mahbereseytan@gmail.com
Back to Front Page

ሙሉጌታ ወልደገብርኤል (ስትራቴጂስት) 02-10-21

ግፍና አመጻ በዚህ መልኩ አገሪቱን ሲያስጨንቅ፤ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ንጹሐን ዜጎች ባልዋሉበት ለአሰቃቂ ሞትና እልቂት ሲማገዱ፥ የሃይማኖት መሪዎች ለምን ዝም ይላሉ? መጽሐፉ እንደሚያዘው ድሃ ተበደለ ፍትህ ተጓደለ! በማለት በግፈኞች እያለቀ ስላለው ህዝብ ለመታደግ ለምን ድምጻቸውን አያሰሙም? ዝምታቸው እስከ መቼ ነው? በማለት በቅንነትና ግራ በመጋባት ጥያቄ የሚያነሱ ምእመናን በቁጥር መበራከትን ተከትሎ፥ ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀ ጽሑፍ ነው። ይህ ጽሑፍ፥ ትናንት፥ ጌታ ተናግሮኛል፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ነው፣ በደለው! ድፋው! እያለ የንጹሐንን ደም ደመ ከልብ ካደረገና ካስጨፈጨፈ በኋላ ዛሬ ደግሞ ኢየሱስ ያድናል! ኢየሱስ ጌታ ነው! በማለት ሰብኮና ዘምሮ በግፍ ካስጨፈጨፈው የትግራይ ህዝብ በእግዚብሔር ስም የሚሰበሰበውን መባ ተካፍሎ አበል ሊሰበስብ የሚመጣውን፤ ሌላው ደግሞ፥ መስቀሉን እያወጣወጠ ነፈሰ ገዳዮችን ከሸኘ በኋላ፤ የህጻናት ለቅሶና ዋይታ አይሰማኝም! እያለ እየሾፈ ከርሞ በዕርቀ ሰላም ስም የሚመጣ ህፍረት የማያወቀው የነፍሰ ገዳይ ቡድን የሚያወግዝ ጽሑፍ ነው።

ገበሬ በማሳው ላይ ሳለ፥ ዮሴፍ ስታሊን ለጉብኝት ይደርስበታል አሉ። ገበሬውም፥ ጓድ ስታሊን! በማለት ሞቅ ያለ ሰላምታ ከሰጠ በኋላ፤ ጓድ ስታሊን፥ የዘንድሮ ምርት እንደምታውቀው ነው፤ አንዱ በአንዱ ላይ ቢደራረብ እግዚሃሩ ያለበት ስፍራ የሚደርስ ድንች ነው ያለን! ይለዋል። ስታሊንም መለሰና፥ እግዚአብሔር የሚባል እኮ የለም ይለዋል። ገበሬውም እውነት ብለሃል ጓድ ስታሊን፥ ድንቹም የለም! አለው ይባላል። ጥጉ፥ መንፈሳዊ መሪ የሚባል ሳይኖር የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ መጠበቅ ሞኝነት ነው።

የኃይማኖት መሪዎችና መንፈሳዊነት

የአፍሪካ መሰረት ያለው ጥቁር ሰው፥ ሰው መሆኑ ቀርቶ እንደ ማንኪያና እንደ ብረት ድስት ከቁሳቁስ ጋር በሚቆጠርበት ዘመን፤ ሂትለር ሰዎች በማንነታቸው የተነሳ እንደ ሳሙና እያቀለጠ ሲጨፈጭፍ፤ ስታሊንና ማኦ የመሳሰሉ የሰው አውሬዎች ተነስተው ሚልዮኖችን እንደ ችግኝ አንድ ጉድጓድ ላይ ቆፍረው ሲቀብሩ፤ ለዘይትና ለነዳጅ ሲባል አገራት በድሮን ሲወድሙ፣ ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ በገፍ ሲያልቁና ሲጨፈጨፉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኃይማኖት መሪዎች ድርሻ የላቀ ነው። ርግጥ፥ ከመጣ ጋር መሄድ የማይችል፤ የማይሆንለትና ፈቃደኛ ሳይሆን የሚቀር ሰው፤ ህሊና ያለውና የጽድቅ ህይወት የሚኖር ሰው እንጅ ሶሻሊስት መጣ ኮሚኒስት፣ ፋሺስት ነገሰ ኒዮ-ሊበራሊዝም ለመጣው መንግሥት ጥቅስ እያቀበሉ ከመጣው ጋር መሄድና ተመሳስለው ማለፍ የኃይማኖት መሪዎች ልዩ መገለጫ ባህሪይ ነው። ዜጎች በልዩ ልዩ ምክንያቶች ይህን እውነታ፣ ለማየት ለመገንዘብና ለመረዳት ባለመቻላቸው ግን ዛሬም ድረስ አጣብቂኝ ሁኔታ በተፈጠረ ቁጥር “የኃይማኖት መሪዎች ለምን ዝም ይላሉ?” በማለት ጥያቄ ሲያነሱ ይደመጣሉ።

በዓለም ታሪክ የኃይማኖት መሪዎች ስለተገፉ አልያም አላውያን መንግስታት በንጹሐን ዜጎች ላይ ከሚፈጽሙት ግፍና በደል የተነሳ ግፈኞችን በመቃወም ድምጻቸውን ያሰሙበት ዘመን ተፈልጎ አይገኝም። ቤተክርስትያን እንደ ተቋም የክርስቶስ ናት፤ የቤተክርስትያን ባለቤት፣ የቤተክርስትያን ጉልላትና መሰረት ህጸጽ የማያውቀው ኃጢኣት የሌለበትና ስለ ሰው ልጆች የመስዋዕት በግ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። መጽሐፍ፥ “በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ” እንዲል ኃላፊነት የተሰጣቸውና አደራ የተጣለባቸው የኃይማኖት መሪዎች ባህሪይ ግን በቅዱሳት መጻህፍት ከተገለጠው እውነት በእጅጉ የሚቃረን ነው። የኃይማኖት መሪዎች፥ ጥያቄ የሚያነሳ ሁሉ በሰይፍና በምሳር እየቆረጡና እየፈለጡ፣ በእሳት እያቃጠሉና እየቀቀሉ የመጡ የክፋትና የሴራ ምንጭ ናቸው። በዓለማችን ዘግናኝ የግድያ ዓይነቶች የተፈጸሙ በኃይማኖት መሪዎች እጅ ነው። የኃማኖት መሪዎች እሳት አያይዘው ሰውን እንደ እሸት ሲጠብሱ የሚታወቁ ግፈኞች ናቸው። እስጢፋኖስን በድንጋይ ወግረው የገደሉት አህዛብ ሳይሆኑ የኃይማኖት መሪዎችና ተከታዮቻቸው ናቸው። ይህ በቅዱሳት መጽሐፍ መዝገብ ላይ የሰፈረ ሐቅ ነው። መንፈሳዊነት ሲባል፥ መንፈሳዊ ቋንቋ መናገር፣ ጥቁር ጀለብያ መልበስ፣ መስቀል መያዝ፣ አንገጥ ላይ መስቀል ማንጠልጠል፣ መስበክ፣ መዘመር፣ ወዘተ ብሎ ለሚያምን ሰው ግን ይህ ሁሉ ተረት ተረት ነው። የኃይማኖት አባት ወይም መሪ ሲባል፥ በሰዉ አእምሮው የተሳለው ስዕል እንዲሁ ቀላል ስላይደለ እንዲህ ያለ ዘግናኝ ግፍና በደለ በተነሳ ቁጥር ድርጊቱ በኃይማኖት መሪዎች እጅ ይፈጸማል ብሎ ስለማያምን ሐቁን ለመቀበል ዝግጁ/ፈቃደኛ አይደለም።

በርግጥ፥ የአማኙ የቅዱሳት መጻህፍት እውቀት ማጣትና መንፈሳዊ ህይወት መጓደል፤ የኃይማኖት መሪዎች አማኙን እንደ ፈለጉ እንዲዘውሩት ጉልበት ሰጥቷቸዋል። ይህን ተከትሎም ሰዎች፥ የኃይማኖት መሪዎች የሚሰሩት ክፉና አመጸኛ ስራ እንዳይጠይቅ፥ የኃይማኖት መሪዎቹ አስቀድመው የተከታዮቻቸውን አእምሮ፥ ትቀሰፋለ፣ ትቆረጣለህ፣ ታልቃለህ፣ ትሞታለህ… ወዘተ በሚሉ የምዋርት ቃላቶች ስለያዙትና ስላደነዘዙት ነው። እውነተኛና ትክክለኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀት ያለውና ራሱን በእግዚአብሔር ጽድቅ ያስታጠቀ አማኝ ግን የኃይማኖት መሪዎች በእግዚአብሔርና በመንፈሳዊነት ስም በሚነዙት አፍዝ አደንግዝ አይደናግረም፤ አይደነግጥምም። ከእግዚአብሔር በቀርም ከጸሐይ በታች የሚፈራው ኃይል የለም፤ አይኖርምም።

ኢየሱስ የኃይማኖት መሪዎች የሚያውቃቸው ግብዞች መሆናቸውን ነው

ግብዝ (ግብነት/ግብዞች) የሚል ቃል በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል የተለመደ ቋንቋ ቢሆንም፤ መጽሐፍ ቅዱስ በሚገልጥበት ልክና ክብደት ግን በሚገባ የተተረጎመ ቃል አይደለም። ግብዝ ተብሎ ወደ አማርኛ ቋንቋ የተተረጎመ “ሂፖክረስይ” ( hypocrisy) የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተገኘው “ hypokrisis” ከሚል የግሪክ ቋንቋ ነው። “hypo” ማለት “ማስክ” ማለት ሲሆን “krisis” ማለት ደግሞ “የመድረክ ጽሑፍ/ተውኔት” ነው። hypokrisis” ወይም ግብዝ ማለት በጥቅሉ የውሸት፣ የማስመሰል-ህይወት፤ አንድም “አክተር” ወይንም “የመድረክ ተዋናይ” ማለት ነው። ኢየሱስ በአካለ ሥጋ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን፥ ግሪኮች መድረክ ላይ በሚሰሩ ድራማዎችና ተውኔቶች የገነኑበት ዘመን ነበር። ይሰሩ የነበሩ የመድረክ ተውኔቶችም ልዩ ልዩ ገጸ ባህሪያት የሚያንጸባርቁ ቢሆንም ሁሉም ነገር የሚሰራው ግን አንድ ሰው ከመጋረጃ በስተጀርባ እየተመላለሰ ልዩ ልዩ ማስኮችና አልባሳት በመለዋወጥ በሚያደርገው ትዕይንት ነበር። ከዚህ የተነሳም፥ ኢየሱስ የኃይማኖት መሪዎች ትክክለኛ ባህሪይና ማንነት በሚያስተምርበትና በሚገልጠት ሰዓት ግብዞች ሲል የሚገልጻቸው። ለምን? የኃይማኖት መሪዎች ህይወት የውሸት ህይወት ስለሆነና ቢፋቁ ቀሚስ የሸፈነው ህይወታቸው ሰይጣን የሚያስቀና ቆሻሻ ህይወት በመሆኑ ነው

ኢየሱስ የኃይማኖት መሪዎች በሚገልጽበት ስፍራ ላይ፥ “በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ” እንዲል ሰዉቹ፥ ሰውና እግዚአብሔር የማይፈሩ፣ ደፋሮችና ነፍሰ ገዳዮች፣ ያልሆኑትን የሌላቸውና ያላለፈባቸው ህይወት መስለው ለመታየት በሚገባ የተካኑ አክተሮች፣ የእግዚአብሄር ስም እየጠሩ ሰውን ከነነፍሱ መቅበር የሚያውቁበት አደጋ ጣዮች በመሆናቸው ግብዞች ሲል ገልጻቸዋል። ይህ ብቻ አይደለም፥ ኢየሱስ፥ “በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል” ሲልም የኃይማኖት መሪዎች ትክክለኛ ማንነት ገልጧል። ለሰሚ ጆሮም እንደሚከተለው ከባድ ማስጠንቀቂ ሰጥቶ አልፏል፥ “ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞርን፥ በገበያም ሰላምታን፥ በምኵራብም የከበሬታን ወንበር፥ በግብርም የከበሬታን ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ” ሲል። ለምን? “አስቀድማችሁ ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ፥ እርሱም ግብዝነት ነው” እንዲል። ለምን? ግብዝነት አንድን ሰው አለሁ እያለ የሚያጠፋና የሚያሰምጥ አደገኛ ኃጢአት ስለሆነ ነው፤ “ ኢሳይያስ ስለ እናንተ ስለ ግብዞች ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው” እንዲል።

እርምህን አውጣ! ልብንና ኩላሊን የሚመረምር አምላክ የማይፈራ ሰው፥ ሰውን ይፈራል፤ አንድም፥ ለሰው ልጅ ያዝናል፣ ይራራልም! ብሎ የሚያምንና የሚያስብ ሰው ካለ ሲበዛ የዋህ ነው። እግዚአብሔር የማይፈራ ሰው፥ አይደለም ሰውን ሊፈራ ቀርቶ ሰውን በእግዚአብሔር ስም ለማጥፋት የማይፈጥረው ሴራ የለም። እግዚአብሔር አምላክ የማይፈራ ሰው፥ ሰዎችን በእግዚአብሔር ስም ማደናገርና ማደናበር የዕለት ዕለት ስራው ነው። ግብዝነት፥ የውሸት ህይወት፤ ከእግዚአብሔር ጋር ቁማር መጫወት ማለት ከሆነ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ቁማርን መጫወት የለመደ የኃይማኖት መሪ ድሃ ተበደለ ፍትህ ተጓደለ! ብሎ ይጮሃልኛል ብሎ የሚጠብቅ ሰው ካለ በእውነቱ ነገር ከጅብ አጥንት ቢጠብቅ ይሻለዋል። የኃይማኖት መሪዎች ይህን ያህል አስቀያሚዎች ከሆኑ ታድያ ይህን ያህል ዘመን እንዴት ሊዘልቁ ቻሉ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። መልሱ አጭርና ግልጽ ነው። ይኸውም፥ ብሔራዊ ትያትር በሮቹ ዛሬም ድረስ ክፍት የሆነበት ምክንያት ዛሬም ገንዘቡን ከፍሎ ድራማ ማየት የሚወድ አፍቃሬ ተውኔት የሆነ ዜጋ ስላለ ነው (ብሔራዊ ትያትር መሄድ/ድራማ ማየት ኃጢአት ነው። እያልኩ እንዳይደለ ይህን ጽሑፍ በቅንነት ለሚያነቡት አንባቢያን ግልጽ ነው ተብሎ ይታመናል)። የምንኖርባት ዓለም የድራማ ዓለም ናት፤ የሃይማኖት መሪዎች ደግሞ በእግዚአብሔር ስም መተወን በእጅጉ የተካኑ የአመጽ ሰዎች ናቸው። ይህ የሚለው እኔ ሳልሆን ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ህያው የሆነ የእግዚአብሔር ቃል ነው።

ጎበዝ፥ አይደለም በኢትዮጵያ ታሪክ በዓለም ታሪክም ቢሆን፥ ስለሚመሩት ህዝብ በነገስታት ፊት የቆሙ፣ የነገሥታቱ አመጸኛ ድርጊት በመቃወም በተከታዮቻቸው ፈንታ የሞት ጽዋ የተጎነጩ የቤተ ክርስትያን አገልጋዮች በጭንቅ ቢገኙ ነው። አማኞች፥ ከእምነታቸው የተነሳ ሲሰደዱ፣ ሲገረፉ፣ ሲታሰሩ፣ አካላቸው ተቆራርጦ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ በስቃይ ለህልፈት ሲዳረጉ፣ ለአራዊት መብል ይሆኑ ዘንድ ተላልፈው ሲሰጡና በሰማዕትነት ሲያልፉ አይተው እንዳላዩ ሰምተውም እንዳልሰሙ በመሆን ረጅም ዘመን ኖሮው በበሽታ የሞቱ የኃይማኖት መሪዎች ስም ዝርዝር ለመጻፍ ብንነሳ ግን ዓለም ብራና ውቅያኖስም ቀለም ቢሆኑልንም አይበቃንም። በነገራችን ላይ፥ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሰማዕት ተብለው የሚታወቁ ብዙሐኑ የቤተ ክስትያን አባቶች ገዳይ ሌላ ማንም ሳይሆን ራስዋ ቤተ ክርስትያን/የኃይማኖት መሪዎቹ የገደልዋቸው ሰዎች ናቸው። በአላውያን ነገሥታት እጅ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ የቤተ ክስርስቲያን አባቶችም ቢሆን የክስ ደብዳቤ በመጻፍ ለገዳዮች አሳልፎ በመስጠት ያስገደልዋቸው እነዚህ የኃይማኖት መሪዎች ናቸው። ደርግ አቡነ ቴዎፍሎስን የገደለበት መንገድ፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክስርትያን ፓትሪያሪኩ አብዮታዊ እርምጃ ይወሰድባቸው! ስትል ለደርግ ጽ/ቤት በጻፈችው ደብዳቤ ነው።

የኃይማኖት መሪዎች ነፍሰ ገዳዮች ናቸው

አንባቢን አንድ ነገር ላስታውሰው እወዳለሁ። ይኸውም፥ የዓለም ጌታ መድኃኔ ዓለምን እንደ ወንጀለኛ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ ነፍሱን እንድታልፍ፣ በመስቀል ላይ እንዲሰቀል የፈረደበትና የሰቀለው ምዕመናን ሳይሆኑ፥ እግዚአብሔርን እናውቃለን፤ የእግዚአብሔር መንገድ እናስተምራለ፤ እግዚአብሔር መንጋውን እንድንጠብቅ፣ እንድናስተምርና እንድንመግብ በዚች ዓለም ላይ ቀብቶናል፤ ሰማያዊ አደራ የተሰጠንና የተጣለብን መንፈሳውያን መሪዎችና አባቶች ነን! በሚሉ የኃይማኖት መሪዎች እጅ የተገደለ ለመሆኑ ማስታወሱ አስፋላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ይህ ሐቅ በብዙሐኑ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የተዘነጋና ሆነ ተብሎ ደብዛውን እንዲጠፋ ተደርጎ የተደመሰሰ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐቅ ነው። ቀደም ሲል ከተጠቀሰው አባባል ጋር ጸብ ያለው ግለሰብ ቢኖር፥ ጸቡ ከጸሐፊው ጋር ሳይሆን ከመጸሐፍ ቅዱስ እውነታ ጋር ለመሆኑ በዚህ አጋጣሚ ለመጠቆም እወዳለሁ።

ኢየሱስ፥ መንፈሳዊ ህጸጽ፤ አንድም፥ ኃጢአት ሲያደርግና ሲፈጽም ተገኝቶ በኃጢአት የተከሰሰ የአመጽ ሰው አልነበረም። ቀለል ባለ አማርኛ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በኃይማኖት መሪዎች እጅ ሲገደል በእውነቱ ነገር ኢየሱስ የአመጽ ሰው ሆኖ ሳይሆን፤ አንድም፥ በደል ተገኝቶበት ሳይሆን፥ የኃይማኖት መሪዎቹ ያስቆጣ የኢየሱስ በደል፥ እውነትን በመናገሩ ነበር። ከዚህ የተነሳም ለሮማውያን (የፖለቲካ ገዢዎች) አሳልፈው በመስጠት በመስቀል ላይ እንዲሰቀል አድርጓል። የኢየሱስ “በደል” ሌላ ምንም ሳይሆን፥ የመንፈሳዊነት እውነተኛ ትርጉም በመግለጡ፣ እውነትን በማስተማሩ፣ ለድሆች በማዘኑ፣ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ በመሆኑ፣ ለተገፉ ፍርድን በማድረጉ፣ ለበሽተኞች ፈውስን በመስጠቱ፣ አስታዋሽ ላጣች ነፍስ መልካምን ነገር በማድረጉ፣ ላዘኑት በማጽናናቱ፣ ሸክም ለከበዳት ነፍስ ተስፋ በመሆኑ፣ አሸን ክታባቸውን አስረዝመው፥ መንፈሳውያን መሪዎች፣ አባቶች፣ መምህር ወዘተ ተብለው ሊጠሩ የሚሹትን ነፈሰ ገዳዮች አስነዋሪ ማንነት በመግለጡና አመጸኞችን በመቃወሙ ነበር።
Full Website