የሰላም ንፋስ፤ አውሎኛው እንዳያውከው ይታሰር

ሙሉቀን ወልደጊዮርጊስ

12/23/2021

አንዳንዴ የሰው አዋዋል ይርመኛል፤ ባሰበበት ቀርቶ ባላሰበው ስፍራ ራሱን ሲያገኝ፡፡ ለምሳሌም ቦሌን አስቦ ውሎው ሳሪስ ወይንም ጣፎ ሲገኝ ማለት ነው፡፡ “ያልተነገረ እንጂ ያልተደረገ የለም” እንዲሉ የዛሬው የብእሬ አጀንዳ የነበረው ብዙ ያልተባለለት የአጠቃላይ ጦርነቱ አካል የሆነውን በኢኮኖሚ የማድቀቅ ተግባር በተለይም የግሉን ዘርፍ ለመስበር፤ ለማጉበጥ፤ ዳግመኛ ቀና እንዳይል ሲደረጉ የነበሩ ስልታዊ ጥቃቶች ላይ ለመጻፍ ነበር፡፡ ሆኖም ሰሞኑን በሚነፍሰው ነፋስ ተሳብኩና ወደዛው አቀናሁ፡፡ አዎ የሰላም ዝማሬ ነፋስ፡፡ በዚህ ሁሉ ሰዋዊና ንብረታዊ ውድመት መካከል ቆመን ስለ ሰላም መዘመር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑ የማያምን ከቶ ማን ሊሆን ይችላል? በዚህ ባሳለፍነው አመት ውስጥ በተላለፉት ዜናዎች ጀሮአችን የሰለቸው ነገር ቢኖር “በዚህ አከባቢ ይህ ተፈጸመ” “በዚያ አከባቢ ይህ ተደረገ” የሚለውን ወሬ እየሰማን በቅዠት አለም ላይ ቆመን “ነገ ምን ይፈጠር ይሆን” እያልን ማለቂያ ለሌለው መጨነቅ ላይ ከርመናል፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ ባለፈው አንድ አመት ብቻ በአገሪቱና በህዝቦችዋ ላይ የተፈራረቀው የ“ደስታና ሃዘን” መለኪያ መስፈርት ተበጅቶለት ቢለካ ሀገራችን በ “ሃዘን” መለኪያው ከአለም ውስጥ በቀዳሚ ተርታ የምትገኝ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በነገራችን ላይ ደስተኛ የሆነ ማህበረሰብ መፍጠር ለዘላቂ ልማትና ሰላም አስተዋጽኦ አለው ብለው ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ሀገሮች ለኛ ብርቅ የሆነውን የ “ደስታ” (Happiness) መለኪያ እንደ አንድ መሳሪያ የሚጠቀሙ መሆናቸውን መግለጽ በሃዘን መለኪያው ክፍታ ላይ ለምትገኘው ሀገር ትምህርት ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ታዲያ ይህ የሰላም ተስፋ ሰጪ ሁኔታ በጭላንጭልም ቢሆን ሲታይ ደስ የማይለው ካለ ራሱን መመርመር ይኖርበታል፡፡ ሳይጠናበት ወደ እእምሮ ህክምና ተቋም ጎራ እንዲል ሁላችንም መምከር ይኖርብናል፡፡ የሰው ልጅ የሁለትዮሽ ገጽታ ያየንበት ዘመን ቢኖር ይህኛውን የሚስተካከል የለም ብንል ትክክል እንደሆን እረዳለሁ፡፡ ቃልና ተግባር ለየቅል ሆነው ያስቸገረበት፣ አገሪቱንም በዘቀጠ የታሪክ ወቅት የምትገኝበት ወቅት እንደሆነም አምናለሁ፡፡ ዘመኑ አፈ ጮሌዎች በቀን ብርሃን ፍቅርና ፍቅር ብቻ የሚሉትን ቃላት እያነበነቡ በውድቅት ሌሊት መሰሪ እቅድ ከመሰሪ አቻዎቻቸው ጋር ሲመክሩና ሲዘክሩ ያየንበት፤ አለሜ የእግዚአብሄር ወንጌልና ወንጌል ብቻ ማስተማር ነው ብለው ሲምሉና ሲገዘቱ የነበሩ ሰዎች የሀጥያት መንገድ የሆነውን የግድያ ወንጌል ሲሰብኩ ጀሮአችንን ባለማመን፣ አፋችንን ከፍተን የሰማንበት፤ ከኔ ወዲያ ላስታራቂነት የሚመጥን ሰው ከቶም በዚች ሀገር የለም ብለው የዘመሩ የማታ ማታ ቢያንስ አንድ ሰው መግደል አያቅተኝም ፉከራቸውና ቀረርቶአቸው ያዳመጥንበት፤ ወደድክም ጠላህም አለም በሰላም አክትቪስትነት የመዘገበኝ እኔ ነኝ ብሎ ሲንከላወስ የነበረ፣ ክላሽ ይዞ አረ ጎራው እያለ ሲንገዋለል በአንክሮ የታዘብንበት ዘመን ነው፡፡ በአጭሩ የሰው ልክነት መስፈርቱ ተደበላለቆብን ኑሮ ከተባለም እስካአሁንዋ ሰአት የዘለቀንበት ዘመን አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ ባገኘሁት አጋጣሚ ዋና ዋና የሚባሉትን የወሬ አስተላላፊ ማእከላትን እከታተላለሁ፡፡ በተለይም ከኢትዮጵያ መንግስትና ከትግራይ የሚሰራጩት፡፡ በዚህ አንድ አመት ውስጥ ብቻ ከተሰራጩት አንኳር ወሬዎች መካከል ስንት ጊዜ ስለሰላም በመስበክ በተጻራሪው ደግሞ ስንት ጊዜ የጥፋትን መልእክት በመርጨት እንደተጠመዱ መነሻ አድርገን ብንመረምር ያለጥርጥር የጥፋቱን መንገድ እንደሚያመዝን ሁላችን የሚያስማማ ሃሳብ ይመስለኛል፡፡ ይህ የጥፋት መልእክት በማስተላለፍ ቀኑን ሙሉ ተጥደው የሚገኙት የመንግስት እና የግል መስለው ነገር ግን መንግስታዊ ጠረን ያላቸው ሜዲያዎች የሚያክል የለም ሊባል እንደሚችል አሁንም ሁላችንም ያስማማናል እላለሁ፡፡ ከመዋእለ ዜናዎቻቸው አንስቶ፤ ሙያዊ ትንተናቸው አካቶ ሌሎችም የመዝናኛ ፕሮግራሞችቻቸው የሚሰበከው ጠብና በቀል የሚጭሩ፤ የተሳሳተ መረጃ የሚግቱ፤ የሚያደነዝዙ ናቸው፡፡ ነጋ ጠባ የሚያቀርቡት ወሬ ለሚቀጥለው ጥፋት ግብአት እንጂ ማስታረቂያ ወይንም አእምሮን ሊያለሰልስ የሚችል ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ታዲያ ህክምና ያስፈልጋል ሲባል እነኚህም አካላት ማካተት ይኖርበታል፡፡ ከሁሉ የሚገርመው የበላይ አካል የተባለው አካል በሚዲያ ግምገማው እንዴት ተበለጥን በማለት ተቋሞቹ ለበለጠ ጥፋት ግብአት እንዲባዝኑ በጀትና የሰው ሃይል መመደቡ ላይ ነው፡፡ የተቋሞቹ ስራ መመዘን ያለበት ምን ያህል ህዝባዊ፤ አውነተኛና ለዘላቂ ሰላም የሚያገለግል ስራ ሰርተዋል? ይህስ እንዴት ይጠናከር? በሚለው ላይ እንጂ በአፍራሽ ላይ ወይም መልሶ ምት በሚመስል ፈሊጥ ጊዜአቸውን ማጥፋትና ሃብት ማባከን መመልከቱ የሚያሳምም ተግባር ነው፡፡ ይህ ተግባር ተቋሞቹ በዲሞክራሲያዊ ግንባታ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ወርቃማ እድል የማቀጨጭ የማእዝን ድንጋይ ማኖር መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡
Full Website