ግብፆች በታሪካቸው ጦርነት አሸንፈው አያውቁም

(ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)

10-20-19

የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የህዳሴ ግድብን አስመልክተው ንግግር አድርገዋል፡፡ አልሲሲ ከዚያ አስቀድመው “የ2011 የፀደይ አብዮት በግብጽ ባይቀሰቀስ ኖሮ የህዳሴ ግድብ አይጀመርም ነበር” ብለው እንደነበርም ከማህበራዊ ሜዲያ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ፕሬዝዳንቱ ብቻ ሳይሆኑ የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሹኩሪ ለሀገራቸው ፓርላማ ባደረጉት ንግግር “ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ላይ የውሃ ሙሌቱን መቀጠሏ ተቀባይነት የለውም” ማለታቸውንም ሰምተናል፡፡ አንዳንድ ግብጻውያን በጋዜጣና በማህበራዊ ሜዲያ አውታሮች ሲወራጩ አይተናል፣ ሰምተናል፡፡ በበኩሌ የግብጻውያን መወራጨትም ሆነ የፕሬዝዳንቱ ንግግር አላስገረመኝም፣ አላስደነቀኝም፡፡ ታሪክ እንደሚነግረን በአፄ ላሊበላና ከዚያም በፊት በነበሩ ዘመናት ግብፆች ግብር እና ታክስ ብቻ ሳይሆን የእጅ መንሻ ጭምር ለኢትዮጵያ ነገስታት እየላኩ ዓባይን እንደልባቸው ይጠቀሙ ነበር፡፡ ግብር እና ታክስ ጊዜውን ጠብቆ ያልተላከለት አፄ ላሊበላ “የዓባይን ወንዝ እዘጋለሁ” የሚል ማስጠንቀቂያ መላኩን ከታሪክ መጽሐፍት አንብበናል፡፡ ግብፆች የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት ጠንከር ሲልባቸው አስፈላጊውን የእጅ መንሻ እየላኩ፣ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት የደከመ ሲመስላቸው እየፎከሩ መኖርን ያውቁበታል፡፡ በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት የደከመ ስለመሰላቸውና አንዳንድ “ሆድ-አደር ባንዳዎችን” በገንዘብ መግዛት ስለቻሉ ተመሳሳይ ዛቻና ፉከራ ማሰማታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ቁም ነገሩ ግብፆች ከፉከራ አልፈው ኢትዮጵያን አሸንፈው አያውቁም፡፡ ይህንን በተመለከተ አንድ የፌስቡክ ወዳጄ “ ወንድሜ፥ [ግብጽን] አትሳሳቺ በላት። የውጪ ጠላት ሲመጣ የእኔ ክልል፣ የእከሌ ክልል ብሎ የሚያስብ ኢትዮጵያዊ የለም። ይሄ ሕዝብ [አሁን] ሥራ ፈቶ እርስ በርሱ ሲነታረክ አይታ እንዳትሸወድ። ኮሽ ካለ ቀድሞ ለመሞት ሲሽቀዳደም ታገኘዋለች። በሉአላዊነቱ የሚደራደር ሕዝብ አይደለም። ለቁራሽ መሬት ሳይቀር ከዳር እስከዳር ሆ! ብሎ ተነስቶ፣ ለምንና እንዴት ብሎ ሳይጠይቅ ውድ ሕይወቱን ሲገብር የኖረ ሕዝብ ነው። እንዲያውም ሳታውቀው ይሄንን የደበዘዘ አንድነታችንን መልሳ እንደ ብረት ታጠነክረዋለች፥ ትሞክር! ” የሚል አስተያየት ጽፎልኝ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ያለው እውነት ይሄ ነው! ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከእስራኤልም ከሌሎችም ጋር ጦርነት አካሂዳለች፡፡ ግን በታሪኳ አንድም ጦርነት አሸንፋ አታውቅም፡፡ ለምሳሌ፡- ግብፅ በእስማኤል ፓሻ እየተመራች በኦቶማን ኢምፓየር ትተዳደር በነበረበት በዚያ ወቅት ግዛቷን ወደ አቢሲኒያ ምድር ለማስፋፋትና ጥቁር ዓባይን ለመቆጣጠር ፈለገች፡፡ ይህንንም ለማድረግ በርካታ መኮንኖችን ከአውሮፓና ከአሜሪካን በመመልመል ከፍተኛ ሠራዊት ገነባች፡፡ በኤርትራ ጉንደት በተባለ ሥፍራ በተደረገ ጦርነት ከቱርክ ጋር የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው የመጡ ግብጻውያን በጦርነቱ ሳይሆን በኢትዮጵያ ተራራ ላይ የገጠማቸውን ቀጭን መንገድ ሲያዩ በድንጋጤ መዋጣቸውን ታዋቂው የታሪክ ጸሐፊ ሀጋይ ኤሪክ ተርኮታል፡፡ የኢትዮጵያ ጦረኞች ካደፈጡበት በመውጣት ፈጣን ጥቃት ሲሰነዝሩባቸው የሚገቡበትን ማጣታቸውን ይኸው ታሪክ ጸሀፊ ያብራራል፡፡ ገዢ መሬት ይዞ ያልታሰበ ጥቃት በመሰንዘር ወታደራዊ የበላይነትን የያዘው የኢትዮጵያ ጦር እንቅስቃሴውን ሲቀጥል የግብፅ ጦር ለወሬ ነጋሪ ሳይተርፍ ሙሉ በሙሉ መውደሙና የዚህ ትልቅ ሽንፈት ዜና በግብፅ ሲሰማ ከፍ ያለ ፍርሃትና ንዴት መፍጠሩም በታሪክ ዘጋቢዎች ተከትቧል፡፡ ጦርነት ታሪክ እንጨምር፡፡ የተጨናገፈውን ወረራ ተከትለው ግብፃውያኑ እንደገና ኢትዮጵያን ለመውረር ሞከሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ወደ 13,000 የሚጠጉ ወታደሮችን ይዘው ነበር፡፡ ረቲብ ፓሻ በተባለ በግብጹ መሪ ወንድ ልጅ የሚመራ ጦር በምፅዋ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገባ፡፡ ጉራዕ ሸለቆ አቅራቢያ 2 ምሽጎችን በጉራዕ እና ከጉራዕ ጥቂት አለፍ ብሎ በሚገኝ ተራራ ላይ ሰራ። በኢትዮጵያ በኩል በነበረው ምቹ ያልሆነ የጦር ሜዳ አቀማመጥ ምክንያት በአንድ ጊዜ 15,000 ወታደሮች ብቻ ነበሩ ለውጊያ የተሰለፉት፡፡ ሁለቱ ኃይሎች ተገናኙ፡፡ ረቲብ በጉራዕ ምሽግ ውስጥ ካሉት 7,700 ወታደሮች ውስጥ 5 ሺዎቹ ከኢትዮጵያውያን ጋር ውጊያ እንዲገጥሙ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ ይህ የግብጽ ኃይል በራስ አሉላ አባ ነጋ በሚመራ የኢትዮጵያ ሰራዊት በፈጣን ሁኔታ ተከበበ፡፡ በተደረገበት ጥቃት ወዲያው ተበተነ፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ባገኙት ድል ሳይኩራሩ ኃይላቸውን ካጠናከሩ በኋላ ጉራዕ በመሸገው ኃይል ላይ ሁለተኛውን ጥቃት ሰነዘሩ፡፡ ግብፆች መከቱ፡፡ በሚቀጥለው ቀን የኢትዮጵያ ጦር ምሽጉን ደረመሰው፡፡ የግብፅ ጦር ብዙም ሳይቆይ ሸሸ። በአፋር በኩል የነበረውን ጦርነት ላክልበት፡፡ በግብጽ በኩል በርከት ያሉ የውጭ ዜጎች በዚህ ጦርነት ተሳትፈዋል፡፡ አዶልፍ አረንድረፕ እና የስዊስ አሳሽ የነበረው ወርነር ሙዚንገር በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሙንዚገር የግብጽን ጦር እየመራ ኢትዮጵያን ለመውጋት በታዳጁራ (ጂቡቲ) በኩል ወደ መሀል ሀገር ዘልቆ ለመግባት ጉዞ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ይህ የሙዚንገር ሠራዊት የአውሳው ሱልጣን በነበሩት በሙሐመድ ኢብን ሃንፍሬ ጦር ተሸነፈ፡፡ ሙዚንገርም በዚሁ ጦርነት ተገደለ፡፡ ይሄ ሁሉ የግብጽ መንፈራገጥ ዋነኛ ዓላማ ሱዳንን እና ኢትዮጵያን ያጠቃለለ ትልቅ ግዛት ለመመስረት ነበር፡፡ ሱዳንን ለተወሰነ ጊዜ ለማንበርከክ ብትችልም ከኢትዮጵያ ጋር ግን ተደጋጋሚ ጦርነት አካሂዳ በሁሉም ጦርነቶች ተሸንፋ የሀፍረት ማቅ ተከናንባለች፡፡ የሚገርመው ነገር ግብጽን ደጋግመው ያሸነፏት የኢትዮጵያ የጠረፍ ግዛት አስተዳዳሪዎች፤ ማለትም በሰሜን በኩል የትግራይና የመረብ ምላሽ (ኤርትራ) ገዢዎች፣ በምስራቅ በኩል የአፋር ሱልጣን እንጂ መላው የኢትዮጵያ ጦር አልነበረም፡፡ ግብፆች በሁለት ነገር ጎበዞች ናቸው፡፡ አንደኛ፤ የረቀቀና የተቀነባበረ የሀሰት አሊያም የተጋነነ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ጎበዝ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ እያንዳንዱ ግብጻዊ በትብብርና ባልተቋረጠ ሁኔታ ከመንግስት ጋር ይሰራል፡፡ ምንም ዓይነት መሳሪያ ሳይኖራቸው “ኒኩሌር አለን” እያሉ ያስወራሉ፡፡ ከተፈጠረች የዓመታት እድሜ ባልነበራት እስራኤል እንክትክቱ የወጣውን የአየር ኃይል በማጋነን ሰማይ ላይ አውጥተው ይተርኩለታል፡፡ በእኛ በኩልስ? በእኛ በኩል ይህንን የግብጽ ፕሮፓጋንዳ በመልሶ ማጥቃት መመከት ሲገባን የእነሱን የውሸት ፕሮፓጋንዳ እንደ ደህና ነገር እየተቀባበልን እናሰራጭላቸዋለን፡፡ የተማርነው ሳንቀር የግብፆችን ባዶ ፕሮፓጋንዳ አንጠልጥለን “ግብፆች እኮ እንዲህ ዓይነት ጦር አላቸው፣ እንዲህ ዓይነት መሣሪያ አላቸው፣ ኒኩሌር ታጥቀዋል፣ የአየር ኃይላቸው አይቻልም፣…” እያልን ፈርተን ህዝባችንን እናስፈራራላቸዋለን፡፡ እውነታው የሚነግረን ወኔቢሱ የግብጽ ጦር የታጠቀውን ቢታጠቅ ጀለቢያውን ሰብስቦ መፈርጠጡን ነው፡፡ ሁለተኛው የግብፆች ጉብዝና የእጅ አዙር ጦርነት ለመዋጋት የሚያደርጉት ጥረት ነው፡፡ ማለትም ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳችን እንድንዋጋ በማድረግ ማእከላዊ መንግስትን ለማዳከም የሚያደርጉት ጥረት፡፡ እኛ እርስ በርስ ስንባላ ዓባይን እንደልብ መጠቀም፡፡ ይህንን በተመለከተ ጀብሀን እና ሻዕቢያን አስታጥቃ ከኛ ጋር በማዋጋት ያለ ባህር በር አስቀርታናለች፡፡ ዛሬም ተመሳሳይ ነገሮችን ትሞክር ይሆናል፡፡ ግን የሚሳካ አይደለም፡፡ ግብጻውያን አንድ ነገር መረዳት አለባቸው፡፡ የፈለገውን ያህል ገንዘብ ቢያፈሱ፤ ያሻቸውን ያህም ተጽእኖ ቢያሳድሩ አንድ ቀን እጃችን ላይ መውደቃቸውና እየተለማመጡ መኖር አይቀርላቸውም፡፡ እናም የህዳሴው ግድብ መጠናቀቁ አይቀሬ መሆኑን ተገንዝበው ከመሰሪ ስራቸውና ከከንቱ ፕሮፓጋንዳቸው ተቆጥበው ሁለቱን ሀገሮችና ህዝቦች የሚያስተሳስሩ የጋራ ፕሮጄክቶችን መንደፍና በጋራ ለመስራት ትኩረት ማድረግ ለሁላችንም የሚጠቅም መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባልቸዋል። በመጨረሻም አንድ ነገር አስረግጨ መናገር ወደድሁ፡፡ ይኸውም፡- በ2011 የፀደይ አብዮት በግብጽ ባይቀሰቀስ ኖሮ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ “ፕሬዝዳንት” ሊሆኑ አይችሉም ነበር፡፡ የህዳሴ ግድብ ግን የፀደይ አብዮት በግብጽ ተቀሰቀሰም አልተቀሰቀሰ መጀመሩ የሚያጠራጥር አልነበረም፡፡
Full Website