ስለ አገራችን ወቅታዊ ሁኔታ
------------------------------------
ኢትዮጵያ እንደ አገር፣ ኢትዮጵያውያን ደግሞ እንደ ህዝብ በቅርብ ጊዜ ታሪካችን አሁን ወዳ’ለንበት የበለጠ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ገብተን አናውቅም። የአገሪቱ ህልውና፣ የህዝባችን አንድነትና ደህንነት ታላቅ ፈተና ላይ ወድቋል። መፃፍና መናገር ያቆምን ወይንም ያልጀመርን ሁሉ ዛሬ ካልተናገርን፣ ዛሬ ካልፃፍን፣ ዛሬ አደባባይ ላይ ወጥተን ካልጮኽን፣ ዛሬ ለአለም መንግስታት አቤቱታችንን ካላቀረብን፣ ማንም እሸናፊ የማይኖርበት – ብዙ ህዝብ የሚያልቅበት፣ የሚፈናቀልበትና የሚሰቃይበት ሁኔታ ውስጥ እንገባለን።
አገሪቱን እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሷት በመጀመሪያ ደረጃ ተጠያቂ ሊሆን የሚገባው ጠቅላይ ሚኒስቴር አቢይ አህመድ ነው። እውነት ነው፤ በአሸብራቂና አደንዛዥ ቋንቋ የህዝቡን ያልተቆጠበ ሙሉ ድጋፍ አግኝቶ ነበር። ዛሬ ካስቀመጥነው ማማ ወርዶ ደካማ ወይንም እኩይ እላማ ያለው መሪ ለመሆኑ ያለንበት አስከፊ ሁኔታ በግልፅ ይናገራል። ከዚህ በፊት የዓለም-አቀፍ መለኪያዎችን ጠቅሼ፣
ኢትዮጵያ እየከሸፈች ያለች ሃገር ( Failed State) መሆኗን ጠቁሜ፣ እስቸኳይ የእርምት እርምጃዎች እንዲወስዱ ያሳሰብኩት። በጊዜው ብዙዎች ተሟግተውኝ ነበር። ዛሬስ ምን ይሉ ይሆን?
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በማናቸውም የዓለም ክፍል ውስጥ እንደዚህ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር፣ በመጀመሪያ ተጠያቂ የሚሆነው መሪው ነው። ሌላውን – በማስረጃ የተደገፈውን ግድፈቱንና ውሸቱን ( በተለይ የውትድርናና የአካዳሚክ ትምህርቱን በተመለከተ) ወደ ጎን ትተን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ እህመድ እገሪቱን መምራት አለመቻሉን የማይገነዘብ የማንበብ፣ የማዳመጥ እቅምና ችሎታ ያለው ኢትዮጵያዊ፤ ለሚታየው አገራዊ ሽብርና ውድቀት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እኩል ተጠያቂ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድፍረት፣ እውቀትና ፍላጎት የለውም። የእርሱ ትኩረት ገፅታውንና ቋንቋውን ማሳመር፣ መስሎ መታየት እንጂ የተናገረውን ወይም ህዝብ የሚፈልገውንና የሚጠብቀውን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ የሚችል መሪ ሆኖ አልተገኘም። ይህ ወይ ከተፈጥሮ ደካማነት፣ ወይም ደግሞ በፅንፈኞች አላማ ተጠልፎ፣ ተገድዶ ከመሳት ወይም ከአእምሮ መዛባት የመጣ ሊሆን ይችላል። እንደዚህ ያሉ በርካታ መሪዎችን በአፍሪካ አይተናል። «ሁሉን እናውቃለን፣ ለሁሉም መልስ አለን!» ብለው፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያልጨረሱ መሪዎች የፖለቲካ ፍልስፍና መምህር ሆነው ለመታየት በመሞከር አገራቸውን ለውድቀት እንደዳረጉ ብዙ መስክረናል። ሙአመር ጋዳፊ «Direct Democracy» ወይንም «ህዝቡን ከመንግስት ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ አዲስ የዴሞክራሲ ስርአት» ብሎ የግሉን ፍልስፍና በመፅሀፍ መልክ አውጥቶ እያንዳንዱ ሊቢያዊ እንደመመሪያ በቃሉ እንዲያጠናው እውጆ ነበር። ( የዚህ መፅሃፍ ሌላኛው ስያሜ «አረንጓዴው መፅሀፍ» የሚል ነው።) እኔም በአንድ ወቅት ቤንጋዚ የሚገኘው የጋዳፊ ድንኳን ውስጥ ተጠርቼ፣ ስለዚሁ ፍልስፍና የተወሰነ ትምህርት ተቀብያለሁ:: የጋምቢያው መሪ መቶ አለቃ ያህ ያህ ጃሜ፣ «Patriotic Reorientation and Construction» ወይም «አዲሱ የእርበኝነትና የአገር ወዳድነት ስሜት»ን ‘አስተምራለሁ’ ብሎ ተነስቶ፣ ከዚያም አልፎ የአገሪቱ ታላቅ ዶክተር «ነኝ! የኤድስ በሽታን እፈውሳለሁ!» ብሎ፣ በሳምንት እንድ ጊዜ ህዝቡ እያሰለፈ ህክምና ይሰጥ ነበር። ህክምናው የውሸት መሆኑ ቢታወቅም ፣ በግልፅ አይነገርም ነበር። ጃሜህ 23 እመት ሙሉ አገሩን ዘርፎ፣ ህዝቡን ጨቁኖ ካበቃ በኋላ ተባርሮ በስደት ወደ ናይጄሪያ ሄደ። የኮንጎው መሪ ጆሴፍ ዲዚሬ ሞቡቱ በፊት ወታደር ነበረ። «Authenticite» በሚል የግል ፍልስፍና የፖለቲካና የባህል አብዮት «አመጣለሁ!» ብሎ ተነሳ። ስሙንም ለወጠ:: «Mobutu Sese Seko Nikki Ngbendu» ብሎ ሰየመ። ትርጉሙም፣ «The all powerful warrior born to win/ ከሁሉም ሃያላን የላቀ፣ ለማሸነፍ ብቻ የተፈጠረ ተዋጊ» የሚል ነው። «የተፈጠርኩት ኮንጎን ለመግዛት ነው።» አለ:: አገሪቱን ለ32 ዓመታት ገዝቶ ዘርፎ፣ አደኽይቶ ለመሰደድ ሲሞክር፣ ሰሜን እፍሪካ ላይ ሞተ:: የደቡብ አፍሪካ መሪዎች የአፓርታይድን ህጋዊነት የሚያፀድቅ ህገ-መንግስትና የፖለቲካ ፍልስፍና አወጡ። የፖለቲካ ፍልስፍናው ጥቁርን ለማግለልና ነጭን የበላይ ለማድረግ ያለመ ስለነበረ፣ ህዝቡ ባደረገው የተራዘመ ትግል ስርአቱ ተገረሰሰ። ኢዲ አሚንም በኡጋንዳ የራሱን ፍልስፍና መስርቶ «አዲሲቱን ኡጋንዳ እፈጥራለሁ!» ብሎ ተነሳ:: አምሳ አለቃ ነበረ፤ ስልጣን በያዘበት ወቅት። ስልጣን ሲይዝ ግን ማዕረጉ « His Excellency President for Life, Field Marshall Ali Haji Doctor Idi Amin Dada, VC MC, Lord of All Beasts of the Earth and Fishes of the Seas and Conqueter of the British Empire in Africa/ የተከበሩ የህይወት ዘመን ፕሬዝደንት፣ ፊልድ ማርሻል አሊ ሃጂ ዶክተር ኤዲ አሚን ዳዳ፣ የድል እና የሰራዊት መስቀል፣ በምድር ላይ የሚገኙ አናብስት እና ባህር ውስጥ ያሉ አሳዎች ጌታ እና አፍሪካ ውስጥ ያሉ የብሪታኒያ ግዛቶች አስመላሽ» ብሎ ራሱን ሰየመ። ከስምንት አመት የጭቆና አገዛዝ በኋላ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተሰድዶ እዚያው አረፈ። መንግስቱ ሀይለማርያምም አገር-ወዳድ ቢሆንም፣ ጨካኝና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ርዕዮተ-ዓለም በመከተሉ አገሪቱን ለወያኔ ዳርጎ አመለጠ:: ሌሎቹ መሪዎች እነዚህን የመሳሰሉ በራሳቸው ተክለ-ሰብዕና ላይ ብቻ ያተኩሩ መሪዎችን ገጠመኝ አንብበው ከታሪክና ከምሁራን ከመማር ይልቅ አዲስ የፖለቲካ ፍልስፍና ፈልሳፊ የሚሆኑት ስልጣናቸውን ለማመቻቸትና ከአዋቂዎች በላይ «ነን!» ብለው፣ አምልኮትን ( cult) ለመፍጠር በመፈለግ ነው። ከመሰረታዊ የዴሞክራሲ ጥያቄ ውጪ የራሳቸውን ገፅታና አዋቂነት ለማሳመር፣ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያራምዱት ይህ የግል የስልጣንና የተመላኪነት ፍላጎት ለአገርም – ለራሳቸውም ሳይበጅ ለአሳፋሪ መንገድ እንደሚዳርጋቸው ታሪክ በጉልህ ያስተምራል።

በአገራችን –በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አገዛዝ «መደመር» ብለው መሪዎች ህዝቡን እያወናበዱት ነው::

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና ዲሞክራሲ ለማስፈን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት በአሸበረቀ እና በማራኪ ቋንቋ የቀረቡት ሃሳቦች ፍቅርና እንድነትን የሚያስተጋቡ ስለነበሩ፣ «እድል እንስጠው!» ብሎ ያልተቆጠበ ድጋፉን ሰጥቷል። ያ ሁሉ ንግግር መና ሆኖ ሲቀር፣ አገሪቱም ወደ ሽብር እየንተራሻተተች ስትሄድ፣ ሌላ አማራጭ ለመፈለግ ይገደዳል።
ዴሞክራሲ አንድ መንገድ ነው ያለው። እንደየአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ሲተገበር ይለያይ እንጂ ሁሉም ዓይነት ዴሞክራሲ በህዝብ አንድነት፣ እኩልነትና ነፃነት ላይ መሰረቱን ጥሎ፣ መሪዎችን በነፃነት የመምረጥ መብት ላይ የተመሰረተ ንድፈ-ሃሳብ ነው። «መደመር፣ መቀነስ!» የሚል የዴሞክራሲ ፍልስፍና የለም።
በዴሞክራሲ አተገባበር ላይ ጥያቄ ቢኖርም፣ አዋቂዎች – ሽማግሌዎች -ተመራማሪዎች – የህዝብ ተወካዮች ይምከሩበት እንጂ የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ቦታ በአጋጣሚ ሰለያዙ ብቻ የፖለቲካና የዴሞክራሲ አስተማሪ ሆኖ መታየት ትንሽነት ነው። ይህ ትኩረት ያጣ አመራር ነው አገሪቱን እዚህ ያደረሳት። መሪዎች ሁሉን አዋቂ ስለሆኑ እይደለም ለስልጣን የሚመረጡት። እውነተኛ አዋቂዎችን፣ ምሁራንን፣ የአገር ተቆርቆሪዎችን፣ የተለያዩ እስተሳሰብ ያላቸውን ቅን ኢትዮጵያውያንን ሰብስበው የተለያዩ እማራጮች ላይ ተወያይተው ለህዝብ ጥቅም «ይበጃል!» ተብሎ አብዛኛው ወገን የተስማማበት ውሳኔ ላይ መድረስ የሚችሉ ናቸው – ጥሩ «መሪዎች» የሚባሉት። መጥፎ መሪዎች ከእነርሱ አስተሳሰብ ያነሰ እንጂ የላቀ ሊያቀርቡ የማይችሉ፣ በእውቀታቸውም ሆነ በራሳቸው የማይተማመኑ፣ በመሾማቸው ብቻ ተድስተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለውን ሁሉ ያለአንዳች ትችት የሚቀበሉ አማካሪዎችን የሚሾሙ ናቸው። እነዚህን ይዞ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ወደ ሰባተኛ ንጉስነት እያመራ ያለው። ቀን ባለፈ ቁጥር ጠ/ሚኒስትር አቢይ መጨረሻው ከላይ እንደተጠቀሱት መሪዎች መሆኑን ሲገነዘብ፣ ስልጣኑ ላይ ለመቆየት ሲል የበለጡ ስህተቶችን ይሰራል እንጂ ከስህተቱ «ይማራል!» ብሎ ማመኑ በብዙሃኑ ዘንድ አክትሟል። ለዚህም ነው አስቀድመን፣ «ሳይቃጠል በቅጠል» ብለን ስንፅፍ – ስንናገር የከረምነው። አንድ ኢትዮያዊ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰላም የኖቤል ሽልማት ሲያገኝ ደስ ይለናል፤ የመከፋት ስሜት አይሰማንም። ለእውነት ስንናገር ግን ይህ ሰው ሽልማቱ ይገባዋል? የኖቤል ሽልማት ማግኘቱ ስልጣን ላይ ለመቆየት ያለውን ፍላጎት ያጠናክረዋል እንጂ አይቀንሰውም። ዛሬ በአገራችን ውስጥ ሰላም የለም። ከኤርትራ ጋር ያለውም አለመግባባት ህጋዊ ይዘት ባለው ስምምነት አልተቋጨም። ኤርትራም ለጦርነት ያላት ስጋት አልቀነሰም። ድንበሩም እንደተዘጋ ነው። ኢትዮጵያ በትግራይ በኩል ባላት ድንበር ላይ ከባድ የስጋት ድባብ እያንዣበበ መሆኑ ይታወቃል። ሰላም በሁለት ወገኖች መልካም ፈቃድ የሚመጣ እንጂ በአንድ መሪ ግፊት ብቻ ወይም ፈቃድ የሚገኝ አይደለም።
ሰላምና አንድነት ሊያስገኝ የሚችል መፍትሄ ለመፈለግና ወደ ፊት ለመራመድ ቢያንስ፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ እውነታ ላይ መስማማት አለበት። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መምራት አልቻለም። ጃዋርን፣ ኦነግን፣ ኦዴፓን፣ አዴፓን አለማውገዝ ከእውነታ መሸሽ ነው። መፍራት ነው። ዋናው የኢትዮጵያ ችግር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው።
የዛሬ አስር ወር አዲስ አበባ ላይ ባደረግሁት ንግግር፣ «ጠቅላይሚኒስትር አቢይ የኦሮሞ ድርጅት መሪም – የኢትዮጵያም መሪ ሊሆን አይችልም። አንዱን መምረጥ አለበት:: የኦሮሞም – የኢትዮጵያምመሪ ሊሆን አይገባም!» ብዬ ነበር። ደግሜም፣ «ዛሬ የህዝብ ድጋፍ ባለው ወቅት ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ይዞ ደፋር የሽግግር እርምጃዎችን ቢወስድ፣ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያስጠብቅ ስላማዊ ሽግግር ሊያስገኝ ይችላል።» ብዬ ነበር። አለበለዚያ ይህች አገር ሌላ ሩዋንዳ «ትሆናለች።» ብዬ፣ እኔን ጨምሮ ሌሎችም ይህንን ሃሳብ አጋርተን ነበር። ዛሬ ወደዚያ እያዘገምን ነው። ሁሉም በእንደዚህ ያለ ለውጥ አይስማማም። ምክንያቱም የተለየ አጀንዳ ያላቸው ይህንን ለውጥ አይፈቅዱም። ይህ ተፈርቶ ግን አገር አይፈርስም። መስዋዕትነቱ አነስተኛ ሆኖ ኢትዮጵያን ማዳን ይቻል ነበር።
Full Website