ህዝብን ባርያ ለማድረግ የሚጠይቀው ብቸኛ ስራ ፍርሃት መልቀቅ ነው ” ኸርማን ጌሪንግ (ከናዚ መሪዎች)

ኻልኣዩ ኣብርሃ

12-09-21

ይህ ፅሁፍ በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጀው አለም በሚገባ የሚያውቀውንና እብዶች የለኮሱት የሁለተኛ አለም ጦርነት አስከፊ ውጤት እንደነ ታማኝ፣ ዘመነ፣ አንዳርጋቸው፣ ዳንኤል፣ መሳይ፣ ስዩም፣ ዳኛቸው፣ መሳፍንት፣ አገኘሁ፣ ወዘተ የመሳሰሉ ከአንድ ብሄር ብቻ የወጡ ኢትዮጵያውያን ኽርማን ጌሪንጎች ወደ ገደል ለሚመሩት ህዝብ ምክር እንዲሆን ታስቦ ነው። ጀርመን አንድ ብሄር ስለሆነ ከ50 አመታት በኋላ መልሶ ተዋሃደ፣ ያጣውን ታላቅነቱን ሳንቆጥር። የኢትዮጵያ ነገር ግን ከዚህ የተለየ ነው። ይህ በሸረሪት ድር የታሰረው የሰማንያ ብሄር ብሄረሰቦች አንድነት ከተበጣጠሰ እንኳንና በአምሳ በአምስት መቶ አመትም መልሶ አይገናኝም። ፊትም ቢሆን የተጣበቀው በጉልበት ነውና በስልትና በቁልምጫ መሆኑ ቀርቶ “በዘመቻ ሚኒሊክ” በጉልበት አንድ ማድረግ መቀጠሉ የኢትዮጵያ የፍፃሜዋ መጀመሪያ የሚሆን መሆኑን ህዝቡ ከስሜት ወጥቶ ቆም ብሎ እንዲያስብ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ። የበሉት ዳቦ ከመሶብ አይገኝም። ቁጭት ጨጓራና ደም ግፊትን ያስከትላል እንጂ በእብደት ያጡትን አገር አይመልስም።  የትግራይ ህዝብ ምንም ሳይበድል የደረበትን ግፍ ከመረዳትና በወገንነት ስሜት የችግሩ ተካፋይ እንደመሆን “አጥፋው፣ አውድመው” እያሉ ጊዜ የማይሽረው ጠላትነት መጋበዝ ከአፍንጫ አርቆ አለማሰብ ነው። አይሁዶች እኮ ስድስት ሚልዮን አልቆባቸው አልጠፉም፣ አረብን የሚያስደነብሩ፣ አለምን የተቆጣጠሩ የማይቀመሱ ኮምጣጤዎች ሆነው ይኖራሉ። ጀርመንን ያወደሟት “የጀርመን ጠላቶች” የተባሉት አይሁዶች ሳይሆኑ በስመ የጀርመን የበላይነት ራሳቸው ጀርመኖቹ ናቸው። ተራውን ጀርመናዊ “ዋናው ጠላትህ አይሁድ ነው፣ ሩስያ ናት፣ እንግሊዝ ናት” እያሉ ሲያጃጅሉት ነበር። እዚህም ህዝቡን በባንዴራ፣ በዘፈን፣ በተዛባ ታሪክ፣ እያሳበዱ ከአንድ ወር በላይ አርቆ እንዳያይ እየተደረገ ነው። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር ጀርመን ወደ ሁለተኛ የአለም ጦርነት ያመራችበት አካሄድ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል። በቀላሉ ሊፈታ ይችል የነበረውን የትግራይ ጥያቄ በእብሪትና ማን አለብኝነት ወደ ሃይል እርምጃ ሲወሰድ ግዙፍ ሾላ እንደዋዛ አፈር ላይ ከጣሏት ቅንጣት ፍሬ እንደሚወለደው በሶስት ቀን ያልቃል የተባለው “ጥቂት መሪዎችን የማሰር ዘመቻ” ወደ አለም አቀፍ ውዝግብ ተቀይሯል። ይህንንም የባሰው ሳይመጣ ወደኋላ መመለስ ከመሞከር ይልቅ “ትግራይን ሳናጠፋ ኢትዮጵያ አትድንም”፣ ወልቃይትን ከማስረከብ ሁላችን እንለቅ” በሚል እሳቱ ላይ ጋዝ እየተደፋበት ነው። የትግራዩ ጦርነት ሲጀመር አራት መንግስታት የተሳተፉበት ነበር። ከዛ ቀጥሎ የአለም ሃያላን በሁለት ጎራ ተሰለፉበት። አሜሪካ ትግራይን እየረዳች ነው በሚል የፈጠራ ወሬ ቱርክ፣ ቻይና፣ ኢራንና ኢምሬትስ ከነ ድሮናቸው ሰተት ብለው ወደ ጦርነቱ ገቡ። ሱዳንንና ግብፅን የትግራይ ወገን አድርጎ በሃሰት በመፈረጅ የሌሎች የአፍሪካ አገሮችን ድጋፍ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው። ይህ አይደለም እንዴ የአለም ጦርነት ማለት? ይህ አይደለም እንዴ “ተቀምጠው የሰቀሉት ቆመው አያወርዱትም” የተባለው?

Videos From Around The World

በጣት የሚቆጠሩ በዘረኝነት የታወሩና የመሬት ወረራ ህልም ያናወዛቸው እንደ ኸርማን ጌሪንግ ያሉ የጀርመን ፓላለቲከኞች ሁለተኛውን የአለም ጦርነት በመለኮሳቸው በአምስት አመት ውስጥ  ከሰባ ሚልዮን በላይ የአለም ህዝብ ሞቷልም የደረሰበትም አልታወቀም። ስድስት ሚልዮን አይሁዶች ከጦር ሜዳ ውጪ በግፍ ተገድለዋል። በዚህ ጦርነት የአራት ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሷል። ከአራት ሚልዮን በላይ ጀርመናውያን የሞቱና የጠፉ ሲሆን የቆሰሉትና የተማረኩትን ግን ቤታቸው ይቁጠራቸው፣ ፈርሶ ካልሆነ። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ምርኮኞች ፎቶ ሾፓች ስለሆኑ መቁጠሩ በሶፍት ዌር ይሰራል! (ወዶ አይስቁ)። እዚች አገርማ ፎርጅድ ምርኮኞችም በገፍ ናቸው። አንድ ጥይት ሳይተኩሱና ሳይተኮስባቸው ከየ እናታቸው ጓዳ ወጥተው ምርኮኛ የሆኑ ሺዎች ናቸው! ይህ በንፁሃን ተጋሩ ላይ የሚደርስ ግፍ ባይሆን ኖሮ በሳቅ የሚያንፈራፍር አሪፍ የኮሜዲ ፊልም ይወጣው ነበር። ወደ ጦርነቱ ጉዳት ልመለስና በ ቦምብ ድምጥማጣቸው የጠፉ ከተሞችና የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተቋማትን ሳይጨምር ጀርመን ለጦርነቱ 300 ቢልዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች፣ አምስት ሚልዮን ዜጎቿንም አጥታለች። በወዶ ዘማቾችና በምልምሎች የተሞላው የጀርመን ሰራዊት ከ14 ሚልዮን ያላነሰ ነበር። አሁን እነዚህ እብዶች ከዚህ ሁሉ ውድመት ለጀርመን ምን አተረፋችሁላት ይባላል? ትርፉ አገሪቱን ክብር አሳጥቶ የአሜሪካ ተረጂ እንድትሆን ማድረግ፣ ለሁለት ተሰንጥቃ በሶቭየትና በምእራቡ አለም ወታደራዊ ሃይል ስር ወድቃ ለግማሽ ምእት አመት ህዝቧን ማለያየ ት፣ በአለም ዙርያ ለጀርመን ህዝብ ከፍተኛ ጥላቻና ጥርጣሬ መፈጠ ር፣ ከፍ ያለ አቅም ያላቸው የጦር መሳሪያዎች እንዳታመርት መታገዷ። ከዚህ የከፋ ምን አለ? “እሾህ ላጣሪው”።

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ወሳኝ ጥያቄ እነዚህ የናዚ መሪዎች በምን ዘዴ አሳውረው ነው የጀርመንን ህዝብ ወደ እንደዚህ አይነት ጥፋት የመሩት? የሚል ነው። መልሱ ከዚህ ፅሁፍ ርእስ ላይ በአጭሩ ተመልሷል። የተብራራ መልስ የሚገኘው ግን ኸርማን ጌሪንግ ወዳልቀረለት የኑረንበርግ አለም አቀፍ ፍርድ ቤት ቀርቦ ከተናገረው ነው። ጌሪንግ እንዲህ አለ:-

“ተራው ህዝብ በተፈጥሮው ጦርነት አይወድም። ይህንን በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ሆኖም ግን፣ ሁልጊዜ ህዝብን መሪዎች ወደሚፈልጉት ነገር ማምጣት ይቻላል። ቀላል ነው! ማድረግ ያለብህ፣ ለህዝቡ ”እየተጠቃህ ነው” ብለህ ማስፈራራት ነው። ጦርነት የማይፈልጉትን ሰላማዊያንንም የአገር ፍቅር የሌላቸው አድርጎ በመፈረጅ አገሪቱን ለአደጋ እያጋለጧት እንደሆነ አስመስሎ መስበክ ነው”።

ይኸውላችሁ! ኢትዮጵያ ውስጥ አገር እያተራመሰ ያለው የጌሪንግ ህዝብን የማጃጃል ፍልስፍና ነው። ህዝብን ለፈለጉት ሰይጣናዊ አላማ የአገር ጉዳይ እያስመሰሉ ማነሳሳት ቀላል ነው። ሰው እንደማንኛውም የእንሰሳ ዘር የመኖርያ ክልሉን ድንበር የሚነካበት አይወድም። ዝሆኖች ሆኑ ጉንዳኖች የራሳችን ነው የሚሉት ወሰን አላቸው። ተፈጥሮ የመከላከያ አቅም በተለያየ ሁኔታ የሰጣቸውም ይህን ክልላቸውን ላለማስደፈር ነው። ይህ የደመነፍስ (ኢንስቲንክት) ጉዳይ ነው። ይህ የፓለቲካ ፍልስፍና ክርክር የሚደረግበት አይደለም፣ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ። ለዚህም ነው ወስላታ ፓለቲከኞች የራሳቸውን የግል ወይንም የቡድን ጥቅም በህዝብ ደምና በህዝብ መከራ ለማስከበር የሚጠቀሙበት የማነሳሻ ዘዴ ጥያቄ የማያስነሳውን የደመነፍስ የህልውና ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩት። ነብር መጣብህ ካሉኝ ወይ መሸሽ ወይ መጋፈጥ እንጂ ቆሜ ጥያቄ አልደረድርም። ለዚህ ነው የተፈጥሮ ህልውና መጠበቂያ ተፈጥሯዊ ስሜቱንና አቅሙን ለራሳቸው አላማ የሚጠቀሙበት። “የትግራይ ሰዎች አማራን ከምድረ ገፅ ሊያጠፉ ከክልልህ ገብተዋል” ሲባል የማይደነግጥ፣ ሞፈር ቀንበሩን ጥሎ የማይነሳ፣ ልጅ ሚስቱን በቅጡ ሳይሰናበት የያዘውን ይዞ የማይዘምት የሰው ፍጡር ይኖራል? “ትግራይ ሆ ብሎ ታጥቆ ወደ አማራ ክልል የገባው በደረሰበት እጅግ ከባድ ጥፋት ራሱን ነፃ ለማድረግና ወንጀል የፈፀሙበትን ለይቶ ለፍርድ ለማቅረብ” መሆኑን ለአማራው የነገረው የለም። ይህ ከተነገረማ አማራው አይነሳም፣ “አጥፊ ግብሩ ያውጣው፣ ግብሩ ያጥፋው” ብሎ ከቀየው ንቅንቅ አይልም። ይህ በአማራ ክልል አላበቃም። ይህ “ክልልህን ሊያጥፉ ነው” የሚለው ቅስቀሳ የሚያነሳሳው አማራን ብቻ ስለሆነ ለቀስቃሾቹ በቂ አልሆነም። ስለዚህ ከፍ ወዳለ የማስፈራሪያ እርከን ማደግ ነበረበት። አገኘሁና ታማኝ እንዳጋለጡት የአማራ “ጥቃት” የመላ ኢትዮጵያ “ጥቃት” እንደሆነ ተደርጎ “ተሰርቶበታል”። አሁን ጀሮን የሚያደነቁረው ጩኸትና ቅስቀሳ “ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው! ሁሉም ዘምቶ ያድናት!” የሚል ነው። በሽብርተኝነት ተፈርጀው ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየተዋጉ ነው የተባሉት የትግራይና የኦሮሞ ሃይሎች ይህን ማድረግ እንደማይፈልጉና ይልቁንም ኢትዮጵያን ወደ ሚኒሊክ ዘመኗ ኤምፓየር እንዳትመለስና ብትንትኗ እንዳትወጣ በፍላጎት ላይ ለተመሰረተ አብሮነት እየሰሩ መሆናቸው ነው የሚታወቀው።

መቶ ሰው አንድ አዳራሽ ውስጥ ኑር ከማለት መቶ ክፍሎች ያሉት ኮንዶ ህንፃ ውስጥ ቢኖር አይመረጥም? አንድ አዳራሽ ውስጥ መኖር የግል የቤተሰብ ምስጢር የለ፣ በግል እንደየምርጫው መመገብ የለ፣ ራቁት መውጣት ሆነ በግል መፋቀር የለ፣ የግል ስሜት ማንፀባረቅ የለ! ኮንዶ ውስጥ መኖር ያው እንደ አዳራሹ አንድ ህንፃ ነው፣ ግን ከላይ የተጠቀሱት የግል ህይወቶች ተከብረው ይኖራሉ። ለኮንዶው የጋራ መናፈሻዎች፣ ጥበቃዎች፣ ሱቆች አሉ። ይህ የግልና የጋራ ህይወትን ያስከበረ ድንቅ የሆነ ሚዛናዊ ህይወት አይደለምን? የመቀጠል ተስፋ ያለው አዳራሹ ውስጥ ተፋፍጎ እንደ እስረኛ መኖር ሳይህን በኮንዶስ ያለው ፍትሃዊ ኑሮ ነው። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትግል ስለ አገር ህልውና ማፍረስና እንዳትፈርስ መታገል ሳይሆን ለኢትዮጵያ አብሮነት የሚበጀው የቱ ነው የሚለው የርእዮተ አለም ፍትግያ ነው። እኛ ያልነው የአዳራሽ ውስጥ ጭፍለቃ እውን ካልሆነ አገሪቱ ትፈርሳለች ማለት ከንቱ አስተሳሰብ ነው። የጎንደር ነጋዴዎች “የሰሊጥ መሬት ከእጃችን ካልገባ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች” እያሉ ዩኒፎርም ለብሰው ፎቶ እየተነሱ ህዝቡን ሲማግዱት መንቃት ካልቻለ ምን ማድረግ ይቻላል?

የትግራይ ሰራዊት ሲጠነክርና አማራን የማጥፋት ፍላጎት እንደሌለው ህዝቡ እየተገነዘበ መምጣቱን ሲገነዘቡ፣ ይህ ሰራዊት ኢትዮጵያን ሊያፈርስ ነው የሚለው ውትወታም ቀለሙ እየለቀቀ ሲሄድ የኢትዮጵያን ህዝብ በትግራይ ላይ የሚያነሳሱበት ዘዴ እየሳሳባቸው መጣ። ይህ ሁኔታ በፈጠረው ስልጣንን የማጣት አደጋ የማነሳሳቱ ፕሮፓጋንዳ አሁንም አንድ እርከን ከፍ አለ። የመጀመሪው እርከን “አማራ ሆይ! ሊያጠፉህ ነውና ተነስ” የሚል ነበር። ቀጥሎ ያደገው ወደ ሁለተኛ እርከን ሲሆን “ኢትዮጵያዊ ሆይ! አገርህን ሊያፈርሷት ነውና ህፃን፣ እዋቂ፣ አዛውንት ሁልህም ተነሳ”። እድገቱ ከክልል ወደ አገር ሆኖ ቆየ። ዘወትር “ኢትዮጵያ ያንተ ናት” ይሉትና ከዛው ቀጥለው “ወልቃይትን፣ ራያን፣ መተከልን፣ ደራን” አስመልስ እያሉ ግራ የሚያጋቡት የአማራ ህዝብ አሁንም ማጭዱን ይዞ ለአጨዳ በወጣበት እግሩ ግንባር እየሄደ ይረግፋል። ቀሪው ኢትዮጵያዊ ብሄር ብሄረሰብ ግን በመጠኑና በዝግታም ቢሆን የተስፋፊዎች ተንኮል እየገባው ያለ ይመስላል፣ ለዚህም ነው ዝምታ ያበዛው። በለቅሶ ላይ ሁሉም ሲያለቅስ ይቆይና ደክሞት ፀጥ ሲል የቅርብ ቤተ ሰብ ግን ጩኸቱን ሲቀጥል ጎልቶ ይሰማል። ብሄር ብሄረ ሰቡ እየገባው ያለው እውነታ ከአማራው ጋር ሆኖ ሲጮህላትና ትግራይን ሲያወግዝላትና ሲወጋላት የቆየላት ኢትዮጵያ የአማራይቱ አሃዳዊት ኢትዮጵያ እንጂ ያቺ አብሮነት በእኩልነት የምታነግሰው ኢትዮጵያ ምንም ሳትሆን በጤንነት በፌደራሊስት ሃይሎች እጅ ስላለች የሚያሳስብ ነገር እንደሌለ ነው። በኢትዮጵያ ህልውና ዙሪያ የተገነባው የፕሮፓጋንዳ ግንብ እየፈረሰ ስለሆነ ኢትዮጵያዊ ጌሪንጎች ቅስቀሳውን ወደ ሶስተኛ እርከን አሳድገውታል:- “አፍሪካን ማዳን!”። አማራን ማዳን፣ ኢትዮጵያን ማዳን፣ አፍሪካን ማዳን፣ ቀጣዩ ደግሞ አለምን ማዳን ሊሆን ይችላል። ሰዎቹ በጣም ደፋሮች ናቸው። “ኢትዮጵያ እንደ ማርስ ሰው አልባ ሆናም ቢሆን እኛ እያለን አትጠፋም” እያሉ የሚናገሩ እውቀት ያልዳሰሳቸው ጋኖች ባለቁበት ጋን የሆኑ ምንቸቶች ናቸው። አወቅን እያሉ በተናገሩ ቁጥር ተሸማቀን አለቅን! ስልጣን የሚያዘውም፣ ሃብታም የሚኮነውና አዋቂ የሚኮነው በአንድ መንገድ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ጥቂት አመታት የምናየው የምንሰማው ግን ኪሱ ያበጠውና ጭንቅላቱ የኮሰሰው ነጋዴ ሁላ ስለ አሜሪካ ዲፕሎማሲ ትንተና ይሰጣል። ብልፅግና ውስጥ በመግባቱና በፓርቲው መመዘኛ ስልጣን ስለተሰጠው ብቻ ሌላው ሁሉ ምንም የማያውቅ መሃይም ይመስለዋል። ብሊንከንን “የአለም ደደብ: የአሜሪካን ስንዴ ነቀዛም፣ አሜሪካን ታሪክ አልባ፣ አሜሪካን አዲስ ቅኝ ገዢ” እያሉ አይጥ ሆነው ዝሆን ላይ የሚያላግጡ መሃይማን ሞልተውናል።

የኢትዮጵያ ፀረ-ትግራይ የማነሳሳት ዘመቻ ሶስተኛ እርከን ላይ እንዴት እንደደረሰ እንመልከት። ዋናው መነሻ የትግራይ ሰራዊት ማመን ከሚፈልጉት በላይ ጠንክሮ በስልጣናቸው ላይ ከፍተኛ አደጋ ስለጋረጠባቸው ነው። “ዱቄት ሆኗል፣ ተበትኗል፣ እየተሽሎከለከ ነው፣ ከመኪና ወርዷል፣ የሱን አይነት በዘራችሁ አይድረስ” ሲሉት የነበረው የትግራይ ሃይል አዲስ አበባ አቅራቢያ ሲደርስ ትርክታቸውን ቀየሩ። “ይህ ሃይል የትግራይ ሳይሆን የአሜሪካ ነው” አሉ። ጥርቅም አድርገው አንዲት የራስ ምታት ክኒን እንኳ እንዳትሾልክ አድርገው የዘጉት ድንበር አሜሪካ መግባት ብትፈልግ እንኳን በየት ገብታ ኢትዮጵያን እንደምትወጋ ግልፅ አላደረጉም። የሌላቸው መረጃ ከየት ያምጡት? ተንታኝ የተባለ ሁሉ በተቀደደለት የውሸት ትርክት ቦይ እየፈሰሰ ታሪክን እየለቀመ ያጣምማል ያጋንናል። በመሰረቱ አሜሪካ ለተገፋው የትግራይ ህዝብ ማድረግ ይገባት የነበረው ከጭንቀትና ከቃላት የዘለለ ብዙም ጠንከር ያለ እርምጃ አልወሰደችም። አሜሪካ የምትጠቀመው በኢትዮጵያ አንድነት በመሆኑ፣ ሆኖም ግን ይቺ አሜሪካ በአንድ ሳህን ላይ እንድትሆንላት የምትፈልጋት ኢትዮጵያ አሜሪካን የሚያሳፍር ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ስትፈፅም ስታይ የምታደርገው ነገር ግራ ገብቷታል። ስታመነታ ግን ቻይናና ሩስያ ማጭ ብለው ቀድመዋት ኢትዮጵያን እያሳጧት ነው። በዚህ የተደናገጡት የአሜሪካ ባለስልጣናት ባገኙት አጋጣሚ ኮታቸውን ገልብጠው እየለበሱ ነው። “የአራት ኪሎ መንግስት በትክክል የተመረጠ ነው፣ ብሄር ብሄረሰብ የማይባልባት ኢትዮጵያ ብትኖር ደስ ይለናል፣ የትግራይ ሰራዊት ከአማራ ይውጣ (የምእራብ ትግራይን ጉዳይ ሳይጠቅሱ)” የሚሉትን ቃላት በዘር አጥፊው ኢሳት ሳይቀር እየቀረቡ ይምበዛበዛሉ። በዚህ አይነት እስስትነት ከኢትዮጵያ ጋር ለመታረቅ ቢሞክሩም የኢትዮጵያ ፓለቲከኞች አሜሪካን ያንበረከኩ ያህል ሆኖ ስለተሰማቸው ጥቃቱን ቀጠሉ። ሁለት ያጣ ጎመን የሆኑት አሜሪካውያን ከዚህ በፊት በሌሎች አገሮች ላይ የወሰዷቸውን ቆራጥና ጊዜ ያልሰጡ እርምጃዎች አሁን ደርሰው ጥርስ አልባ የሚያገሳ አንበሳ ሆነዋል። በዲፕሎማሲ አለም ድክመት ማስጠቂያ ነው። ይህ የአሜሪካ መንዘላዘል ነው ቱርክና ኢሚሬት በድፍረት ኢትዮጵያ ገብተው ትግራይን የሚወጉት። የአሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ቀበቶዋን በማላላቷ መርኋን ጨብጣ እንደልብ እንዳትሮጥ ካደረጓት ፈተናዎች አንዱ የራሷ ዜጎች መቆጣጠር አለመቻሏ ነው። ዜጎቿ ለፍትህ ብለው የትም አለም ቢታገሉ የአሜሪካ ዴሞክራሲና ሰብአዊነት የቆመለት አላማ ነው። የአሜሪካ ዜጎች የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ትግራይ ላይ ባለው ፍትህ አልባነት ክንዳቸውን ቢያነሱ ለአሜሪካ ህዝብ ኩራት ነው። የኢትዮጵያና የኤሪትርያ ባንዴራዎችን ይዘው ወደ ትግራይ የእርዳታ መስመር እንዳይከፈትና አሜሪካም በዚህ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እንዳትገባ የሚሉ አረመኔ ዜጎቿን በህግ እንደማስታገስ በሰልፈኛው ብዛትና ጩኸት ተደናግጣ የሰብአዊነት ጎዳናዋን ትስታለች ብሎ ያሰበ የለም። በዚህም ሆነ በዛ የአሜሪካ ባለስልጣኖች ጠበቅ ማለት ሲያቅታቸው ኢትዮጵያ አጋጣሚውን በመጠቀም አፍሪካን ልታነሳሳባቸው እየሞከረች ነው። “ሃሽታግ ኖሞር”/ይበቃል” በሚል መፈክር በዳያስፓራው የተለኮሰው እንቅስቃሴ የትግራይን ህዝብ የሰቆቃ ድምፅ ያዳፈነ በአሜሪካ ባለስልጣናት ልልነት የጎለመሰ ኢሰብአዊ ንቅናቄ ነው። ይህ አፍሪካ አህጉር ድረስ የደረሰው ፀረ-ትግራይ የዲፕሎማቲክ ዘመቻ “አፍሪካ የአሜሪካ ቅኝ ግዛት የመሆን አደጋ ላይ ናትና አፍሪካዊ ሁሉ ተነስ” የሚል ነው። በዚህ የተደሰቱት ሩስያና ቻይና አሜሪካን ከአፍሪካ ለመንቀል ጥሩ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል። ይህ ሁሉ አለም አቀፍ ውስብስብ ገመድ የተጎነጎነው በቀላሉ ለሚፈታው የትግራይ ችግር ነው::- የትግራይ ግዛቶች ይመለሱ፣ አገልግሎቶች ይከፈቱ፣ እርዳታ ያለ ገደብ ይግባ፣ ወንጀለኞች ይቀጡ፣ የጠፋው ይካስ፣ ህወሓትን ማሳደድ ይቁም፣ የታሰሩት የፓለቲካ እስረኞች ይፈቱ፣ ሁሉም ያሳተፈ መንግስት ይመስረት። በቃ! ይኸው ነው! በዚህ የሚፈርስ ክልል አለ? በዚህ የሚፈርስ አገር አለ? በዚህ የሚጎዳ አህጉር አለ? ከኩይሳ ተራራ መፍጠር ካልሆነ?

Full Website