ሓዱሽ ንጉሰ (አግረሲቭ)

ጥር 2012

ከጅዋቆ ተንቤን ትግራይ

ባለፉት ፅሑፎቼ የተሰው ስገልፅ ከመቐለ ከተማ ወጥተው የተሰው አልገለፅኩም። ዛሬ የምገልፅላቹህ ይህንን ነው። ከመቐለ ህወሓት እንደተመሰረተች ከመጀመርያው ብዙዎች ጎርፈው የትግል ሜዳውን ተቀላቅለዋል። መጀመርያ ከተሰለፉት ብዙዎቹ መቐለ ነፃ ስትወጣ አልተመለሱም። ሊመለሱ ብለው ወደ ትግሉ አልተቀላቀሉም። ዕድሉ ገጥሟቸው የተመለሱት የገጠማቸው ችግር ከፍተኛ ነበር። በአንድ መፅሔት ሕርይቲ ምህረተዓብ ከመቐለ አብራት ወጥታ ሳትመለስ የተሰዋች ጀግናዋ ልዕልቲ መኖርያ ቤት ሂዳ እናትዋን ስታገኝ እልል ብለው ተቀብለዋት አገላብጠው ከሳሟት በኃላ እህትሽስ? የሚል ከባድ ጥያቄ ሲጠይቃት በቃላት መመለስ ሳትችል ቀርታ ስቅስቅ ብላ በማልቀስ እናትና ታጋይዋ ተግባብተው አልፍውታል። ሌሎችም ወንድምህስ? ተጠይቀዋል። ይህ ግን ለወዳጆች ብቻ የተጠየቀ ጥያቄ አልነበረም። ብርሃነ ገብረክርስቶስና ንግስቲ ገብረክርስቶስ በጀግንነት የተሰዋው ማይክል ገብረክርስቶስን ቀብረው ነው መቐለ የተመለሱት። አባትና እናት ዘመድ አዝማድ ወንድማቹሁስ ብሎ ሲያፋጥጥባቸው ጊዜ ምን ብለው ይመልሳሉ? ይህ ጥያቄ ከመቐለ ነፃ መውጣት በፊት ብዙ የትግራይ ከተሞች ያለው ወላጅ ሲጠይቅ ቆይቷል። ግን ያኔ ጥያቄውን ሌላ ቦታ ነው ያለው ወይም ያለችው ብሎ እያድበሰበሱ ይመለስ ነበር። መቐለ ከተገባ በኃላ ማድበስበስ አስቸጋሪ እየሆነ መጣ። ብርሃነ ማንጃ፣ ገብረግዛብሄር ማንጃ ከመቐለ የወጡት ሁለቱ ወንድማማቾች በጀግንነት ተሰውተው አልተመለሱም። ጀነራል አማረ ገብረየሱስ፣ ካሕሳይ ገብረየሱስ፣ ህይወት ገብረየሱስ፣ በጀግንነት ከተሰዋው ወንድማቸው ገብረአምላኽ ገብረየሱስ ከአንድ ቤተሰብ ታግለዋል። መቐለ ተክለሃይማኖት መሃይም በሚል ቅፅል ስም የሚታወቅ የዩኒቨርስቲ ተማሪ፣ መምህር ገብረመድህን ድፍኦ፣ ሃይለ በዙ፣ አበራ ማንካ፣ ኪዳነ ግርማይ፣ ሮምሃ ቀስቅስ፣ ወልዱ ሃይለስላሴ . . . ወዘተ ለትግሉ ካበረከተቻቸው ጀግኖች ውስጥ ጥቂቶች ናቸው።

መቐለ ውስጥ በድሮ አጠራር እንዳቦይ ፍቃዱ በአሁን ጊዜ ቀበሌ 14 የሚባል መንደር አለ። በዚህ መንደር በያንዳንዱ ቤት ያልታገለ ሰው ማግኘት ይከብዳል። በዛው ልክ የተሰውት ብዙ ናቸው። የመቐለ ነዋሪ የገለፀልኝን ላውጋቹህ። የአቦይ ፍቃዱ መንደር የረባ ኑሮ ያላቸው በጣም ጥቂቶች ናቸው። አብዛኛው በጣም ዝቅተኛ ኑሮ ያለ ህዝብ የሚኖርባት መንደር ነበረች። አሁንም ያው ናት። ይኸው ብሎ ቤቶቹን እያሳየ ስም ዝርዝር ውስጥ ገባ። በሃይለስላሴ ጊዜ የትግራይ ክለቦች ተጫዋች የነበሩ ለዛውም ዝነኞች ተጫዋቾችና የሚያምር የስፖርተኛ ቅርፅ የነበራቸው እምሩና ፀጋብርሃን ቤታቸው የተቀራረበ ነው። አሳየኝ። ሁለቱም በጀግንነት ተሰውተዋል። እምሩ በኢዱ የባላባቶች ድርጅት በነበረ ጦርነት ቀደም ብሎ በጀግንነት የተሰዋ ነው። ፀጋብርሃን በእግር ስፖርት ታዋቂ እንደነበረው በውጊያ አመራር ህውሓት አሉኝ ከምትላቸው መሪዎች አንዱ ሆኖ ከደርግ በነበረ ውጊያ በጀግንነት የተሰዋ ነው። እጥፍ ብሎ አንድ ቤት እያሳየኝ ይህ የአብርሃ ካህሳይ ማንጁስ የሚል ስም የሰጣቹሁት ቤት ነው። ወንድሙም መቐለ ከተቆጣጠራቹሁ በኃላ ታግሏል። ብሎ ሳይጨርስ ዞር ብሎ ይህ ደግም ከሃረር የጦር አካዳሚ ምክትል መቶ አለቃ ተመርቆ ወደ ትግል ሄዶ ሳይመለስ የቀረ ጥላሁን ካህሳይ እናንተ ሰመረ ቸንቶ የምትሉት ቤት ነው። ሰመረ ቸንቶ ህወሓት ወታደራዊ ሳይንስ እንዲኖራት አስተዋፅኦ ከአደረጉት አንዱ እና በተግባርም ወታደራዊ ኮማንደር ሆኖ በዙ ውጊያዎች የመራና በትግል ሜዳ ሆኖም ወታደራዊ መፅሓፍ የሚያነብ ጀግና መሪ አዋጊ እንደነበረ የማስታውሰውን ያህል እኔም ተረኩለት። እዛው እያለን ይህ ደግሞ አስፋው ሃይለኪሮስ ቤት ነው። እዚህ አጠገቡ ያለው ቤት የሓጎስ ገመቹ ቤት ነው። ሁለቱም ወዳጆች ነበሩ። ለትግል ወጥተው ሓጎስ ወዲ ገመቹ ሲመለስ አስፋው ሃይለኪሮስ በጀግንነት መሰዋቱን ገልፆልናል አለኝ። በዛ ማዶም የጀነራል ታደሰ ጋውናና ጀነራል ታደሰ ወረደ ቤቶች ይገኛሉ። ጎረቤታሞች ነበሩ።

ቀጠለ እዚህ ፊት ለፊት ያሉ ሁለት ቤቶች ደግሞ ብዙ ታግለዋል። ቀደም ብሎ የወጣው አለምሰገድ ገብሩ ነበር አለኝ። ቤቱን እያሳየኝ። አዎ ብዬ እኔም አለምሰገድ ገብሩ ከሃረር የጦር አካዳሚ የተመረቁትን ም/መቶ አለቆች ይዞ አብሮ መውጣቱን ሰምቻለሁ። አለምሰገድ በትግራይ ከነበሩ ክለቦች የሚጫወት የነበረ እንደ እሙሩና ፀጋብርሃን ታዋቂ ተጫዋጭ የነበረና የትግራይ ምርጥ ቡዱን አባል ሆኖ በአገር አቀፍ የእግር ካስ ውድድሮች ይሳተፍ የነበረ መምህር ሆኖ ይስራ የነበረ ነው። ብዙ ውጊያውች በጀግንነት የተሳተፈና በመጨረሻም የህዝብ ግኑኝነት ስራ ላይ ተመድቦ በህዝብ የሚወደድ ታጋይ እያለ በአፋር አካባቢ ሲቀሳቀስ በጠላት በተቀበረ ፈንጂ ህይወቱ ያለፈ ነው ብዬ የማቀውን ያህል ተረኩለት። እሱም ታሪኩ እየጣመው በመነሳሳት ምንም ቤት ሳይዘል መግለፁ ቀጠለ። የአለምሰገድ ገብሩ የእህቱ ልጅም ከአለምሰገድ እናት ስለአደገ ዳንኤል ገብሩ የሚባልም አሁንም በህይወት ይኖራል ህወሓት መቀለ ከገባች በኃላ ትግሉን ከተቀላቀሉ አንዱ ነው አለኝ። ከአለምሰገድ ገብሩ ቤት ፊት ለፊት ያለውን ቤት እያሳየ ይህ ደግሞ የጌታቸው አሰፋ ቤት ነው። ወንድሙ ዳንኤል አሰፋ እና እዚህ ጎረቤታቸው ካለው ቤት አብሮት የታገለ አለም አብርሃ የሚባል ነበር በርሃ እንደወጣ አልተመለሰም። በጀግንነት ከተሰዉት ውስጥ ነው። መቐለ እንደገባቹህ የጌታቸው አሰፋና ዳንኤል አሰፋ ወንድሞች ሌሎች አራት ተከትለዋቸው ወጥተዋል። አባታቸው ሻለቃ አሰፋ በደርግ ተረሽነዋል። የጌታቸው ታናሽ ወንድምም ያለፍርድቤት ውሳኔ አዲስ አበባ ከርቸሌ ታስረው ከተሰቃዩት የህወሓት የከተማ ሴሎች ነበረ። ከመቐለ መቆጣጠር በኃላ ከዳንኤል አሰፋ አብሮት የወጣውና ተሰውቶ ያልተመለሰው አለም አብርሃ ወንድም ጌታቸው አብርሃ ወደ ትግሉ ተቀላቅሏል። የሚተርክልኝ ሰው እያዘነ እሱም እንደ ወንድሙ ከድል በኃላ የመከላከያ ሰራዊት አባል ሆኖ መቶ አለቃ ማዕርግ ደርሶ በሻእብያ ወረራ በዛላንበሳ ግንባር በጀግንነት ተሰዋ። ትልቅ ወንድማቸውም የህወሓት ሴል አባል ነህ ተብሎ በአዲስ አበባ ከርቸሌ ያለፍርድ ለአስር ዓመታት ታስሯል። በተጠጋጉ ቤቶች ይህ ሁሉ ታጋይ ተሰልፏል።

ቀጠልን። ሰሎሞን ለማ የሚባል ሆስቴል በድጋፍ እየኖረ የሚማር የዚህ ሰፈር ልጅ ነበር በሰባ ዓ/ም ታግሎ ብዙ ሳይቆይ በጀግንነት ከተሰዉት ነው አለኝ። እዛው እያለ ይህ ቤት የማማ ዘመዳ ቤት ነው አለኝ። ከሃረር አከዳሚ በም/መቶ አለቃነት ተመርቀው ከታገሉት ታደለ የሚባል የእህታቸው ልጅ ነው። ያስተማሩት ማማ ዘመዳ ናቸው። ልጄ መቶ አለቃ ሆነልኝ ብለው ለሁሉም ሲናገሩ ነበር ይላሉ፣ ሳይጠግቡት ወደ ትግል ሜዳ ሄዶ አልተመለሰም አለኝ። ታደለን አስታውሳለሁ። በኢዱ ጦርነት ወቅት የተሰዋ ጅግና ነው አልኩት። ከኢዱ ጦርነት በምናደርግበት ወቅት ከፍተኛ የሎጂስቲክስ ችግር ነበረን። ውጊያ ለማድረግ ከሩቅ ቦታ ተጉዘን ተወርውረን ነበር ኦፕረሽን ደፈጣ የምናደርገው። የታመሙ የቆሰሉ ብፆት እየደገፍንና እየተሸከምን ነበር የምንጋዘው የምንተውበት ቦታ አልነበረንም። ታደለ ታሞ እያለ ውጊያ ገብተን እየተዋጋ ተዳክሞ በባላባቶቹ የኢዱ ታጣቂዎች ቁጥጥር ውስጥ ይወድቃል። እንደነ አሞራው እንደ ገብሩ ቀሺ በጠላት እጅ ወደቀ። ተሎ እንዲገላግሉት ጀግናው ታደለ አድሓሪነታቸውን እየተናገረ አላስቀምጥ ሲላቸው ‘ቀደድቲ ወረቀት’ ሲተረጎም ‘ወረቀት ቀዳጆች’ ብለው ለህወሓት የተማሪዎች ስብስብ ብለው ይሰድቡ ነበርና ይህን ስድብ ሰድበው ረሸኑት። ህወሓት ያልተሰደበው ስድብ የለም። ታደለ ግን ‘ድል ለህወሓት!’ እያለ ህልፈተ ህይወቱ አለፈች። ዓላማውና ጀግንነቱ እስከ አሁን የህወሓት ባህል ሆኖ ዘልቋል! ስለው አስጎብኚው ይህ ሁሉ ታሪክ ይዛችሁት ልትሞቱ ነው ወይ? ለምን አትፅፉትም። አትነግሩንም አለ። ትክክል  ተናግራል። አንድ ወቅት ይፃፋል እየተባለ አልተፃፈም። ታሪክ መስራት እንጂ ታሪክ መተረክ አልቻልንበት ይሆን? አልኩትና ቀጥል የሌሎችም አሳየኝ አልኩት።

እሱም ቀጠለ። ቀደም ብሎ የወጣው የሓዱሽ ባሌማ ቤት ይህ ነው አለኝ። ቀጠል በማድረግ ይህ ደግሞ የንግስቲ ሃየሎም ቤት ነው። ታግላ ነበር። አጠገቡ ጎረቤት ያለው የሰሎሞን ካሕሳይ ቤት ነው። እዚህ ያለው ህድሞም አኸዛ ጣንጡ ቤት ነው። ሦስቱ በተመሳሳይ ጊዜ ትግል ሜዳ ወጥተው ሁለቱ በህይወት ሲገኙ ሰሎሞን ካሕሳይ ሜዳ እንደወረደ በጀግንነት መሰዋቱን መስማቱ ገለፀልኝ። አልማዝ አለሙ ከማይጨው ወደ ትግል ሜዳ ወጥታ በጀግንነት ከተሰዉትም የእህትዋ ቤት እዚህ መንደር ይገኛል ብሎ የአልማዝ አለሙ እህት ቤት አመላከተኝ። አይበቃህም? የማቀውን ሁሉ ነገርኩህ አለኝ። ጥያቄ ልጠይቅህ አልኩት። እሺ ጠይቀኝ አለኝ። አንተ እንዴት የዚህ ሰፈር ልጅ ሁነህ ሳትታገል ቀረህ? አልኩት። እኔ ብታገል ኑሮ ይህ ሁሉ ታሪክ ማን ይነግርህ ነበር ብሎ ጥያቄየን በጥያቄ መለሰልኝ። ፈገግ በማለት ከጀግኖቹ ሰማዕታት ጥልቅ ትዝታ ወጣ ለማለት ብሞክርም በቀላሉ ሊተወኝ አልቻለም። በሃዘን ሁኜ አመስግኘው ተሰነባብተን ተለያየን።

የህወሓት አመራር ከመጀመርያው ጀምሮ መስዋእትነት አየከፈለ መጥቷል። ሙሴና ስሑል ድርጅቱን ሲመሰረት ለህዝባዊ ዓላማ እስከ መስዋዕትነት ስለተሰለፉ በተግባር በጅግንነት ተሰውተዋል። ስሑል ልጆቹን ጥሎ ወደ ትግል ሜዳ የወጣው ስልጣን ፈልጎ የትግራይ የበላይነት ለማምጣት ነው? ካላሉን በስተቀር የህወሓት መሪዎች የሚመሩትን ሰራዊት ጀግንነት ያስተማሩት በስልጣን ናፍቆት ከጀርባ ሆነው ግባ በለው በማለት ሳይሆን አብረዉት እየተዋጉ በጀግንነት እየተሰዉ ነው። የመጀመርያ የነበሩ ማእከላይ ኮሜቴዎች እንደዚህ በመስዋእትነት የህወሓት ሰራዊት የዓላማ መስዋእትነት መክፈል በመጀመራቸው በቀጣይነት ይህ ባህል ሆኖ ቀጥሏል። አግአዚ፣ አታክልቲ ቀፀላ ዶክተር፣ ሸዊት ወዲ ዳኛው በጀግንነት መስዋእት በመሆን የጀግንነት ባህሉን ተጠናክሮ እንዲቀጥል አድርገዋል። ከቁንጮቹ ብቻ አይደለም መስዋእትነት እየከፈሉ የመጡት ቀጥሎ ያለውን እርከን የሚመሩ አመራሮችም ከመጀመርያው የትግል ዓመታት ተሰውተዋል። ቀለበት፣ ዋልታ፣ ፀጋብርሃን፣ ጥላሁን ሰመረ ቸንቶ፣ ዳንቡሽ፣ ኩህለን፣ ማንጁር ተካ ፍትዊ በጣም ብዙ ክፍለጦር አመራሮች ማዕርግ ያልተሰጣቸው ጀነራሎች ተሰውተዋል። ጀግንነት መስዋእትነት የህወሓት ልዩ መለያ እንዲሆን በደማቸው በአጥንታቸው ታሪክ ሰርተዋል። በውግያ ወንድሙ እህቱ እንደተሰዋች እያወቀ ቅናት ይዞት በሚቀጥለው እሷም እሱም እንደ ወንድሟ እንደ እህቱ ይሰዋል ትሰዋለች።

ስለ ተሰው የህወሓት ሰማእታት ስናነሳ ብዙ ያልተባለለት አንድ ጉዳይ ላንሳ። የህወሓት ሴት ታጋዮች በተመለከተ ነው። በዓለም ታሪክ ሴቶች በጦርነት የነበራቸው ድርሻ የሚወሳው ቁስለኞችን በማከም ምግብ በማብሰል የቁስለኞች ልብስ በማጠብ ከፍተኛ ታሪክ ሰርተዋል። በሆላንድ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጀርመን የፋሽስት ናዚ ጦር አገራቸውን ወሮ በያዘበት ወቅት በዘመኑ የነበሩ ጀግኖች ወጣት ሴቶች ከጠላት ጋር የሚሞዳመዱ ባንዳዎችን እየለዩ ተደራጅተው እየተመካከሩ በፍቅር የተጠመዱ እየመሰሉ ጫካ ውስጥ ወስደው ይገድሉዋቸው ነበር። ጀርመኖች ሰላዮቻቸውን የሚያጠፋ ምትሃት ምንድነው በማለት ክትትል በማድረግ ቀይ ፀጉር የነበራትን ሆላንዳዊት ይዘው ይረሽኗታል። ባለ ቀይ ፀጉርዋ ጀግና ሆላንዳዊት ሃውልት ተሰርቶላት እስከአሁን ስሟ ይጠራል። ሌሎችም በስለላ ተሰማርተው በኛም እቴጌ ጣይቱ በአድዋ ጦርነት፣ በቅርቡም ማርታ መብራህቱ የመሳሰሉ ታሪክ ሰርተው አልፈዋል።

የህወሓት ሴት ታጋዮችና የትግራይ ሴቶች በሙሉ በሚባል ደረጃ ያ በዓለም ይሁን በአገራችን ሌሎች ሴቶች የፈፀሙትን ገድል ፈፅመዋል። የህወሓት ሴት ታጋዮች በልዩ የፈፀሙት ከወንዶቹ ባልተናነሰ ቁጥር ያላቸው ካላሽን ቦምብ ታጥቀው ላይና ታች ተጉዘው ውጊያ ውስጥ ገብተው ተታኩሰው ገድለው ምሽግ አፍርሰው የጠላትን ወታደር ማርከው አይተናል። ፈንጂ ከሚረግጡ ረግጠው፣ ምሽግ ሲያፈርሱ ከጠላት ቦምብ አካላቸው ተበጣጥሶ የተሰዉት የቆሰሉት አካለ ጎደሎ ሁነው ለምስክርነት የቆዩት ብዙ ናቸው። ’’ሴት ያታግላሉ። የሴት እኩልነት በተግባር ያረጋግጣሉ’’ ለመባል ሳይሆን እረኝነታቸውን ጥለው፣ ታጭተው ሰርግ ሊደረግ ሲጠባበቁ የነበሩ ለጋ ወጣቶች ለትግል መሰለፍ በትግራይ ህዝባዊ ትግል ውስጥ የተለመደ በመሆኑ በዓለም ሁሉ የተለመደ ነገር መሰሎን ይሆን? ይህን ታሪክ እስከ አሁን ያላጎላናው አንጂ ልዩ ነው እኮ። ታሪክ መስራት እንጂ ታሪክ መዘገብ አንችልም ብለን የሰነፎች መፈክር አንግበን ይሆን! ሴት የህወሓት ታጋዮች በትግሉ ወቅት ሁሉም ችግር ተቃቁመው አልፈዋል። ሽንት በሚጠጣበት በጥም ሳይሸነፉ የዘለቁ አሉ። ጥንካሬያቸው በቃላት መግለፅ በማይቻል ደረጃ ነው። የወር አበባቸው በሚታይበት ወቅት ድብብቆሽ የለም። ሸክማቸው ለማቅለል መተጋገዝ ባህል ነበረን። ውሃ እንዲተጣጠቡ ውሃ ችግር ባለበት ሁሉም ይተባበራቸዋል። አንዳንዶቹ ብፆትን እናስቸግራለን ብለው ደህና ነኝ ብለው እምቢ ትብብር አንፈልግም ይሉ ነበር። እሺ የሚላቸው ባያገኙም እነሱ የምራቸው ነው። ከታችኛው አመራር ጀምሮ እስከ ክ/ጦር የጦር መሪዎችም የተፈጠሩት በዚህ ልዩ የሆነ ታሪካዊ ተሳትፎቸው ነው። በዛው ልክም ብዙ በጀግንነት ተሰውተዋል።

ህወሓት ወንድወሰን ከበደን ከአማራ፣ ባህበሎምን ከደቡብ፣ ሴኮንና አዜብ መክትን የመሳሰሉ ጀግኖችን አቅፎ ታግሏል። ከውጭ ትውልድ ያላቸውም እንደ ኬርያ አብዱ ከሽሬ አታግሎ ተሰውታለች። ኬርያ ቻይና ቦምብ የሚባል መያዣ ዱላ የሚመስል እጀታ ያለው ከጎንዋ ታጥቃ በአረብ ፊትዋ ያየ ሰው ይገርመው ነበር። ቦምብ በመወርወር ትታወቅ ነበር። መካከለኛ አመራር ደርሳ ብዙ ውጊያዎች አዋግታለች። የጣልያን ዘር ያለውም አልቀረም። ፃዕዱ በአባትዋ ጣሊያናዊት ብትሆንም እናትዋ ኢትዮጵያዊትና ትግራወይቲ የነበረች እና ተወልዳ ያደገችው ትግራይ መቐለ በመሆኑ እንደሁሉም የትግራይ ህዝብ የትግል ሜዳ ወርዳ ታግላለች። በህይወት አለች። ህወሓት ቅመም የሆነች ድርጅት ናት። ህዝብ ይወዳታል። ገዥዎችና ስልጣን ፈላጊዎች ጨቃኞች ደግሞ አምርረው የጠሏታል። ለዚህ ነው አፋቸውን ከፍተው አስከአሁን የሚሰድቧት፣ ሊያጠፍዋት ተንኮል የሚሸርቡባት፣ ወላጅዋን የትግራይ ህዝብ በገበያ ቀን በአውሮፕላን በቦምብ የሚቀጠቅጡባት። አልንበረከክም ሲል ደግሞ ወረቀት ቀዳጆች፣ ወንበዴዎች፣ ገንጣይ አስገንጣይ፣ አይጥ፣ ከፋፋይ ዘረኞች፣ ፀረ አንድነት ሃይሎች፣ የቤተሰብ ስብስብ፣ የቀን ጅቦች፣ ኮንፈዴራሊስቶች … ወዘተ ወደፊትም ብዙ ስድቦች እየፈጠሩ የሚሳደቡት። ነግር ግን ባይሳደቡ ነበር የሚገርመው።
Full Website