ህወሓት:- አዎ! የቤተሰብ ስብስብ ነው።

ክፍል ሁለት

ሓዱሽ ንጉሰ (አግረሲቭ)

ከጅዋቆ ተንቤን ትግራይ

ጥር 2012

በፖለቲካ ትግል ወቅት ቤተሰብ እንደ ቤተሰብ ለአንድ ዓላማ መሰለፍ ያለ ነገር ነው። የዓለማችን የፖለቲካው ዓለም ቤተሰቦች በአንድ ላይ የመሰለፍ ጉዳይ አነጋጋር አይደለም፡፡ የአገራችን አንዳንድ ፖለቲከኞች የሚያመልኩት የአሜሪካ ፖለቲካ ስንክሳር ስናይ የከኔዲ ወንድማሞችና ቤተሰቦች የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ሁነው ለፕሬዚደነት ምርጫ በየተርሙ ተወዳድረዋል፣ የሪፓፕሊካኑ የቡሽ ቤተሰብ አባትና ልጅ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሁነው መርተዋል፣ ፕሬዚደንት ክሊንቶንና በሃላ ባለቤታቸው ሂላሪ ክሊንቶንም የውጭ ጉዳይም ሆነው ካገለገሉ በሃላ ዕጩ ፕሬዚደንትም ሁነው ተወዳድረዋል። በምስራቁ ዓለምም የሳውዲ ንጉሶች ለብዙ ዓመታት ለልጅ ልጆቻቸው እያወረሱ አገሪቱን ገዝተዋል። በአሜሪካና በሳውዲ መካከል ያለው ልዩነት በ’ምርጫ’ና በውርስ የሚደረግ ስልጣን የመያዝ ፖለቲካ መሆኑ ብቻ ነው።

የህወሓት የቤተሰብ ድርጅትነት ግን ልዩ የሚያደርግ እውነታ አለው፡፡ ለስልጣን የተደረገ ሳይሆን ለትጥቅ ትግልና ለመስዋዕትነት የተሰለፉ የተገፉ ቤተሰቦች ስብስብ መሆኑ ነው። ከዚህ ቤተሰብ ለትግል ከወጡት ቀላል የማይባሉት በየቀበሮ ጉድጓድ ተቀብረው የቀሩ መሆናቸው ለየት ያደርገዋል። ከዛ ቤተሰብ ጥቂቶች በአጋጣሚ የተረፉ ትዳር መስርተው ልጆችም አፍርተዋል። የደርግ ውድቀትም አይተዋል። ህዝባዊ መንግስት ሲመሰረትም አይተዋል። በህዝብ ተመርጠውም ለስልጣን በቅተዋል። ህዝብ ለሰላም ለልማትና ለዲሞክራሲ በሚደርግው ጉዞ ለማገልገል ታድለዋል። እነዛ በለጋ  ዕድሜቸው በየሸንተረሩ ለህዝባዊና ለአገራዊ ቅን ዓላማ መስዋእት ሆነው የተቀበሩትን ቤተሰቦቻቸውን  አደራ ለመትግበር ችለዋል።

የአሜሪካና ሳውዲ ሳወራ የአገሬ ረስቼ እንዳይመስላቹ። የሰቆጣ ማዘር እነ መዝሙር ፋንቴንና ነፃነትን ሁሉንም ሌሎች ልጆችዋን በሙሉ ቤተሰብዋን ጠቅልላ ይዛ ኢህዴንን የተቀላቀለችው ለትግል ለህዝባዊ ዓላማ እንጂ ለእርካብ ብላ አልነበረም። በስልሳዎቹና ሰባዎቹ የአዲስ አበባ ነዋሪ ቤተሰብ ያዳረሰው በወቅቱ ህዝቡ በተነሳሳበት ወቅት ሁሉም ቤትና ቤተሰብ ታላቅ ታናሽ እና ወንድ ሴት ሳይል የኢህአፓ አባል ሆኖ የቀይ ሽብር ተፋፍሞበታል። ይህ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይታጠር በሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች አዳርሷል። ለአብነት የበረከት ስምኦን ወንድም ኢህአፓን ተቀላቅሎ ተሰውቷል። በወቅቱ የነበረው ትግል ያላንካካው ቤት አልነበረም። ያላንካካው ቤተሰብ አልነበረም።

የቤተሰብ ነው ተብሎ ወደ ሚከሰሰው ህወሓት ልመለስና በለፈው (http://www.aigaforum.com/amharic-article-2020/tplf-yes-it-is-a-family-organization.htm) የጀመሪኩላችሁን ልቀጥል ፡፡ የነዛ በየሽንተረሩ ስለቀሩት ቤተሰብና በአጋጣሚ ስለተረፉት ብፆት! ከራያ ስጀምር ወልደገብርኤል ሐጎስ፣ ገብሩ ሐጎስ፣ ኪሮስ ሐጎስ ሁለት ወንድምና እህት ለትግል ተሰልፈው ወልደገብርኤል በጀግንነት ተሰውቷል። ሁለቱ በህይወት ቀርተው ትግላቸውን ቀጥለዋል። አፈወርቂ ገብረተንሳይ ከወንድሙ ጀነራል ፃድቃን ከአንድ ቤት ታግለው አፈወርቂ በመስዋእትነት ሳይመለስ ቀርቷል። ደስታ ካሳ፣ ፍረወይኒ ካሳ፣ ይብራህ ካሳ ከአንድ ቤት ሲሰው ወንድማቸው ገብረአሊፍ ብቻ በህይወት ተመልሷል። ቀደም ብለው ከዚህ አካባቢ ታግለው በጀግንነት ከተሰውት ሃይለማርያም ሃይለስላሴ (ወዲ ባሻይ) ይገኛል። ወዲ ራያ እና ጋል ራያ እየተባሉ ስንቶች በጀግንነት ተሰውተዋል። አሁንም በዚህ ቅፅል የሚጠሩ ትግሉን እየቀጠሉ ያሉ ብዙዎች ናቸው። ኽልተአውላሎ ስናነሳ በመጀመርያ የህወሓት የትግል ዓመታት ታግለው የተሰው ጀግኖች አግአዚ፣ ዮሓንስ ድንኩል፣ ሙሉ ማንጁስ፣ ይክአሎ (ወዲተናኘ)፣ አምበሳው ካሣ እና ወንድሙ ማሞ (ሃረማያ የነበረ)፣ ገረመስቀል ደሊ፣ ሃይሉ ኪሻፋ . . . ወዘተ ይገኛሉ። የአጋሜ የወልዋሎ ጀግኖች ሰማዕታት የተወሰኑትን ለማንሳት ሙሉጌታ አብርሃ፣ ንግስቲ፣ በርሀ ሶብያ፣ ወዲ ሓንታ፣ ይኩኖ፣ ኪዳነ አብርሃ ለህዝባዊ ዓላማ በየሸንተረሩ የቀሩ ጀግኖች ታጋዮች ናቸው። ተምቤን ከመጀመርያው የህወሓት ምስረታ ጀምሮ ልጆችዋን ያሰለፈች የትግራይ እምብርት የራስ አሉላ አገር ናት። ሰሎሞን ሳምሶን፣ አሉላ ሃይሉ፣ አብርሃ ማንጁስ፣ መረሳ ዳምቡሽ . . .  ወዘተ ማንሳት ይቻላል፡፡ ስዬ አብርሃ ሁለት ወንድሞቹ አብረውት ታግለዋል፣ አባቱና ወንድሙ በደርግ ተረሽነው ከመቀሌ ኩሐ በሚወስደው መንገድ ዳር ከሌሎች የትግራይ ተወላጆች በአንድ ጉድጓድ ተቀብረው ከደርግ መደምሰስ በኃላ በቁፋሮ ቅሪቶቻቸው ተገኝቷል፣ ወንድሙም ያለምንም ፍርድ ለዓመታት ከርቸሌ ታስሮበታል። ተምቤን የትግሉ የስምሪት ማዕከል በመሆን አገልግላለች። ኢህአዴግ የተመሰረተበት ስፍራም በዚሁ ተምቤን ይገኛል። ደርግ ለመደምሰስ ተቃቁሞ የነበረው ስትራተጂካዊ አመራር ይሰጥበት የነበረ ኮማንድ ፖስትም በተምቤን ይገኛል።

ወደ አክሱም እንሻገር የጀነራል ገዛኢ የትውልድ ስፍራ። ብዙ የጀግኖች ቤተሰቦች ለትግሉ መስዋእትነትን ያበረከተ አካባቢ ነው። ሃይለ፣ ይርጋዓለምና አበበ ሦስት ወንድማሞች ለህወሓት ዓላማ በፅናት ታግለው የተሰው ናቸው። አዜብ ረዳኢ፣ ኤልሳ ረዳኢ፣ ወንድማቸው ወዲ ረዳኢ በሚል የማስታውሰው ከአንድ ቤት ወጥተው በጀግንነት የተሰው ናቸው። ርግበ ሰሎሞን፣ ፅገ ሰሎሞን፣ ሁለት እህታሞች ከአክሱም የተገኙ ሰማእታት ናቸው። ለገሰ የኑስ የጀነራል ሳሞራ ወንድምም በጀግንነት ከተሰው አክሱም ለትግሉ ከለገሰቻቸው ሰማእታት ውስጥ አንዱ ነው። የክንፈ ገ/መድህን ወንድም ዮሓንስ፣ ዋልታ ገመድህን፣ አታክልቲ ቀፀላ፣ ኢሳቅ በርትዕ፣ ጎዲፋይ፣ ነጋሽ ሸሪፎ፣ ድልዊ . . . ወዘተ መጀመርያ አካባቢ ታግለው ድርጅቱን ከፍ እንዲል መስዋእት ከሆኑት ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያክል ነው። ወልቃይት ፀገዴ ከመጀመርያው ጀምሮ በህወሓት ትግል የሚሳተፉ ልጆቻቸውን አበርክተዋል። ሳይመለሱ በጀግንነት ተሰውተው ከቀሩት ውስጥ ካሕሳይ አበራ፣ ሓሚድ (ማየት የተሳነው) በደርግ ተከቦ ከወንድሙ ጋር ሆኖ የተሰዋ ልዩ ታሪክ ያለው ጀግና ነው። ሓለውያ በሽርና ወንድሙ አህመዲን በሽር በጀግንነት ከተሰው ቤተሰቦች ጥቂቶች ናቸው። ኑሩ ያሲን፣ ጌታቸው አዘናው የዚሁ አካባቢ ብርቅዬዎች በትግል የመረጡትን የጀግንነት ሞት ፅዋ የተቋደሱ ናቸው። እነዚህን በጥቂቱ ማንሳት ቻልኩኝ እንጂ ዝርዝሩ ተዘርዝሮ አያልቅም።

በትግራይ የገጠር ወረዳዎች ‘ምስላፍ’ በሚል ፕሮግራም ቤተሰቦቻቸው ፊት ወደ ትግል ሜዳ ለመውረድ የሚወስኑበት መድረኮች ነበሩ፡፡ አንዴ ሳይሆን በየዓመቱ ጥሪ በተደረገ ቁጥር ወጣቶች ወደ ትግል ለመግባት የሚወስኑበት፡፡ ትዳራቸውና የሰርግ ፕሮግራማቸውን ጥለው ከእጮኞቻቸው ወይም ደግሞ ከወንድም እህቶቻቸው አንድ ላይ ሆነው ወስነው ወደ ትግል ሜዳ ይጎርፋሉ፡፡ ወላጆቻቸውም ጥይት በግንባርህ እንጂ ስትሸሽ ከጀርባ እንዳይመታህ ብለው መርቀው በመሸኘት የህወሓት ማሰልጠኛ ጣቢያዎችን አጥለቅልቀዋል። ይህ በመሆኑ የህወሓት ሰራዊት በመስዋዕትነትና በጦር ጉዳተኞች ቁጥሩ እንዳይመናመንና ሁሌም በተሟላ ቁመና እንዲገኝ አድርገዋል። በዚህ ምክንያትም የሰራዊቱ ስብጥር በመሰረቱ የገበሬ ሰራዊት ሆነ። ይህም ከተሜውና የተማረው ክፍል ቁጥሩ በጣም አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ደግሞ ከ1972 ዓ/ም በኃላ ህወሓት ውስጥ የገበሬው ቁጥር በመብዛቱ የሚሰዋውና አካሉ የሚጎድለውም የዚህ የህብረተሰብ ክፍል እንዲሆን አድርጎታል። እነ ማንጁር ተካ ፍትዊ፣ ኩሑለን፣ ህይወት ላምፐን፣ መኮነን ዛና (ዋልካ የተሰለፈ)፣ ህይወት ላፍላፍ፣ ማርታ፣ ወዲዓላ፣ ፃዕዳ አሰፋ፣ ተስፋይ ኪነት፣ ገብረእግዛብሄር ስፖናቶ . . .ወዘተ ብዙ ሺዎች በከፍተኛ ጀግንነት ተሰውተዋል። ከገጠሩ የህብረተሰብ ክፍል የወጡት አንዳንዶቹ ወጣቶች እስክ የክፍለጦር አዛዥ ድረስ ደርሰው ተሰውተዋል።

የህወሓት ገበሬ ጀነራል አሜሪካ ተምሬያለሁ፣ ራሽያ ሰልጥኛለሁ ብለው የሚቀባጥሩት የደርግ ጀነራሎችን አምበርክከው ጦራቸውን ደምስሰውና ማርከው ድል ላይ ድል እየተጎናፀፉ ተሰውተዋል። ቀሺ ገብሩና አሞራው የዚህ ገበሬ የህወሓት ሰራዊት ማሳያዎች ናቸው። ንቃተ ህሊናቸው ከፍ ያሉና በመርሆ ቀልድ የማያቁ ሁነው በፋሽስት መንጋጋ ሁነውም ለህወሓት ዓላማ ብለው ምንም ሳይፈሩና ሳይርበደበዱ ዓላማቸውን እየገለፁ መገመት በሚያስቸግር ጀግንነት ተሰውተዋል።

ሁሉም የትግራይ ገጠር ወረዳዎች በብዙ ሺ ወጣት ቤተሰቦች ለትግል አሰልፈዋል። ለመጥቀስ ያክል ዕዳጋዓርቢ፣ ማይቅነጣል፣ እምባስነይቲ፣ ዓዲአሕፈሮም፣ ሓሓይለ፣ እገላ፣ የጭላ፣ አምበራመጠቓ፣ ሃገረሰላም፣ ዓዴት፣ ናዕዴር፣ ጭላ፣ ዛና፣ ላዕላይን ታሕታይን አድያቦ . . . ወዘተ፡፡ በተለይ በልዩ መዝገብ መመዝገብ የሚገባው የኩናማ ብሄረሰብ በህወሓት ትግል ያደረገው ተሳትፎ  ነው። አስተዋዩ መሪ መለስ ዜናዊ በአንድ ጉባኤ ወደ ትግል ሜዳ ስለ ማሰለፍ ጉዳይ ተነስቶ ስለ ኩናማዎች አንድ ሐቅ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ገለፀ፡፡ መለስ ለተሰብሳቢው ለትግሉ ከፍተኛ ቁጥር በማሰለፍ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው የኩናማ ህዝብ ነው አለ። የኩናማ ህዝብ ቁጥሩ በጣም አነስተኛ ሆኖ እያለ ከህዝብ ቁጥሩ የማይመጣጠን የሰው ሃይል ለትግል አሰልፏል ሲል አደራሹ ለዚህ ህዝብ ክብር ለመግለፅ በከፍተኛ የጭብጨባ ድምፅ አዳራሹን አናግቶት እንደነበር አስታውሳሎህ። ኢሮብና አፋርም ከህወሓት ውልደት ጀምረው ልጆቻቸውን በህወሓት ለሚመራው ትግል አበርክተው በደም የተፃፈ የማይፋቅ ደማቅ ታሪክ ከትበዋል።

ወልቃይት ፀገዴ፣ ቃፍታ፣ መዘጋ፣ ወጅራት፣ ሳምራ፣ ግጀት፣ ፊናርዋ፣ ደላ-ስላዋ፣ ኦፍላ፣ መኾኒ፣ መቻረ ሜዳ፣ ገረዓልታ፣ ሐውዜን፣ አፅበደራ፣ ዝባን አሰፈ ሶብያ፣ ኢሮብ አሊቴና፣ ሳዕሲዕ ዕዳጋሓሙስ፣ ብዘት ዳሞ አቡነአረጋዊ፣ አፋርም ከከደሓራ፣ አሳጋራ፣ በራህሌ፣ ከሽኸት፣ ኮነባ፣ ባዳ፣ ሓጂ ያሲን ከሁሉም ወደ ህወሓት ጎርፈዋል።  በጎረፈው መጠን ያክል በዛው ልክ የሚመጥን ጀግንነት በመፈፀም ተሰውተዋል። በጀግንነት አካላቸው ጎድሏል። አካላቸው የጎደሉትም ከደርግ መገርሰስ በኃላ መሞላቀቅ ሳያምራቸው ራሳቸውን አስተምረው መስዋት ሆኖ ከቀረው የሰውነት አካላቸው ይዘው ለልማታዊና ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የተደረገው ትግል ከማንም ዝቅ ሳይሉ በከፍተኛ ቆራጥነት ትግላቸውን ቀጥለዋል። በራሳችን ጥረት ኑራችን እንመራለን ብለው በማህበር ተደራጅተው ጥገኛነት ተፀይፈው ለመኖር ዳግም መስዋእትነት ከፍለዋል።

የገጠሩ የህብረተሰብ ክፍል ልጆቹን እንዲሰለፉ በማድረግ ብቻ ተሳትፎውን አልገደበም። በትግሉ የመጀመርያ ዓመታት በኢኮኖሚ ደካማ የሆነውን ህወሓት በፍላጎቱ ካለችው እያካፈለ፣ እያበላና እያጠጣ ትግሉ በኢኮኖሚ እጥረት እንዳይዳከም በቀላሉ የማይታይ ድጋፍ አድርጋል። በማህበርም ተደራጅቶ መሳርያ ያለው መሳርያው ለግሉ ሳይሆን ለህብረተሰቡ ድህንነት መጠበቅያ እንዲሆን በማድረግ ሚናውን ተጫውቷል። ትግሉ አየተጥናከረ ሲመጣም በየአካባቢው የታጠቁ የህብረተሰቡ ክፍሎች የህወሓት ሠራዊት በሌለበት ወቅት ወይም ቁጥሩ በጣም አነስተኛ በሚሆንበት ወቅት ወያናይ ሁነው የደርግ ጦር እንቅስቃሴና የደርግ ነጭ ለባሾች (ህዝቡ ባንዳ ብሎ የሚጠራቸው) ህዝቡን ለማባሳበስ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በተለያየ አቅጣጫ በመሆን እየተዋጉ ህዝቡ እንዳይጎዳ ይከላከሉ ነበር። በዚህም ቀላል የማይባሉ ወየኒቲ ተሰውተዋል። ለነዚህ ነው የህወሓት የኪነት ቡዱን ዝነኛው ‘ንገርኒዶ አብሻይ’ (እማዬ ንገርኝ አባቴ የት ሄደ?) የሚል ድራማዊ ዘፈን የዘፈኑት። ትግሉ መራር እንደነበረና እናቶች ባሎቻቸውን ልጆቻቸውን ያጡበት ትግል ለማስታወስ ነው።

ከትግራይ አልፎ ጭቁኖች ብሄር ሳይለያቸው በአላማ አንድነት ከህወሓት ጎን ተሰልፈው ተሰውተዋል። ባህበሎም በሚል የትግል ስሙ የሚታወቀው ጴጥሮስ በለጠ የደቡብ ብሄረሰቦች ተወላጅ ከህወሓት የመጀመርያ የትግል ዓመታት ተቀላቅሎ ታግሏል።  ከትግል ጓዱ ከሆነችው ታጋይ ትዳር መስርቶም ’እማዬ ንገሪኝ አባቴ የት ሄደ?’ ብሎ የሚጠይቅ አንድ ልጅም ወልዶ በጀግንነት ተሰውቷል።

Full Website