ትውልዳዊ ምክንያታዊነት - ለኹለንተናዊ ስኬት!

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ 6-15-19

የሰው ልጆች ሕይወትና ኹለንተናዊ እንቅስቃሴያቸው በዋናነት በኹለንተናዊ ፍላጎት/ቶች እና በኹለንተናዊ ግንኙነት/ቶች ውስጥ የነበረ፣ ያለና የሚኖር ኹለንተናዊ ትስስር - የፈጣሪ ስጦታ ስለመኾኑ አኗኗራችን ዐቢይ ምስክር ነው፡፡

ህይወታችንን ምን አይነት? በምን ያክል መጠን? መቼ? እንዴት? በምን? በማን? ለምን? ከሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች ባሻገር ያለ ፍላጎትና ያለ ግንኙነት ማሰብ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፡፡

በጽንሰ ሀሳባዊ ትንታኔ ምክንያታዊነት ለማንኛውም - በየትኛውም አካባቢ ለሚኖር ሰው እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ የሕይወቱ አካል - የኹለንተናዊ ፍላጎቶቹና ግንኙነቶቹ ማሟያ - መሣሪያ እንደኾነ ቢታወቅም በተግባር በዓለምም ኾነ በነጠላ በሀገራችን በምክንያታዊነት አለመኖር የብዙዎችን ግለሰባዊ ሕይወት በስሜትና በአሉባልታ ተመርቶ - የማይወጡት ኹለንተናዊ አዘቅጥና ውርደት ውስጥ እንዲገባ አላደረገምን? ከራሳቸው ጋር የተጣሉ፣ ከራሳቸው ጋር የተራራቁ፣ ማድረግ በሚፈልጉትና በሚያደርጉት መሐከል ተቃርኖ የተበራከተባቸውስ ብዙዎች አይደሉምን? በኢ - ምክንያታዊነት የተነሣ የብዙዎች ትዳር አልተናጋምን? በስሜታዊነት መሠልጠን የተነሣ የብዙዎች ትዳር እንደበሶ አልተበጠበጠምን? ብዙ ወንጀሎችስ አልተፈጸሙምን? እንኳንስ ለመፈጸም - የተፈጸመውን ድርጊት ለመስማት ነውር የኾኑ ነገሮች ተበራክተው የሚታዩ አይደሉምን? ምክንያታዊነትን መሠረት ያደረጉ ግንኙነቶች ባለመኖራቸው የብዙ ለቁጥር የሚያታክቱ ጓደኝነቶች፣ ቤተሰባዊ ሰንሰለቶች፣ ጉርብትናዎች፣ የሥራ ባልደረብነቶች፣ ከባቢያዊ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች፣ ፓርቲያዊ እንቅስቃሴዎች፣ ድርጅታዊ ዕድገቶች - - - አልታወኩምን? የነበሩ አስደሳችና አስደናቂ ግንኙነቶች በአጭሩ አልተቀጩምን? የት ይደርሳሉ የተባሉ - የፍቅር ግንኙነቶች በነበር አልቀሩምን? ብዙ ገዥዎች አንደበታቸውን ባለመጠበቃቸውና ባለማረማቸው - ከምክንያታዊነት ይልቅ በኢ - ምክንያታዊነት እንደከብት በመመራታቸው ብዙዎች እንዲፈናቀሉ፣ እንዲሞቱ፣ ደህንነት እንዳይሰማቸው፣ ተስፋ እንዲያጡና እርስ በራስ እንዲጠራጠሩ አልኾኑምን?  ሀሰተኛነት በእጅጉ እንዲንሰራፋ - አሉባልታ ገዥ እንዲኾን ዋና ፊታውራሪ አልኾኑምን? ሰነፎችና የሕዝብ መዥገሮች ከምክንያታዊነት ይልቅ ኢ - ምክንያታዊነትን የሕልውናቸው ዋስትና አላደረጉምን? ቀላል የማይባሉ በቁጥር በርካታ የኾኑ ምሁራን - ምሁራን ተብዪዎች፣ ጸሃፊዎችና ደራስያን ከምክንያታዊነት ይልቅ በኢ - ምክንያታዊነት ውስጥ ተደብቀው መራራቅ የማይገባውን አላራራቁትምን? ለመንጋነት መበራከት የአንበሳውን ድርሻ አልተወጡምን? እስከዛሬ በኢ - ምክንያታዊነት ጉዞ ጥላቻና ጠላትነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አልተሰራፋምን? እርስ በራስ መጠራጠርና መከፋፈል ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ፣ ተሰምቶ በማያውቅና አድማሱም ልቆ አልተገኘምን? ከአዋቂዎች ይልቅ አላዋቂዎች፤ ከአስተዋዮች ይልቅ ትዕቢተኞች፤ ከዕውነተኞች ይልቅ ሀሰተኞች፤ ከሃቀኞች ይልቅ አጭበርባሪዎች፤ ከዕሳቤ ባለቤቶች ይልቅ ዕሳቤ አልባ የጥቃቅንና አነስተኛ ቅንጭብጫቢ ሀሳብ አነብናቢዎች ሰፊውን መድረክ እንዲቆጣጠሩት ምቹ ኹኔታ አልፈጠረምን? ግብረገብነት በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ አልደበዘዘምን? ሀገራዊና ሕዝባዊ ዕሴቶች በአደባባይ አልተጣሱምን? ብዙ ሕዝባዊና ሀገራዊ በብዙ ሚሊዮን ወጪ የተዘጋጁ መድረኮች እጅግ የወረዱ የገዥዎች ፍሬ ከርስኪ ወሬዎችና ቀረርቶዎች እንዲሞሉ አላደረገምን? ከትላልቅ ዕሳቤያዊና ምክንያታዊ ትላልቅ ጉዳዮች ይልቅ እጅግ የማይረቡና ከነሱ የማይጠበቁ ሃሜቶችና ጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳዮች የተበራከቱበት መኾኑ በገሃድ የሚታይ አይደለምን? በርካታ መግለጫዎችና ንግግሮች ያልታረሙና ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜታዊነት፤ ከትርጉም ያለው ሀሳብ ይልቅ አሽሙር የሚበዛባቸው አይደሉምን? ከአስማሪነታቸው ፉከራና ፍሬ አልባ አድናቆት የሚደሰኮርባቸው አይደሉምን? ከፍ ሲልስ የብዙዎች ድጋፍ ከምክንያታዊነት ይልቅ ኢ - ምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ መኾኑስ ከማን የተሰወረ ነው? ጠላትነትስ የሕልውናቸው መሠረት ያደረጉ አይደሉምን? ጠላትነትን ካላቀነቀኑስ በራሳቸው መቆም ስለመቻላቸው ማን በሙሉ ልብ ሊገልጽ ይችላል? የብዙ ግለሰባዊ፣ ቡድናዊ፣ ድርጅታዊና ተቋማዊ አለመግባባቶች፣ ግጭቶች፣ ጠላትነቶችና ጦርነቶችስ የኢ - ምክንያታዊነትና የስሜታዊነት ውጤቶች አይደሉምን? ችግሮቻችን በሙሉ በውይይትና በሠለጠነ ማስተዋል በተሞላበት መደማመጥ ሊፈቱ የሚችሉ አይደሉምን? ታድያ ስለምን አቃተን? ማንስ ነው ከምክንያታዊነት ይልቅ ኢ - ምክንያታዊነት የሚፈልገው? ለምን? ሕልውናውንስ በርሱ ላይ ማድረግን ለምን ሻተ? ምን ስለሚያጣ? ምክንያታዊ ትውልድ እያንዳንዱ እንቅስቃሴውን ለምን? እንዴት? መቼ? በማን? ስለምን? በምን? እያለ ይጠይቃል፤ ያስጠይቃል፤ ያልታረሙ አንደበቶችን በታረሙ አንደበቶች ይተካል፤ ስሜታዊነትን በአመክንዪ ይቀይራል፤ ገረድነትና አሽከርነትን በጌትነትና በነጻነት ይለውጣል፤ አስመሳይነትን በግልጽነት ያከስማል፤ ሀሳብ አልባነትን በዕሳቤ የበላይነት ያረጋግጣል፤ ርዕይ አልባነትን በርዕይ ባለቤትነት ያተጋል፤ ኢ - ምክንያታዊነት ላይ ምክንያታዊነትን ያሠለጥናል፡፡ ምክንያታዊ ትውልድ ከትላንት ይማራል፤ በጎውን ከትላንት በመውሰድ ዛሬ ላይ የራሱን አሻራ ያኖራል - ለማኖርም ይተጋል፡፡ ለነገና ከነገ ወዲያ በማሰብ ትውልዳዊ መሠረትን በማይናወጥ ዕሳቤ ላይ ይጥላል፡፡ ይህ የሚጠፋው ማን አለ? የሰው ልጅ ከምክንያታዊነት ሲርቅ ወደ ኢ - ምክንያታዊነት ይቀርባል፡፡ በአንጻሩ ወደ ምክንያታዊነት ሲቀርብ ከኢ - ምክንያታዊነት ይርቃል፡፡ አንደኛው ከሌላኛው ጋር ሕብረት የለውም፡፡ ሊኖረውም አይችልም፡፡ የአንዱ ባህሪያትና ጠባያት ለሌላኛው ባህሪያትና ጠባያት ግጣም መኾን የማይችሉ ተቃራኒ የኹነቶች መገለጫ ናቸው፡፡ ምክንያታዊ ትውልድ በምንም አይነት መንገድ መንጋ አይኾንም፡፡ ለአመክንዮ፣ ለዕውነትና ለዕምነት ግን መንጋ ይኾናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በነገሮች ላይ የሚኖረው ዕምነትና መተማመን ከጠባቂው፣ ከአስገኚውና ከመጋቢው በላይ በመሪው ላይ ከሚኖረው ግንኙነት የተነሣ ለላቀ ዕሳቤና ምክንያታዊነት - መንጋ ሲኾን መንጋነቱ በምክንያቱ ላይ ካለው ዕምነት የሚመነጭ እንጂ በአስተላላፊው አልያም በቧንቧው ላይ እንዳልኾነ ማሰተዋል እጅግ አስፈላጊ ይኾናል፡፡ በሰው ልጅ ታሪክ ተደጋግሞ እንደተስተዋለው በተለያዩ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አስተምህሮቶች፣ ዕሳቤዎችና ርዕዮቶች ላይ ብዙዎች ኹለንተናዊ መስዋዕትነትን እንዲከፍሉ አድርጓቸዋል፡፡ መንጋነትን መለያቸው አድርገውትም - መንጋነትን ለማበራከት የመንጋነት ባሕሪያትና ጠባያትን ተጠቅመው ብዙ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ በነዚህም ውስጥ ምክንያታዊነት - ለምክንያታዊነት ኹለንተናዊ ህልውና መንጋ መኾኑን በባህሪያቱና ጠባያቱ በኩል አሳይቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር ምክያታዊነት ውስጥ ካለ ምክንያታዊ መንጋነት በዘለለ ምክንያታዊነት የኢ - ምክንያታዊነት መንጋ ፈጽሞ ሊኾን አይችልም፡፡ ለባህሪውና ለጠባዩም ቢኾን አይስማም - ሊስማም አይችልም፡፡ በዚህም ውስጥ አንድ ታላቅ ዕውነት ይመዘዛል - “ምክንያታዊ መንጋ አልያም መንጋ ምክንያታዊ ሊኾን ፈጽሞ አይችልም፡፡” ምክንያታዊ ያልኾነ አንደበቱን የማይጠብቅና የማያርም፣ በስሜታዊነት መሰሉን ለመንዳት የሚተጋ፣ ማስመሰልና ሀሰተኛነትን የማንነቱ መገለጫ ያደረገ፣ አሽከርና ገረድነትን የሕልውናው መሠረት ያደረገ ግለሰብም ኾነ ቡድን የትውልድ አለኝታና መከታ ሊኾን ፈጽሞ አይቻለውም፡፡

“ምክንያታዊ ትውልድ እንኳንስ የራሱ ያለፈ ትውልድም ኾነ የሚመጣ ትውልድ አለኝታ ነው! ምክንያታዊ ትውልድ እያንዳንዱን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን በምክንያት በመምራት ያለፈ ትውልድ በጎ ዕሴት ጠባቂና አስጠባቂ፤ የራሱን ትውልዳዊ ኃላፊነት በመወጣት የሚቀጥለውን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚመጣው ትውልድ መኩሪያና አለኝታ ይኾናል፡፡”

Full Website