ህወሓት፡- አዎ! የቤተሰብ ስብስብ ነው።

ሓዱሽ ንጉሰ (አግረሲቭ)

ከጅዋቆ ተንቤን ትግራይ

ጥር 2012

የህወሓት 45ኛው ልደት በሚቀጥለው ወር የካቲት 11 ሊከበር ነው። 40ኛ የልደቱ በዓል በድምቀት ነበር የተከበረው። ከሁሉም የአገራችን ክፍሎች የተውጣጡ አርቲስቶች ተሳትፈው ነበር። ወቀሳው ይህ ሁሉ ደማቅ ታሪክ ለምን ደበቃቹሁት? ስንት መፅሐፍና ፊልም ይወጣው ነበር የሚል ነበር። ያኔ ወቀሳው ትክክል ነበር ከልብ ስለነበር። ብዙ ሳይቆይ ግን ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ የነበረው ፀረ ህወሓት እንቅስቃሴና ስድብ ነው የቀጠለው። ምስኪኑ ሠራዊት ፍቅሬ ለይተው በኤል ቲቪ ምርመራ ተደርጎበታል። ለምን ሄድክ? ለምን አደንቅክ? ተብሎ።

የህወሓት 45ኛው ልደት ሲናከብር ቀጥሎ ያለውን ሃሳብ በማንበብ የካቲት 11 ምን እንደሆነ ለመረዳት ይጠቅማል በሚል ነው።

ህወሓት ያልተሰደበው የስድብ ዓይነት የለም። ከሁሉ የሚያስቀኝ ስድብ ግን ወያኔ የቤተሰብ ስብስብ ነው የሚለውን ነው። ለተሳዳቢዎቹ ስድብ ይመስላቸዋል። ወያኔ ማለት ስድብ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ። ስድብ ማለት የሚያም፣ ስሜትን የሚጎዳ፣ በተጫባጭ ደግሞ የሚሰደበው አካል ስህተቱንና ጥፋቱን የሚነግርና የሚያጋልጥ መሆን ሲችል ነው። ፋሽስት ያልሆነን ፋሽስት ብትለው ሰደብከው ወይም አጋለጥከው ማለት አይደለም። አንድ ምሳሌ እንይ። አብይ አህመድ ስልጣን እንደያዘ ይህ ሰው ፀረ ህዝብ ነው። ፀረ ኦሮሞ ህዝብ ነው። ሲባል ማንም ሰሚ አልነበረም። ያኔ ይህን ያሉት ከሰውዬው ባህሪ ተነስተው ነበር። ነገር ግን ሊህቁና ህዝቡ በተግባር ስላላየ አልተቀበለውም። እንዲያውም መሲህና የለውጥ ሰው ተደርጎ ማንም አይንካው፣ እሱን የሚነካ ጠላታችን ነው ብሎና ደግፎ መንበረ ስልጣኑን ላይ ተደላድሎ እንዲጨብጥ አደረገው። አሁን ደግሞ ከእንቅልፉ ሲነሳ የካበውን መልሶ እንዴት አድርጎ ከፊቱ እንደሚያርቀው ጨንቆታል። አሁን አብይ ጨፍጫፊ ቢባል የኦሮሞ ህዝብ ይቀበለዋል። በተለይ ወለጋ የሚኖረው ኦሮሞ በየዕለቱ እያየው ስለሆነ ጨፍጫፊ ብቻ አይገልፀውም ብሎ ሌላ ስድብም ይጨምርበታል። የደርግ ቡችላ፣ የፈረንጅ አለቅላቂ ይለዋል። ይህ ደግሞ ስለሚገልፀው በሚስማር እንደተያያዘ እንጨት ወይም ቆርቆሮ ውስጥ ደርሶ ሰርስሮ ገብቶ ያመዋል። ያንተ ያልሆነ ታሪክ ወይም ጥንካሬህን የሚገልፅ ወይም ማንነትህን የሚገልፅ ግን ስድብ ሊሆን አይችልም። ሰለዚህ ተሳዳቢዎች ሆይ ስድብ አይደልም፡፡

ህወሓት አዎ! የቤተሰብ ስብስብ ነው። የአድዋ ከተማ ሰው ብቻ የተሰባሰበበት ድርጅት ነበር። በተለይ በመጀመርያው የትግሉ ዓመታት ድርጅቱ የአድዋ ሰው ይበዛበት ነበር። አዎ! ይህ ማለት በዛ ወቅት የተሰውት የህወሓት ታጋዮች የዚህ ከተማ ጀግኖች ወጣቶች ናቸው ማለት ነው። ከማል፣ ሓየት፣ ቡሽራ፣ ወዲረታ፣ አወጣህኝ፣ ወዲ ሓጎስ፣ አፅብሃ (ሸዊት) ወዲ ዳኛው፣ ዳንኤል ጅፊዒት፣ ተኽሉ ሓዋዝ፣ ማለፍያ፣ ጋል ጥረጨው (ርግበ) . . . ወዘተ ከዛች ትንሽ ከተማ ብዙዎች በለጋ ዕድሜያቸው ከትምህርታቸው፣ ከሞቀ ኑራቸውና የከተማ ህይወት ይልቅ ለዓላማ ብለው “ፈቖዶ ሽንጥሮ’’(በየ ሸጡ) እየዘመሩ ቀሩ። እናት አባት የቀሩት ያልታገሉ ወንድምና እህት ካሏዋቸውም ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ለህዝባዊ ዓላማ አስቀድመው ላይመለሱ ‘ይህ ነው ሞት!’ ብለው የመረጡትን ዓይነት ሞት መርጠው ተሰው።

ቤተሰብ ማለት የአንድ ከተማ ልጆች አብሮ አደጎችንም ሊያጠቃልል ይችላል። ግን ስለ ከአንድ ቤት ከአንድ እናትና አባት የወጡ ቤተሰብ ነው ወያኔ የምትሉ “ተሳዳቢዎች” አቦይ ስብሓትና እህታቸውን ቅዱሳን፣ አባይ ወልዱን ወንድሙን አውዓሎምን፣ ባለትዳሮችም ቆጥራቹሁ መለስና አዜብ፣ አርከበና ንግስቲ (የብርሃነ ገብረክርስቶስ እህት)፣ ፀጋይ በርሀና ቅዱሳን ባለትዳሮች መሆን . . . ወዘተ አይተው ይሆናል የተሳሳቱት ብዬ ልገምት። እነዚህማ ወንድማሞች ወይም ባለትዳሮች ሊታገሉ ወጥተው የትግል ጥይት በአጋጣሚ የሳተቻቸው ወይም የሚገድል ቦታ ላይ ያልመታቸው ናቸው። እንቁጠር ካልን ከአንድ እናት አባት የተሰውና በዕድል ይሁን በአጋጣሚ የቀሩ እንይ። ዳንኤል ኪዳነማርያም (ጂፊኢት)፣ አወጣህኝ ኪዳነማርያም፣ ፅጌ ኪዳነማርያም ሦስቱም ከአንድ ቤተሰብ ታግለው የትግል ሜዳ ላይ የቀሩ የአድዋ ከተማ ብርቅዬ ልጆች ናቸው። እንዳ ወዲ ረታ ግዛው ረታ፣ ማለፍያ ረታ እና ትንሽ ወንድማቸው ሓለፎም ረታም የአድዋ ፈርጦች ነበሩ። ተሰውተው በርሃ ላይ የቀሩ! ወንድማቸው ፀሃየ ረታም ከርቸለ እስርቤት ሲማቅቅ ቆይቶ በህይወት ተርፏል። የፈትለወርቅ (የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር) ወንድምና እህቶች ሓየት ገ/እግዛብሄር፣ ርግበ ገ/እግዛብሄር፣ አልማዝ ገ/እግዛብሄር (ጋል ጥረጨው) ከአድዋ የተገኙ ሰማዕታት ቤተሰብ ናቸው። ወሸኔ፣ ከሶስት ወዲ ዝራብዕ በሚል ቅፅል ስም የሚጠሩ አራተኛ እህታቸውም ተናኘ ሁሉም ከዐድዋ የተገኙ በትግራይ በረሃ ሲታገሉ የተሰው ናቸው። በህይወት ያለው ጌታቸው ተፈሪም ሁለቱ ወንድሞቹ አለማየሁ ተፈሪና ሉቃስ ተፈሪ ቀብሮ ነው በአጋጣሚ ተርፎ እየኖረ ያለው። የስብሃት ነጋ ወንድም አባይ ነጋ ልጆች ሣራ አባይና እያሱ አባይ ተሰውተዋል። ብዙ ብዙ ብዙ … ማንሳት ይቻላል። ህወሓት አዎ! የቤተሰብ ድርጅት ነው። አንድ ቤተሰብ ያሳደገው ወንድምና እህት አንድ ላይ ወደ ሞት ወይም ድል ብሎ የሚጎርፍበት ድርጅት ነው ህወሓት። ያ መራራና በጣም ረዥም ጊዜ የወሰደ ትግል ረስተው አዲስ አበባ ህወሓትን ያዩ ሰዎች እርካቧንና ወንበርዋን ብቻ በሚያይ አይናቸው እያዩ የቤተሰብ ድርጅት የሚሉት፣ ይህን በደም የተፃፈውን ታሪክ ማየት ስለማይችሉ ነው።

የህወሓት የልደት ስፍራ በሆነው ሽሬ አካባቢም ህወሓትን ያልተቀላቀለ ቤት ማግኘት አይቻልም። በዚህ ምክንያትም ወያኔ የቤተሰብ ስብስብ መቧሏ እውነትነት አለው ባይ ነኝ። ህውሓት ሲነሳ ሁሌም ስሙ ገኖ የሚነሳው ስሑል ብቻውን አልታገለም። ብቻውም አልተሰዋም። ወንድሙ ፍትዊ፣ የእህቱ ልጅ ይርጋ ማንጁስ፣ የወንድሙ ልጅ መሪር፣ የራሱ ልጅም ለምለም ስሑል ተሰውተዋል። በጀግንነቱ ወደር የሌለው ጀነራል ሃየሎም ቤተሰብም እንዲሁ በትግሉ ዋጋ ከፍለዋል። ወንድሙ ፍቅረ አረአያ ለህወሓት እየሰራ በአረመኔው ደርግ ተይዞ ተረሽኗል። የሃየሎም ታላቅ እህት አምለሱ ልጅ ብርሃነመስቀል ከሃየሎም አንድ ላይ ወደ ትግል ወጥቶ ተሰውቷል። የሃየሎም የአጎቱ ልጅ ሃይለአብ ለትግል ወጥቶ በጀግንነት ተሰውቷል። የአዲአውዓላ ትንሽዬ የገጠር ከተማ ከያንዳንዱ ቤት ያልታገለ ቤተሰብ ማግኘት አይቻልም። ለአብነት ለመግለፅ ዳኛው የተባለ ነባር ወያናይ አራት ልጆቹ ለትግል ሸኝቶ ሦስቱ ገብረንጉስ ዳኛው፣ ክፍሉ ዳኛው እና ሦስተኛ ወዲዳኛው በሚል የማስታውሰው ሲሰዉ አራተኛዋ ጋል ዳኛው በህይወት አለች። በፅምብላ እንዳባጉና በጣም ትንሽዬ ከተማ ብዙ ታግለዋል። እነጀነራል ሰዓረ መኮንን ጨምሮ። የሙዝሊሞች ቤተሰብ ከሆኑት የወሃበይና ፈረጅ ወንድማሞች ልጆች አራት እህታሞችና ወንድማሞች ለትግል ወጥተው ጀሚላና ሶፍያ ወሃበይ በጀግንነት ሲሰዉ በአጋጣሚ ወንዶቹ ሁለቱ ተርፈው በህይወት አሉ። አንዱ ትግርኛ ተናጋሪ በመሆናቸው ከታሰሩት የሜቴክ የፖለቲካ እስረኞች አንዱ ነው። እንደ ቤተሰብ ታግለው ሁሉም ተሰውተው ቀሩ። ከዚህ አካባቢ ከሽሬ ሳንወጣ ከደርግ መደምሰስ በኃላ የተሰው አባትና ልጅ ላውጋቹሁ። ኮ/ል ነጋሲ የኮማንዶ አባል የሆነ በትጥቅ ትግሉ ብዙ የውግያ አውድማ ላይ ተሳትፎ ደርግ ከተገረሰሰ በኃላ ቤተመንግስት ጥበቃ የተመደበችው ሻለቃ ኮማንዶ አዛዥ ነበር። የመለስ የቅርብ ጥበቃም በስሩ ነበር። የዚህ ታጋይ አባት በሽሬ አድያቦ ህወሓት ከመጀመርያው የትግል ወቅት ጀምሮ የድርጅቱ አባልና ህዝባዊ ሚሊሻ (ወያናይ ይባላሉ ታጣቂዎቹ) አባል ነው። ነጋሲ ገና ልጅ እያለ ወደ ትግሉ ከመቀላቀሉ በፊት መሆኑ ነው። ዘንድሮ ባንሰራፋው ኃላቀር አስተሳሰብ እነዚህ አባትና ልጅ ሙሉ በሙሉ ኤርትራዊ ትውልድ ነበራቸው። ግን እነሱም የሚያምኑት ድርጅቱም የሚያቃቸው ታጋይ እንደ ኢትዮጵያውያን የትግራይ ጭቁን ህዝብ ነበር። ይህን እውነታ ደግሞ ሁለቱም በአንድ ቀን በዛው በተፈጠሩበት ሽሬ ታህታይ አድያቦ መስውዓት በመሆን በደማቸው ፈርመው አረጋግጠዋል። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በባድመ ግምባር ላገራቸው ዳር ደምበር ሲሉ አንድ ቤተሰብ በአንድ ላይ ተሰውተዋል።
Full Website