Back to Front Page
አዲስ የፖለቲካ መንገድ እንፍጠር!

አዲስ የፖለቲካ መንገድ እንፍጠር!

(ምዕራፍ ይመር) 9-3-19

ዘመን አልፎ - ዘመን ሲተካ፣ የሚለወጡ በርካታ ዘይቤዎች አሉ። ቴክኖሎጂ መዘመኑ፣ አንድ የዘመን ልዋጤ ዘይቤ ነው። የሰው ልጆች አስተሳሰብ - ሌላኛው የልዋጤ አካል ነው። ሌሎች፣ በየዘርፋቸው የሚለወጡ ሁናቴዎችም አሉ - ጊዜ በገፋ መጠን። የፖለቲካ መንገዳችንም በ'ነዚሁ ስር ይመዘገባል። «የፖለቲካ መንገዳችን» ስል፣ ጥንት የተጓዝንበት - ዛሬ የምንዝበት - ወደፊት የምንዳረስበት ባህል ማለቴ ነው። እኛ ሃገር፣ ዘመን በተለወጠ መጠን የማይለወጠው ዘይቤያችን፣ ይኼው የፖለቲካ መንገዳችን ነው።

ትናንት በደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ግጭት ስትመሳቀል የኖረችው ሃገራችን፣ በ1983 ዓ.ም. ከደርግ ስርዓት ተላቅቃ ኢህአዴግን ስትቀበል፣ የልጆቿ ተስፋ «አዲስ የፖለቲካ መንገድ መጣልን!» የሚል ነበር። ተስፋቸው በረዥሙ ሳይዘልቅ ተቀጨ። ተረኛው እንደአምናው የመግደል ልብሰ-ተክህኖውን ተላብሶ ለሩብ ክፍለ-ዘመን ያህል ጨቁኖ ገዛ።

ገዢው ቡድን - ኢህአዴግ ከአንድ ዓመት ወዲህ፣ አዳዲስ ፊቶችን ወደ አመራርነት ቦታ በማምጣት፣ «ሪፎርም አካሄድኩ!» ሲል ለፈፈ። አመራሮቹ ከዚህ በፊት ታይተው አይታወቁም። አዳዲስ ፊቶቹ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችን በመልቀቅ፣ የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገር ቤት በማምጣት...የድጋፍ ወሰናቸውን አሰፉ። የኢትዮጵያውያን - የተኮላሸ ተስፋ ዳግም አንሰራራ።

«የፖለቲካ ባህላችን ሊለወጥ ነው!» ተባለ። ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ስራ ተሰራ። ዘፈን ተዘፈነ። ከበሮ ተደለቀ።

ይሄኛውም እንደትናንቱ (አንዳንዶች የስርዓት ቅየራ የተካሄደ ያስመስሉታል። ነገር ግን አልተካሄደም። ትናንት የነበረው ነው - ዛሬም የቀጠለው።) አጥፊ መንገዱን በለሰለሱ ቃላት እያሰማመረ መቀጠሉን ተያይዞታል። ሃገራችን ላይ ታይቶ የማይታወቅ መከራ እየጠራ ነው። ጠርቶም ዋጋ እያስከፈለን ነው።

አዙሪታሙ የሃገራችን ፖለቲካ ከመለወጥ ይልቅ ህመሙ የባሰበት «ለምን ይሆን?» ብለን ብንጠይቅ፣ ሁለት መልሶችን እናገኛለን። አንደኛው፣ ተረኝነትና ባለጊዜነት ያዋለደው ትምክህት ከባለስልጣናት ልብ አለመጥፋቱ ነው። አንዱ የነበረውን አፍርሶ (እንደ'ነዚህኞቹ ሳይፈርስም) ስልጣን ላይ ሲወጣ፣ «ሲሾም ያልበላ፣ ሲሻር ይቆጨዋል!» የሚል፣ አበዋዊ ብሂል ልቡን ይሰልብበታል። ስልቱን የቀያየረ ዘረፋ እንዲፈፅም ይገፋፋዋል። ስልጣኑ ይበልጥ ሲጥመው፣ ስልታዊ ጥቅለላን በ«ለውጥ» ስም ያጧጡፋል። የ«ለውጥ» ወረቱ ሲያልቅበት የለየለት አምባገነን ይሆናል። በያዘው ቦታ የማይረካ ጥመኛ ያደርገዋል። ከመሰረቱ ያለው፣ ያደገበት የስልጣን አስተሳሰብ ወደ'ዚህ ዕኩያዊ ድርጊት ይከትተዋል። እዚህ ላይ ድርጅታዊ ባህል የሚፈጥረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም።

Videos From Around The World

ሁለተኛ፣ ለተቀናቃኝ ቡድኖች ያለው አመለካከት በጠላትነት የተቃኘ መሆኑ ነው። ተገዳዳሪ ሃይል - በፖለቲካ መድረክ ውስጥ - እንደአጥፊ ሃይል አይቆጠርም። እንዲያውም የተገዳዳሪ ሃይል መኖር የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ጥራትን ያመጣል። ጥራቱ የሚገመገመው በህዝቡ ምርጫ ሆኖ ቢገኝም፣ የሃይላቱ ድርጅታዊ ጥንካሬ ግን ወሳኝ ነው። በእኛ ሃገር የተለመደው፣ ድርጅታዊ ጥንካሬ በጥብቅ አፋኝነት የመግለፅ ልማድ አለ። መዋቅሩ የደረጀ ሃይል፣ ሃሳቡን ለሰፊው ህዝብ ማስረፅ ስለሚቻለው፣ ጥንካሬውን ያዳብርና ሙሉዕ ጠንካራ ይሆናል። ይህ የድርጅታዊ ጥንካሬ አረዳድ በገዢውም ሆነ በተቀናቃኝ ወገን ባለመኖር፣ የፖለቲካ መንገዳችን እንዲንሻፈፍ ሆኗል።

ሁለቱ፣ ዋና - ዋና ችግሮች በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፈታት የሚችሉ ናቸው። የፖለቲካ ፈቃደኝነቱ እስካ'ለ ድረስ። የፖለቲካ ባህላችንም የመለወጥ መንገዱ የሚጀረምረው፣ ዴሞክራሲያዊ ሰብዕና በሁላችንም ዘንድ ሲኖር ነው። ዴሞክራሲን በግለሰብ ደረጃ መቀበል አስፈላጊ ነው። አልለወጥ ያለው ገዢ ቡድን ላይ ጫና ማሳረፉ እንዳለ ሆኖ፣ ተቀናቃኝ ቡድኖች ውስጥ የሚታዬውን ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ባህርይ ማረም፣ ጊዜ የማይጠበቅ ጉዳይ ነው። አዲስ የፖለቲካ መንገድ መፍጠር የዚህ ዘመን ትውልድ ግዴታ ነውና ትውልዱ መሰናክሉን በማለፍ፣ የተሻለን ነገ ለመፍጠር ዛሬ ላይ መትጋት አለበት።


Back to Front Page
Full Website