ቀጣዩ ምርጫ፤ ስለትላንት ሙሾ በሚያወርዱ እና ዛሬ ላይ ሆነው ስለነገ ራዕይ ባላቸው መካከል ነው።

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ    ጥር 2 ቀን 2012 (01/11/2020)

ሰበብህን ቆጥበው፤ ጊዜ የማግኘት ጉዳይ ሳይሆን፤ ጊዜ የመስጠት ጉዳይ ነው፤ ላንተ በጣም አስፈላጊ ከሆነ፤ ጊዜ ስጥ”።     ያልታወቀ ሰው ከተናገረው የተወሰደ፡፡

በሃገራችን የፖለቲካ ጉዳይ፤ በተለይም ኢሕአዲግ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ፤ ምርጫ አወዛጋቢ ያልሆነበት ጊዜ የለም፡፡ ኢሕአዲግ፤ በጉልበቱ የሽግግር መንግሥት አቋቁሞ፤ እራሱን ያ ፀደቀውን ቻርተር ጥሶ፤ ጊዜውን ካራዘመ በኋላ፤ ሃገራችን ውስጥ “ቋሚ የሆነ መንግሥት ” ይመሰርት ዘንድ፤ በግንቦት 1987 ዓም ነበር የመጀመርያው “ሃገራዊ ምርጫ” የተካሄደው፡፡ ይህ ምርጫ ከመደረጉም በፊት ሆነ ከተደረገ በኋላ ከፍተኛ ውዝግብ ያስነሳ ከመሆኑም በላይ፤ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፈው ሃይል፤ ሜዳውን ሙሉ ለሙሉ ለገዥው ፓርቲ ትቶ፤ ገዥው ፓርቲ፤ ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው መንግስት ተቋቋመ፡፡

ከሌሎች የምርጫ ጊዜዎች፤ የ1987ቱን ምርጫ የተለየ የሚያደርገው፤ ለዚህ ምርጫ ምዕራባውያን ትኩረት ሰጥተውት፤ ተቃዋሚው በምርጫ ሊሳተፍ የሚችልበትን መንገድ ለማመቻቸት ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት ነበር፡፡ የአሜሪካን መንግስት፤ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት፤ በየካቲት 1987 ዓም፤ የፕሬዝዳንቱ የ ጸጥታ ጉዳዮች አማካሪ የነበሩት፤ አንቶኒ ሌክ የመሩት ቡድን፤ ከገዥው ፓርቲ እና ከተለያዩ የተቃዋሚ ሃይሎች ጋር በኋይት ሃውስ፤ ያደረጉት በርካታ ውይይቶች፤ የጥረቱ ምሳሌ ሆኖ ይጠቀሳል። ለዚህ የኢትዮጵያ ምርጫ፤ ምእራብውያኑ ትኩረት ሰጥተው በገዥው ፓርቲ ላይ ያደረጉት ግፊት፤ አንዳንድ ተቃዋሚ ጎራ ውስጥ የነበሩ “የፖለቲካ ልሂቃን” የተሳሳተ የፖለቲካ ስሌት በማድረግ፤ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ በመድረሳቸውም፤ ምዕራብውያኑ፤ ከሚገባው በላይ በገዥው ፓርቲ ላይ ከፍተኛ ጫና አድርገው፤ ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ምህዳሩን ይበረግዳል ብለው ገመቱ። በዚህም የተነሳ፤ ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ ይመሩት ከነበረው የፖለቲካ ድርጅት በስተቀር፤ ሁሉም በሚባል መልኩ፤ ገዥው ፓርቲ የምርጫ ጊዜውን ካላራዘመ እና የምርጫ ቦርዱን ካልቀየረ በስተቀር በምርጫው አንገባም ሲሉ ደመደሙ። ዶ/ር በየነም፤ በተቃዋሚው ጎራ በተደረገባቸው ከፍተኛ ጫና፤ ወደ ምርጫው ለመግባት የወሰኑትን ውሳኔ፤ በመከለስ፤ የግንቦት 1987 ምርጫ ላይ እንደማይሳተፉ ገለ ፁ።

Videos From Around The World

ይህ በተቃዋሚው ጎራ፤ የተወሰደው የተሳሳተ ውሳኔ፤ የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት ይልቅ በማጥበቡ፤ ሃገራችንን፤ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል። ይህ ፀሃፍ፤ በወቅቱ፤ በዋሽንግተን ዲሲ ይተላለፍ የነበረው የሕብረት ሬድዮ አዘጋጅ እና አቅራቢ ከነበሩት አንዱ ነበር። የዚህ ሬድዮ ዝግጅት የፈጠረለትን አጋጣሚም ተጠቅሞ፤ በተቃዋሚ ጎራ የነበረው የፖለቲካ ሃይል ወደ ምርጫው እንዲገባ ከፍተኛ ግፊት አድርጓል። ለኦነግ፤ ለኢድኃቅ፤ ለመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት፤ ለአማራጭ ሃይሎች፤ እንዲሁም በወቅቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር በአሜሪካ ለነበሩት ለአምባሳደር ብርሃኔ ገብረክርስቶስ፤ ቃለ መጠይቅ በማድረግ እና፤ መንግስትና ተቃዋሚው፤ ስምምነት ፈጥረው፤ ምርጫው ሁሉን አሳታፊ እንዲያደርግም ፤ በቃለ መጠይቆቹ ሞግቷል። ሆኖም፤ በተቃዋሚው እምቢተኝነት፤ እና ያለምንም እስትራተጂ በተወሰደ እርምጃ፤ ተቃዋሚው፤ በአለም መድረክ ላይ የነበረውን ተደማጭነት አጣ። ምዕራብውያኑም፤ ተቃዋሚው ሰበብ ፈላጊ እንጂ፤ የተፈጠረለትን አጋጣሚ ተጠቅሞ፤ በትግሉ፤ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ተግቶ ለመታገል የቆረጠ አይደለም ሲሉ ደመደሙ።

ምንም እንኳን የተቃዋሚው ሃይል፤ ሕዝቡ በ1987ቱ ምርጫ ባለመሳተፍ ገዥው ፓርቲ፤ መንግሥት የመሆነ “ሕጋዊነት” (legitimacy) እንዳይኖረው በምርጫው ላይ ማዕቀብ እንዲደረግ ቢሞክርም፤ ሕዝቡ በምርጫው ተሳተፈ፡፡ ከዛም በላይ፤ በርካታ ግለሰቦች፤ “በግል ተወዳዳሪነት” ገዥውን ፓርቲ ተቃውመው በምርጫው በመሳተፍ፤ ገዥው ፓርቲ ብቻውን መንግሥትን እንዲቆጣጠር እና፤ መንግሥትም ምርጫው “ፍትሃዊ እና ነ ፃ” ነው እንዲል አደረጉት። የሚያሳዝነው፤ የተቃዋሚው ሃይል፤ በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀስ፤ ሁኔታዎችን ለመምራት፤ የረጅም እና የአጭር ጊዜ ዓላማና ግቡን ነድፎ የማይንቀሳቀስ፤ ለሚፈጠሩ ነገሮች ምላሽ በመስጠት (react) የተጠመደ በመሆኑ፤ ትግሉን በቅጡ ሊመራ አልቻለም። ይህ ፀሃፍ፤ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር፤ ኢሕአፓ በሳንዲያጎ አዘጋጅቶት ለነበረው ስብሰባ “lack of strategic planning, the deficiency in the Ethiopian opposition camp” የሚል ሰፊ ሃተታ ያለው ጽሁፍ በማቅረብ፤ ገና ከጅምሩ፤ ተቃዋሚው የአጭር እና የረጅም ጊዜ አላማና ግብ፤ እንዲሁም የሚጓዝበትን መንገድ እንዲነድፍ፤ የምክር ሃሳብ አቅርቦ ነበር። ሆኖም እስከ መጨረሻው ያይነው ነገር፤ ተቃዋሚው በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ነው። በዚህም ምክንያት ነው “አንጋፋ የነበሩት”፡ እንደ ኢድኃቅ አይነት እና መድህን የተባሉት ድርጅቶች፤ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ሊከስሙ የቻሉት።

በዚህ ፀሃፍ እምነት፤ የተቃዋሚው ጎራ ትልቁ ችግር፤ ከስህተቱ ለመማር ፈቃደኛ ያልሆነ መሆኑ ነው። ከ1987ቱ ምርጫ ምንም ዓይነት ትምህርት ያልወሰደው የተቃዋሚ ሃይል፤ ለግንቦት 1992ቱ ምርጫም የማይሳተፍ መሆኑን፤ በአደባባይ አወጀ፡፡ በምርጫ ለመሳተፍ ያንገራግሩ የነበሩ፤ ሃገር ውስጥ የነበሩ ድርጅቶችም ላይ የወከባ ዘመቻ ተጀመረ፡፡ ምርጫ ውስጥ መሳተፍ እንደ ክህደትም ተቆጠረ፡፡ አንዳንዶቻችን፤ የምርጫው ሜዳ፤ ለገዥው ፓርቲ መተው የለበትም ብለን በማመናችን፤ በተለይም በግል እንወዳደራለን ብለው ዝግጅት ያደርጉ የነበሩ ሰዎችን በአንድ አጀንዳ ስር በማስተባበር፤ በየምርጫ ጣባያው የሚኖረው ውድድር፤ አንድ የኢሕአዲግ ተወዳዳሪ፤ ከአንድ ተቃዋሚ ጋር ሊወዳደር የሚችልበትን፤ መድረክ ለማዘጋጀት፤ በ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አንጋፋ ሚና ካላቸው ሰዎችም ጋር ውይይት ተደረገ። ይህ ሁኔታ በውይይት እና በጥናት ደረጃ ላይ በነበረበት ጊዜም፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት በመጀመሩ፤ ለተጀመረው ንድፈ ሃሳብ እንቅፋት ሆነ። በዚህ ውስብስብ ጊዜም ነበር፤ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢዴፓ) የተባለ፤ በአቶ ልደቱ አያሌው የተመራ ድርጅት ገና ብቅ ከማለቱ፤ በግንቦት 1992ቱ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያበሰረው፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ጥሩ ዜና ነበር፡፡ ኢዴፓን ተከትሎ፤ ሌሎች በሃገር ውስጥ የነበሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች በምርጫው ተሳተፉ ፤ በምርጫ 1992ም ተቃዋሚው ጎራ ገዥውን ፓርቲ ምጥ አስያዘው፡፡

በምርጫ 1992፤ ተቃዋሚው ባደረገው የምርጫ ተሳትፎ ምክንያት፤ የፌደራል ምክር ቤትም ውስጥ ሆነ በአንዳንድ የከተማ እና ክልል ምክር ቤቶች መቀመጫ ለማሸነፍ በመቻሉ፤ በየምክር ቤቶቹ ስብሰባዎች፤ ገዥውን ፓርቲ በመሞገት እና፤ የፖሊሲዎቹን ድክመት እና አደገኛነት በማጋለጥ፤ ለፖለቲካው ሂደት ያበረከቱት አስተዋ ጽኦ የሚናቅ አልነበረም። ተቃዋሚው ይህንን ያገኘውን ድል በማስፋት፤ የሕብረተሰቡን ልብ በማሸነፍ፤ ገዥውን ፓርቲ በራሱ የፖለቲካ ቁማር ከጨዋታ ውጪ ከማድረግ ይልቅ፤ እርስ በእርሱ በመጠላለፍ እና አንዱ ሌላውን በመተንኮስ ጊዜና ሃይል ማባከኑን ቀጠለ። “ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ” የሚለው የሕዝብ ግፊት በማየሉም ነው፤ በነሃሴ 1995 በአሜሪካ ሃገር ሜሪላንድ ግዛት ውስጥ፤ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ሕብረት (ሕብረት) የተባለው ድርጅት የተመሰረተው፡፡ ሕብረት ግን ወደ ታሰበለት ግብ ሳይደርስ፤ ገና ከጅምሩ፤ በውስጡ የነበሩት ድርጅቶች መንጠባጠብ ስለጀመሩ፤ ጉልበት አጣ፤ ያው ፖለቲካው ወደለመደው መጠላለፍ ቀጠለ፡፡ የዚሁ መጠላለፍ ምክንያት ነው በህዳር 1997 ቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ (ቅንጅት) የተባለውን ድርጅት የፈጠረው፡፡ ቅንጅት ከጅምሩ፤ ትግሉ ከኢሕአዲግ ጋር ሳይሆን፤ ትግሉ ከሕብረት ጋር ነበር፡፡ በሁለቱ መካከል የነበረው ሹክቻ ቀርቶ፤ ትግላቸውን በኢሕአዲግ ላይ እንዲያነጣጥሩ፤ ብዙ ግፊት በማድረጋችን፤ በሚያዚያ 1997፤ ምርጫው አንድ ወር ብቻ ሲቀረው፤ በቅንጅት እና በሕብረት መካከል ትብብር ተፈጠረ፡፡ ይህ የሚያሳየው፤ ተቃዋሚው፤ በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀስ እና ሃገራዊ ራዕዩ፤ የደከመ እንደነበር ነው፡፡ የግንቦት 2002 ምርጫም ሆነ፤ የግንቦት 2007 በኢትዮጵያ የተደረጉት ምርጫዎች የሚያሳዩት፤ በተቃዋሚው ጎራ መካከል፤ ኢሕአዲግን በጠላትነት ከመፈረጅ ባለፈ፤ ምንም ዓይነት፤ የአጭር እና የረጅም ጊዜ የጋራ አጀንዳ ነድፎ የማይንቀሳቀስ መሆኑን ነው።ምንም እንኳን መድረክ የተባለ ስብስብ ቢኖርም፤ በመድረክ ውስጥ ያሉ ብሔር ተኮር ድርጅቶች፤ የየብሔራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ከመቆም በቀር፤ ምንም ዓይነት ብሔራዊ የጋራ አጀንዳ ነድፈው የማይንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው፤ በህዳር 2007 የተነሳው አመጽ፤ ያለምንም ፖለቲካ ድርጅት መሪነት፤ በወጣቱ ግብታዊ ስሜት ሊቀሰቀስ የቻለው፡፡

ይህ ግብታዊ አመጽ፤ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ለውስጥ ለለውጥ ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ ሃይሎች ጉልበት በመፍጠሩ፤ ገዥው ፓርቲ፤ ከውስጡ ተገዝግዞ ዛሬ ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ዛሬ ደግሞ ለውጡን የሚመራው ሃይል፤ በሃገራችን፤ የዲሞክራሲያዊ ስልተ ስርዓት እንዲገነባ፤ ሕዝቡ ወዶና ፈቅዶ የመረጠው የፖለቲካ ሃይል የመንግሥትን ሃይል እንዲቆጣጠር ተግቶ በሚሰራበት ወቅት፤ የዚህ ሂደት እንቅፋት በመሆን ላይ ያሉት፤ በተቃዋሚ ጎራ ውስጥ የተሰልፉ ሃይሎች መሆናቸው አስገራሚ ነው። ሌላው ቀርቶ፤ ለመጀመርያ ጊዜ በታሪካችን፤ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች በምርጫ ፖለቲካ ውስጥ እንዲሳተፉ፤ ፈረ ቀዳጅ ሆኖ ድፍረት የሰጠው ኢዴፓ እንኳን፤ “የምርጫው ጊዜ ይራዘም” ሲል መስማቱ፤ አስገራሚ ነው። ሌላው አስገራሚ ነገር፤ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፈው ሃይል፤ ሃይሉን ሰብሰብ አድርጎ፤ ለሃገር ይጠቅማል የሚለውን፤ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ኑሮ እቅድ ነድፎ፤ ለግንቦት 2012 ምርጫ እራሱን ለማዘጋጀት ከመትጋት ይልቅ፤ ምርጫው ውስጥ ላለመሳተፍ “ሰበብ” መደርደሩ ነው፡፡ በሃገራችን ውስጥ ከ130 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች መኖር እራሱ፤ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፈው ሃይል፤ መሪ ያጣ፤ የፖለቲካ ሃይል ለመሆኑ፤ ምስክር ነው፡፡ በመቶ የሚቆጠሩ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን፤ አስተባብሮ፤ ቁጥራቸውን መቀነስ ያልቻለ የፖለቲካ ሃይል፤ ስንት የተወሳሰብ ችግር ያለባትን ሃገር በመሪነት ተረክቦ ሊያስተዳድር ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል ወይ?

የምርጫ ቦርድ በተወካዮች ምክር ቤት ያ ጸደቀውን የምርጫ ሕግ ተከትሎ፤ ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የምንሰማው አቤቱታ ሰበብ እንጂ፤ ምርጫ ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚያግድ አይደለም። ጊዜ ሰጥቶ ተግቶ በመስራት፤ ፖሊሲ ነድፎ፤ 10 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ማሳመን የማይችል የፖለቲካ ድርጅት፤ እንዴት ነው በሚሊዮን የሚቆጠር መራጭ ሊያሳምን የሚችለው? ይህንን ተከትሎ የምንሰማቸው አቤቱታዎች፤ ትላንትና ላይ ቆመው የወደፊቱን ማየት በማይፈልጉ የፖለቲካ ሃይሎች ነው፡፡ በግንቦት 2012 ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ ምርጫ እንደሚካሄድ ለማንም ሚስጥር አይደለም፡፡ ይህ ከአምስት አመታት በፊት ጀምሮ ይታወቅ ነበር፡፡ በሃገር ውስጥም ያሉ ይሁኑ ከሃገር ውጪ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ በአሁኑ የለውጥ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ የወሰኑት፤ በ1987 የጸደቀውን ሕገ መንግስት ተቀብለው ነው፡፡ ሕገ መንግስቱም በየአምስት ዓመቱ ብሔራዊ ምርጫ እንደሚኖር ደንግጓል፡፡ ከዛም አልፎ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ምርጫው እንደሚካሄድ እና ተቃዋሚ/ተፎካክሪ ድርጅቶች፤ መርሃ ግብራቸውን በመንደፍ ለሥልጣን እንዲወዳደሩ፤ ሥልጣን መያዝ የሚቻለውም በሕዝብ ምርጫ ብቻ መሆኑን ደግመው ደጋግመው መክረዋል፡፡ የግንቦት 2012 ምርጫ መካሄድ፤ ለማንም አዲስ ዜና ሊሆን አይገባውም፡፡

አሳዛኙ ነገር፤ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ውስጥ የታዘብነው፤ ለምርጫ ውድድር ከመዘጋጀት ይልቅ፤ በሙሾ ፖለቲካ ጊዜ ማባከንን፤ የሕዝብን ተስፋ ማጨለም እና፤ የራስን ድክመት ለመሸፈን ስበብ በማብዛት የተገኙ እድሎችን ማበላሸት ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ዓይነት የፖለቲካ ሃይሎች አሉ፡፡ አንደኛው ሃይል፤ ትላንት ላይ ቆሞ የወደፊቱን ለማየት ያልፈቀደ እና፤ በሙሾ ፖለቲካ፤ የፖለቲካ ሕይወቱን ማርዘም የሚችል የሚመስለው፤ እንዲሁም በአቤቱታ ሊፈጠር በሚችል፤ ትርምስ ሥልጣን በአቋራጭ ይዛለሁ ብሎ በቅዠት ውስጥ ያለ ነው፡፡ ሌላው የፖለቲካ ሃይል ደግሞ፤ ካለፈው ተምሮ፤ ዛሬን ተጠቅሞ፤ ነገ ሕዝቡ የተሻለ ሕይወት እንዲኖረው፤ ሃገራችን ነገ የተሻለች ሃገር እንድትሆን ተግቶ የሚሰራ ነው፡፡ ብዙዎቹ የብሔር ድርጅቶች፤ መሪዎቻቸው፤ ትላንት ላይ ቆመው የሚያላዝኑ በመሆናቸው፤ በምርጫው ላይ አሉታዊ ተ ጽእኖ ሊኖራቸው ይችላል። ይህን አሉታዊ ተጽእኖ ግን አቅጣጫ ሊያስቀየር የሚችለው፤ በተለይ የድርጅቱ አባላት፤ በአጠቃላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በትላንት ላይ ቆመው በቀሩት እና፤ በወደፊት መፃኢ እድሉ ላይ ባተኮሩ ድርጅቶች መካከል ያለውን ልዩነት በመረዳት፤ የወደፊት እድሉን ብሩህ የሚያደርጉ የፖለቲካ ድርጅቶችን በመምረጥ እና፤ የፖለቲካ ነጋዴዎችን፤ አጨበርባሪነት እምቢ በማለት ነው።

ስለትላንትና  እያጋነኑ በማውራት፤ በሕዝቡ ውስጥ ጥላቻን በመዝራት ጊዜ እና ሃይል የሚያባክኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ለሕዝብ የሚጠቅም ምንም ዓይነት መርሃ ግብር የላቸውም፤ ሕዝቡ ይህንን በቅጡ ሊረዳ ይችላል። ዛሬ ላይ ሆነን፤ እንደ ኦፌኮ መሪዎች፤ የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ፤ ከጥቁር አሜሪካውያን ታሪክ ጋር በሚያነፃጽር የሃሰት ትርከት፤ ሕዝብ በመቀስቀስ እና ስለኢሕአዲግ ኢፍትሃዊነት በማውራት ምርጫ ላይ ተሳትፎ፤ ማሸነፍ የሚቻል አይመስለኝም። ጥያቄው እነዚህ እና መሰል ድርጅቶች፤ የኢኮኖሚ፤ የማህበራዊ መርሃ ግብራቸው፤ እንዲሁም የፖለቲካ ፍልስፍናቸው ምንድነው የሚል ነው። እንደ ጃዋር መሐመድ ያሉ ጽንፈኞች፤ የሚፈልጉት የፖለቲካ ሃይል በምርጫ ከተሸነፍ፤ ሁከት ለመፍጠር እየተዘጋጁ መሆናቸው፤ ምልክቶቹ እየታዩ ነው። ጃዋር፤ ለኒውዮርክ ታይምስ በሰጠው ቃለ ምልልስ፤ ምርጫው ፍትሃዊ እና ነፃ መሆኑን የሚመዝነው በእሱ መመረጠ እና አለመመረጥ መሆኑን መግለፁ፤ አስቂኝ ብቻ ሳይሆን፤ የፖለቲካ እንⶽጭ መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳየበት ነው። ይኸው ግለሰብ፤ በቅርቡ የምርጫ ቦርድን የሚያምነው 50% መሆኑን እንደገለ ፀ አቶ ያሬድ ጥበቡ በፌስቡክ ገፃቸው ለጥፈዋል። የምርጫ ቦርድን ተአማኒነትም ሆነ፤ ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ መሆኑን የሚመዘንበትን ሚዛን፤ መስፈርቱን የሚነግሩን እንደ ጃዋር ዓይነት ሰዎች ዓላማቸው አንድ ነው፤ ይህም እኛ ካላሸነፍን፤ ምርጫው ነፃ አልነበረም ለማለት ነው። እነዚህ ሃይሎች ግን ቀጣዩን ምርጫ ሊያሸንፉ የሚችሉበት መርጋ ግብራቸው እና ማራጭ ሃሳባቸው ምን እንደሆነ እንኳን አይነግሩነም።

በዚህ ፀሃፍ እምነት፤ እነዚህ የፖለቲካ ሃይሎች፤ ሙሾ ከማውረድ ባለፈ አቅም የላቸውም። ኦፌኮም ሆነ በመድረክ ስር የተሰባሰቡት የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ ን ፈ ሃሳብ አቅርበው የሚያውቁት መቼ ነው ? እስከዛሬ የነበረው “ፖለቲካ” “ኢሕአዴግን በመኮነን” ላይ ብቻ ያተኮረ ፖለቲካ ነው፡፡ ዛሬ ትላንት አይደለም፤ ኢሕአዴግን በመኮነን ብቻ መጽደቅ አይቻልም፤ “የራስን የጽድቅ” ሥራ ሰርቶ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ በሚቀጥለው ምርጫ ኢሕአዴግ የሚባል የፖለቲካ ድርጅት እንኳን አይኖርም፡፡ ስለዚህ፤ ኢሕአዲግ አሳሪ ነው፤ ገራፊ ነው፤ ገዳይ ነው የሚል አጀንዳ ቦታ አይኖረወም፡፡ በዚህ ጸሃፍ ግምት፤ ዛሬ ላይ ሆነው፤ የነገን ተስፋ በመሰነቅ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሁለት የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ፤ እጅግ የሚደነቅ ተግባር እያከናወነ ያለው፤ ኢዜማ የተባለው የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ በኢዜማ ውስጥ የተሰባሰቡ የፖለቲካ ሃይሎች፤ ብቃታቸውን እና፤ የድርጅት ስርዓታቸውን (ዲስፕሊን) በተግባር አሳይተዋል፡፡ ምርጫው አይቀሬ መሆኑን በመረዳት፤ ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች አሰባስቦ አንድ ድርጅት ያዋቀረው ይህ ድርጅት፤ ስለትላንትና ስሞታ በማቅረብ ጊዜውን ሲያባክንም ሆነ፤ በትላንትና ታሪክ ላይ “የፖለቲካ ልፍያ” ውስጥ ሲንቦጫረቅ አናየውም፡፡ ይህ ፀሃፍ፤ ኢዜማ ውስጥ ካሉ ከማናቸውም ጋር ግላዊ ግንኙነት የለውም። በአንድ ወቅት ብቻ ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ዶ/ር ሳᎀኤል ዮሃንስ ጋር፤ በአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ላይ ለውይይት ከመቅረብ እና የተወሰነ ውይይት በግል ከማድረግ ውጭ፤ ምንም ዓይነት የጠበቀ ግንኙነት የለውም። ይህ ጽሁፍም አላማው ኢዜማንም ሆነ ሌላውን የፖለቲካ ድርጅት ምረጡ ወይም አትምረጡ ለማለት የተዘጋጀ አይደለም። የጽሁፉ ዓላማ፤ ሃገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የሚፈጥሩትን ሰበብ አቁመው፤ ጊዜያቸውን ተጠቅመው፤ ለሕዝብ አማራጭ እንዲያቀርቡ ለማሳሰብ ነው።

ከኢዜማ አካሄድ ብዙ መማር ይቻላል፤ ኢዜማ በበርካታ የምርጫ ጣብያዎች እጩዎቹን አዘጋጅቷል፤ ለአይቀሬው ምርጫ መርሃ ግብሩን ነድፎ፤ አባላቶቹ እንዲወያዩበት አድርጓል፤ “የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” ዓይነት ሰበብ ከኢዜማ አይሰማም። ኢዜማ ዛሬ ላይ ሆኖ፤ ለነገ፤ ለሃገር ያለውን ራዕይ፤ በወረቀት አስፍሮ የምርጫ ዘመቻ በማድረግ ላይ ያለ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ሃገራችን ዛሬ የምትፈልገው እንዲህ ዓይነት ይፖለቲካ ሃይል ነው። ለኢዜማ ተመጣጣኝ፤ ተፎካካሪ የሚሆነው፤ በቅርቡ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ መሪነት የተመሰረተው፤ የብልጽግና ፓርቲ ነው። የብልጽግና ፓርቲ ከኢሕአዴግ የወረሳቸው፤ ድርጅታዊ መዋቅሮች እና ሃብት ስላለው፤ በሃገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በክልሎች ደረጃ የመወዳደር ብቃት አለው። በዚህ ፀሃፍ ግምት፤ ብልጽግና ፓርቲ፤ እንደ ኢዜማ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ጉዳይ በእውቀት የተካኑ ሰዎች የሉትም። ብዙዎች፤ ብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ያሉ የአመራር አካላት፤ አቅማቸው ውሱን ነው። ሆኖም፤ እንደ ዶ/ር አብይ ያሉ፤ ብቃት ያላቸው መሪዎች፤ ሌሎች ብቃት ያላቸውን ልሂቃን ወደ ብልጽግና ፓርቲ ሊጎትቱ ይችላሉ። ትልቁ ነገር፤ ብልጽግና ፓርቲ በትላንትና ላይ ቆሞ ሙሾ እያወረደ አይደለም፤ ለሕዝብ የነገ ራዕዩን እያቀረበ ያለ እና፤ ለሕዝብ ተስፋ የሰጠ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ቀጣዩ ምርጫ፤ ስለፍትህ፤ ዲሞክራሲ፤ የፕረስ ነፃነት፤ ወዘተ ዓይነት አጀንዳዎች ብዙውን የክርክር ቦታ የሚወስዱ ሳይሆኑ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚደረግው የሥራ ፈጠራ፤ የቤት እጦት ቅነሳ፤ የሕክምና ተቋማት መስፋፍያ፤ የትምህርት ፍኖተ ካርታውን እና ትምህርት ቤቶችን ማሻሻያ፤ በሃገሪቱ ውስጥ የብሔራዊ ከበርቴውን ሊያሳድግ የሚችል የቀረጥ ሕግ፤ ሕፃናት እና አዛውንት ተኮር መርሃ ግብር፤ የፍትሕ ስርዓቱን ማሻሻያ፤ እንዲሁም በሃገሪቱ ውስጥ ያሉትን መሰረታዊ ልማቶችን ማሻሻያ፤ ተገቢ የሆነ የሞንተሪ እና የፊሲካል ፖሊሲውን ቀርፆ፤ የምርት አቅርቦት አሻሽሎ፤ የኑሩ ውድነትን መቀነስ እና፤ በተለይም ደግሞ፤ የሕዝብ ቁጥርን ጭማሬ ፍጥነት የሚገድብ እቅድን የተመለከቱ ክርክሮች ትኩረት የሚያገኙበት ይሆናሉ የሚል ግምትም አለ። ከምንም በላይ ቀጣዩ ምርጫ፤ ትላንት ላይ ቆመው ሙሾ በሚያወርዱና፤ ዛሬ ላይ ሆነው ስለወደፊቱ የሃጋራችን እድገት ራዕይ ባላቸው ሃይሎች እንደሚሆን፤ በርካታ ምልክቶች እየታዩ ነው። ስለዚህ፤ ሁሉም የፖለቲካ ሃይል፤ ጎራዴውን ሳይሆን አዕምሮውን በመሳል፤ ለውድድር ይዘጋጅ እላለሁ።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ።

Full Website