በዚህ ወቅት ትግራዋይ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ይችላልን?

ከ አብይ  ኢካቦድ 05-20-21

ሃገር ማለት ዜጎችና ሕዝቦች ባንድ ጥላ ስር በመቻቻልና በመፈቃቀድ በአንድ ማዕድ ዙሩያ ካፈሩት ሃብት በጋራና በተመጣጣኝ ክፍፍል በመቋደስ የሚደረግ ሕብረት፤ ትብብርና ተግባቦት ነው። በማዕዱ ዙሩያ የሚደረገው እውነተኛ ግኑኝነት፤ በምትሃት፤ በመለኮታዊ ጥበቃ፤በጋብቻና ልዓላዊነትን ለማስከበር የተደረጉ አስደናቂ የውጊያ ታሪኮችና ሌሎች  ትስስሮች የሚተካ አይደለም። እነዚህ ሁሉ ጠንካራ የትስስር ገመዶች እያሉ ሕዝቦች በሚያስማማና በወዳጅነት የሚያስተሳሰረው ውል ከሌለና ኖሮም በተግባር ላይ ካልዋለ፤ ሃገሪቱ ከመነጣጠል አያድንዋትም።

ሃገርን ለማስቀጠልና ለማኖር፤ ጋብቻ፤ መንፈሳዊ እሴት፤ ባሕልና ሌሎች ግብአቶች በጣም አስፈላጊዎች መሆናቸውና፤ አካል ሆነው የቆሙት ዜጎችና ሕዝቦች የማያያዣና መስተሳሰሪያ ጅማቶች መሆናቸው ባይካድም፤ እነዚህ እንደ ድሮአቸው እየቀጠሉ ባሉበት ሁኔታ በዜጎችና በሕዝቦች ላይ ተገቢና ተቀባይነት የሌለው በደልና ተገቢ ያልሆነ ጥቃት ከደረሰ ጅማቶቹና ክሮቹ የማያያዛቸውና የማሰተሳሰራቸው አቅም ተዳክሞና አንሦ አካላትን አያይዘው የማሰቀጠሉ ብቃት ሊያከትም ይችላል። እኚህ ግብአቶች ምንም እንኳ በጣም አስፈላጊ ቢሆኑም፤ እምብርትና አሰኳል ከሆነው የዜጎች መብትና የሕዝቦች መፈቃቀድና መቻቻል ውጭ ግን ፋይዳ አይኖራቸውም።

አንዳንድ ወገኖች፤ “ኢትዮጵያ እርሰ በርሱ የተጋባ፤ ለረዥም ጊዜ ከውጭ ለሚሰነዘርበት ጥቃት አንድ ሆኖ የመከተ፤ ድንቅ ታሪክ ያለውና በመንፈስም እግዚአብሔር የማይነጣጠል አንድ ሃገር አድርጎ የፈጠረው አንድ ሕዝብ ያላት ሃገር ነች” ይለሉ። አዎ! የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋብቻ የተሳሰረ ነው። አዎ! የኢትጵያ ሕዝብ በታሪክ የውጭ ጠላቶችን አንድ ሆኖ በተደጋጋሚ መክቷል። ዳሩ ግን እግዚአብሔር በአንዱ ሕዝብ ላይ አሬሜናዊትና ጭካኔ የሞላበት እርምጃና ዘርን የማጥፋት ሥራ እየተፈጸመበት፤ ኢትዮጵያ የግድ አንድ አገር ሆና ትቀጥል ከቶ አይልም፤ ከሕያው ቃሉም አንድ ይሀን የሚደግፍ ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም።

Videos From Around The World

አንዱ ባለንጀራዩ፤ ባገሪቱ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አስመልክተን ስንማጎት፤ ስለ ኢትዮጵያ የመበታተን አደጋ አስመልክቶ “አይምሰልህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈጽሞ አይበታተንም፤ ምክንያቱም ሕዝቡ እርሰ በርሱ የተጋበ ከመሆኑ በተጨማሪ እግዚአብሔርም የሕዝቦቹ መበታተን አይፈቅድም” ብሎኛል። ዳሩ ግን “ኤርትራ አንዷ የኢትዮጵያ አካል ነበረች፤ ኤርትራዊያንም ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር እንደ ሌሎች ሕዝቦች በጋብቻ የተሳሰሩ ነበሩ፤ ታድያ የጋብቻ ትስስሩና ሌሎች ለመስተሳሰር የሚጠቅሙ እሴቶች ኤርትራን ከኢትዮጵያ ከመገንጠል አዳነ ወይ?” ስለው፤ ምንም መልስ አልነበረውም። ከሌሎች የተገነጠሉ ሃገሮች ክስተት ተመርኩዞ የጋብቻው ትስስሩ ልክ እንደ ኢትዮጵያ እንደ ነበረና፤ ከመገነጣጠል ግን እንዳልተደገ የሚታወቅ ነው። ሌላው እግዚአብሔር ሰዎች በሕብረት ቢኖሩ መልካም እንደ ሆነ ቢናገርም፤ ይሄ አንድነት በፍቅርና በእውነት የተገነባ እንጂ፤ እንዲሁ ፍቅርና እውነት ሳይኖር፤ በደልና ጥቃት እያለ፤ የወንድማማች ፍቅር ሳይኖር በግድ አብራችሁ ኑሩ የሚል አምባገነንትንና በደል እንዲበዛ የሚያዝ የጽድቅ ባሕሪውን በገዛ ራሱ የሚሽር አምላክ አይደለም።

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮችና ብሔረሶቦች ጥንቅርና ስብስብ መሆኗ የሚካድ አይደለም። በዚህ ግልጽ እውነት ላይ ምንም ብዥታ የለም። እንደ በርካታ ሕዝቦች ቅንብርና ሕብረት፤ ሁሉም ዜጎችና ሕዝቦች ዴሞክራሰያዊ መብታቸው ተጠብቅላቸው ኖሯል ወይ? ለሚለው ጥያቄ መልሱ አሻሚ ከቶ አይደለም። መልሱ “ፈጽሞ አልተጠበቀም” ነውና። የሕዝቦች መብት ሳይጠብቁ ኢትዮጵያ አንድ ሆና ትቀጥላለች ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። አገሪቱ እንደ አገር ሆና ትቀጥል ዘንድ ኢህአዴግ የሁሉም ዜጎችና ሕዝቦች ዴሞክራስያዊ መብት ሊያካትት የሚችል “ህገ-መንግሥት” አቀርቦ ለተወሰኑ ዓመታት እስከነ ጉድለቱም ቢሆን ገቢር ለማድረግ ተሞክሯል። ሕገ-መንግሥቱ እንከን የለበትም ማለት ባይቻልም፤ እርሱ ተዘጋጅቶ ከመቅረቡ በፊት ከነበሩት አገዛዞች አኳያ የሕዝቦችና የዜጎች ዴሞክርሳያዊ መብቶች በማጎናጸፍ ላይ የላቀና የጎላ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

አሁን ያለው ገዥ ፓርቲና መንግሥት ይሄን በሕዝቦች መፈቃቀድ የጸደቀው የቃል ኪዳን ውል፤ በአንድም በሌላም መንገድ በመሻርና በመቦርበር፤ ብሔሮችና ብሔረ-ሰቦቹ ባንድ ጥላ ስር እንዲኖሩ ያደረጋቸው የቃል ኪዳናቸው የጸና ውል አንጓውንና አከረከራዊን በመሰባበርና በመቀለጣጠም፤ ይኼውና በሃገሪቱ በመከፋፈልና በመበታተን ጠርዝና ጫፍ እንድትገኝ አድርጎቷል። አንድ ልብስ መሰፋት ያለበትና አንድ ጫም መዘጋጀት ያለበት በለባሹ ተክለ ሰውነት መጠንና  በእግሩ ርዝመትና ልክ እንደ ሆነ፤ በአንድ አገር የሚኖሩ የተለያዩ በርካታ ሕዝቦችን የሚያስተቃቅፍና የሚያስተሳሰር አሰተዳደር መዘጋጀት ያለበት ይሄንን ባገናዘበ መልኩ መሆን ግድ ይላል። በሕዝቦች ፍላጎትና መፈቃቀድ ጸድቆና በተግባር እንዲውል ተደርጎ የነበረው ሕገ መንግሥት ከሞላ ጎደል በገዥው ፓርቲውና አሃዳዊያን ትብብር ስለተሻረ፤ እነሆ በሕዝቦች ላይ በተለይም በትግራይ ሕዝብ ላይ ታይቶ የማይታወቅ አረሜናዊ እርምጃ በመወሰድ ላይ ስለ ሆነ፤ ሕዝቦችን አንድ አድርጋ የምትቆም ኢትዮጵያ የመኖሯ ዕድል የመነመነ ነው። በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ “ጋብቻው እየገደለኝኛ እየጎዳኝ ስላለ የሚበጀን መለያየት ነው” በማለት ፍችን የሚጠይቅበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

የኢትዮጵያ ፊታ-ብሔር ላልተስማሙና በብጥብጥ ላይ ላሉ ባለ ትዳሮች፤ ፍችን የሚፈቅድ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥትም፤ አንድ ብሔር ያለ አግባብ ከተበደለ በሪፈረንደም የመለየትን መብት የሚፈቅድ ነው። በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ በገዛ መንግሥቴ በሚለው የፌደራል መንግሥትና፤ ጠላቱ በሆነው ግፈኛና አውሬ የኤርትራ ሰራዊት እንዲሁም በተሰፋፊውና ነውረኛ የአማራ ምሊሻ፤ ልዩ  ሃይልና ፋኖ፤ ዘግናኝ ድርብርብ አሬሜናዊ ጣራ የነካ በደል ሲደርስበት፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ራሱን ሊቆጥር የማይችልበት ጫፍ ላይ ደርሷል። ግፉና በደሉ አቻ የለሽና የትየለሌ በመሆኑ የተጋሩን ልብ ኩፉኛ ያቆሰለና ያደማ ከመሆኑ በሻገር ኢትዮጵያዊነትን እንዲያንገሸግሸውና እንዲጠላው አድርጎታል።

በክርሰትና እምነት ጦርነት የሚደጉፉተና ቡራኬ ሰጥተው የሚያበረታቱ ያይደለ፤ አበክሮና አጽንቶ የሚቃወሙት ነው። በአዲስ ኪዳን ጦርነት ይነሳና ይቀሰቀስ ዘንድ የሚያበረታታና የሚደግፍ አንድ ቁጥር ወይም ጥቅስ ማቅረብ አይቻልም።  የኢትዮጵያ መንግሥትና የብለጽግና ፓርቲ ከጥንስሱ ለራሱ ፖለቲካ ፍጆታና ፋይዳ ይበጀው ዘንድ፤ የተለያዩ እምነት ያላቸውን አካላት ጠፍጥፎ አንድ የሃይማኖት ማሕበርን አቋቁሟል። ከእነዚህም ዋናዎቹ፤ ኦርቶዶክስ፤ ካቶሊክ፤ ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያንና እስልምና ናቸው። እነዚህ የሃይማኖት ተቋማትን በዚህ መልኩ ፖለቲካዊ ፋይዳ ያገኝበት ዘንድ ከቋቋመ በኋላ፤ መሪዎቹ ወደ ትግራይ “ሕግን ለማስከበር” በሚል ሹፋን እስከ አፍንጫቸው የታጠቁትን ሠራዊቱ ሲልክ መርቀውና ባርከው ሸኝቷል። ይሄ በጣም የተሳሳተና በተለይም በአዲስ ኪዳን ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው። በዚህም በብልጽግና ፓርቲ የተመሰረተው የሃይማኖት ማሕበር (interfaith Union)  በትግራይ ሕዝብ ላይ በደረሰው ኢሰብአዊ በደልና አሬሜናዊ ግፍና ፍዳ ተጠያቂና ግብራበር ነው።

ከሃይማኖት መሪዎቹ አንዱ የሆኑት የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ፓትራይርክ ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ እንዳይናገሩ ለስድስት ወር ከታገዱ በኋላ፤ በግላቸው ባገኙት እድል እግዳውን ሰብረው፤ ዓለም ሁሉ ያወቀውና ፀሐይ የሞቀውን በትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰው ታይቶ የማታወቀውና አቻ የለሹን አረሜናዊ እኩይ ድርጊት በይፋ አውግዟል። ይህም “እውነት ተናግሮ በመሸበት ማደር” የሚለውን የአቦው አባባል ያሰረገጠ፤ እውነትን የሙጥኝ ብሎ ከተበደለና ከተገፋ ሕዝብ ጎን መቆመን የሚያሳይ፤ ነፍስን እስከ ማጣት ድረስ ዋጋ የሚያስከፍል ተገቢ ውሳኔ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎን አቻዎቻቸው የሆኑት የሌሎች ቤተ-እምነት መሪዎች፤ እውነቱ አያወቁ እርሳቸው “የመጣው ይምጣብኝ!” ብለው ደፍረው ስለ ተበደለው ሕዝብ ሲናገሩና፤ ጦርነቱ ያብቃ፤ በደሉና ግፉም ያቁም በማለት ነፍሳቸውን ለሰይፍ ሰጥተው ሲናገሩ፤ ጭጭ ሲሉ ማየት፤ የሚያስተዛዝብና ከእምነታቸው ጋር ፊት ለፊት የሚላተም አድራጎት እንደ ፈጸሙ የሚያሳይ ነው። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ካርዴናል፤ በትግራይ ሕዝብና እርሳቸው እረኛ ሆኖው በሚመሩት የትግራይ የካቶሊከ እምነት ተከታይ በሆነው መእምን፤ ይኼ ያክል አስደማሚ ግፍ ሲፈጸምበት ጭጭ ማለታቸው፤ ቃለ እግዚአብሔር ከሚናገረው እውነት ጋር መጣላታቸው በግልጽ የሚያሳይ ነው። የእግዚአብሔር ቃል፤ ከተበደለና በግፍ ከተጠቃ ወገንና ሕዝብ ጎን መቆም የተገባ መሆኑ እንደሚናገርና እንደሚያሳስብ አጥተዉት አይደለም።

ጦርነት ሲታወጅና፤ ሰራዊት ለዉጊያ ሲተም፤ ቀድሞ “ገድ ይቅናህ፤ እግዚአብሔር መከናወኑን ይስጥህ!” በማለት መርቆና ባርኮ ሕዝብን በመናኛ ውኃ በማይቋጥር ምክንያት ለጥፋት መሸኘት ምንኛ የሚያሳዝን ነው? እንደ መሪ ምነዋ በዚህ ቀውጢና ፈታኝ ጊዜ አፍዎትን በእጅዎት ለመጫን ከጀሉ? በትግራይ ሕዝብ ላይ ጀርባና አካል ላይ የሚያርፈው፤ የአለንጋና የጅራፍ ግርፋት እኔ ላይ እንዳይዞር ከሚል ስጋትና፤ አልፎ ተርፎም በትግራይ ወጣቶች ግንባር ላይ አፈ-ሙዝ ተደቅኖበት ነድሎ ከሚሰረስረውና ከሚበታትነው አረር አንዱ ቢደቅኑብኝስ ብለው? እውነትና የራስ ፍላጎት ታግለው፤ እውነት ድል እንደ ነሳችው እንደ አቻዎት እንደ አቡነ ማትያስ ነፍስ፤ ነፍስዎት አውነትን የሙጥኝ ብላ መያዝ ለምን አቃታት? ጦርነትን ደግፎ ሕዝብ እየጠፋ ዝም ብሎ ማየትን፤ ወይስ ያላጠፋ ሕዝብ በግፍ እየተበደለ ነውና “ጦርነት ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ያቁም! “ በማለት ድምጽን ድምጽ ለሌለው ሕዝብ ማሰማትና መናገር? እግዚአብሔር “በጎቼንና ጠቦቶቼን አደራ ጠብቁልኝ” በማለት ታማኝ አድርጎ በሰጠዎት አደራ መሰረት፤ ምንም ጥፋት በሌለው ሚስኪን ሕዝብ ላይ እንዲህ ዓይነቱ ዘገናኝና አረሜናዊ በደልና ጥቃት እየተካሄደበት እያዩና እየሰሙ፤ እንዴት ዝም ማለትን መረጡ?

የወንጌላዊያን ሕብረት መሪዎችና ተውካዮችስ ምን ነካችሁ? ሠራዊትን ባርኮና መርቆ በደሉና ጥፋቱ በውል  ወዳላወቃችሁት ሚስኪን ሕዝብ መላክ ከምር መጽሐፍ ቅዱስ የሚደግፈው ነውን? እናንት የጽድቁ ንጉሥና የሰላሙ አምላክ መንጋውን ትንከባከቡለትና ትጠብቁለት ዘንድ የውክልና ስልጣና Deligated Authority የተሰጣችሁ አይደላችሁን? እርሱ በጽድቅ የሚፈርድ ጻድቅ፤ አባት ሌላችው አባትና የመበልቶች ረዳት ከሆነ፤ በጠርነቱ ጠንቅ አባት ላጡትና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው መበልቶችና በግፍ ለተደፈሩ ሔዋኖች ዘብ መቆም ሲገባችሁ ምንውሳ፤ ስለ በደላቸው ብዛት መጮኽ አቃታችሁ? ልጅ አባቱን እንደሚመስል፤ የእግዚአብሔር ልጆች ነን ስትሉ አባታችሁ መምሰላችሁ የቱ ጋር ይሆን? ያ ሁሉ አረሜናዊ በደል በሕዝቡ ላይ ሲወርድና የዎዩታው ድምጽ በዓለም ዙሩያ ሲይስተገባ ለምን፤ ምላሳችሁ ከጥርሳችሁ ኮርኒስ ወይም ጠራ ጋር ተጣብቆ ድርግም ብሎ ጠፋ? ለምን? አረ ለምን? ያኦርቶዶክሱ ፓትሪያክ በድፍረት አረሜያዊውን ግፍ እንዲያቆም ለዓለም ሲመጸኑ፤ እናንተ ለምን ዝም አላችሁ?

እስትንፋሰ እግዚአብሔር የሆነው የእግዚአብሔር ቃል፤ “እውነትን ታውቃላችሁ፤ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ይላል። አርነት የሚያወጣው እውነት በቃል የምናነበንበው ብቻ ሳይሆን፤ በአካቢያያችንና በዙሪያችን የሚሆነውን ተገንዝቦ ትክክለኛ እማኝና ምስክር ሆኖ መቆም ነው። እናማ የገዛ የአገራችን ሕዝብ ነው የምትሉትን የትግራይ ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ ዓይነቱ  ዘግናኝ፤ ዝቃጭና አረሜናዊ እርምጃ ሲወሰድበት “ምን ተዳየ!” ብሎ አፍን ለጉሞ ጭጭ ማለት፤ አርነት ከሚያወጣው እውነት ጋር ወግኖ መቆም ይሆንን? እውነትን አውቀዉትና አጣጥመውት መኖር በነጻነት መኖር መሆኑ ከዚህ ቁጥር እንኳን መገንዘብ አቅቶአቹሁ ይሆን? ለመሆኑ እናንተ የተበደለና አሳሩን እያየ ያለውን በጎናችሁ የሚኖር የገዛ ሕዝባችን የምትሉት ስቃይ፤ በቅርብ እያያችሁና እየሰማችሁ፤ ዝም ልትሉ፤ ያኦርቶዶክሱ ፓትሪያርክ ግን ነገሩ ከንክንዋቸው ብቻቸውን እንዲጨኹ ያደረጋቸው ዋናው ምክንያት ምን ይሆን?

እናንተ እስከ አሁን ድረስ “ሕግን ለመስከበር” በሚል መፈክር ሠራዊቱ ከሌላ ቂመኛና ወስላታ የጎሮቤት መንግስሥት ተቀናጅቶ ሕዝብ ሲጨፈጭፍ፤ ንብረት ሲዘርፍና ሲያቃጥል፤ መሰረተ-ልማቶችን ሲያወድም፤ እህል ሲዘርፍ፤ ሰብል ሲያቃጥል፤ ሕዝቡ እግዚአብሔር ይኖርበት ዘንድ ከሰጠው ከርስቱና ከጉልቱ በግፍ ነቅሎ በነቂስ ሲያባርረው፤ ሴቶቹን ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ እርኩሰት ሲያጨማልቃቸው፤ ለቀጣዩ ዓመት አርሶና አለስልሶ እህል ዘርቶ እንዳይሰበሰብ፤ ቀንበሩና ሞፎሩ ሲያቃጠልበት፤ ከ3000 ሺህ ሕጻናት በላይ ያለ አባትና ያለ እናት ብቻቸውን እንዲቀሩ ሲደረጉ፤ ትምሕርት-ቤቶች፤ ዩኒቨርሲቲዎች ሲዘረፉና ባዶ እንዲቀሩ ሲደረጉ፤ የጤና ጣቢያዎች ሕዝቡ በጤና እጦት እንዲጠፋ ሆን ተብለው ባዶ ሲደረጉ፤ ወጣቱ ግንባር ላይ አፈ-ሙዝ ደቅኖ ባሩድ በሚያሳዝን መልኩ ጭንቅላቱን ሰንጥቆ እንዲደፋ ሲደረግ አላወቃችሁም? አልስማችሁምስ? የገናናው አምላክ “የመንጎቼና የጠቦቶቼ ጠብቁልኝ” ጽኑ የአደራ ቃል የሚከበረው በዚህ መልኩ ነውን?

በ(ማቴ23፡24)ጌታ ኢየሱስ፤ “እናንት የታወራችሁ መሪዎች፤ ትንኝን አጥራታችሁ ትጥላላችሁ፤ ግመልን ግን  ትውጣላችሁ” በማለት እውራን መሪዎቹን ይወቅሳቸዋል። ቁጥሩ በትንሽና ጥቃቅን ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ አቢይና ትልቅ የሆነውን ነገር ገሸሸ የማደረግ አባዜ የሚያሳይ ነው። ትልቅና አብይ የሆነው የትግራይን ሕዝብ አንገብጋቢ አሬሜናዊ ኡኩይ ጥፋትና በደል ቸል ብሎ፤ ስለሚቀጥለው እሁድ የምሰባክ መዝሙርና ስብከት፤ ስለሚሰጠው መባና አስራት፤ ስርግና ሽኝት የእውራን መሪዎች ባሕሪና ተግባር ነው። እንዲህ ዓይኖቶቹ መሪዎች በጅምላ ከምድር ገጽ በቅንጅት (by design) እንዲጠፋ ስለሚደረገው ሕዝብ ቅንጣት ፍቅር የሌላቸው ናቸው። ፍቅር ትልቁና ዋናው እግዚአብሔርን የሚገልጽ ባሕሪ (attribute) ነው። ካለ ፍቅር የሚደረግ ማንኛውም ደቃቃ እንቅስቃሴና ልምምድ ደግሞ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የሌለውና ፋይዳ-ቢሰ ነው። ትንኝን ማጽዳት ፋይዳና ተቀባይነት የሚኖረው፤ በቅድሚያ  ትልቁን ግመልን ካልዋጡ ብቻ ነው። የዛሬዎቹ የእምነት መሪዎች በትግራዩ ሁኔታ አቋማቸው “ትንኝን የሚያጸዱ፤ ነገር ግን ግመልን የሚዉጡ አውራን” እንደ ሆኑ ቁልጭ አደርጎ አሳይቶአቸዋል።

እዚህ ላይ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት፤ “የትግራይ ሕዝብ ይሄ ሁሉ በደልና ፍዳ የደረሰበት፤ ወያኔ (TPLF) የስሜን ዕዝ ላይ ያደረሰበት ድንገተኛ ጥቃት ነው” በማለት ብዙዎች በመደጋገም የሚያነሱት ምክንያት ነው። “የሞኝ ለቅሶ፤ መልሶ መላልሶ” እንዲሉ፤ የእኚህ ሰዎች ለቅሶ ይህችውና ይችው ናት። ለሕዝብ ክብርና ፍቅር ያለው ሰውና በትክክለኛው የማሕበረ- ሳይንስ አስተምህሮ መሰረት፤ አንድን ሕዝብ በማንኛውም መስፈሪያና መለኪያ እንዲህ ዓይነቱ ዘግናኝና አሬሜናዊ ፍዳ ይቅርና፤ አፍንጫ እላፊ አንዲት ቡጢ እንኳን ልትሰነዝርበት አይገባም። በመሆኑም የፍልስፍና ድሕነት የተጠናወታቸው ስለሆኑ፤ “ደቀ-መዝምሩ እንደ መምሕሩ” እንደሚባል፤ እንደ ነውጠኛው ጭራቅ መሪያቸውሁ “የትግራይ ሴቶች የተደፈሩት በወንዶች ነው፤ የሰሜን ዕዝ ሠራዊት የተጨፈጨፈው ግን በሳንጃ ነው” በማለት ማላዘናችው መስማት ምንኛ የዘቀጡ መሆናችሁ ቁልጭ አድርጎ የሚያጋልጣችው ነው።

በትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰውና እየደረሰ ያለው አረሜናዊ እኩይ ግፍና ፍዳ የተፈጸመው TPLF በሰሜን ዕዝ በፈጸመው አግባብነት በሌለው እርምጃ ነው በማለት የምያሳቡቡት፤ ማንኛውም ጤና አእምሮ ያለው ስው የማይቀበለው ነው። ይህም ከላይ እንደ ተገለጸው፤ አንድ ሕዝብ ላይ ይኼ መሰሉን አሰቃቂና አስከፊ ጥቃት አልሞና አቅዶ ለመፈጸም የሚያስችል አንዳች አሳማኝና ተቀባይነት ያለው ምክንያት ሊኖር አይችልም ከሚለው እውነት በመንደርደር ነው።

ለመሆኑ የአማራ ክልል በተጋሩ ላይ አግባብነት የሌለው የግፍ እርምጃ የወሰደው፤ በትግራይ ላይ ጦርነት ከመታወጁ ከሦስት ዓመታት በፊት፤ የአማራ ክልል መሪዎችና ሊህቃኖቹ በጭፍንነትና በግፍ ከክልሉ ሃያ ሽሕ ተጋሩ ጠራርጎና ንብረቱን ሁሉ ነጥቀውና ቀምተው ወደ ሱዳን ሲያባርርዋቸውና ሲያስድድዋቸው አልነበረም እንዴ? “የወጋ ቢረሳም፤ የተወጋ አይረሳም” እንዲሉ፤የወጋችሁን ረሳታችሁታልና የረሳችሁትን ታሰታውሱ ዘንድ፤ ልንረሳ የማንችለው የተወጋነው ልናስታውሳችሁ በመፈለግ ነው። ይኼ ድርጊት የተፈጸመው በትግራይ ሕዝብ ላይ “ሕግን ማሰከበር” በሚል ስም፤ ዘርን የማጥፋት እርምጃና እናንተ “የሰሜን ዕዝ ጥቃት” በማለት ከምትጠሩት የሚቀድም መሆኑ ዘንግታችሁት ይሆን? በዚህ ወቅት ምንም እንኳ ምድራችሁ፤ ምድራችንና ወገናችን፤ መቃብራችሁ መቃብራችን ብሎ አምኖአችሁ ለበርካታ ዓመታት የኖረውን ሚስኪን ትግራዋይ ሰበብ ፈጥራችሁ ድንገት ስታባሩሩት፤ በትግራይ ይኖሩ በነበሩ አያሌ የአማራ ተወላጆች፤ ልዩ እንክብካቤና ጥበቃ ተደረገላቸው እንጂ አንድም ክፉ ጥቃት አልተወሰደባቸውም። “አንገት የተፈጠረው አዙሮ ለማየት ነው” እንደሚባል፤ ምነውሳ ዞር ብሎ ማየት እስኪያቅተው ድረስ አንገታችሁ ሰብቶ ደነደነ! ለምንስ ቀልበስ ብሎ የኋሊትን ማየት የተሳነው የብረት አንገት ሆነ?

ሌላው ይደረጋል ተበሎ የማይታሰብ ትዕይንት፤ በአማራ ክልል ወደ ትግራይ የፌደራል መንግሥት የሚቆጣጠረው አውራ-ጎዳና አረበኞቻችሁ ፋኖዎች ከሁለት ዓመት በላይ ዘግተውት በትግራይ ሕዝብ አንገት ላይ ሳንጃ የሻጡት በአገሪቱ መሪ ተብየና በሊህቃናችሁ ይሁንታና ተቃባይነት በማግኘቱስ አልነበርምን? ይሄ አረሜናዊ ግፍ በሰሜን ዕዝ ተፈጸመ ከምተሉት ጥቃት የውሸት ፈጠራ ትርክት በጊዜ አይቀድምምን? በይዘቱስ? መሣሪያ ታጥቆ ለሞት የተዘጋጀ ሠራዊት ሰይፍ ቢሚዘዝበት ይከብዳል ወይስ፤ ሕዝቡ ይጠብቀኛል ብሎ ግብር ከፍሎ ባሰለጠነውና ባቆመው የገዛ ሠራዊቱ በአንገቱ ላይ ሳንጃ ሲሽጥበትና ታይቶ የማይታወቅ መዓት ሲያወርድበት?

ከባዕድ ቂመኛ እወሬ ጎሮቤት መንግሥት መክሮና ዘክሮ በሚያሰቀቅ መልኩ ሕዝቡን ሲገድለውና ሴቶችን ተደርጎ በማያታወቅ ሁኔታ  ሲያጨማልቃቸው፤ አባት ዓይኑ እያየ ወጣት ሴት ልጁን በመፈራራቅ ሲደፍሯት፤ ሕዝቡ በርሃብ ያልቅ ዘንድ የእርሻ በሬዎቹን ከፊቱ አርድው ሲኮመኩሙ፤ የገበሬው እህል ከጎተራው ተዘርፎ በገዛ የጋማ ከበቶቹ ተጭኖ ሲወሰድ፤ በማሳው የነበረው ሰብል በእሳት ሲያጋዩት፤ ከቅም አያት፤እስከ አያትና ከትውልድ ወደ ትውልድ፤ ተደላድለውና ተመችቶአቸው ይኑሩበት ከነበረ ከርስታቸውና ከጉልታቸው፤ ከቀያቸው፤ ከሞቀ ቤታቸውና ጓዳቸው በጭካኔ አባራውና አፈናቅለው፤ የገዛ ወገኖቻቸቸውን ከጎንደርና ከጎጃም በመቶ ሽዎች ጠርተው ማስፈር፤ ከምር በመደጋጋም ከሚነሳው  ውሃ  ከማይቋጥር አንካሳ  “የስሜን ዕዝ ጥቃት” ጋር የሚነጻጸር ነውን??

የውጭው  ዓለም በትግራይ የምትፈጹምትን ዘገናኝ ግፍ እንዳይሰማና እንዳያውቅ፤ ሁሉንም የመገናኛ አውታር ጥርቅም አድርጎ ሕዝቡ መተንፈሻና መላወሻ እንዲያጣ አድርጎ ማደቀቁስ በስሜኑ ዕዝ ጦራችን ጥቃት ደርሷል በማለት ደጋግማችሁ ለምትለፉፉትና ለምትደሶኩሩት ማካካሻና ማወራራጃ ነውን? በሰሜን ጦር ጦስ ይህ ሁሉ ሆነ የሚለው  ልብ-ወለድ ትርክታችሁ፤ ትግራይን ቀድማችሁ ለማጥፋት ከጭራቁና ሰው በላው የኤርትራ መሪ፤ የአማራ ክልልና ሊህቃን በጥቂቱም ከሶማሊያው መንግሥት ከሁለት ዓመት በላይ የዶለታችሁት የጥፋትና ዘርን የማጥፋት ሴራ ዝግጅታችሁን የመለኮሻ ክብሪት አድርግችሁ የሰሜን ዕዝን ጥቃት አቀረባችሁ እንጂ፤ አመክንዮታችሁ በሃቅ ላይ ጸንቶ ከቶ የማይቆም ተልካሻና ሰንካላ ነው።

የትግራይ ሕዝብ ንብረት ከትንሽ እሰከ ትልቅ ወደ ጎጃም፤ ጎንደርና አዲስ አበባ፤ ብሎም ወደ ኤርትራ ዘርፎ መውሰዱስ የሰሜኑ ዕዝን ጥቃት አጸፋ ለመውሰድ ይሆንን? ይች አበሰኛዋና መዘዘኛዋ የሴሜኑ ዕዝ ጥቃት ምን ያክል ትመነዘር ትሆን ጃል? የትግራይ ሕዝብ እግዚአብሔር ከቸረው ርስትና ጉልት ተነቅሎ አንድም ሳይቀር እስኪጠፋ ድረስ ይሆን?

ለመሆኑ የግድያ ግብረ አበራችሁ፤ ከኢትዮጵያ ጋር ታርቄአለሁ ያለው ለበርከታ ዓመታት ለመግዛትና ለመርገጥ ሲቋምጥላት የነበረቸውን አገር፤ እግሩ የረገጠ እለት “Game Over” በማለት የጮኾው ምንን የሚያሳይ ነው? ከዚያ በኋላስ የሶማሊያው ግብዝ መሪ ፎርማጆን ጨምሮ በምልልስ፤ በአማራ ከተሞች፤ በሞቃዱሾና በአዲስ አባባ ይደረጉ የነበሩ ምክክሮች በትግራይ ላይ የተዶለቱ ጥፋቶች አልነበሩምን? የአገሪቱ መራሄ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የደረሰው የአንበጣ ተፈጥሯዊ አደጋ፤ ትግራይን ከወሎ የሚለየውን ቀጭን መሬት ነጥለው፤ ወሎ ላይ የመከለከያ ኬሚካል ሲረጭ፤ በትግራይ ላይ ግን “አንበጣም ከእኛ ጋር ተደመረ” በማለት በመርዘኛ የእፉኝት ቃላቸው ሲነድፉትና እግዚአብሔር የጥፋታቸው ግብር አበርና ተባባሪ አድርገው ሲሳለቁበት፤ የትግራይን ሕዝብ ቅቤ ማጠጣት ነውን? ማንም ሊሰጠውና ሊነሳው የማይችለው የማይገደብ እስከ መገንጠል ድረስ መብቱ ለሆነው ለትግራይ ሕዝብ፤ ለምን ምርጫ አካሄደ? ብሎ የተረጨው “ቆዩ እናቶች ካላዘኑ፤ ልጆች ያለ ወላጅ ካልቀሩ፤ አዛውንቶች ያለ ጧሪና ቀባሪ” በሚል ቀድሞ በተነገረ ዛቻ መሰረት አይደል እንዴ በትግራይ ላይ ጦርነት የታወጀው? ይሄ ሁሉ ትእይንት ጦርነቱ በይፋ ከመጀመሩ በፊት የታየ መሆኑ ካልተካደ፤ እንዴት ነው፤ ለትግራይ ሕዝብ አሳርና አበሳ መንስኤው የስሜን ዕዝ ጥቃት ነው ሊባል የሚችለው?

በተጨማሪም የትግራይ ቴክኖክራቶችና ባለስልጣናት እየለዩ ማሰርና መግደል (የተገደሉት የትግራይ ጄነራሎች ልብ ይሏል) እንዴት ሊብራራ ይችላል?  በትግራይ ልማት ተሰማርተወ ከፍተኛ ሥራ የነበራቸው የውጭ በለሞያተኞች፤ ከቦሌ ወደ ትግራይ እንዳይገቡ መከልከሉስ እንዴት ይታይ ይሆን? የኢትዮጵያው መሪ በኤርትራው የውትድርና ማሰልጠኛ ማለትም በሳዋ፤ በሰለጠኑት ወታዶሮች ምረቃ መገኘትና፤ የኤርትራው መሪ፤ በደብረ ዘይት የአየር ሃይል መገኘትስ ከቶውኑ ምን የሚያሳይ ነበር? እንዲህና እንዲያ እያሉ አያሌ ገሃድ የሆኑ የጦርነቱ ፊታውራሪ ምልክቶች ቀራርሞና አሰባስቦ ማቅረብ የሚቻል ቢሆኑም፤ መስሚያ ጀሮ ያለውና በቅንነት ለሚያስብ እኚህ ከበቂም በቂ ናቸውና፤ ጀሮ ያለው ዛሬ ይስማ እያለኩኝ የብዕሬ ፈሳሽ ከሚፈሰው እንባዩ ቀላቅየና፤ ስለ ተበደለው ሕዝቤ እያማጥኩና በሶቆቃ ላይ ሆኜ የከተብኩት እንደ ሆነ ይታወቅልኝ

እግዚአብሔር ትግራይን ከመከራዋ ይገላግላት፤ ማንም ረዳት የለምና!!!

ጌታ ሆይ! የትእቢቶኞች ክንድ ስበርና ቀለጣጥም!

የትምክሕተኞችም የወገባቸው ጅማት ፍታና አላላ!

ማስተዋል ላጡትም የልባቸው ዓይን አበራ ጆሮአቸውም ክፈትና በእውነት ላይ እንዲቆሙ እርዳቸው!! አሜን!!!

Full Website