አሁን የቀረው ዐቢይ አህመድ ዓሊ

ሽንፈቱን አምኖ መቀበልና ለድርድር መቀመጥ ነው

ሙሉጌታ ወልደገብርኤል 04-13-21

መንደርደሪያ፥

ኢትዮጵያ የምትባል በንጹሐን ዜጎች ደም የጨቀየች መንግሥት አልባ አገር በአሁን ሰዓት በዓለም መድረክ ላይ የምትታወቀው በሌላ በምንም ሳይሆን፥ አገሪቱ የቅርብና የሩቅ አገራትና መንግስታት (ስፍር ቁጥር ከሌለው ሠራዊቶቻቸው ጋር) በጉዳይዋ ላይ ጣልቃ እንዲገቡ በመፍቀድ፣ በመጋበዝ ብሎም ከፍተኛ ክፍያ በመፈጸምና በመግዛት በሉዓላዊ ግዛትዋ ሥር የነበረውን ህዝብ በማስጨፍጨፍ፣ ሀብቱና ንብረቱን በማውደም፣ እንዲህ ያለ ግፍና በደል በሰው ልጅ ላይ ይፈጸማል ተብሎ የማይታመንና የማይገመት አረመኔዊ ድርጊት በመፈጸም፤ በአጠቃላይ፥ በብሉይ ኪዳን ዘመን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ላለፉት ሺህ ዓመታት ዓለማችን ያላየችው አንድን ዘር ፈጽሞ የማጥፋትና ስመ ዝክሩ የመፋቅ ዘመቻ በመፈጸም ዓለምን ያስደመመች የደም መሬት በመሆን ታውቃለች። ከዚህ የተነሳም ኢትዮጵያ እንደ ማንኛውም አገር የምትታወቅበትና የምትከበረበት ምዕራፍ አብቅቶ አገሪቱ በአሁን ሰዓት ቀልድ ሆናለች። የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ኗሪ የሆነውና “መሪ” ነኝ ብሎ የሚያምን ዐቢይ አህመድ ዓሊም እንደ “መሪ” የሚቀበል አንድም የዓለም ማህበረሰብ ለሽታ ተፈልጎ አይገኝም። የዓለም ማህበረሰብ ዐቢይ አህመድ ዓሊን እጅግ ከመናቁ የተነሳ እንዳበደ ውሻ ተጸይፎታል፤ ፊቱን ማየት ሆነም ድምጹን መስማትም አይሹም።

ሐቁ፥ ያልበሰለ፣ ሐሰተኛ ወሬ ለመንዛት ብቻ የበቃ፣ “መሪ” ነኝ ብሎ የሚያስብና የሚያምን ግለሰብ እንጅ አገርና ህዝብ በአግባቡ ለመምራት የሚያስችል አቅም፣ ብቃትና ትምህርት ያለው ሰው (አመራር የሚሰጥ ሰው) በመተጣቱ ይኸው አገሪቱና የአገሪቱ ህዝቦች በነጋ በጠባ ቁጥር የገዳይ አሻራ በሌለበት ሁኔታ እንደ ቅጠል እየረገፈ ያለውን ዜጋ ሬሳ ለመቁጠር ተገዷል። “ኢትዮጵያዊነት ፈሪሃ እግዚአብሔር ነው!” በሚል ሐሰተኛ ማስክ ለዘመናት የተደበቀ፥ ምቀኛ፣ ምዋርተኛና ነፍሰ ገዳይ ኢትዮጵያዊ ማንነት በድጋሜ ያለ አንዳች ርህራሄ ሰውን የሚክል ፍጥረት ገና አልሞተም በለው ግደለው! እየተባለ እንደ እባብ ሲቀጠቅጡ ከመገለጡ በላይ “የኢትዮጵያ አምላክ!” እየተባለ የሚዜምለትና የሚነገርለት አምላክ እውነትም ዳጎን መሆኑን ጭምር አሳይቶናል። አንድም፥ እግዚአብሔር የሚያውቅና የሚፈራ ሰው አይደለም ሰውን የሚያክል ፍጥረት በአሰቃቂ ሁኔት ቀጥቅቶ ሊገድል ቀርቶ ሰውን በክፉ ዓይን አይመለከትምና። ይህ የምለው፥ ሰው ከወርቅና ከአልማዝ ይልቅ የከበረ መሆኑን ለማስመር ታስቦ እንጅ ምናምንቴ ሰው አለቦታው ከመቀጡ የተነሳ በአገሪቱ ላይ እየደረሰ ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውድቀትና ድቀት በዝርዝር ማተቱን ዘንግቸው አይደለም። ኢትዮጵያ፥ የነበራት ነገር ሁሉ በሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ አጥታ ሞትም ነዳጅም በወረፋ የሚከፋፈልባት፣ ከፊተኛው በደል ይልቅ እጅግ የከፋ ዘረፋና ወንጀል እየተፈጸመባት የምትገኝ የከሰረች አገር ለመሆን በቅታለች። በአጭሩ፥ በቅድሳት መጻህፍት ላይ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ የነበረበት “ዘመነ መሳፍንት” ተብሎ ይታወቅ የነበረውን ህግና መሪ አልባ ማህበረሰብ የአሁኒቱ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ የሚገልጽ ነው።

Videos From Around The World

አሁን የቀረው …

“የሰሜን ዕዝ” ተነካ በሚል ሐሰተኛ ውንጀላ ሽፋን በትግራይ ህዝብ ላይ የተፈጸመው የተቀናጀ ወረራ ዛሬ የዘመቻው አራተኛ ምዕራፉ (phase) ተጠናቆ አምስተኛውንና የመጨረሻውን ምዕራፍ መከሰት በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን። ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ሂደት ትግራይን የመውረር አጀንዳ ኦሪጅናል አካል ሲሆን አራተኛውንና አምስተኛውን ምዕራፍ ግን በወረራው ማግስት አንድ ተብሎ የጥይት ድምጽ ከተሰማ በኋላ ወያነ ትግራይ መሬት ላይ በተጨባጭ ካስመዘገበው ድል የተነሳ ወራሪው ኃይል ተጨማሪ ክፍል እንዲጽፍ ተገድዶ የተጻፈ ምዕራፍ ነው። ምዕራፎቹ ምንድን ናቸው? ተብሎ ለሚነሳው ጥያቄ በግርድፉ የሚከተለውን ይመስላል። ይኸውም፥

ፌዝ 1 . በሐሰተኛ ውንጀላ ትግራይን መውረር፤

ፌዝ 2 . የጦርነቱን መጠናቀቅ (ሐሰተኛ “ድል”) በአፋጣኝ ማወጅ፤

ፌዝ 3. ትርክቱን ለማስቀጠል በቀጣይነት ሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት፤

ፌዝ 4. ለደረሰበት ኪሳራና ሽንፈት ምክንያት መደርደር፤

ፌዝ 5. በመጨረሻ፥ ሽንፈቱን በመቀበል ለድርድር መቀመጥ የሚሉ ናቸው።

1. በሐሰተኛ ውንጀላ ትግራይን መውረር

በሱማሌ፥ “የክልሉ ባለ ስልጣናት ሱማሌን ለመገንጠል እያሴሩ ነው”፤ በአማራ፥ “መፈንቅለ መንግስት ተመኮረብን” የደቡብ ህዝቦች ክልል የመሆን ጥያቄ “አካሄዳችሁ ህገ መንግስታዊ ጥሰት ነው”፤ በአፋር፣ በኦሮሚያ ወለጋ እንዲሁም በጋምቤላና በቤንሻጉል ጉምዝ ልዩ ልዩ የህግ ሽፋኖችን እንደ ምክንያት በመጠቀም ታንክና መትረየስ እያስዘመተ የሚታሰር እያሰረ የሚገደል እየገደለና የሚሾም እየሾመ ያሻውን ፈጽመዋል። “ታዲያ ጊዜው ሲደርስ ልክ እንደ ነብር ኮቴን ሳያሰሙ ከጀርባ ቀብ ማድረግና ህልሙን በአንድ ጀንበር ማምከን መረሳት የለበትም፤ ወይንም ስውር የሆነ ወጥመድ ማዘጋጀት ይበጃል” (እርካንብ እና መንበር ገጽ 37) ብሎ የሚያምን ዐቢይ አህመድ ዓሊ የቀረችው ትግራይ ነበረችና ትግራይን ለመውረርና የትግራይን ህዝብ በኃይል ለማንበርከክ፥ ከኢምሬት፣ ከሱዳን፣ ከሶማሊያና ከኤርትራ መንግስታት ጋር በመምከር፥ የፌዴራል፣ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የሱማሌና የአፋር ስፍር ቁጥር የሌላቸው ምሊሻዎችና ወታደሮች አስከትሎ በትግራይ ላይ ወረራ ፈጽሟል። የፈጸመው ወረራ በውስጥም በውጭም ተቀባይነት እንዲኖረው፣ ምክንያታዊ ለማድረግና ለማስመሰል፣ ብሎም፥ ህዝባዊ ድጋፍ ለማግኘት “የሰሜን ዕዝ ተነካ” የሚል ሐሰተኛ ውንጀላ በመፈብረክና በማስተጋባት የትግራይን ለመውረር ተችሎታል።

በርግጥ፥ ወደ ትግራይ የሚያስገቡ መንገዶች በሁሉም አቅጣጫዎች ክፍት ናቸው። የትግራይ ህዝብም እንግዳ ተቀባይ ህዝብ እንደ መሆኑ መጠን ማንም ይሁን ምን ሁሉም ዘው ብሎ መግባት ይችላል። ታድያ፥ መግቢያ በሮችና መንገዶች የበዙላት ያህል፤ ትግራይ፥ ለጠላት የሚሆን መውጫ በር የላትም። ዘው ብሎ መግባት የተቻለው ወራሪው ኃይል በትግራይ መሬት ላይ ተንሰራፍቶ መቀመጥ ቀርቶበት ቁሞ መሄድን አልተቻለውም። መጀመሪያ ዙሪያውን 360 ዲግሪ መክበብ፣ ቀጥሎ ከተቀረው ዓለም መነጠል፣ በመጨረሻ ሙሉ በሙሉ መደምሰስ! የሚለው የሶቬቶች የቆየ ጀኖሳይዳል ወታደራዊ ስልት ተጠቅመው በቀናትና በሳምንታት ውስጥ ትግራይን አናንበረክካለን፤ የትግራይ ህዝብም ላይነሳ እንሰብረዋለን፤ እንቀብረዋለን! ብሎው የተነሱ የኢሳይያስ፣ የዐቢይ አህመድ ዓሊና የአማራ ልሒቃን ሠራዊት አንጻራዊ ስትራቴጂ ማለትም ጠላት በመረጠው ሰዓትና ቦታ ሳይሆን ይልቁንም በተመረጡ ስፍራዎችና አከባቢዎች ላይ ድንገታዊና መጠነ ሰፊ ጥቃት በመክፈት፣ የጠላት ኃይል መበጣጠስም ማብረክረክና ማሽመድመድ በመቻሉ የወራሪዎቹ ህልምና ምኞት ለማጨናገፍና ለማምከን ተችሎታል። መጽሐፍ፥ “የእስራኤል ልጆች ግን እንሽሽ ከከተማም ወደ መንገድ እንሳባቸው/እናርቃቸው አሉ” እንዲል በአጠቃላይ ውጤት የሚያምነው ወያነ ትግራይ ከተሞቹንና ንጹሐን ዜጎቹን ሰለባ ላለማድረግና ለመታደግ የትግራይ ከተሞች በመላ እየለቀቀ በመውጣት ከጠላት ጋር ለመግጠም በሚያስችለው ስፍራ ላይ እየመሸገ ራሱን ሲይዘጋጅ፥ በተለቀቀው ስፍራ እየገባ መቐለ የደረሰው ዐቢይ አህመድ ዓሊ ይህን አጋጣሚ ወያነ ትግራይ እንደተሸነፈ፣ እሱም “አሸናፊ” እንደሆነ በማስመሰል ሐሰተኛ የድል ዜና ለማሰራጨትና ለማወጅ ተጠቅሞበታል።

በነገራችን ላይ፥ ሰዎች በትግራይ ህዝብ ላይ የተፈጸመውን ግፍና በደል ሲናገሩ በሰሜን ዕዝ ላይ የሆነውን ነገር አስመልክተው ግን ትንፍሽ አይሉም! እያለ ሲያማርር የተሰማው ዐቢይ አህመድ ዓሊ፥ የዓለም ማህበረሰብ የጦርነቱ መንስኤና ዓላማ በተመለከተ “ሰሜን ዕዝ ስለተወጋ ነው” የሚለው ውሃ የማይቋጥር የዐቢይ አህመድ ዓሊ ፕሮፓጋንዳ እውነትነት የሌለው ተራ ውሸት መሆኑን ብቻ ሳይሆን የትግራይን ህዝብ ለመውረር፣ ለምንበረከክና ለመጨፍጨፍ ታስቦ የተፈበረከው “የሰሜን ዕዝ ተጠቃ” የሚለውን ትርክት የሚገዛው አጥቶ ለከፋ ኪሳራ መዳረጉን ሲናገር ተደብቆ ሳይሆን በፓርላማ በይፋ ነው።

2. በአስቸኳይ ሐሰተኛ “ድል” ማወጅ

የዚህ ምዕራፍ ዋና ዓላማ በሐሰተኛ ውንጀላ በትግራይ ህዝብ ላይ የታወጀው ጦርነት እውነትም “የህግ ማስከበር ዘመቻ” ነው ወይም ነበር! ተብሎ እንዲታመን ከነበረው ጽኑ ፍላጎት የሚመነጭ ሲሆን በዋናነት ግን፥ በተለይ ወኔና ቁጭት ጀግነትና እልህ ሁሌም የማይለየው በአሸናፊነት መንፈሱ የአገሪቱ ኩራት የህዝቦችዋ አለኝታ እየተባለ ብዙ የተዘፈነለት የኢትዮጵያ ሠራዊት ጦርነቱ በተጀመረው በመጀመሪያ ጥቂት ቀናት ውስጥ በምዕራብና በደቡብ ግንባሮች ላይ የደረሰበት ከባድ ኪሳራና የተከናነበው ሽንፈት ዐቢይ አህመድ ዓሊን ክፉኛ ስላደናገጠው፤ በሌላ አባባል፥ በኢትዮጵያ በኩል ጦርነቱ ከታሰበውና ከታመነው ውጤት ሌላ ፈጽሞ ያልተጠበቀ አቅጣጫ በመያዙ፣ በተለይ፥ ከተሞችን ለቆ የመውጣት የወያነ ትግራይ ስልታዊ ማፈግፈግ እንደ ትልቅ አጋጣሚ በመጠቀም መቐለ እንደገባ ሳይውል ሳያድር “ጦርነቱ ተጠናቋል!” ለማለት የተጣደፈው በዓለም መድረክ ላይ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ የነበረውን የትግራይ ሁኔታ፥ ከተቻለ ጦርነቱ ምንም ዓይነት ሽፋን እንዳይገኝ ሙሉ በሙሉ ለማክሰምና ቤታዊ ማስመሰል፤ ካልተቻለ ደግሞ በአስቸኳይ የጦርነቱ ማብቃት በማወጅ ትግራይ በተመለከተ ሊዘገብና ሊሰራ የሚችለውን ዜና በመጠኑም ቢሆን እንዲደበዝዝ በማድረግ፣ የዓለምን ማህበረሰብ ማዘናጋትና ጎን ለጎን ደግሞ ያለና የሌለ አቅማቸውን ተጠቅመው (መርዝና አደገኛ ኬሚካሎችን ሳይቀር በመጠቀም) በጨለማ ትግራይን ሙሉ በሙሉ ለማውደም የተሴረ ነው። ይህ ማለት፥ ትልቅ - ትንሽ፣ ህጻን - ሽማግሌ፣ ሴት - ወንድ፣ ካህን - ምእምን ወዘተ ሳይባል ትግራዋይ ደም ያለው ፍጥረት ሁሉ ጉድጓድ ቆፍረው ለመቅበር ያስችለናል ብለው ስላመኑ ጭምር ነው።

3. የተፈበረከው ትርክት ለማስቀጠል በቀጣይነት ሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት

በውሸት ላይ የተመሰረተና የተገነባ ክስ ብቻውን መቆም አይችልምና ሌላ ተጨማሪ ውሸት መፈብረክና ማሰራጨት የተገደደው ዐቢይ አህመድ ዓሊ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ሐሰተኛ ምስክርነት መስጠትና ማሰራጨት ተገዷል። ድርጊቱ ተቋማዊ እንዲሆንም በውስጥም በውጭም የሚገኝ ማንኛውም የኢትዮጵያ ባለስልጣን ትግራይን በተመለከተ እውነታውን በመሸምጠጥ ሐሰተኛ መረጃ እንዲያሰራጭ የሚያስገድድ ጭምር ነው። “እንደ ውሻ ጠላት ላይ በመጮህ ማምለጫን ማመቻቸት ዘላቂ መፍትሄ ባይሆንም ለግዜው ይጠቅማል” (እርካንብ እና መንበር ገጽ 37) ብሎ የሚያምን ዐቢይ አህመድ ዓሊ የሰራዊቱ አለቃ ብርሃኑ ጁንታ፣ መሐመድ ተሰማ፣ ባጫ ደበሌ፣ ሬድማን ሁሴን፣ ዲና ሙፍቲ፣ ደመቀ መኮነን፣ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፥ ሙፈርያት ከማል፣ ዳንኤል በቀለ፣ ሂሩት ዘመነ፣ አብርሃም በላይ፣ ዛጊድ አብርሃ፣ አገኘው ተሻገርና ለወሬና ለሐሜት የተፈጠሩ ጓዶቹ የአማራ ልሒቃን ዳንኤል ክብረት፣ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያን፣ የወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ህብረት፣ ወዘተ፥ ወያነ በወታደራዊ ቋንቋ ተደምስሷል፣ ተቀብረዋል፣ የለም፣ ፈልጋችሁ አታገኙትም፣ የአንዲት ጋንታ ያህል የሰው ኃይል የለውም፣ የተበተነ ዱቄት ነው፣ አሁን የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን ነው፥ ከሚለው ጀምሮ ኤርትራ አልገባችም፣ ውሸት ነው፣ በቀጣይ በምንሰጣቸው አከባቢዎች ታይተዋል፣ ገብተዋል አይወጡም፣ ትግራይን ለቀው ለመውጣት ተስማምቷል፣ እየወጡ ነው፣ ወያነ በአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት መለዮ በማዘጋጀት ላደራጃቸው ታጣቂዎች በማልበስ ኤርትራ እንደወረረች በመግለጽ ህዝብን እያደናገረ ነው! እስከሚለው የለየለት ፕሮፓጋንዳ የሚያጠቃልል ነው።

በነጋ በጠባ ቁጥር ሐሰተኛ ምስክርነት እየሰጠ፣ እየፈበረከና እያሰራጨ ሰፊውን ህዝብ ለጥቂት ወራት ማታለልና ማወናበድ የተቻለው ዐቢይ አህመድ ዓሊ አሁን ግን ቀናቶቹ ያበቁ ይመስላሉ። በመሆኑም፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ለደረ በት ኪሳራና ለተከናነበው ሽንፈት ሊያካክስ የሚችል ውሸት መፈብረክና ማሰራጨት ባለመቻሉ ሳይወድ በግዱ አዲስና አራተኛው ወደ ሆነው ምዕራፍ ለመሸጋገር ተገዳል። ይኸውም፥ መሬት ላይ ያለው ሐቅ ላለፉት አራትና አምስት ወራት ሰበር ዜና እየተባለ ሲነገር እንደከረመ ሳይሆን ሐቁ ኩልል እያለ መውጣትና መሰማት ሲጀምር ሶቪየቶች አፍጋኒስታን ውስጥ ለተከናነቡት ታሪካዊ ውርደትና ሽንፈት የአከባቢው የመልክዓ ምድር አቀማመጥና የአየር ጸባይ ለሽንፈታቸው ምክንያት አድርገው በይፋ ሲገልጹ እንደተሰሙና እንደሚሰሙ እንዲሁ ዐቢይ አህመድ ዓሊና ጀነራሎቹም በተመሳሳይ ተፈጥሮ ማለትም የትግራይ ተፈጥሮአዊ የመልክዓ ምድር አቀማመጥ ሳይቀር ለሽንፈታቸው ተጠያቂ ሲያደርጉ ተደምጧል።

4. ለደረሰበት ኪሳራና ሽንፈት ምክንያት መደርደር

ይህ አራተኛው ምዕራፍ፥ የኢሳይያስ አፈወርቂ፣ የዐቢይ አህመድና ዓሊና የአማራ ልሒቃን ኦሪጅናል ምክርና እቅድ ላይ የነበረ ሳይሆን ወያነ ትግራይ ቀጥል አራተኛ ብለህ ጻፍ! ብሎ ያስጻፏቸው አዲስና ድንገተኛ ምዕራፍ ነው። ወራሪው ኃይል በሐሰት ውንጀላ ትግራይን ሲወር የነበረው ዕቅድ በቀናትና በሳምንታት ውስጥ የትግራይ ህዝብ ዳግም ላይነሳ በመስበርና በመቅበር ቀጥሎም መሬት ላይ የሌለ ሐሰተኛ ድል በአስቸኳይ በማወጅ በጨለማ ትግራይን ሙሉ በሙሉ አውድሞና አብርሶ ሊገነባት ያሰባትን ምንሊካዊት ኢትዮጵያ ፈጥሮ ቀደም ሲል የፈጠረው ሐሰተኛ ትርክት የሚያቀጥል ሐሰተኛ ምስክርነቶች እያስኮመኮመ ተመቻችቶና ተደላድሎ ለመኖር ነበር ሃሳቡ። የትግራይ ህዝብ ግን በወራሪ ኃይሎች ተንኮልና ሴራ ሳይፈታ ወገባቸውን መፍታት ስለተቻለው ከዚህ የተነሳም ወራሪው ኃይል የደረሰበት ኪሳራ ዝም የሚያስብልና ሰላም የሚሰጥ ስላይደለ ዐቢይ አህመድ ዓሊ አፉን ከፍቶ የሚከተለውን በአደባባይ ይናገር ዘንድ አስገድዶታል። ይኸውም፥ “የመጀመሪያው ኦፕሬሽን ገፋ ቢል ሦስት ሳምንት ነው የፈጀብን፤ ዩኒፎርም አለው ቦታው ይታወቃል በሁሉም ዓይነት ተኩሶች ይፋለማል። በሦስት ወር ያስወገድነው ኃይል ወደ ሽምቅና አርሶ አደር ተመሳስሎ ከቦታ ቦታ መሽሎክለክ ሲጀምር ግን ሦስት ወር ልናጠፋው አልቻልንም። የሚታይ ጠላት ማጥፋትና ተድብቆ የሚመሳሰል ጠላትን ማጥፋት አንድ አይደሉም አስቸጋሪና አታካች ናቸው” እንዲል። ልብ ይበሉ፥ ከዚህ ቀደም “ውጊያ ጀምረህ ስታበቃ ፊት በጥፊ አይመታም ምናምን አትልም፤ እሱ በቦክስ ውድድር ውስጥ ያለ ህግ ነው ፋወል የሚባለው” ሲል የተደመጠው ራሱ ዐቢይ አህመድ ዓሊ መሆኑ ማስታወሱ አስፈላጊ ነው። “ወንድ ነኝ” ብሎ የሚያምነው ዐቢይ አህመድ ዓሊ በቁጥር አነስተኛ ተብሎ የሚታመነው ህዝብ ለመውጋት የሌሎች አገራትና መንግስታት ትክሻ ላይ ተፈናጥጦ መምጣቱን ሳይዘነጋ ነው።

በተረፈ፥ የአማርኛ ቋንቋ ችግር ያለበት ሰው ካልሆነ በስተቀር ቀደም ሲል የተመለከትነው የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ አይነቱ የዐቢይ አህመድ ዓሊ ንግግር ትርጉም ያስፈልገዋል የሚል እምነት የለኝም። የዚህ ንግግር መልዕክትና ዓላማ አንድና አንድ ነው። ተሸንፈናል፤ የተሸነፍነው ግን እኛ አዲስ የመከላከያ መልዮ ለብሰን ታንክና መትረየስ፣ ድሮንና ተዋጊ ጀቶች ይዘን ከተማ ላይ ስንጠብቃቸው እነሱ ግን ቁምጣ ለብሰው ድንጋይና ዱላ ይዘው አንዳንዴም ክላሽ ይዘው መንገድ ላይ አድፍጠው እየጠበቁ ስለመቱንና ስለጨረሱን ነው፤ ነው እያን ያለው። ይህ ማለት ታድያ የሃይል ሚዛኑ ሙሉ በሙሉ ወያነ ትግራይ እጅ ላይ መውደቁን ብቻ ሳይሆን እነሱ ጀምረውታል እኛ ደግሞ እንጨርሰዋለን! ብሎ በገፍ የዘመተው የትግራዋይ ወጣት የሜዳው ባለቤት መሆኑን በተጨባጭ የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም፥ “የሰሜን ዕዝ ተወጋ” በሚል ፈሊጥ በትግራይ ህዝብ ላይ የተከፈተው ጦርነት ግቡ እንዳልመታና እንደከሸፈ የሚያሳይ ንግግር ነው። ለጥቆም፥ ይህ የዐቢይ አህመድ ዓሊ ንግግር ሽንፈቱን የሚያሳይ ንግግር ከመሆኑ ባሻገር ቀጥሎ ሊመጣ ያለውን ምዕራፍ ምንነት ፍንጭ የሚሰጥ ጭምር ነው። ይኸውም፥ ሽንፈቱን አምኖና በጸጋ ተቀብሎ ለድርድር መቀመጥ ይሆናል።

5. ሽንፈቱን ተቀብሎ ለድርድር መቀመጥ

“ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል” ይሉሃል ይህ ነው። “የሰሜን ዕዝ ተጠቃ ሳይሆን ተዋረደ ነው የሚባለው” ተብሎ የተከፈተው የጦርነት ዘመቻና የተሰማው ፉከራ መጨረሻው እሺ በቃ እደራደራለሁ! በሚል ይቋጫል፤ ነፋስ “ከዱቄት” ጋር ይቀመጣል ብሎ መገመት የሚከብድ ነው። ተወደደም ተጠላም ግን ዐቢይ አህመድ ዓሊ መትረፍ ካለበት፣ የሚተርፍ ከሆነ ሊተርፍ የሚችለው ‘ኢጎውን’ ወደ ጎን በመተው ይህን መራራ እውነት ሳያላምጥ ለመጎንጨት የቻለ እንደሆነ ብቻ ነው።  በርግጥ፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ በትግራይ ላይ የፈጸመው ወረራን ተከትሎ በአገር ውስጥና በዓለም ማህበረሰብ ፊት እየገጠመው ያለ መጠነ ሰፊ ኪሳራ ሽንፈትና፥ በተለይ በምዕራቡ ዓለም ማህበ ሰብ ዘንድ ተቀባይነቱን ፈጽሞ ማጣቱን ክፉኛ እንዳስጨነቀው፤ ጉዳዩም በሰላም እልባት የሚያገኝበት ሁኔታ ለመፍጠር ከህወሐት መሪዎች ጋር ለመደራደር በጓዳ ሹክ ያላቸው ና እያመነታ ለመሆኑም ታውቋል። ዳሩ ግን፥ ባለሞያዎቹ ‘የTplf ሰራዊት’ የሚሉት ወያነ ትግራይ ላሽ ስላደረገውና ስላጥመለመለው ሳይሆን በአሜሪካና በአውሮፓ አገራት ከፍተኛ ግፊትና አስገዳጅነት ለድርድር ለመቀመጥ መገደዱን የሚያሳብቅ ምስል እንዲፈጠርለት ይፈልጋል በማለት ዐቢይ አህመድ ዓሊ ከህወሓት መሪዎች ጋር ለመደራደር ፍንጭ ማሳየቱን፤ ቀስ በቀስ እያኮበኮበ ለመሆኑም የሚገልጹ ማስታወሻዎች መተላለፍና መቀባበል ጀምሯል። ይህ የዐቢይ አህመድ ይህ ፍላጎት በሰበር ሳይሆን በሎህሳስ እንዲሆንለት ይፈልጋል ሲሉም ያክሉበታል። ያም ሆነ ይህ ግን፥ አሁን የቀረው ዐቢይ አህመድ ዓሊ የከፋ ኪሳራ ሳያስተናግድ ሽንፈቱን አምኖ መቀበልና ለድርድር መቀመጥ መሆኑን ታምኖበታል ነው። ዐቢይ አህመድ ዓሊ ለድርድር የሚቀመጠው ሰውየው በባህሪው ሰላም ወዳድ ስለሆነና በድንገት ሰላም የማውረድ ፍላጎት ስላደረበትም ሳይሆን ያሰበውን ለማከናወን ሳይችል በመቅረቱና በቀኑ መጨረሻም ለድርድር ከመቀመጥ ውጭ ሌላ አማራጭ ስለሌለው ነው። ታድያ፥ ለድርድር እቀመጣለሁ የሚለው ዐቢይ አህመድ ዓሊ ከተቀመጠም ለድርድር የሚቀመጠው ወዶ ሳይሆን ተገዶ ስለሚሆን ቀኑ ደርሶ የሰላም ሰነድ እስኪፈራረም ድረስ ሰውየው የቻለውን ያህል ሐሰተኛ መረጃ መፈብረክና ማሰራጨት ይቀጥላል የሚል እምነት ነው ያለኝ።

E-mail: mahbereseytan@gmail.com

Full Website