የአብይ መንግስ ት የሚታነቅበት ገመድ ውስጥ አንገቱ አስገብቷል

ህዳሴ ኢትዮጵያ

መስከረም 27፣ 2013 ዓ.ም.

የትግራይ ክልል ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ያቋቋመው መንግስት እውቅና ነፍገህ፣ ከወረዳ እና ከቀበሌ ጋር ነው የምገናኘው፣ ለወረዳ እና ለቀበሌ ብቻ አገልግሎት እንዳይቋረጥ አደርጋሎ ማለቱ በጣም አስቂኝ የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ነው፡፡ ተወደደም ተጠላም ህወሓት ከ98% በላይ የትግራይ ህዝብ መርጦታል፡፡ ለዛውም ህወሓት የቀን ጅብ በሚባልበት ወቅት፤ ህወሓት የዘራፊዎች ቡድን በሚባልበት ወቅት፣ ህወሓት አገርን ዘርፎ መቐለ ተሸሽጓል በተባለበት ወቅት የትግራይ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ህወሓትን መምረጡ በትምክህተኞች ከፍተኛ መደናገጥ ፈጥሯል፡፡ አሁን ህወሓትን መስደብ ማለት የትግራይ ህዝብን ምርጫ መስደብ ማለት ነው፣ የትግራይ ህዝብን ምርጫ ማንቋሸሽ ማለት ደግሞ እኔ አውቅልህአሎህ ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው የአብይ መንግስት እኔ አውቅልህአሎህ የሚል ፈላጭ ቆራጭ የአሃዳዊ ስርአት ለመመለስ የሚጥር ጥገኛ ስርዓት ነው የምንለው፡፡

Videos From Around The World

የትግራይ ህዝብ፤ ምርጫዬ የማያከብር መንግስት መንግስቴ አይደለም፡፡ እኔ የመረጥኩት ህጋዊ መንግስት የማይቀበል ሀይል ፀረ ህገመንግስት እና ፀረ “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት” በመሆኑ እንደ ደርግ ታግለን ማስወገድ እንጂ ምንም ግንኝነት ማድረግ አያስፈልግም እያለ ያለው፡፡

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የፌደራል ተወካዮች ምክርቤት እና የፌደሬሽን ምክርቤት የስልጣን ዘመናቸው የጨረሱ ህጋዊነታቸው መስከረም 25፣ 2013 ዓ.ም. ያለቀ የቀድሞ ምክርቤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ምክርቤቶች በአሁኑ ወቅት ራሳቸውን አክስመው ለሽምግልና ባላደራ ምክርቤት ስልጣናቸው ማስረከብ እንጂ ክልሎችን፣ ህዝቦችን፣ ዜጎችን የሚነካ ማንኛውም ህግ ማውጣት አይችሉም፣ የመንግስት ገንዘብም ንብረትም መጠቀም አይችሉም፡፡ ስለዚህ አሁን ያሉት የፌደሬሽን እና የተወካዮች ምክርቤቶች ህገወጥ ምክርቤቶች ናቸው፡፡

የዛሬው የፌደሬሽን ምክርቤት ተብዬው ውሳኔ፣ ከመስከረም 25፣ 2013 ዓ.ም. በፊት ቢወስነው ንሮ፤ ውሳኔው በትግራይ ክልል ጦርነት እንደማወጅ ነበር የሚቆጠረው፡፡ ምክንያቱ፣ ፌደራል መንግስት ከፈለገ የሚሰጥ ካልፈለገ የሚከለክለው ባጀት የለም፡፡ ፌደራል መንግስት የሚበጅተው ባጀት ከክልሎች የሰበሰበው፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም የሚበደረው እና የሚሰጠው እርዳታ እንጂ መንግስት በመሆኑ የፈጠረው ሀብት አይደለም፡፡ በህገመንግስቱ መሰረት መንግስት ከአገር ውስጥ የሚሰበስበው ገንዘብ በሶስት የተከፈለ ሲሆን እሱም የፌደራል ገቢ፣ የክልል ገቢ፣ እና የጋራ /የፌደራል እና የክልል/ ገቢ ነው፡፡ የክልል ገቢ ራሱ ክልል የሚሰበስበው ሲሆን ለራሱ ሲጠቀም፤ የፌደራል ገቢ እና የጋራ ገቢ ደግሞ በፌደራል ተሰብስቦ በጋራ እኩል ይካፈሉታል፡፡ የፌደራል ገቢ ደግሞ ፌደራል መንግስት ራሱ ሰብስቦ ለፌደራል መንግስት ፕሮጀክቶች እና ለክልል ድጎማ ያውላል፡፡ ይህም በግልፅ በጋራ የቃልኪዳን ስምምነታችን ወይም በህገመንግስታችን ተቀምጧል፡፡ ይህ ስምምነት ማንም እየተነሳ የሚቀይረው ወይም የሚጥስ ውሳኔ የሚሰጠው አይደለም፡፡ አንድን ክልል ያልተሳተፈበት፣ ህገመንግስት ነክ ውሳኔ ማንኛውም የስልጣን አካል ሊወስን አይችልም፡፡

በዚህ መሰረት አንድን ክልል ራሱ የሚሰበስበው ገንዘብ እና ከፌደራል የሚበጀትለት ድጎማ አንድላይ አድርጎ ክልሉ ባቀደው መሰረት ወጪ ያደርጋል ይተገብራል፡፡ ይህም የክልል ምክርቤት ይቆጣጠረዋል፣ የክልሉ ጠቅላላ ኦዲተር ኦዲት አድርጎ ለምክርቤት ያቀርባል፡፡ ምክርቤቱም በሪፖርቱ መሰረት ተወያይቶ ውሳኔዎች ያሳልፋል፡፡

ፌደራል መንግስትም ያቀደው ፕሮጀክት፣ የፌደራል የሚባል ልዩ ግዛት የለም እና በክልሎች ራሱ ወርዶ ወይም በትብብር ይፈፅማል ወይም ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ይህም የፌደራል ተወካዮች ምክርቤት ይቆጣጠረዋል፡፡የፌደራል ጠቅላላ ኦዲተር ይመረምረዋል ሪፖርትም ለፌደራል ተወካዮች ምክርቤት ያቀርባል፡፡የተወካዮች ምክርቤቱም በሪፖርቱ መሰረት ተወያይቶ ውሳኔዎች ያሳልፋል፡፡

ከዚህ ውጭ የክልል ምክርቤት በፌደራል ፕሮጀክትና ባጀት ገብቶ ሊፈተፍት አይችልም፤ የፌደራል ተወካዮች ምክርቤትም የፌደሬሽን ምክርቤትም በክልል ባጀት ወይም ድርሻ ገብቶ ሊፈተፍት፣ ሊቆጣጠር፣ ሊከለክል ፈፅሞ አይችልም፡፡

በህገመንግስቱ መሰረት አንድን ክልል እንደ ክልል የድጎማ ባጀት ሊከለከል አይችልም፡፡ አንድ ክልል የሰበሰበው ገንዘብ ይሁን፣ ፌደሬሽኑ ባወጣው የባጀት ቀመር መሰረት በድጎማ የተሰጠው ባጀት፤ የክልሉ ምክርቤት ባፀደቀው ዕቅድና ባጀት መሰረት ያውላል፣ ከክልሉ ምክርቤት ውጭ ማንም የፌደራል አካል መጥቶ ለምን እዚህ ታውላለህ ብሎ ሊጠይቅ ወይም ሊከለክል የሚችልበት ህጋዊ መሰረት የለም፡፡ ክልሉ ገንዘቡን አውጥቶ ቢያቃጥል እንኳን የሚጠይቀው የክልሉ ምክርቤት ነው፡፡

ክልሉ በባጀት አጠቃቀም ችግር ካለበትም፤ ማንም ይመለከተኛል የሚል ወገን አስተያየት እና ቅሬታ የማቅረብ መብት ቢኖሮውም፤ የማስተካከያ እርምጃ የመውሰድ መብት ግን የለውም፡፡ በባጀት አጠቃቀም በእቅድ አፈፃፀም እርምጃ የሚወስደው የክልሉ ምክርቤት እንጂ የፌደሬሽን ምክርቤት ወይም ሌላ ወገን አይደለም፡፡ የፌደሬሽን ምክርቤት፣ እኔ ስላላመንኩበት ብሎ በባጀት ቀመር መሰረት የተደለደለ የባጀት ድጎማ መከልከል ወይም እርምጃ መውሰድ አይችልም፡፡ ይህ ካደረገ በጋራ ስምምነት የፀደቀውን ህገመንግስት ሆን ብሎ አንድን ህዝብ ለመቅጣት ተጣሰ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ህገመንግስት የሚያስከብሩ ተቋማት በዚህ ላይ የራሳቸው አቋም በመውሰድ እንዲያስተካክሉ ዕድል ይሰጣል ካልሆነ ተበደልኩ ያለውን ክልል የራሱን እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል፡፡ ይህ ህጋዊ አሰራርን ተከትሎ ህጋዊ ምክርቤቶችን ባሉበት የሚደረግ ነው፡፡ አሁን ያለው የአገራችን ጉዳይ ግን ከትግራይ ክልል ውጭ ሌላ ማንም ህጋዊ የክልልም የፌደራልም መንግስት የለም፡፡ ስለዚህ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በፌደራል መንግስት ስም ውሳኔዎች መወሰን፣ ህጎች ማውጣት አይችልም ቢያወጣም በህጋዊው ክልል ተግባራዊ አይሆንም፡፡

አሁን ያለው ብቸኛው አማራጭ ይህ ህገወጥ መንግስት ከስልጣን ወርዶ ለባለአደራ መንግስት ስልጣኑን ማስረከብ እና ባለአደራ መንግስትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ነፃ ገለልተኛ ሆኖ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ፤ አሁንም ህገመንግስቱን የመጠበቅ ሓላፊነት የተሰጣቸው የፀጥታ ኣካላት ህገወጡን አካል ከስልጣን በማውረድ የባለአደራ መንግስት እንዲያቋቁሙ እድል ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሁሉም በየፊናው የየራሱ እርምጃ ይወስዳል፤ የትግራይ ክልልም ራሱን በራሱ የመከላከል እና መብቱን የማስከበር እርምጃ የመውሰድ ጉዳይ እጁ ላይ ነው፡፡ ይህ ህገወጥ ጥገኛ ሀይል በስልጣን ላይ ካለ አሁን በአገራችን ያለው የሰላም እና የመረጋጋት ችግር ተባብሶ ኢትዮጵያችን ምናልባት የሶማሊያ ዕጣ ሊደርሳት ይችላል፡፡ ይህ ከመድረሱ በፊት ግን በህገመንግስቱ መሰረት አገሪቱና ህገመንግስቱ የመጠበቅ ሀላፊነት የተሰጠው የመከላከያ ሰራዊታችን ባፋጣኝ ይህን ህገወጥ ሀይል ከስልጣን በማስወገድ ኢትዮጵያን እንዲታደጋት ይጠየቃል፡፡ ስለዚህ ደም መፋሰሱ ከመቀስቀሱ በፊት፣ ገመድ አንገቱ ላይ ያስገባውን ብልፅግና፣ ገመዱን ከአንገቱ አውጥቶ ከወንበሩ ይልቀቅ ካልሆነ ደግሞ ወንበሩን ከብልፅግና በማላቀቅ እዛው ራሱን እንዲሰቅል ማድረግ ነው፡፡

Full Website