ከወጋሕታ ብርሃን መጋቢት 2012

ከሳላሳ ዓመታት ጦርነት በኃላ በሪፍረንደም ከኢትዮጵያ ነፃነትዋን ያወጀችው ኤርትራ ህዝቡ በከፈለው መስዋዕትነት ልክ እስካሁን ድረስ የተመኘውን አላገኘም። በትግሉ ያረጋገጠውን ነፃነት የኢሳያስ አፈወርቅ ቡዱን በጉልበትና በማን አለብኝነት ስሜት ስልጣን ላይ እንደወጣ አለ፡፡ እስካሁን የህዝቡ ጥያቄዎች የሆኑት የህገመንግስት ጥያቄ እና የምርጫ ጥያቄ አልመልስም ብሎ ጭራሽ ስልጣን ወይም ሞት ብሎ ለነፃነት ብዙ መስዋዕትነት የከፈለ ህዝብ ለሌላ ሳላሳ ዓመታት ጭቆና ዳርጎታል።

ኢሳያስ አፈወርቅ የሃገረ ኤርትራ ስልጣን እንደያዘ ኤርትራን የአፍሪካ ሲንጋፖር እናደርግታለን ብሎ መጀመርያ ላይ ምኞቱን ቢገልፅም እንኳን ኤርትራ ሲንጋፖር ለማድረግ የሚያስችለው የፖሊሲ  ዕቅድ ይሁን የፕሮግራም ስትራተጂ አልነበረውም። ሌላው ይቅርና የነፃነት ትግሉ በጎ ነገሮችም ይዞ መቀጠል አልፈለገም፡፡ ስልጣን እንደያዘ ወዲያውኑ ያደረገው ነገር የኤርትራን የነፃነት ትግል መርቶ ለውጤት ያበቃውን ድርጅት ማዳከም ነበር፡፡ ሕግሐኤ (ሻዕብያ) ምንም ጉባኤ እንዳያካሄድ ማድረግ፣ ሌሎች ፓርቲዎች እንዳይደራጁ መከልከል፣ ከመንግስት ሚዲያ ውጭ ምንም አይነት ነፃ የሆነ የግል ሚድያ እንዳይኖሩ ማድርግ እና . . . ወዘተ አድርጎ የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭ ስርዓት የሰፈነባት ኤርትራ ፈጠረ። የኤርትራ ህዝብ እንደሚለዉም ትግርኛ የሚናገር የደርግ ስርዓት ተመለሰ፡፡

የአለም ህዝብ እንደሚያስታውሰው ኤርትራ ነፃ ከወጣች ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ የመጀመርያ ተቃውሞ ለአቶ ኢሳያስ ገጠማቸው፡፡ በነፃነቱ ትግል ጊዜ አካላቸው የጎደሉ ነባር ታጋዮች ሰላማዊ የተቃውሞ ጥያቄ በማቅረባቸው በኢሳያስ መንግስት ያለ ርህራሄ በጥይት ተጨፈጨፉ። ይህንን ተከትሎ በትግሉ ወቅት የከባድ መሳርያ ተካሽ የነበሩና ልዩ የሰራዊት አካል የነበሩ የአስመራ አየር ማረፍያን በመቆጣጠር በጥድፍያ የተደራጀ ተቃውሞ በማሰማት ኢሳያስ አፈወርቅ እንዲያነጋግራቸው ጠየቁ። አቶ ኢሳያስ ጉዳዩን እንዲቀለብሱ ሌሎች የጦር አመራሮች ቢልክም ተቃውሞ ያሰሙት የሰራዊቱ አባላት የተላኩት የጦር አመራሮች ለማናገር እምቢ በማለታቸው ኢሳያስ ተገዶ በአስመራ ስታድዮም የሰራዊት አባላቱን ሰብስቦ ጥያቄያቸውን ለመስማት ተገደደ። በዚህ ስብሰባ ነገሩ አቀዝቅዞ በተቃውምው መሪዎች ላይ ጥናት በማካሄድ በመቶዎች የሚቆጠሩ በማሰርና በማሳደድ እና ግድያ በመፈፀም ስልጣኑን አራዘመ።

ኤርትራውያን እንደሚሉት ኤርትራ የተስፋይቱ ሃገረ ሲንጋፖር ሳትሆን የአፍሪካ ሰሜን ኮርያ ሆነች። ሚሳይል ባይኖራትም፡፡ መላው የኤርትራ ወጣት ወታደር በማድረግ ከሳውድ አረብያ በስተቀር ከሁሉም ጎረቤቶችዋ ጋር ጦርነትና ግጭት ውስጥ ገባች። ከየመን፣ ከጁቢቲ፣ ከሱዳን እና በስተመጨረሻም ከኢትዮጵያ ጋር ተጋጨች። አቶ ኢሳያስ የውስጥ ጉዳያቸው ትተው በውጭው በጎረቤቶቻቸው ጉዳይ መፈትፈት ዋናው ስራቸው አደረጉ። በዚህ የተከፉ ነባር የነፃነት ታጋዮች  በተከታታይ የአገሪትዋ ዕጣፈንታ ጉዳይ ለመወያት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ሁሉም እስራትና ግድያ ገጠማቸው። ከደርግ ምን ይጠበቃልና፡፡

የኤርትራው መሪ ኢሳያስ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ በመፈፀም አስከፊ ውጤት የነበረው ጦርነት በሁለቱ አገሮች ተካሂዶ፡፡ በአልጀርስ ስምምነት ጦርነቱ ቆመ። የተባበሩት መንግስታት ታዛቢ ጦር በኤርትራ ግዛት ውስጥ ገብቶ የሁለቱ አገሮች ዳርድንበር የፀጥታ ሁኔታ እንዲታዘብ ኢሳያስ ሳይወድ ተቀበለ። ከጦርነቱ በኃላ በነፃነቱ ትግል ወቅት ትልቅ ሚና የነበራቸው ከፍተኛ የኤርትራ አመራሮች ኢሳያስን ስለ ጦርነቱ ሁኔታ እንገምግም ብለው አጥብቀው ቢጠይቁትም አሻፈረኝ በማለት እምቢ አላቸው። በደብዳቤም በሽምግልናም ቢጠይቁትም ለውይይት ዝግጁ ሳይሆን ቀረ። መድረክ የተከለከሉት አመራሮች በየግላቸው በተገኙ የሚድያ አውታሮች ለውጥ እንደሚያስፈለግ፣ ተረቅቆ የነበረው ህገመንግስት ተግባራዊ እንዲሆን፣ የምርጫ ስርዓት እንዲኖር፣ የመደራጀት መብት እንዲፈቀድ፣ ፓርቲዎች እንዲኖሩ እና  ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገው ጦርነት አጀማመሩ፣ አመራሩና ጠቅላላ አያያዙ መገምገም እንዳለበት ገለፁ። በዚህ የተበሳጨው ኢሳያስ ሁሉንም ተቃውሞ ያሰሙትን አመራሮች  ከየቤታቸው በመልቀም  ምንም የፍርድ ስርዓት እንደያገኙ በማድረግ በረሃ በሚገኝ በማይታወቅ ቦታና ህጋዊ ባልሆነ እስር ቤት አጎራቸው። በአሁኑ ሰዓት አብዛኛዎቹ ከምድር በታች በተሰራ እስር ቤት ታስረው መኖር ስላልቻሉ በበሽታ እየተሰቃዩ ለሞት ተዳርገዋል። የቀሩትም ስቃያቸው ረዝሞ ሞታቸው እየጠበቁ ነው። ከዚያን ግዜ በኃላ በኤርትራ ሰላማዊ ጥያቄ የሚባል ነገር ተስፋ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ ተደመደመ። የኤርትራ ሰራዊት ሁሉ ነገር ሲጨልምባቸው በሜካናይዝድ ክፍለጦር አዛዥ የተደረገው በታንኮች የተደገፈውና በአስመራ በሚገኘው የቴሌቭዥን ጣቢያ በመቆጣጠር ተጀምሮ የነበረ ተቃውሞ ብዙም ሳይገፋ በአጭሩ ተቀጨ።

የኤርትራ ወጣት ለኢስያስ ትልቅ ተቃውሞውን የሚገለፀው አገሩን ቀየውን ጥሎ በመኮብለል ሆነ። በመቶ ሺዎች ብዙ ሺ ከፍለውና ሂወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ወደ ጎረቤት አገሮች ተሰደዱ። ያልቀናቸው ተይዘው ታሰሩ። የደጋገሙ ተይዘው ተረሸኑ። ለዓመታት ይህ ክስተት ቀጠለ። ወጣትዋን ለሰሃራ በርሃ፣ ለሰውነት አካላት ነጋዴዎችና ለሚድትራንያን ባህር ሻርኮች በመስጠት ወጣት አልባ ኤርትራ ተፈጠረች። ኢኮኖሚዋ ምንም ስርዓት የሌለውና ከጦርነቱ በኃላ ምንም የልማት ስራ የቆመባት አገር ሆነች፡፡ ኢሳያስ ለዚህ ተጠያቂው ወያኔ ነው እያለ የዘመን መለወጫ፣ የነፃነት ቀንና የሰማዕታት ቀን ተብሎ በሚያደረገው የበዓል ንግግሩ ያለመታከት ሳያወሳ የቀረበት ቀን የለም።

ኢሳያስ ከዚህ የተሳሳተ አስተሳሰቡ ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራተጂ ዋነኛው አጀንዳውና ስራው አድርጎ ተያያዘው፡፡ በኢሳያስዋ ኤርትራ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ነን የሚሉ ሰብስቦ በመያዝና ከሶማሊያም አልሸባብንም በመያዝ ስልጠና፣ ትጥቅና ስንቅ በማቅረብና በማሰማራት ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ነበር። በኢትዮጵያ የነበረው ግብረ መልስ ውጤታማ ስለነበረ እነዚህ የተላላኪ ስብስቦች የኤርትራ የሞተውን ኢኮኖሚ ከመጋጥ ውጭ ኢሳያስ የረባ ጥቅም ሊያገኝባቸው አልቻለም ነበር። የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ነን ተብየ ተላላኪዎችም በውስጣቸውም በየጊዜው ሲፈጠር የነበረ ልዩነት ለመፍታት የኢሳያስ ደህንነቶች ጊዜ የገደለ ስራ ነበር። ለማተራመስ የተሰጣቸው ፈንጂዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደገባ ሳይጠመድና ሳይተኮስ አብዛኛው በኢትዮጵያ የፀጥታ አካላት እጅ እየገባ ጌቶቻቸውን ቅር ሲያሰኙ ቆይተዋል። ከኤርትራ ድንበርም ተሻግረው ኢትዮጵያ እንደገቡ የረባ ስራ ሳይሰሩና ምንም ጊዜ ሳይቆዩ በህዝብ፣ በሚሊሻና በመንግስት የፀጥታ አካላት ተከበው ተማርከው ዕድሜያቸው እያጠረ ኢሳያስ ሲቸገር ነበር። ከሁሉም በላይ ኢሳያስን ቆሽቱ ሲያቃጥለው የነበረ ጉዳይ ፈንጂ ይዞ እጅ ከፍንጅ የሚያዘው፣ ተከቦ ድንበር ላይ የሚማረከው ተላላኪው ወይ ደግሞ በሶሞሊያም ሞቃዲሾ የሚያዘውን አልሸባብ አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ለሚድያ ከሚያቀርባቸውና ከሚያጋልጣቸው ተላላኪዎቹ በላይ የኢትዮጵያ መንግስት ለተባበሩት መንግስታት የኤርትራና የሶማሊያ ተቆጣጣሪ አካል እየሰጠ ማዕቀብ እንዲደረግበትና ማዕቀቡ እንዲራዘም እያደረገ የነበረውን እንቅስቃሴ ነበር። እዚህ ላይ ኢሳያስ እየላካቸው እንደገቡ ሳይሰሩ ሲያዙበት የነበረ ሚሲጥር ለምን እንደነበረ አሁንም ማወቅ የቻለ አይመስለኝም። ነገር ግን ዕድሜ ለኮ/ል ዓብይ ቂም በቀሉን ግን ተወጥቷል ባይ ነኝ። እንዴት?

የኢሳያስ መንግስትና የኢሳያስዋ ኤርትራ በዚህ አገር በማያሰኝ ጠብጫሪ ሁኔታቸው ከሁሉም የዓለም አገሮች ተነጥለው ለብዙ ግዝያት ቆይተው ነበር፡፡ ብቸኛው ወዳጃቸው ኮ/ል ጋዳፊ  ሊቢያ በቀለም አብዮት ከታመሰች በኃላ በመሞታቸው ብቻቸውን ቀርተው በሳህል የበርሃ ስርዓት አገሪትዋን ማስተዳደር ተስኗቸው ዛሬ ነገ ኤርትራ ትበተናለች ሲባል እያለ አዲስ ሁኔታ ተፈጠረ።

ይህም በኢትዮጵያና በሱዳን የተካሄደው የቀለም አብዮት ቀድሞ ለውጥ በመምጣቱ ኢሳያስ በለስ ቀንቷቸዋል፡፡ ኤርትራም በጣም የከፋ ሁኔታ ላይ ብትገኝም አቶ ኢሳያስ ማደንዘዣ መድሃኒት በማግኘታቸው ዕድሜያቸው ረዝሞ በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ የራሳቸው ጥረት እስኪመስላቸው ድረስ ራሳቸውን ሲያሞኙ እያየን ነው። ኢሳያስ በጦርነት ውስጥ ነን እያሉ የኤርትራን የኢኮኖሚ ልማት ሲገድሉ፣ በተቃራኒው አቶ መለስ ከኤርትራ ጋር በጦርነት ላይ ነንና መጀመርያ ሰላም ይሁን ሳይሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ዋናው ጠላት ድህነት ነው በማለት በድህነት ላይ  ጦርነት ከፍተው በኢኮኖሚ ድል ላይ ድል ተቀዳጅተው ባፈሩት ሁለገብ ልማት ላይ የኤርትራው ኢሳያስ ኢትዮጵያ ውስጥ ተገኝተው አይናቸውን በጨው አጥበው የልማት ስራዎች ለመመረቅ በቁ። የኤርትራ ህዝብም በድንበርም በአውሮፕላንም ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ባየው ልማትና እድገት ማመን አቃተው፡፡ ተደመመ፡፡ ኤርትራ ኢትዮጵያ ካሳየችው የልማትናየእድገት ጎዳና አንፃር የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል እንኳን ለምን አልለማችም ብሎ ለመጠየቀ ተገደደ፡፡ በኃላም ለካ ኢሳያስ ነጋጠባ እንደሚሰብከው ጠላቱ ወያኔ ሳይሆን የኢሳያስ መንግስት ራሱ መሆኑ ተገነዘበ፡፡ ኤርትራ ለዚህ ልማት አልባነት የዳረጋት ምክንያት የኢሳያስ ፀረ ህዝብነት መሆኑ በሚገባ መገንዘብ ጀመረ። ኢትዮጵያ ውስጥ ልማት ብቻ ሳይሆን የሚጠይቅ ህብረተሰብም መፈጠሩ አየ፡፡ በመሆኑ ደፍሮ መናገርም እንደሚቻል ተምሮ እንደ ኢሳያስ አገላለፅ ‘መቅበጥ’ በመጀመሩ ኢሳያስ ብዙ ሳይቆይ ደንበሩን ያለምንም መግለጫ ዘጋግተ አረፉ። ግንኙነቱ በህዝቦች መካከል መሆኑ ቀርቶ በኢሳያስና በኮ/ል ዓብይ መካከል ሆነ ቆይቶ ነበር።

አሁንም ኢሳያስ ከኢትዮጵያ ጋር የነበረው ችግር ተፈቷል ቢልም ወጣቶችን መግፈፍና ሳዋ ማሰልጠኛ መላክ አላቆመም። ሰራዊቱ ማደራጀትና ስልጠና መስጠትም አላቃረጠም። ኤርትራ ውስጥ ወጣት ማለት ወታደር ማለት ሰለሆነ ወጣቱ በገፍ አገሩን ጥሎ መኮብለልና መሰደድ እስካአሁንዋ ሰዓት አላቃረጠም። የሚሰደደው ቁጥሩ እየጨመረ አንጂ እየቀነሰ አይደለም። የኢሳያስ ሰራዊት ተራ ተዋጊ የሚባለው በሙሉ መኮብለል ተያይዞታል። ቆራጡ መሪ ኢሳያስም ቀልድ አያቁምና ግፋ እንዲካሄድ አድርገው ወዲያውኑ እንደ ኮሮጆ ሲጎድል እንደምትሞላው አይነት ይሞሉታል።

ከቅርብ ግዜ ወዲህ ኤርትራ ውስጥ የሰራዊትም የህዝብም ስብሰባዎች በሰፊው እየተካሄዱ ነው። ኢሳያስ ለመጀመርያ ጊዜ ተንቀዋል። በሰራዊትም በህዝቡም የሚነሱ ጥያቄዎች ከዚህ ቀደም በኤርትራ ያልተለመዱ ናቸው። የኤርትራ ዲያስፖራ በመላው ዓለም ‘ይአክል’ /ይበቃል/ በሚል መፈክር ሲያደርገው የነበረ ተቃውምና ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች በሙሉ በድፍረት በየስብሰባው እየተነሱ ናችው፡፡ ስብሰባ መሪዎቹ የሚመልሱት ሲያጡ ይህ ከኛ በላይ ነው እስኪሉና ስብሰባዎች ሲቋረጡ ታይተዋል። ከፍተኛ ተቃውሞ ከገጠማቸው ጉዳይ አንዱ ስለ ኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ነው። ግንኙነቱ ለምን በዝርዝር በግልፅ ለህዝብ ይፋ አይሆንም? ከአቅራቢያችን ከትግራይና ከአፋር ህዝብ ያለን ዝምድናና መቀራረብ ትታችሁና እየዘለላቹህ ለምን አዲስ አበባ፣ ጎንደርና ባህርዳር ትሄዳላቹህ? ግንኙነቱ ለምን ህዝብ ለህዝብም አይሆንም? ለምን ድንበር ተዘጋ? የሁለት መሪዎች ግንኙነት ብቻ ሆኖ ለምን ቀረ? ኢሳያስ በንግግሩ ኮ/ል ዓብይ ምራን ለምን ይላል? ሁለት አገር አይደለንም እንዴ? ባለፉት ዓመታት ኤርትራውያን ብዙ ስቃይ አሳልፈን እያለን በኢትዮ-ኤርትራ ግንኝነት መሻከርና ጦርነት ወቅት የከሰርነው ነገር ያጣነው ነገር የለም እንዴት ይላል? በጦርነቱ ያለቀው ወጣትስ? በስደት ምክንያት የሰሃራና የሜድትራርያን ባህር የዋጠው ወጣትስ አላጣንም? አልከሰርንም? የሚሉ ጥያቄዎችን ጠይቃል።

የኢሳያስ ባለስልጣናት በተለይም ስለ ድንበሩ ተጠይቀው የመለሱትን መልስ አጥብቆ ተቃውሟል። ይህም የኮ/ል ዓብይ መንግስት ሰራዊት አንስቶ መሬታችንን ለማስረከብ ዝግጁ ነው። እያደናቀፈ ያለው ወያኔ ነው። ከምርጫው በኃላ ኮ/ል ዓብይ ካሸነፈ እንዲያሸንፍም ሙሉ ዓቅማችንን ተጠቅመን እየሰራን ነውና ያሸንፋል ያኔ ሁሉ ነገር ያስረክበናል። ካላስረከበንም ተዋግተን መሬታችንን እናስመልሳለን የሚለውን መልስ ሰራዊቱም ህዝቡም በጥብቅ እየተቃወመው ነው። የኢሳያስ ባለስልጣናት ኮ/ል ዓብይ እንዲያሸንፍ ወይደግሞ ሌላው ተልዕካቸው ለማሳካት ሙሉ ዓቅማቸው ተጠቅመው እየሰሩ መሆናቸው መግለፃቸው ሀቅ ነው፡፡ ኢሳያስ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሀዋሳና ባህርዳር ቢሮ ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ፀሐይ የሞቀውና ከሊቅ እሰከ ደቂቅ የሚያውቀው ነውና። ለተቃዋሚ ድርጅቶች ቢሮ ለመክፈትና እንደልባቸው ለመንቀሳቀስ የማይፈቅደው የብልፅግና መንግስት የኢሳያስ ድህንነቶችና የሰራዊት መረጃ ሰራተኞቻቸው እንዳሻቸው በመላ አገሪቱ በነፃ እንዲንቀሳቀሱ ፍቃዱ ሰጥቶቸዋልና።የኤርትራ ህዝብ ተቃውሞ አፍኖ የሚገኘው ኢሳያስ የራስዋ አሮባት የሌላ ታማስላልች እንደሚባለው በኢትዮጵያ ጉዳይ ዝም ማለት አልችልም ብሎ ያለ ምንም ሐፍረት በአደባባይ እየገለፀ ያለበት ጉዳይም ከምን እንደሚመነጭ ለመገመት አይከብድም።
Full Website