ህዳሴ ኢትዮጵያ

ሓምለ 5፣ 2011 ዓ.ም.

መግብያ

የህወሓት መግለጫ እና የብአዴን/አዴፓ የመልስ ምት መግለጫ ሳነብ ድሮ በትጥቅ ትግል ጊዜ በወያኔ እና በደርግ ይደረግ የነበረ የቶክስ ልውውጥ ስልቶች እንዳስታውስ አደረገኝ እና መግለጫዎቹ በመገምገም ሀሳቤን ለአንባቢያን ለማካፈል ይህን ፅሁፍ ማቅረብ ወሰንኩኝ፡፡ ፅሁፉ ሳቀርብ የህወሓት መግለጫ ከራሱ ህወሓት/ወያኔ ከደርግ ጋር ያደርገው የነበረ የቶክስ ስልት ሳመሳስለው የአዴፓ/ብአዴን መግለጫ ደግሞ ደርግ ከወያኔ ጋር ያደርገው የነበረ የቶክስ ስልት ጋር በማመሳሰል ነው፡፡

በወያኔ እና በደርግ ይደረግ የነበረ የቶክስ ልውውጥ ስልቶች እና የአሁኑ የሁለቱ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች መግለጫ መመሳሰል

በትጥቅ ትግል ጊዜ ደርግ እና ወያኔ በሰው ሀይል ብዛት፣ በመሳርያ ጋጋታ፣ በዘመናዊ ትጥቅና ስንቅ ፈፅሞ የሚወዳደሩ አልነበሩም፡፡ በዛን ጊዜ የደርግ/ኢሰፓ አባላት ለወያኔ ምን ይሉ ነበር መሰላቹ "ሬጣጥስ ያ ዳዕሮ ይንቕንቕ" ትርጉሙ በጣም ቀጫጫ ምንም ጉልበት የሌለው ሰው በጣም ትልቅ ዋርካ ያንቀሳቅሳል በሚል ይቀልዱበት ነበር፡፡ ወያኔ በረሀላይ እንደ አይጥ እየተሽሎከለከ ህዝብን የሚያስቸግር አውሬ በመሳሪያ ሳይሆን በገመድ አስረን እናመጣታለን በማለት ፉከራ እና ቀረርቶ ያስነሳና ወደ ጦርነት ሂዶ ሲመለስ ግን የያዘው መሳሪያና ገመድ ጥሎ ጓዶቹ ሳይቀብር ፈርጥጦ ነበር የሚመለሰው፡፡  ወያኔና ደርግ አንድ ጦርነት ላይ ሲገጥሙ፣ ወያኔ ከ12 ሰው የማይበልጥ አንድ ቡድን በቆረጣና ሌሎች ስልቶች ከሻለቃ እስከ ብርጌድ ይደመስስ ነበር፡፡ በፍልሚያው ጊዜ በወያኔ ወገን አንድ ሰው አንድ ጥይት ሲተኩስ በደርግ ሰራዊት በኩል ደግሞ በፍልሚያው ያለ ሰራዊት በሙሉ ከነከባድ መሳሪያው ወደ ተተኮሰበት አቅጣጫ በሞጅሙዕ ወይም አውቶማቲክ ለበርካታ ደቂቃዎች ያለ እረፍት ያርከፈክፉታል፤ እንደገና የወያኔ አንድ ታጣቂ በሌላ አቅጣጫ እየዞረ አንድ ሌላ ጥይት ሲተኩስ ደርግ አፈሙዙን አዙሮ በተመሳሳይ ለበርካታ ደቂቃዎፍ ያርከፈክፋል፡፡ ወያኔ አንድ ሁለት ሆኖው አውቶማቲክ ካካ ካካ ቡው ቡው ሲያደርጉ ደርግ-ሞኙ ሁሉም የወያኔ ሰራዊቱ እዛ ያሉ መስሎት ሙሉቀን ሲደበድብ ነበር የሚውለው፡፡ በመጨረሻም ወያኔ በቆረጣ ስልቱ ቆራርጦ ነበር የሚጥላቸው፡፡ ይህ ስልት ለደርጎች ብቻ ሳይሆን ለኢህአፓ፣ የሰራ ስልት ነበር፡፡

ታድያ ይህ ከአዴፓ መግለጫ ምን ያያይዘዋል ትሉ ይሆናል?

የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ በወቅታዊ የአገራችን ሁኔታ በመገምገም ባወጣው መግለጫ መሰረት "አዴፓ/ብአዴን ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሚያደርገው ያለ ሴራ አቁሞ፣ የአመራሮች ግድያ ፈፃሚዎች እና እቅድ ነዳፊዎች በማጋለጥ ወደ ህግ ማቅረብ አለበት" የሚል ታርጌቱን በትክክል ያነጣጠረ ትክክለኛውን ዒላማ የመታ አንድ ጥይት በመተኮሱ ምክንያት፤ ትላንት የአዴፓ/ብአዴን ስራ አስፈፃሚ አንድ ጥይት ወደ ተተኮሰበት አቅጣጫ በመጅሙዕ ወይም በአውቶማቲክ ልክ እንደ ደርግ አስቀድሞ ያዘጋጀውን ጥይቶች ዘከዘከው፡፡ የጥይቱ አተኳኮስም ታርጌት ለይቶ አነጣጥሮ ሳይሆን የጥይት ድምፅ ሰምቶ የተደረገ ተኩስ እና ታርጌት ያልመታ ወይም ለተተኮሰበት ጥይት መከላከል ያልቻለ የቀቢፀ ተስፋ ቶክስ ሆኖ ስላገኘሁት ነው ከደርግ ጋር ያመሳሰልኩት፡፡

የህወሓት መግለጫ ጥርት ያለ እና ታርጌቱም የለየ ነበር፡፡ የህወሓት መግለጫ ያተኮረድ በአሁኑ ወቅት በፌደራላዊ ስርዓት ላይ በተደረገው የመፈንቅለ መንግስት እና የከፍተኛ አመራር ግድያ እንዲሁም በዚህ አጀንዳ ዙርያ የአዴፓ/ብአዴን ከፍተኛ አመራር ስለ ጉዳዩ /ሰኔ 15፣ 2011 ዓ.ም./ አስመልክተው በተናጠል የሰጡት መግለጫዎች በማትኮር ሲሆን እሱም ፡-

"ሁሉም የአዴፓ አመራር ከብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ የተለየ ዓላማ አልነበረውም፣ ሁላችን አንድ ነበርን ሌላ ስውር ወይም ድብቅ ዓላማ የለም"

የሚል ነበር፡፡ በህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ መግለጫ መሰረት ይህ የአዴፓ አመራር አባባል ችግሮችን በማድበስበስ ለማለፍ የሚደረግ ሙከራ ትክክል አይደለም፤ ወንጀልና ወንጀለኞችን ለመደበቅ የሚደረግ ሴራ ነው፡፡ በአዴፓ አመራር ውስጡ ከብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ ጋር አብሮ ያቀደ፣ ሴራ የሸረበ አመራር አለ፡፡ ስለዚ ከመፈንቅለ መንግስቱ እና ከግድያው በስተጀርባ ያሉትን ወንጀለኞች አዴፓ በጥልቀት ገምግሞ በማውጣት ለህግ ማቅረብ አለበት፤ መፈንቅለ መንግስቱም በአማራ ክልል ብቻ የታጠረ ሳይሆን በአጠቃላይ በፌደራል ስርዓታችን የተቃጣ እና በአዴፓ የማእከላይ ኮሚቴ አባላት ባሉበት ደረጃ የተደረገ ሴራ በመሆኑ ለመላው የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ይቅርታ መጠየቅ አለበት የሚል መግለጫ ነበር ያወጣው፡፡ የህወሓት መግለጫ ያነጣጠረው በሰኔ 15ቱ በተከሰተው አደገኛ አስነዋሪ ድርጊት የተሳተፉ የአመራር ኣባላት ላይ ያነጣጠረ እንጂ ድርጅቱ ካሁን በፊት የፈፀማቸውን ችግሮች ወይም ውንጀላዎች የያዘ አልነበረም፡፡

የአዴፓ/ብአዴን መግለጫ ግን ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ እንደሚባለው ነበር፡፡ በወቅታዊ ሁኔታ ገመገምናል ብሎ ስለ ወቅታዊ ሁኔታ ምንም ነገር ሳይል ህወሓት ከ1968 ዓ.ም የአማራ ጠላት እንደነበር እንዲሁም ባለፉት 27 ዓመታት የተፈፀሙ ችግሮች ብቸኛ ተጠያቂ እንደሆነ፣ ህወሓት ወንጀለኞች ደብቆ የያዘ እንደሆነ የሚገልፅ ነበር፡፡ በይቅርታ እና በፍቅር ተደምሬአለሁ ያለ የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ስለ ወቅታዊ ጉዳይ ግምገማ ተቀምጦ ድርጅቱ አዴፓ/ብአዴን ሳይፈጠር ህወሓት ፈፀመው የተባለ ውንጀላ በዛሬ መግለጫው ሲቀርብ ለትዝብት የጣለው እና እውነት ይህ መግለጫ የአዴፓ/ብአዴን ነውን? የሚል ጥያቄ የሚያነሳ ሆኖዋል፡፡ እንደ ግለሰብ እንደዚህ ዓይነት ዘርዘር ያለ መግለጫ ለማውጣት ሀሳብህን አደራጅተህ ሁሉም እንዲረዳው እና መልእክቱ በደንብ እንዲተላለፍ የጥቂት ሰዓታት ድካም ያስፈልጋል፡፡ እንደ ድርጅት ግን በዝርዝር ለመገምገም እና መግባባት ላይ ለመድረስ ጥቂት ቀናት ማስፈለጉ የግድ ነው፡፡ ታድያ የአዴፓ/ብአዴን ስራ አስፈፃሚ እንዴት በጥቂት ሰዓታት ይህን መግለጫ ማውጣት ቻለ? መልሱ የታወቀ ነው ይህ የ40 ዓመታት ቂም አስቀድሞ የተዘጋጀ ወይም ወይም በሌላ አባባል ጥይቱ ጎርሶ ቃታው መሳብ ብቻ እየተጠባበቀ የነበረ በመሆኑ ልክ እንደ ደርግ ወታደር አንድ የወያኔ ጥይት በመተኮሱ ዓይኑን ጨፍኖ ተኩስ ወደተሰማበት አቅጣጫ የተተኮሰ እና ጥይቱም አዲስ የማይታወቅ ሳይሆን ድሮ ኢህአፓ ይጠቀመው የነበረ ጥይት ወይም መግለጫ ነበር፡፡ ይህን መግለጫ ስገነዘብ እንደ ፖለቲከኛ፣ የአዴፓ ስራ አስፈፃሚ ሁሌም ራሱን ችሎ መቆይ እንደማይችል ተደርጎ ነው እንዴ የተፈጠረው የሚል ጥያቄ የሚያስጭር መግለጫ ሆነብኝ፡፡

መግለጫው አክሎ መቼ ጥናት እንዳደረገ ወይም መቼ የህዝብ ድምፅ እንደተደረገ ባይገልፅም ህወሓት በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ እንደተጠላ፣ የትግራይ ህዝብም በህወሓት እየተሰቃየ እንደሆነ በመግለጫው አትቶ፣ ስራ አስፈፃሚው ህወሓት ለጠየቀው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ሳይሰጥ የስራ አስፈፃሚው መግለጫው ትህነግ/ህወሓት በማለት ጀምሮ ትህነግ/ህወሓት በማለት ጨረሰ፡፡ በአጠቃላይ የአዴፓ ስራአስፈፃሚ መግለጫ የሚያመላክተው በሰኔ 15፣ 2011 ዓ.ም. በፌደራላዊ ስርዓታችን ላይ የተቃጣው መፈንቅለ መንግስት እና የከፍተኛ አመራር ግድያ በቅማንት፣ በከምሴ፣ እንዲሁም በመተከል/ፓዌ አከባቢዎች የተደረገውን ዘር የማጥፋት እንቅስቃሴ ተደማምሮ ከዚህ ሁሉ ትራጄዲያዊ ተግባራት ጀርባ ማን እንዳለ ማን ስምሪት እንደሰጠ፣ የክልሉ ልዩ ሀይል ስልጠና አሰጣጥ ጀምሮ እስከ ግድያው መፈፀም የነበሩ፣ የተሳተፉ ወንጀለኞች እንዳይጋለጡ ከለላ የሰጠ እና አጀንዳ ለማስቀየስ በማሰብ በህወሓት ላይ ዘመቻ መክፈቱ ያበሰረ አሳፋሪ መግለጫ ነበር፡፡

የአዴፓ/ብአዴን ስራ አስፈፃሚ መግለጫ ሳነብ ወደ አእምሮዬ የመጣብኝ ነገር ቢኖር የአዴፓ/ብአዴን ስራ አስፈፃሚ ብቃት እና ዓቅም መመዘን ነበር እና በአንድ በኩል ኢህአዴግ እነዚህ ብቃት የሌላቸው ከተላላኪነት ውጭ ምንም አበርክቶ ያልነበራቸው ከፍተኛ አመራሮች ይዞ 27 ዓመት ሙሉ መዝለቁ ሳደንቅ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኢህአዴግ እውነትም የእጁ ነው ያገኘው፤ እነዚህ አሽከሮች 27 ዓመት ሙሉ ተሸክሞ በመጓዙ እነሆ ኢህአዴግ በመበስበስ አደጋ ተውጦ የሚያድነው ብቁ ስትራቴጂስት አመራር አጥቶ ነብስ ጊቢ ነብስ ውጪ ላይ ይገኛል አልኩኝ፡፡

አሁንም እነዚህ አመራር የሚመሩት ድርጅት አማራ ክልል እርስ በርሱ ሊያፋጁት እንጂ አንድም የሚረባ ነገር እንደማይሰሩ ይታወቃል፡፡ ዕድሚያቸው ሙሉ ነፃ ሆኖው ሲሰሩ ያልነበሩ፣ ራሳቸው እንደተናገሩት ከተላላኪነት ሌላ የማያውቁ አመራሮች እንዴት በስተርጅና ነፃ ሁነው ህዝብን ያገለግላሉ ተብሎ ይታሰባል? የአማራ ህዝብ ራሱ ይመልሰው እና በሚቀጥለው ምርጫ ድምፅ ይስጥበት፡፡

ከሁሉም በላይ ይሉኝታ ቢስነታቸው የገረመኝ ነገር ባለፉት 27 ዓመታት የተመዘገቡ መልካም ውጤቶች የብሄር ብሄረሰቦች አንድነት እና አብሮነት፣ እንዲሁም ብዙሀነት በማረጋገጥ ላይ አዴፓ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደነበረው ሲያትት ክፉ ክፉውን ግን ህወሓት እንደፈፀመው፤ ህወሓትም ብቸኛ ተጠያቂ እና የማይድን ድርጅት ብሎ ሲገልፅ ማየት እውነትም የአዴፓ ስራ አስፈፃሚ ይሉኝታ ቢሶች እና ታጥበው የማይጠሩ የደርግ ርዝራዦች ለማለት ዳዳኝ፡፡ ምክንያቱም ሁለመናቸው የደርግ አካሄድ መርጠው እየተጓዙ ያሉ ጨለምተኞች ሆኖዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት አካሄድ የሚሄድ ደግሞ የህዝብ አመኔታ የሌላቸው ህዝብን በአግባቡ መምራት ያቃታቸው ፀረ ህዝቦች እና ፀረ ዴሞክራሲ ሀይሎች ናቸው፡፡

በአሁኑ ሰዓት አዴፓ የአማራ ክልል በአግባቡ መምራት አቅቶት፣ የህዝቡን ሰላም እና መረጋጋት ማስጠበቅ አቅቶት የህዝብ አመኔታ ስላጣ የሚይዘው የሚጨብጠው አጥቶ መምራት ያልቻለ ተጠያቂ ድርጅት ነው፡፡ የዚህ ድርጅት ሰበብ ለአማራ ህዝብ፣ ለአጎራባች ህዝቦች እና ለኢትዮጵያ ህልውና ከፍተኛ ስጋት በመሆኑ ሁሉም በትኩረት ሊከታተለው ይገባል፡፡

ብአዴን ለዚህ ስርዓት እውን መሆን ከፍተኛ ትግል ካደረጉ እና ከፍተኛ መስዋእትነት ከከፈሉት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ እንደነበር ምንም የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ የአማራ ጭቁኑ ህዝብ በስሙ ይነግዱ የነበሩ ገዢዎች ምንነት በማጋለጥ ከአማራ ህዝብ ጫንቃ አሽቀንጥሮ የጣለ ብአዴን ነበር፡፡ አማራ ህዝብ አሁን ለደረሰበት እና በማንነቱ ተከብሮ በአገሩ ጉዳይ ወሳኝ እንዲሆን በማድረግ ብአዴን ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ሁሉ ባለፉት 27 ዓመታት በአገራችን የተፈጠሩ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ፀረ ዴሞክራሲ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ችግሮችም ተጠያቂ መሆኑ ሊካድ አይገባም፡፡

Full Website