነትን መሣሪያ (means) በማድረግ ወደ ሚፈልጉት ኹለንተናዊ ሂደት ለመምራት ጥላቻን ቅመም አድርገው ስለመጠቀማቸው ታሪክ ህያው ምስክር ነው፡፡ በሕብረተሰብ የትላንት½ የዛሬና የነገ የዕለት ተዕለት ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚኖሩና የነበሩ ግንኙነቶች½ ግጭቶችና ሂደቶችን ስናስተውል ጥላቻ በተለይ ጠላትነት የብዙ ነገሮች መሣሪያ (means) በመኾን አገልግሏል፡፡ ጥላቻ በተለያየ ዐውድ የተለያየ ዕይታ እንዳለው ይተነተናል፡፡ የሃይማኖት ሊቃውንት ኃጥያትን መጥላት እንዳለብን ይሰብካሉ፤ በተለያየ የሥልጣን ፖለቲካ የተደራጁ ኃይሎች እነሱ ከቆሙበት ርዕዮት በተቃርኖ የቆሙትን እንደጠላት ያስቀምጣሉ/ ይፈርጃሉ፤ ብዙ ጦርነቶች በጥላቻና በጠላትነት ትርክት ላይ የቆሙ ናቸው፤ አብዛኛው "የዓለም ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው" ከሚለው ቁንጽል ታሪካዊ ብያኔ አንጻር ጠላትነትና ጥላቻ የህልውናው መሠረት እንዳደረጋቸው አይካድም፡፡ ጥላቻ ምንድነው? ማን ምንድነው የሚጠላው? ለምን? ከጥላቻ ምን ይገኛል? የጥላቻ ዓይነት፣ መጠንና አድማስ እንዴት ይተነተናል? የጥላቻስ መልኩ እንደምን ያለ ነው? ጥላቻ በማን? እንዴት? ከምን ይመነጫል? የጥላቻ ጉዳትና ጥቅሙስ ምንድነው? ያልን እንደኾነ ብዙ ከብዙ አቅጣጫ ሊታዩ የሚችሉ ሀሳቦች ይኖሩታል፡፡ ጭፍን ጥላቻ ወዳጅን ጠላት - ጠላትን ወዳጅ ያስደርጋል፡፡ ጭፍን ጥላቻ እውነትን ሀሰት - ሀሰትን እንደእውነት ያሳያል፡፡ ጭፍን ጥላቻ ስሜታዊነትን ባለቤት በማድረግ ከምክንያታዊነት ያርቃል፡፡ ጭፍን ጥላቻ ይሉኝታ ቢስነትን የማንነቱ መገለጫ በማድረግ ከሞራል በእጅጉ ያርቃል፡፡ ጭፍን ጥላቻ በአርቆ ማሰብ መቃብር ላይ ለአርቆ አለማሰብ ሃውልት ያሰራል፡፡ ጭፍን ጥላቻ አቋም አልባነትን በመያዝ አቋም መያዝን በእጅጉ ይጠየፋል፡፡ ጭፍን ጥላቻ ከውስጥ ይልቅ ወደ ውጭ፤ ከወደ ፊት ይልቅ ወደ ኃላ መመልከትን ባሕሪያዊ የህልውናው መሠረት ያደርጋል፡፡ ጭፍን ጥላቻ ዝቅጠትን ዕድገት፤ ውርደትን ክብረት አድርጎ ይሰብካል፡፡ ጭፍን ጥላቻ ከዕምነት፣ ከዕውነት፣ ከሃቅ፣ ከመርህ፣ ከአቋም፣ ከነጻነት በእጅጉ ርቆ ከስሜት፣ ከውሸት፣ ከማስመሰል፣ ከሴራ፣ ከባርነትና ከገረድነት ጋር የሚፈጥረው ጋብቻ ውጤት የብዙ ችግሮች ምንጭ ከመኾን ባለፈ የብዙ ሀገራዊና ሕዝባዊ ችግሮች ካንሰር ስለመኾኑ ዓለም ምስክር ናት፡፡ ጭፍን ጥላቻ ማስተዋል፣ ጥበብና ትዕግስትን እንደጠላት ያስመለክታል፡፡ ጭፍን ጥላቻ ያለ ጠላትነት - ጠላትነት ያለ ጭፍን ጥላቻ ፈጽሞ ሊኖር አይችልም፡፡ አንዱ በሌላኛው - ሌላኛው በአንደኛው ውስጥ የሚኖር ውሕዳዊ መሣሪያ ነው፡፡ ጭፍን ጥላቻ ሃይማኖተኛ ነኝ እያሉ ኢ - ሃይማኖተኛ የማያደርገውን ያስደርጋል፤ ሥልጡን ነኝ ባዩን ስዩጡንነት ያጋልጣል፤ ምክንያታዊ ነኝ ብሎ የሚመጻደቀውን የስሜት ባሪያነቱን ያስረግጣል፤ ጭፍን ጥላቻ በትዕቢት መወጠር፣ ትምክህተኝነትና ማን አለብኝነትን ባሕሪያዊ የማንነቱ መገለጫዎች ያስደርጋል፡፡ ጭፍን ጥላቻ ራስን ከመለወጥ ይልቅ ሌላውን ለመለወጥ መትጋት፤ ከራስ ኹለንተናዊ መዳበር ይልቅ የሌላውን ኹለንተናዊነት ማፍረስ ላይ ይተጋል፤ ከራሱ ማግኘት ይልቅ የሌላው ማጣት እጅጉን ያስደስተዋል፡፡ ቅንዓትና ሴረኛነት፤ ሃሜትና አለማስተዋል ጠባያዊ ማንነቱ ናቸው፡፡ ጭፍን ጥላቻ በግለሰብ፣ በቡድንና በተቋም ደረጃ ይቀነቀናል፤ በማወቅና ባለማወቅ ይዳብራል፤ በንቃት (consciously) እና ያለ ንቃት (unconciously) ይፈጸማል፡፡ ጭፍን ጥላቻን ባለቤት ማድረግ ይሉኝታ ቢስነት፣ ሃሰተኛነት፣ ባሪያነት፣ አሽከርነትና ገረድነትን ገንዘብ ማድረግ ነው፡፡ ጭፍን ጥላቻ የጨለማ ጉዞ ከመኾኑ ባሻገር የብርሃን ጉዞ ጠላት ነው፡፡ ጭፍን ጥላቻ ስድብን normal እና የተለመደ ከማስደረጉ ባሻገር ነውርን ጌጥ፣ እርግማንን ምርቃት - ምርቃትን እርግማን አድርጎ ያስቆጥራል፡፡ ጭፍን ጥላቻ መፈረጅ፣ መፍረድና መደምደም የተባሉ 3 የ"መ" ህጎች ባለቤት ነው፡፡ በዚህም መታሰር - ለርሱም ቢኾን አሽከርና ገረድ መኾን የሚል ግዴታን ይይዛል፡፡ በጭፍን ጥላቻ የታወረ ሰው ነገሮችንና ኹለንተናዊ እንቅስቃሴዎችን ከጥላቻና ከጠላትነት አንጻር ብቻ ይመለከታል፡፡ ያመላክታል፡፡ እያንዳንዱ ኹለንተናዊ እንቅስቃሴውን የጠላውን አካል ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ በአሉታ በመተርጎም፣ አቃቂር በማውጣትና ጥላሸት በመቀባት ያካሂዳል፡፡ በአንጻሩ የራሱንና መሰሌ የሚለውን አካል አሉታዊ እንኳ ቢኾን በአዎንታ መተርጎም፣ የማይያያዝ ነገር አያይዞ ማጉላትና በባዶ ማወደስ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው - መገለጫ ያደርጋል፡፡ ያስደርጋል፡፡ ለዚህም በእጅጉ ይተጋል፡፡ ያስተጋል፡፡ በጭፍን ጥላቻ የታወረ ግለሰብ፣ ቡድንና ተቋም የሕዝብና የሀገር ካንሰር ነው፡፡ ሕዝብና ሀገርን ይበክላል፡፡ ይጎዳል፡፡ ኹለንተናዊ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ያስከፍላል፡፡ ትውልዳዊ ዕዳን ያበዛል፤ ጥላቻን በመዝራት የጥላቻ ፍሬ እንዲበራከት ምቹ ኹኔታዎችን ይፈጥራል፡፡ ያበራክታል፡፡ የትጋቱ ውጤታማነትም በጭፍን ጥላቻ ፍሬ ላይ የተመሰረተ ይኾናል፡፡ ጭፍን ጥላቻ በተበራከተበት ማሕበረሰብ ውስጥ ማስመሰል፣ ማዳላት፣ ማጠልሸት፣ ማማትና ማራገብ የተለመዱ የኢ - ሥልጡንነት መገለጫዎች መኾናቸው እንኳ እየታወቀ ያለ ምክንያት፣ ያለ በቂ ማስረጃና መረጃ ሰዎችን መጥላትና ማስጠላት ሲደረግ ለምን? እንዴት? በምን? ስለምን? ብሎ ትርጉም ባለው መንገድ የሚጠይቅ ባለመኖሩ ለመንጋነት ምቹ ኹኔታን ይፈጥራል፡፡ ጭፍን ጥላቻ ባለበት መንጋነት - መንጋነት ባለበት ጭፍን ጥላቻ መኖራቸው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ የመኾናቸው ማሳያ ነው፡፡ መንጋ ገዥ እንዳለው ኹሉ ጭፍን ጥላቻም - እጅጉን በጭፍን ጥላቻ የታወሩ፣ ማስተዋል የተሣናቸው፣ ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ፣ ዐይን እያላቸው የማያዩ፣ ስሜት እያላቸው የማይሰማቸው፣ አፍንጫ እያላቸው የማያሸቱ፣ መቅመስን በምላሳቸው ማከናወን ዳገት የሚኾንባቸው እንኳንስ የሚታይና ሊደብቁት እንኳ ከቶ የማይቻልን ነገር - ለመደበቅ የሚሞክሩ፣ ሃሰተኛነትን በሙሉ ልብ በአደባባይ የሚያቀነቅኑ፣ አስመሳይነትን በአኗኗራቸው ውስጥ በገሃድ የሚተገብሩ፣ አንዳች ትርጉም ያለው ፍሬ የሌለባቸው፣ የአምልኮ መልክ እንጂ ዕምነት አልባ፣ ባዶ ቃላት ደርዳሪ - የፍቅር እንቅፋት፤ ፍቅር አልባ - የፍቅር ደስኳሪዎች፤ ሀሳብ አልባ - የሀሳብ አነብናቢዎች፤ ተስፋ አልባ - የተስፋ ረሃብተኞች - ኾነው በድፍረት ያለ ዕውቀት ሲቀደዱ መስማት የተለመደ ነው፡፡ በጭፍን ጥላቻ የታወሩ - የጭፍን ጥላቻ ማማ ላይ የወጡ ብዙ ይለፈልፋሉ - አንዳች ቁም ነገር ግን አይገኝባቸውም፤ ብዙ ጸያፍ ነገርን በማውጣት የታወቁ ናቸው፤ ነውራቸውን በኩራት ሲደሰኩሩ ይሉኝታ ቢስነታቸው ጎልቶ ይታያል፤ ለቃላቸው የማይታመኑ - አንደበታቸውን የማይጠብቁ - ተራ አጭበርባሪዎች እንደኾኑ ጥቂቶች ቢረዱና ቢገነዘቡም ብዙዎች ባለመረዳታቸውና ባለመገንዘባቸው - እስኪረዱና እስኪበስሉ የበሰሉትና የተረዱት ኹለንተናዊ የሕይወት፣ የአካል፣ የዕውቀት፣ የገንዘብ፣ የስሜት - - - መስዋዕትነት መክፈላቸውን የግድ የሚል ኾኖ ይገኛል፡፡
Full Website