የብልጽግና ፓርቲ ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ

ማርሽ ቀያሪ አንቀጾች

ራሚደስ Nov 19/19

በAddis Standard ድህረ-ገጽ የተለጠፈው የብልጽግና ፓርቲ ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ ያቃጨለው ደውል ቀላል የማይባልና ላለፉት ሶስት አስርት አመታት ገደማ ኢህአዴጋዊው የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ፕሮጀክት ሥር ነቀል ለውጥ የሚያስከትል መሆኑን ያበሰረ ወይንም ያረዳ ነው፡፡ ይህ ረቂቅ በኢህአዴግ እህት ድርጅቶችና በግንባሩ ጠቅላላ ጉባኤ ፀድቆ ወደ ተግባር መግባት ከቻለ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ቢያንስ በወረቀት ላይ ሰፍሮ ከሚገኘው ያልተማከለ አስተዳደር ወደ ኢሠፓ መሰል የተማከለ አስተዳደር አስፈንጥሮ እንደሚያስገባው እሙን ነው፡፡

በረቂቅ ሰነዱ ምዕራፍ አንድ አንቀጽ 5 የሰፈረው የፓርቲው የስራ ቋንቋ/ዎች አርዕስት ምንም እንኳን ፓርቲው ሁሉንም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚያከብርና የብሔራዊ ክልሎች የስራ ቋንቋዎችን እንደ ፓርቲው የስራ ቋንቋ አድርጎ እንደሚወስድ ቢያትትም ቅሉ የክልል የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ከክልሉ የስራ ቋንቋ በተጨማሪ ቢያንስ አንድ የብልጽግና ፓርቲ የስራ ቋንቋ እንደየክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ሊጨምር ግድ ይለዋል ይላል፡፡ ይህ በተራ ቁጥር (ሐ) የተቀመጠው ሐሳብ የክልል ፓርቲ ጽ/ቤቶች ከክልሉ የስራ ቋንቋ በተጨማሪ እንዲጨምሩ የሚገደዱት ቋንቋ ምንም እንኳን ህብረ ብሔራዊነትና አገራዊ አንድነትን ለማጎልበት ሚና ሊኖረው እንደሚችል ባያጠራጥርም ክልሎች የሚጨምሩት ቋንቋ ምንነት ድብቅ አጀንዳ ያዘለ እንደሚሆን የሚገምቱ አይጠፉምና አጨቃጫቂ ነጥብ እንደሚሆን ከወዲሁ መገመት አያዳግትም፡፡

ሁለተኛው አሳሳቢ ጉዳይ የሚሆነው በረቂቁ ምዕራፍ ሦስት አንቀጽ 15 የተገለጸው የፓርቲው ብሔራዊ ጉባኤ በዋነኛነት የህዝብ ቁጥርና የአባላት ብዛት መሰረት ያደረገ አወካከል እንደሚኖረው ያትታል፡፡ ውክልናና መዋቅራዊ ስብጥሩ አሁንም ማንነትንና ቁጥርን ማዕከል ያደረገ ከሆነ የብልጽግና ፓርቲ ከኢህአዴግ ውርስ ቅርስ ማስቀረቱን እያሳበቀ በምእራፍ ሁለት አንቀጽ 9 ቁጥር (መ) ላይ የተገለፁትን “ዜጎችንና ህዝቦችን” በእኩልነት የማገልገሉን ጽንሰ ሀሳብ ወደ ተግባር መተርጎሙ እንደሚያዳግት ጥርጥር የለውም፡፡ አንድ ዜጋ ሊደርስበት የሚገባው የድርጅት መዋቅራዊ እርከን የሚወሰነው ለዜጋው ብሄር ተለክቶ የተበየነው ኮታ ወሳኝ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ምናልባት የዛ ዜጋ ብሔር ኮታ ሞልቶ ከሆነ ይህ ዜጋ ምንም እንኳን አቅምና ችሎታ ቢኖረውም የሱ ብሔር ሌላ ዜጋ ወይ እስኪወርድ ወይ እስኪሞት መጠበቅ ግድ ይለዋልና፡፡ የቡድንና የግለሰብ (ይቅርታ የዜጋ ተብሏል ለካ) መብት አስታርቆ መጓዙ ወረቀት ላይ የሰፈረውን መተግበር ከበሮ ሲይዙት ያደናግር አይነት ነውና፡፡ ወደ ዋናው ነጥብ ስንመለስ  በአንቀጽ 17ም የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ብዛትና ስብጥር በጉባኤው እንደሚወሰንና አሁንም የህዝብ ብዛትን ታሳቢ ያደረገ እንደሚሆን ያመለክታል፡፡ ይህ እንግዲህ ከዚህ ቀደም በኢህአዴግ አደረጃጀት ተለምዶ በነበረው አገራዊ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ አካል የሆነው የፓለቲካ ድርጅት አካላት በህዝብ ቁጥር ሳይሆን በግንባሩ አባልነታቸው ብቻ እኩል የውሳኔ ድምጽ የነበራቸውን የሚንድና የህዝብ ቁጥር እጅግ ወሳኝ የሚሆንበት ስርአት እንዲፈጥር ያደርገዋል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ወንበር፣ አመታዊ የበጀት ድልድል እና የፌደራል የስልጣን ክፍፍሎች በህዝብ ቁጥር አንጻር መቀመሩ ምክንያታዊነቱ ባያከራክርም አገራዊ አጀንዳዎች የሚወስኑበት የፖለቲካ ፓርቲ ግን በህዝብ ቁጥር ምክንያት አንዱ ከፍ ያለ ሌላው ደግሞ በአገሩ ጉዳይ ለመወሰን ዝቅ ያለ መብት መኖሩ አሁንም እጅግ አከራካሪ ለወደፊቱም ችግር ያረገዘ እንደሚሆን ጥርጥር አይኖረውም፡፡

ሶስተኛው እና ማርሽ ቀያሪ ተብሎ የሚገመተው ነጥብ ደግሞ በምዕራፍ አራት አንቀጽ 23 የተቀመጠው ስለ ፓርቲው የክልል ቅርንጫፍ አካላት አወቃቀር የሚያትተው ነው፡፡ በተራ ቁጥር 6 የተቀመጠው የፓርቲ የክልል ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለክልሉ ጉባኤና ለእናት ፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ እንደሆነና የክልል ኮሚቴው አስቸኳይ ስብሰባ መጥራት ቢያስፈልገው እንኳን የእናት ፓርቲውን ማዕከላዊ ኮሚቴ ፈቃድ ማግኘት እንደሚገባው ኮምጠጥ ባለ አማርኛ ይገልፀዋል፡፡ በአንቀጽ 27ም የክልል ቅርንጫፍ ፓርቲ ጽ/ቤት ተጠሪነቱ ለክልሉ ቅርንጫፍ ኮሚቴና ለእናት ፓርቲው ዋና ጽ/ቤት መሆኑን ይገልጸል፡፡ ይህ ማለት በአጭሩ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ስልጣናቸው ከክልላቸው እንደሚመነጭ ሁሉ የአሁኖቹ የክልል ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች፣ የክልል ኮሚቴና አስተባባሪ ኮሚቴ ስልጣን የሚመነጨውም የሚሞተውም እዚሁ አራት ኪሎ በሚከትመው የእናት ድርጅት ጽ/ቤት እና በውስጡም በፓርቲው ፕሬዝዳንትና እሱ በሚጠረንፈው ማዕከላዊና ስራ አስፈጻሚ አካላት መሆኑን በግልጽ ያስቀምጣል፡፡

በአጠቃላይ ይህ አደረጃጀት ምንም እንኳን አጋሮች ድሮውን ከ4 ኪሎ እና ከመቀለ በቀጭን ሽቦ በምትተላለፍ ትእዛዝ ጉዳያቸውን ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ ስለሰነበቱ አዲስ ነገር እንደማይሆንባቸውና አግኝተው ያጡት መብት ብዙም ፍንትው ብሎ ስለማይታያቸው አዲሱን የድርጅታዊ አወቃቀር ሊቀበሉት ይችላሉ፡፡ ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ፡፡ ዳሩ ግን እንደ ኦዲፒና ህውሃት ያሉ ጡንቻቸው ፈርጥሞ ግንባሩን እና ማዕከላዊ መንግስትን እስከ ማሽመድመድ የሚደርስ አቅምና ቁመና የተላበሱ ድርጅቶች ይህንን አዲሱን አደረጃጀት ይገዙታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል፡፡ ምናልባት ኦዲፓ ዛሬ ከተቆናጠጡት ቁልፍ የስልጣን መንበር አንጻር ቢቀበሉት እንኳን ወደፊት የ4ኪሎ ጀምበር ከኦሮሞ ልሂቃን ዘንድ የጠለቀች ጊዜ ወደየት ቅርቃር እየገቡ እንደሆነ የሚገነዘቡ አካላት ኦዲፒ ውስጥ ይጠፋሉ ብሎ መገመቱ አዳጋች ነውና፡፡

Full Website