Back to Front Page

የኢዜአ ትዝብቶቼ

ክፍል አንድ

(በደሳለው ጥላሁን­-ኢዜአ) 7-13-19

አቤት ጊዜው እንዴት ይሮጣል፡፡እነሆ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከሁለተኛ ዲግሪ የትምህር ቆይታ በኋላ ወደ ስራ ገበታዬ ከተመለስሁ ድፍን አንድ አመት ሊሞላኝ የ10 ቀናተ  እድሜ ብቻ ቀሩኝ፡፡ ይሄን ተከትሎ በተማርኩት የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ምክንያት በተቋሙ ከሚኖረኝ አራት አመታት የቁም እስረኝነቴና "የጓንታናሞ" የግዞት ቆይታዬ አንድ ዓመት ሊነሳ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሁለት ዓመታት የትምህርት ቆይታዬ እና የተቋሙ የአስራ አንድ ወራት የስራ ጊዜዬ በብዙ መሰናክሎች የተሞላ ነው፡፡ በተለይ የትምህርት ቆይታዬ ለእኔ በጣም አስቸጋሪና  ከመሰናክልም በላይ ነበር፡፡

ጉዳዩ በተቋሙ በተለይ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እኔን ጨምሮ በሌላው የተቋሙ ሰራተኛ ላይ እየተፈጸሙ ካሉ በርካታ በደሎች ውስጥ እንደ አንድ ማሳያ የሚወሰድ ነውና ጠቀመም አልጠቀመም የሚከተለውን ልል ወደድሁ፡፡

"ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ" እንዲሉ አበው ነገሩ እንዲህ ነው ጊዜው 2008 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ተቋሙ ደግሞ አገራዊ የለውጥ ጅማሮውን ተከትሎ ዛሬ ህልውናው ካከተመው የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳች ጽህፈት ቤት እንደ አንድ ዳይሬክቶሬት ከነበረበት አደረጃጀት ወጥቶ በአዋጅ ራሱን በመቻል እየተንቀሳቀሰ የነበረበት ወቅት፡፡

ታዲያ በዚህ ጊዜ የተቋሙ የእስትራቴጅክ እቅድ አካል የሆነውን የሰራተኛ የአቅም ግንባታ መርሃ ግብር መነሻ በማድረግ ተቋሙ በጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት የትምህርት ዘርፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ለማስተማር ማስታወቂያ ያወጣል፡፡

እኔም እንደ አንድ የራሱን አቅም በትምህርት ለማሳደግ ፍላጎት እንዳለው ሰራተኛ የወጣውን ማስታወቂያ ሳየው በጣም ደስ አለኝ ጊዜም ሳልሰጥ ተመዘገብሁ፡፡ እኔን ጨምሮ እድሉን ለማግኘት ከተመዘገበው 40 ያህል የተቋሙ ሰራተኛ ውስጥ የመመልመያ መስፈርቱን ያለፍን 10 ሰዎች ተመረጥን፡፡

ታዲያ የተቋሙን መመዘኛ ስላለፍን ብቻ ትምህርት አንጀምርምና እኔም ሆንኩ ሌሎች ጓደኞቼ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያወጣውን የመግቢያ ፈተና መርሃ ግብር በመጠበቅ ፈተናውን ተፈተንን፡፡ ከቀናት በኋላ ፈተናውን ከተፈተን የተቋሙ አስር ሰዎች ውስጥ አምስታችን ፈተናውን ስናልፍ ሁለት ሰዎች ደግሞ ተጠባባቂ ሆኑ፡፡

እውነት ለመናገር የሌሎች የስራ ባልደረቦቼን ስሜት ባላውቅም ትምህርት ለመማር ከነበረኝ ፍላጎት አንጻር ፈተናውን ማለፌን ስሰማ እጅግ በጣም ደስ አለኝ፡፡ ጊዜ ሳልሰጥ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማቅናት የተለጠፈውን የፈተና ውጤት አየሁ የኔም ሆንኩ የአራቱ የስራ ባልደረቦቼ በመግቢያ ፈተናው ያመጣነው ውጤት እጅግ በጣም ጥሩ ነበር፡፡

የትምህርት እድሉ በተቋሙ ለመጀመሪ ጊዜ የተሰጠ እንደመሆኑ መጠን በፈተናው ማለፋችን ከተሰማ በኋላ እኔ እየሰራሁ በምገኝበት የአዲስ አበባው ዋና ቢሮም ሆነ በክልል ቅርንጫፎች ከሚገኙ የሙያ ባልደረቦኖቻችን በአካልም በስልክም የእንኳን ደስ አላችሁ መልክቶች መጉረፍ ጀመሩ፡፡ ይሄ ደግሞ በወቅቱ የፈጥረው ደስታ ልዩ ነበር፡፡

በዚህ ወቅት ታዲያ አንዳንድ የዋና ዳይሬክተሩ የቅርብ ወዳጆች እኔንም ሆነ ፈተናውን ያለፉ ሌሎች የስራ ባልደረቦቼን በግል ሂዱና ዋና ዳይሬክተሩን አመስግኑት፣ በእስዎ መጀን በሉት እያሉ ይጎተጉቱን ነበር፡፡

ነገር ግን በወቅቱ እኔም ሆንኩ ሌሎች የሙያ ባልደረቦቼ የመልክተኞችን ሃሳብ አልተቀበልነውምና በተናጠልም በቡድንም ሂድን አላመሰገንም፤ምስጋና ባያስፈልገውም ቅሉ፡፡

ጊዜ ቁሞ አይጠብቅምና ትምህርት የሚጀመርበት ጊዜ በመድረሱ እኔም ሆንኩ ጓደኞች ከላፕቶብ ውጭ የስራ መሳሪያዎቻችንን አስረክበን ፈተናውን ያለፍን አምስቱ ሰራተኞች በጋዜጠኝነትና የስነ ተግባቦት ትምህርት ዘርፍ፣ ተጠባባቂ የነበሩት ሁለቱ የሙያ ባልደረቦቼ ደግሞ በህዝብ ግንኙነት ትምህርት ዘርፍ ትምህርታችንን ቀጠልን፡፡

እውነት ለመናገር ሌላው የተቋሙ ሰራተኛም እንደሚመሰክረው በወቅቱ ለትምህርት የገባነው ሰባቱም የተቋሙ ሰራተኞች በየተመደብንበት የስራ ክፍል ከሰኞ እስከ ሰኞ 24 ሰዓት ሊባል በሚችል መልኩ የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካት የምንሰራ ነበር፡፡ ይሄም በወቅቱ ዋና ዳይሬክተሩ ያለምንም ማቅማማት በየመድረኩ አፋቸውን ሞልተው ይናገሩት የነበረው ነው፡፡

ሁላችንም የትምህርት እድል ተጠቃሚዎች ትምህርት እየተማርንም ቢሆን በትርፍ ሰዓታችን ተቋሙን ለማገዝ ፍላጎት ነበረን አንዳንዶቻችን ትምህርት በጀመርን ጥቂት ወራት አካባቢ በቅርብ ኃላፊዎቻችን በኩል ተጠርተን አንዳንድ ስራዎችን አግዘናል፡፡

ነገር ግን ዋና ዳይሬክተሩ በወቅቱ እኔም ሆንኩ ሌሎች የሙያ ባልደረቦቼ በማናውቀው ምክንያት የነብር አራስ ሆኑ፣ ወትሮም ቢሆን ኩርፊያ የሚቀናቸው እሳቸው አይናችሁን ላፈር አሉን፡፡ አሰራርና መርህን አክብሮ ከመስራት ይልቅ ዋና ዳይሬክተሩ ሲደሰቱ የሚደሰቱት፣ ሲከፋቸው የሚከፉት የማኔጅመንት አባላትም እንዲሁ፡፡

በወቅቱ አማራጭ ያልነበረን እኛም ትምህርቱ በራሱ የተቋሙ ተልዕኮ ነውና ትምህርታችን ላይ በርትተን መስራት ጀመርን፡፡

ነገር ግን ትምህርት ከጀመርን ከስድስት ወራት በኋላ አንድ ክስተት ተከሰተ ለተቋሙ ሰራተኛ የሚከፈለው ደመወዝ ሰራተኛው ከሚሰራው ስራ አንጻር እና ሌሎች የመንግስትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙኃን በወቅቱ ከሚከፍሉት ደመወዝ ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ ስራተኛውን በስራ ገበታው ላይ ማቆየትን ታሳቢ ተደርጎ የጥቅማ ጥቅም መመሪያ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡

ልብ በሉ እንግዲህ የጥቅማ ጥቅም መመሪያው የወጣው በአዳማ ከተማ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሁሉ ነገር ተሟልቶላቸው በከተሙ ሶስት የተቋሙ የማኔጅመንት አባላትና በዋና ዳይሬክተሩ አቅጣጫ ሰጭነት ነው፡፡

የጥቅማ ጥቅም መመሪያው መውጣቱ እሰየው ባልከፋ ነበር፡፡ ነገር ግን መመሪያው ከወጣ በኋላ ሰራተኛ ሳይወያይበትና የሚጨመረው ተጨምሮ የሚቀነሰው ተቀንሶ የራሱ ሳያደርገው፣እኛም ተማሪዎች ምንም አይነት መረጃ ሳይኖረን  ሰራተኛ እንደተወያየበት ተደርጎ  ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተላከ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትም በተቋሙ የጥቅማ ጥቅም መመሪያ ላይ ሙያዊ አስተያየት እንዲሰጥበት በወቅቱ ለነበረው ወደ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ይልከዋል፡፡

ጉዳዩ የተላከለት የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴርም የሚጨመረውን ጨምሮ የሚቀነሰውን ቀንሶ የጥቅማ ጥቅም መመሪያውን ወደ መራለት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በመላክ "የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ የጥቅማ ጥቅም አገልግሎት መመሪያ ቁጥር 010/2009" ሆኖ  እንዲጸድቅ አደረገ፡፡

ገና ከመጀመሪው በትምህርት ላይ የምንገኝ የተቋሙን ሰራተኞች አይናችሁን ላፈር ብለው ለሰላምታ እንኳን የተጸየፉን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ተንኮል ቢጤ አስበው የጥቅማ ጥቅም መመሪያው የመጨረሻ አንቀጽ ላይ ልዩ ልዩ ድንጋጌ በሚለው አንቀጽ ስር በትምህርት ላይ ያለ ትምህርቱን አጠናቆ እስከ ሚመለስ የጥቅማ ጥቅም እድሉ ተጠቃሚ አይሆንም የሚል ሃሳብ እንዲጨመር ያደርጋሉ፡፡

በወቅቱ የ2ኛ ዲግሪያችንን እየተማርን የነበርን የተቋሙ ሰራተኞች የጥቅማ ጥቅም መመሪያውን መውጣትና መጽደቅ እንዲሁም የእኛን ተጠቃሚነት ያገለለ መሆኑን ስንሰማ ሰባታችንም ተሰባስበን መከርን፡፡ በተስማማንበት መሰረትም ጉዳዩ እንዲታይልን ለተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አመለክትን፡፡

ያለምንም መነሻ ምክንያት ተማሪዎቹን እንደ ነፍሰ ገዳይ ማየት የጀመሩት ዋና ዳይሬክተሩ የእኛን ስሜት ተረድተውና የተቋሙ አሰራር በሚፈቅደው አግባብ በማነጋገር ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ጉዳዩን ለተቋሙ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ይመሩታል፡፡

በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሃሳብ ለመስጠት ግራ የተጋቡት የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ሙያዊ ምክር ለመጠየቅ ጉዳዩ ወደ ሚመለከታቸው በወቅቱ የነበረው የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ባለሙያዎችን ሙያዊ ምክር በደብዳቤም በአካልም ይጠይቃሉ፡፡

"ባለሙያዎቹም ጉዳዩ እኮ እዚህ ድረስ የሚደክማችሁ አይደለም በተቋሙ የበላይ ኃላፊ ውሳኔ የሚያልቅ ነው ከመጀመሪውስ እንዴት ይከለከላሉ ከተቋሙ አልተሰናበቱ ደግሞስ 'መስሪያ ቤቱ መኖሪያ ቤት ሰጥቶት የነበረውን ሰራተኛ ትምህርት ስለጀመርህ ከመኖሪያ ቤትህ ውጣ ይለዋል?' ይዛችሁት የመጣችሁት ጉዳይም ይህ ማለት ነው" ሲሉ በምሳሌ አስረድተው ይመልሷዋል፡፡

Full Website