የትግራይ ህዝብ ሰላም እንጂ እንደ ቄሮና እንደ ፋኖ  ግርግር አይፈልግም

ዮሃንስ አበራ ( ዶር ) 7-25-20

የማነ የተባሉ በመረጃ ድረገፅ ላይ ያሰፈሩት ቃል ቢያንስ ቢያንስ ሃላፊነት የጎደለው ነው እላለሁ። አንዴ ሁለቴ ይህን ቡድን በሚመለከት በፃፍኳቸው አስተያየቶች ላይ ስሙና አርማው ሽብር የሚለቅ መስሎ ስለተሰማኝ የሰላማዊ ትግል ስሜት በሚሰጥ ስምና አርማ ቀይሮ በሰላም የህዝብ ድምፅ በማግኘት ላይ አተኩሮ እንዲሰራ መክሬ ነበር። ህወሓት ስልጣኗን ለተሻሉና ህዝብ መሻላቸውን አምኖ ለሚመርጣቸው አመራሮች ሙሉ በሙሉም ባይሆን በከፊል እንድታስረክብ የማይፈልግ ሰው ያለ አይመስለኝም። የተሻለ ማግኘት ማን ይጠላል አመታት ትግራይ በብዙ ምሁራን በልፅጋለች። ይህን ፀጋ በመጠቀም በመጠቀ እውቀት ላይ የተመሰረተ የልማት አመራር እንዲሰፍን መደረጉ የማይቀር ታሪካዊ ግዴታ ነው። አሁን ወሳኙ ጥያቄ ይህ ለውጥ እንዴት ይምጣ ነው። በአለም ላይ ተመራጭ የሆነው የለውጥ አመጣጥ ሰላማዊ ትግል  መሆኑ ለአፍታም አያከራክርም። በትጥቅ ትግል ወይንም በጎዳና ግርግር፣ ሰላምን በማደፍረስ፣ ስርአት በማሰናከል፣ ሽብር በመፍጠር፣ ማህበራዊ ትስስርንና፣ የተለመደው ኢኮኖሚያዊ ህይወትን ስልት በማሳጣት የሚመጣው ለውጥ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍልና በታለመለት መስመር ተክትሎ ለመሄዱም ዋስትና የማይሰጥ ነው። ሰላማዊ ትግል ቀላል አይደለም፣ ትእግስት፣ የአላማ ቅንነትና ፅኑነት ያስፈልገዋል። ለዚህም ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል። ስልጣን እንደምፅዋት በያዘው አካል በቀላሉ የሚመፀወት ነገር አይደለም። ስልጣን የያዘው አካል ስልጣኑን አሳልፎ መስጠት ላይፈልግ ይችላል። ስልጣን መልቀቅ ቢፈልግም እንኳን የሚተካው አካል ከሱ የተሻለና ህዝባዊ ሃላፊነት የሚወስድ ለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አለበት። ህወሓትን የሚተካት ፓርቲ ወይንም ፓርቲዎች ህዝቡን አሁን ካለበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርሱና ደህንነቱንም የሚጠብቁ መሆናቸውን የማረጋገጥ ሃላፊነት አለባት። ህወሓት ይህን ሃላፊነቷን ያለ ራስ ወዳድነት እንድትወጣው ታሪክ ይጠብቅባታል። ስለዚህ ትግራይ ውስጥ ለውጥ የሚመጣው በህዝባዊ ምርጫ ብቻ መሆኑ መቀበል ግዴታ ነው። ህወሓትን መጥላት አንድ ነገር ነው ስለ ትግራይ ህዝብ የወደፊት ኑሮ ማሰብ ግን ሌላ ነገር ነው። ሁለቱን ማቀላቀል ተገቢ አይደለም። እያሉ የሚከራከሩ ሰዎች ከልብ አዝንላቸዋለሁ። በፓለቲካ አለም አንድ ችግርና አንድ የመፍትሄ ቁልፍ የሚባል ነገር ኖሮ አያውቅም። የማነ የተባሉት መሪ ና ትዴፓ ስልጣን ሲይዙ ለትግራይ ህዝብ ከህወሓት የበለጠ ምን በጎ ነገር ሊያቀርቡለት እንደሆነ ከመናገር ይልቅ ህወሓት ላይ የስድብ ናዳ በማውረድና ሞትን በመመኘት ለትግራይ ህዝብ ታላቅ ውለታ የሰሩለት ሆኖ ይሰማቸዋል። የተሻሉ መሆናቸውና ለውጡን የሚያመጡትም ህዝቡን በማይጎዳ ዘዴ መሆኑን በተጨባጭ ካላሳዩ የትግራይ ህዝብ ከልጅ ልጅ እንዲያበላልጥ የሚጠብቁት በምን ተአምር ነው :- "... እንደ ቄሮና ፋኖ የወጣቶች የእምቢተኝነት ትግል በማካሄድ ለ 30 ዓመታት በትግራይ ህዝብ ጫንቃ የሰፈረውን አስከፊ ስርዓት በመገርሰስ የትግራይ ህዝብ የታገለለትን፣ ልጆቹን የገበረበትን፣ አካሉን የከፈለለትንና ንብረቱ የወደመበትን ትግል ወደ ትክክለኛ አቅጣጫና ዓላማ ለማስገባት እንታገላለን " ። ከመጀመሪያው አባባላቸው ብጀምር፣ ቄሮና ፋኖ ያካሄዱት ሰላማዊ ትግል ነበር፣ በሁለት እጆቻቸው " ኤክስ " ሰርተው የነኩት ህንፃ፣ የነኩት መኪና፣ የነኩት ሰላማዊ ሰው፣ የነኩት ድርጅት የነኩት ፋብሪካ፣  የዘጉት መንገድ፣ ያባረሩት ህዝብ፣ የዘረፉት ንብረት ሳይኖር ነው ለውጥ ያመጡት እያሉን ከሆነ የልጆች ጨዋታ እየተጫወትን መሆን አለበት። ህወሓትን ከስልጣን ለማስወገድ በትግራይ ህዝብ ላይ የቄሮንና የፋኖ ስልት እንጠቀማለን የሚሉ ከሆነ የትግራይን ህዝብ ሰላማዊ ህይወት በማደፍረስ ከህወሓት በላይ የህዝብ ጠላት የሚሆኑት እነሱ ናቸው። ከመቶ አመት በኋላ የትግራይ ህዝብ ያገኛትን የ 30 አመት ሰላም የሚያደፈርስበት ማንም ቡድን የማንኛችንም የትግራይ ህዝብ ልጆች ጠላት ስለሆነ እንታገለዋለን። ትግራይ ውስጥ የምግብ ችግር፣ የዉሃ ችግር የአስተዳደር ችግር እንዳለ እናውቃለን። የሃብታምና ድሃ ልዩነት ሰፍቶ ቅጥ ያጣ መሆኑን እናውቃለን። ይህ በትእግስት፣ በዘዴ በጊዜ ሂደት የሚፈታ እንጂ በግርግርና በሁካታ የሚቀረፍ አይደለም። ሰው እኮ በሰላም ስላሳደረው አምላክን ያመሰግናል እንጂ ጧት ተነስቶ ለምን ፆም አሳደርከኝ ብሎ አይራገምም። ሰላም ከሁሉም ይመረጣል። የትግራይ ህዝብ እውነተኛ ልጅ የሆነ ሁሉ ለህዝቡ የሚመኝለት በቅድሚያ ሰላም ነው። ዴሞክራሲ፣ ልማት፣ መልካም አስተዳደር የሰላም ልጆች ናቸው። መተካካት እኮ የሚተካው ከተተካው የሚበልጥ ለመሆኑ ዋስትና አይሰጥም። ይህም አራት ኪሎ ላይ በተጨባጭ ታይቷል። ስለዚህ ፈንቅል ሆነ ሌላ እኔ እበልጣለሁ ባይ ለመብለጡ ምንም ማረጋገጫ የለም።
Full Website