Back to Front Page
ውጭ ከሚኖሩ የሲዳማ ማህበረሰብ አባላት የተላለፈ አገራዊ  ጥሪ  ኦክቶበር ፴ ቅን ፳ ፳

የሲዳማ ህዝብ ለዘመናት የሚደርስበተን በደል እና እራሱን ለማስተዳደር የከፈለውን መስዋእትነት መላው የሀገራችን ህዝቦች ይገነዘቡታል ። በደሉ መንግስታዊ በመሆኑ አይነቱና ስፋቱ ይለያይ እንጂ በሌሎች ላይም ተመሳሳይ በደሎች  ሲፈፀሙ ኖረዋል ፣እየተፈጸሙም ይገኛሉ ። ችግሩን ከመሰረቱ ለመቀየር አንዱ እርምጃ ብሎ ህዝባችን ክልላዊ መንግስት መመስረትን ማእከል ያደረገ ተጋድሎ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም የክልል አደረጃጀቱ እውን ሆኗል ። ሆኖም የሲዳማ ህዝብ ውድ ልጆቹን ገብሮ በህዝባዊ ድምጽ እውን ያደረገው ክልላዊ መዋቅር የሲዳማ ህዝብ በራሱ ተከልሎ ደሴት እንዲፈጥር ሳይሆን በአገራዊ ፓለቲካ የበኩሉን እንዲያበረክት ጭምር ነው። ለአገራዊ ችግሮች አገራዊ መፍትሄ ማፍለቅ እንዲያስችለው ነው። የክልሉ ህዝብ የአገራዊ ችግሮች አካል ሳይሆን የመፍትሄ አካል እንዲሆን በክልሉ ያሉ ሃይሎችን ለማስተባበር ነው።

አዲስ ክልል በመሆኑም ለአገሪቱ አዳዲስ ሀሳቦችን ፣ በክልሉም ሆነ ከዚያ ውጭ በአገር አቀፍ ደረጃ በህዝቦች መካከል የተበላሹ ግኑኝነቶችን ለማስተካከል አዲስ ሀይል እና አቅም ሆኖ እንዲወጣ ብዙዎች ተስፋ ጥለው ነበር ። ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት ራስን ችሎ ማሰብን ፣የራስን አቋም ያለ ምንም ተጽኖ መያዝ መቻል ፣ በአገራዊም ሆነ ክልላዊ ጉዳዮች ላይ የራስን ትንታኔና ውሳኔ መወሰን መቻልን የሚያጠቅልል ነው። ሆኖም ላለፉት ጥቂት ወራቶች በክልሉ ተወካዮች በኩል የተስተዋለው ነገር የክልሉም ሆነ የአገሪቱ ህዝቦች ከጠበቁት አንጻር ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም ከነበሩ ነባር ክልሎችም በከፋ መልኩ የትዕዛዝ ተቀባይነት እና ሃይል አለ ብሎ የሚያስብበትን አከባብ በጭፍን የመከተል ሁኔታ ተስተውሏል። ይህ ስርአት  እንዲቀጥል በማእከላዊ መንግስት የተዘረጋው ወጥ የፓርቲ ሰንሰለት ከፍተኛ አስተዋዕጾ ቢኖረውም የራስ አስተዳደር እንዲመጣ ዋጋ ለከፈለው የሲዳማ ህዝብ ተወክለናል የሚሉ የገዥው ፓርቲ አመራር አካላት ባህሪ በዋናነት ተጠያቂነት አለባቸው።

አገርን የሚመራው መንግስት በመካከሉ በተፈጠረ ልዩነት እና ክፍፍል ምክኒያት በህዝቦች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያመጣ የሚችል ውሳኔ ሲወሰን በየምክር ቤቱ እየተገኙ እጅ ማንሳትን የመሰለ ታዛዥነት የለም ። የሲዳማ ህዝብ በሲዳማ ላይ ሲደርስ የነበረ ግፍ እና በደል  በሌሎች ላይ ሲደገም መቃወም የማይቸል ተወካይ ሊኖረው አይችልም ። ከላይ ማእከላዊ መንግስቱን ጨብጠዋል የሚባሉ አካላት በተለዋወጡ ቁጥር ለሚመጣው ተላላኪና ታዛዥ ከመሆን ራስን በራስ እንደሚያስትዳድር አካል ገለልተኛ የሆነ ክልላዊ አቋሞችን መያዝ የሚችሉ አመራሮችን ዛሬም የሲዳማ ህዝብ ይፈልጋል። ይህ እውን የሚሆነው ዲሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ ምርጫ ሲኖር ብቻ ነው። አሁን ባለው አገራዊ  እና ፓለቲካዊ ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ ፈጽሞ የማይታሰብ ብቻ ሳይሆን ከተደረገም ለቀጣይ የዲሞክራሲ ሽግ ግ ር ውስብስብ ችግሮች እንዲፈጠሩ በር ይከፍታል። በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በሃሳብ ልዩነት እና ፓለቲካ እምነት ተለይተው በእስር በሚገኙበት፣ ህዝብ በማንነቱ የተነሳ እየተጨፈጨፈ በሚገኝበት  ፣በክልሎች መካከል ጦርነት ቀረሽ ውጥረት ባየለበት እና ምርጫ ለማካሄድ ሃላፊነት ያለበት መንግስት በህዝብ አመኔታ ባጣበት በዚህ ወቅት ለምርጫ እንዘጋጅ የሚለው የገዥው መንግስት  ራስን በስልጣን ለማሰንበት ከታለመ አጀንዳ ውጭ አገራዊ ፋይዳ አይኖረውም ። ስለሆነም ያለ ምንም በቂ ምክኒያት ከህገ መንግስታዊ የጊዜ ገደቡ ውጭ እንዲራዘም የተደረገው  ምርጫ  የአገሪቱን ሁኔታ ከግንዛቤ ባስገባ መንገድ እና ጊዜ ብቻ ማካሄድ ያስፈልጋል። ይህ እስከሚሆን ድረስ ግን  ሁሉን አቃፊ የሆነ የፓለቲካ ስርአት እንዲዘረጋ እና አገሪቱ ከገባችበት ቀውስ ሊያወጣት የሚችል አስታራቂ አገራዊ ሀሳብ  በአፊኒ ስርአት በመታገዝ እንዲያቀርብ አዲሱን የሲዳማ ክልል እንጠይቃለን ። የሀገር ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ አካላት ሁሉ  አገሪቱ የገባችበትን ቀውስ ያገናዘበ መፍትሄ ወደ ማፈላለግ እንጂ አዳዲሰና ውስብስብ ችግሮችን በተለመደው ግን አዋጭ ባለሆነ መንገድ ለመፍታት የሚያደርጉትን ግብግብ አቁመው የህዝቦችን አንድነትን እና ሰላም የሚያስጠብቁ አማራጮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን።
Full Website