wakwoya2016@gmail.com

ወቅታዊ ችግሮ ችን

ቁጥር አንድ

ባይሳ  ዋቅ - ወያ 11-29-19

******

ዓመታት የውጪ አገር ኑሮ በኋላ ወዳገሬ ከተመለስኩ ዓመት ሊሆነኝ ነው። ከኢትዮጵያ የወጣሁት “ዓዋቂ” የሚባል የዕድሜ ደረጃ ሳልደርስ ስለነበር ካገር የወጣሁት የኢትዮጵያን ሕዝብ የኑሮ ዘይቤ፣ ባሕላዊ እሴቶችና ሌላ ሌላም የሕዝቡ መገለጫ የሆኑትን ቅርሶች በውል ሳላውቅ ነበርና ተመልሼ የማሕበረሰቡ አካል ለመሆን መጀመርያ ላይ ትንሽ አዳግቶኝ ነበር። ዛሬ ግን ከሞላ ጎደል ተለማምጃለሁ ማለት ይቻላል። ማታ ማታ እግራችንን እናፍታታ ብለን ከጓደኛዬ ጋር የመንገዱን ጥግ ይዘን ስንኳትን፣ ከግራና ከቀኝ በሚፈስሰው ከሞላ ጎደል ወጣት በሆነው “የሰው ጎርፍ” ካንዱ ዳር ወደ ሌላኛው መላተሙንም ተለማምጄአለሁ። መልመድ ያቃተኝ ትልቁ ነገር ግን አዲስ አበባ ያኔ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ዘመን የነበራት ሕዝብ ቁጥር ባንድ ትውልድ ዘመን ይህን ያህል ተበራከቶ ማየቱን ነው። አዎ! ያገሪቷ ሕዝብ ቁጥር ማመን ከሚያቅተን በላይ ጨምሯል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ሃምሳ ሚሊዮን የማይሞላ ሕዝብ የነበራት አገር ዛሬ የመቶ ሃያ ሚሊዮን ሕዝብ ባለቤት ሆና ከአፍሪካ አሕጉር ሁለተኛውን ደረጃ ይዛለች። ይህ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ካስከተላቸው በርካታ ወቅታዊ ችግሮች ጥቂቶቹን ለመዘርዘር ያህል፣

ከላይ ባንድ ስንኝ ጠቅሼ ያለፍኩት “የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር መጨመር” (population growth) አመላካች የሆነውን “የሕዝብ ጎርፍ” በሚል ሁለት ቃላት ሥር ለማጠቃለል የሞከርኩት ሥራ አጥቶ በየሜዳው የተኮለኮለውና ቢያንስ ቢያንስ የሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብሎም የዩኒቬርሲቲ ትምህርቱን ጨርሶ ምርታዊ ሊሆን ያልቻለውን ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጋ የወጣቱን ትውልድ ነበር። የዚህ የሥራ አጡ ትውልድ ክምችት በተለምዶ እንደሚታወቀው በዋና ዋና ከተሞች ብቻ ሳይሆን በየየዞኑ፣ በየወረዳውና በቀበሌ ደረጃ መሆኑን ራሴ በተዘዋወርኩባቸው የኢትዮጵያ ገጠሮች አስተውያለሁ። በተቻለኝ መጠን በየቦታው ተሰብስበው የማገኛቸውን ሥራ አጦች ጊዜ ወስጄ በሥነ ሥርዓት አነጋግሬአለሁ። ብዙዎቹ ለነሱ የማሳየውን መቆርቆር ሲያመሰግኑ ያን ያህል ደግሞ “እዚህ ችግር ውስጥ የከተተን የናንተ ትውልድ ነው? ብለው በቁጭት ያነጋገሩኝም ነበሩ። ግምታቸው ትክክል ወይም ስህተት ነው ብዬ ሳልገመግማቸው ወይም ሙግት ሳልገጥም፣ ረጋ ብዬ ያለፈውን ሕይወታቸውን፣ አሁን ያሉበትንና ለወደፊት ምን እንደሚያስቡ ለማጥናት ሞክሬያለሁ። በዚያም መሠረት የችግሩን መንስዔ፣ ግዙፍነት፣ ባገሪቷ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን አደጋና መንግሥት በአስቸኳይ መውሰድ ያለበትን እርምጃ የሚያሳይ ረቂቅ ፕሮጄክት አዘጋጅቼ “ገዢ ፍለጋ” ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ብዬ የማስባቸውን የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ደጅ እያንኳኳሁ ነው። ለጊዜው “ገዢ” ባላገኝም፣ ማንኳኳቴን ግን ቀጥዬበታለሁ። ይህ በኔ ግምት፣ የችግሮች ሁሉ ችግር የሆነው የስምንት ሚሊዮን የተማረው ወጣት ሥራ ማጣት ጉዳይ ከኤንጂኔር ታከለ ኡማ ጥቃቂን የአዲስ አበባ ከተማ የመንግሥት ፕሮጄክት ባሻገር፣ ያገራችን የፖሊቲካ ድርጅቶች ለጉዳዩ ቅድሚያ ሰጥተው የፖሊቲካ ቅስቀሳ አጄንዳችቸው ውስጥ አለማካተታቸው ግን የባሰ አሳስቦኛል።

የችግሩ መንስዔ

ሥራ አጥነት በሁሉም አገር ያለ ማሕበራዊ ክስተት ነው። አደጉ በተባሉት አገራት እንኳ ሥራ አጥነት አለ። ልዩነቱ ግን ባደጉት አገራት አንድ ዜጋ ተምሮ ሥራ ቢያጣ ወይም ይሠራ ከነበረበት መሥርያ ቤት ተሰናብቶ ወይም ራሱን አሰናብቶ ሥራ አጥ ቢሆንም፣ መንግሥት ያዘጋጀው “የደህንነት መረብ” ስላለ፣ ሥራ አጡም ሆነ ቤተሰቡ ለችግር አይዳረግም። ሌላ ሥራ እስኪገኝለት ድረስ መንግሥት አስፈላጊውን እንክብካቤ ያደርጋል ማለት ነው። እንግዲህ ልዩነታችን ሥራ በማጣት ላይ ሳይሆን፣ አንድ ዜጋ ሥራ አጥ ሲሆን መንግሥት የሚያደርግለት እንክብካቤ ላይ ነው።

ላገራችን ስምንት ሚሊዮን ወጣት ሥራ ማጣት መንስዔ ናቸው ብዬ የገመገምኩት የሚከተሉት ናቸው።

በኔ ግምት ትልቁ ያገራችን ችግር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በማይገኝለት መልኩ እየጨመረ የሄደው የሕዝባችን ቁጥር ጉዳይ ነው። የሕዝብ ቁጥር መጨመር ብቻ ሳይሆን፣ ከሌላው ዓለም በተለየ መልኩ፣ የወጣቱ ቁጥር መጨመሩ ነው። በመንግሥት ዘገባ መሠረት ወደ 75% የሚጠጋው ያገራችን ሕዝብ ዕድሜው ከሰላሳ ዓመት በታች ነው። ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጋው ሥራ አጥ ወጣቱ ትውልድ የዚህ የ 75% አካል ነው ማለት ነው። በመሠረቱ የአንድ አገር “የሠራተኛ ጉልበት” መብዛት ተፈጥሮ በነጻ የሚለግሰው ውድ ሃብት ነው። መንግሥት ግን ይህንን ተፈጥሮያዊ ኃብት ባግባቡ ለመጠቀም ከሠራተኛው ጉልበት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ብሄራዊ ፖሊሲ አቅዶ ሥራ ላይ ካላዋለ በስተቀር፣ ይህ በነጻ የተገኘው “የሠራተኛ ጉልበት” አገራዊ ሃብት መሆኑ ቀርቶ አገራዊ ጥፋት ሊያስከትል የሚችል ኃይል ሊሆን ይችላል። ለዚህም ነው “የሠራተኛ ጉልበት” እንደ ኒዩክሌር ኃይል ነው የሚባለው፣ በደንብ ከተጠቀሙበት የኃይል ማመንጫ ሆኖ ያገሪቷን ኤኮኖሚ አሳድጎ የዜጎችን ኑሮ ያሻሽላል። አለበለዚያ ደግሞ ቦምብ ሆኖ ዜጎችን ሊጨርስ ይችላል። ሌላው ለወጣቶቻችን ሥራ አጥነት ቁጥር መጨመር ከባድ አስተዋጽዖ አድርጓል ብዬ የማስበው ከዚሁ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያያዥ የሆነው፣ ያገሪቷ የኤኮኖሚ ዕድገትና የትምህርት ፖሊሲው አለመጣጣም ነው። ያደጉ አገራት ለአገራቸው የሚያስፈልጋቸው በተለያየ የቴክኒክ ሙያ የሠለጠኑ ወጣቶችን እንጂ ከፍተኛ የዩኒቬርሲቲ ድግሪ የተቀዳጀ አለመሆኑን ስላመኑበት አብዛኛውን ወጣት ትውልድ ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ወደ ሙያ ትምህርት ቤት
Full Website