ahayder2000@gmail.

ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል

(ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)

01-11-20

ፕሮፓጋንዳ ማለት “እውነቱንም፣ ውሸቱንም፣ ግማሽ እውነት የሆነውንም ነገር ደጋግሞ በመናገር ህዝብን ማሳመን” መሆኑን በርካታ በመስኩ የተደረጉ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ የፖለቲካ ሣይንስ ሊቃውንት ደግሞ ፕሮፓጋንዳ የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን ያስተምራሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ፕሮፓጋንዳን ለበጎም ለመጥፎም ዓላማ ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ በዚህ ረገድ በ2ኛው የዓለም ጦርነት የሂትለር የፕሮፓጋንዳ ሚንስትር የነበረው ጆሴፍ ጎብልስ በወቅቱ የተዋጣለት ሥራ መስራቱ ይነገራል፡፡ ጎብልስ የናዚ ፓርቲ ዓላማዎች በጀርመን ህዝብ ዘንድ እንዲሰርፁ አድርጓል፡፡ የምእራባውያንን የኢምፔሪያሊት ፕሮፓጋንዳ መክቷል፡፡ ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ “ውሸት ሲደጋገሞ እውነት ይመስላል” የሚል አባባል ተደጋግሞ ሲነገር ሰምተናል ብየ አስባለሁ፡፡ ደርግ እና ኢህአዴግ የትጥቅ ትግል ያደርጉ በነበረበት ወቅት ይህቺን አባባል የተጠቀሙባት ይመስለኛል፡፡ በሁለቱም ወገን ጧትና ማታ የፕሮፓጋንዳ ቱማታ ይዥጎደጎድ እንደነበር በልጅነት አእምሮዬ መዝግቤ ይዣለሁ፡፡ ምሳሌ ላቅርብ፡፡ በ1980ዎቹ መጀመሪያ በደርግ በኩል ወያኔና ሻዕቢያን “ገንጣይ/አስገንጣይ” የሚል ታርጋ ለጥፎ በየጊዜው የሚወስዷቸውን እርምጃዎች በጋዜጣ፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን በማቅረብ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ይነዛባቸው ነበር፡፡ ለዚህ ነው “ገንጣይ፣ አስገንጣይ፣ ድልድይ አፍራሽ፣ ጎጠኛ…” የሚሉት እሳቤዎች እስከ ዛሬ ድረስ ከአንዳንዶቻችን አእምሮ ሊጠፉ ያልቻሉት፡፡ በአንድ ወቅት “ወያኔዎች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የስንቅ መያዣ ከረጢት አድርገውታል” በማለት በደርግ በኩል የተለቀቀ ፕሮፓጋንዳ እስከ አሁን ድረስ ከብዙዎች አእምሮ ያልተፋቀ ነው፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ አቶ መለስ “ባንዲራ ጨርቅ ነው” ሲሉ “ዱሮውንም የበሶ መቋጠሪያ አድርገውት ነበር…” የሚሉ ሰዎች ጥቂት የሚሰኙ አልነበሩም፡፡ በህወሓት/ኢህአዴግ በኩል ደግሞ “ፋሺስቱ ደርግ ባደረገው የአውሮፕላን ድብደባ አንድ ክምር ጭድ በማቃጠል 3 ዶሮዎችን ገድሏል…” የሚል ፕሮፓጋንዳ ይደመጥ ነበር፡፡ የደርግ ፕሮፓጋንዳ የተማረውንና ከተሜውን ለማሳመን ዒላማ ያደረገ ሲሆን፤ የህወሓት/ኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ ደግሞ አርሶ አደሩን ዒላማ ያደረገ ነበር፡፡ ወደዚህ ዘመን ፕሮፓጋንዳ እንምጣ፡፡ ፕሮፓጋንዳ ዛሬም መሣሪያነቱ አልቆመም፡፡ ከመደበኛው መገናኛ ብዙሀን አውታሮች በተጨማሪ በኢንተርኔት አማካይነት በሚለቀቅ የወሬ ውሽንፍር አእምሯችንን ለማጠብ (Brain washing) የሚደረገው ጥረት ለጉድ ነው፡፡ እነ “fake news” (የሀሰት ዜናዎች) የዚህ ዘመን የፕሮፓጋንዳ ዘዴዎች ይመስሉኛል፡፡ በዚች መጣጥፍ ትኩረት የማደርግበት ርእሰ ጉዳይ ግን በቀጥታ ፕሮፓጋንዳን በተመለከተ ሳይሆን በሀገራችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተደጋገመው ስለሚነገሩ “ፕሮፓጋንዳ መሰል” ሁኔታዎችን በሚመለከት ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጎንደር፣ በጎጃም፣ በአርሲ፣ በሶማሌ፣ በሐረር፣ … መስጊድ ተቃጠለ፤ ቤተ-ክርስቲያን ነደደ… የሚል ወሬ ይሰማና “ማን አቃጠለው” ብለን ስንጠይቅ “ህወሓት በገንዘብ የገዛቺው ኃይል” የሚል ሹክሹክታ እንሰማለን፡፡ ህወሓት ገንዘብ ሰጠች ብቻ ሳይሆን የገንዘቡ መጠን ጭምር “ይህን ያህል ሚሊዮን ብር በእንቶኔ አካውንት ውስጥ ተገኝቷል” የሚል አስተያየትም ይደመጣል፡፡ የገንዘቡ መጠን ብቻ ሳይሆን የቀድሞው የደህንነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ (አንዳንዶች ጌታቸው መንፈሱ ይሏቸዋል) ነገሩን እንዳቀናበሩት ሲወራ እንሰማለን፡፡ ትንሽ ቆየት ብሎ በሌላ የሀገሪቱ አካባቢ ሌላ ቃጠሎ፣ ሌላ ግድያ፣ ሌላ አስደንጋጭ ሁኔታ ተከስቶ “ማን አደረገው” ሲባል አሁንም “የህወሓት እጅ አለበት፡፡ ይህን ያህል ሚሊዮን ብር የያዙ ሰዎች ተይዘዋል” የሚል ሌላ ሹክሹክታል እንሰማለን፡፡ በአጠቃላይ፤ በዩንቨርስቲዎች ተማሪዎች ተጋጭተው ህይወት ጠፋ ሲባል - አቀናባሪው ህወሓት ነው የሚል ወሬ ተከትሎ ይመጣል፡፡ መስጂድ ተቃጠለ ሲባል - የህወሓት እጅ አለበት የሚል ሹክሹክታ ይሰማል፡፡ በጅግጂጋ ቤተ-ክርስቲያን ተቃጠለ - የህወሓት ቅጥረኞች ያደረጉት መሆን አለበት ይባላል፡፡ … በመላ ሀገሪቱ ባሉ ተቋማትና በግለሰቦች ሀብትና ንብረት ላይ ጭምር ለደረሱ ጥፋቶች ሁሉ “ከበስተጀርባው የህወሓት እጅ አለበት” የሚለው ድምዳሜ እስከ አሁን ድረስ አላቋረጠም፡፡ ከህወሓት ሌላ ከጥፋቶች በስተጀርባ ስማቸው የሚነሳው የአብን እና የኦነግ ስሞች ናቸው፡፡ እዚህ ላይ መነሳት የሚገባቸው ጥያቄዎች፡- “ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ (የአሁኑ ብልጽግና ፓርቲ) ተንኮል አይሰራም? ተቃዋሚዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው የሸፍጥ ሥራ አይሰሩም? ፀረ-ኢትዮጵያ የውጪ ኃይሎች እርስ በርስ እንድንባላ ሴራ አይጎነጉኑም?” የሚሉት ሁኔታዎች መታየት አለባቸው፡፡ አንድ ስፍራ ላይ ችግር አለ ብለን እዚያ ላይ ስናፈጥ በሌላ በኩል ችግር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ማድረግ መልካም ነው፡፡ ይህን ሁሉ ሴራ፣ ሼርና ተንኮል እውነት ህወሓት ፈጽማው ከሆነ፤ ከሞያሌ እስከ አሶሳ፣ ከጂግጂጋ እስከ አፋርና ኢሣ፣ ከጂማ እስከ ጭልጋ፣ ከሮቤ እስከ ወራቤ፣ … የጌታቸው መንፈሱና የህወሓት “የጥፋት መዋቅር” ሲዘረጋ መንግስት የት ነበር? የገንዘብ ዝውውሩም ሆነ የመረጃ ቅብብሎሹ ሲከናወን መንግስት የማንን ጎፈሬ ያበጥር ነበር? ህወሓትና አቶ ጌታቸው በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ እጃቸውን መዘርጋትና ያሻቸውን ማድረግ የሚያስችል አቅም አላቸው ማለትስ ምን ያህል አሳማኝ ነው? በአንድ በኩል ህወሓትን “ህዝብ እንደጠላት” እየተነገረ፤ በተለይም ከትግራይ ክልል ውጪ ባሉ አካባቢዎች የህወሓትን ተልእኮ ወስዶ የሚያስፈጽመው ማን ነው? በየአካባቢው እየሄዱ እሳት የሚለኩሱት፣ ጠብ የሚጭሩት የትግራይ ተወላጆች ናቸው? እውነት ይህንን ሲያደርጉ የተያዙ የትግራይ ተወላጆች አሉ? ካሉ ለምን እንድናያቸው አይደረግም? ለምን ስማቸው አይገለጽም? የህወሓት የገንዘብ ምንጭስ አይደርቅም? ብር ያትማሉ እንዴ?... የሚሉት ተጨማሪ ጥያቄዎችም በአግባቡ ሊታዩ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከመስጊዶችም ሆነ ከቤተ-ክርስቲያናት ቃጠሎ፣ ከዩንቨርስቲዎች ረብሻ፣ ከኢንቨስትመንቶች ውድመት.… ጀርባ በትክክል የህወሓት ወይም የአብን አሊያም የሌላ አካል እጅ ካለበት ማስረጃው ቀርቦ በይፋ ለህዝብ ይነገር፡፡ ካልሆነ ግን እንዲህ ያለው ውዥንብርና ፕሮፓጋንዳ የህወሓትን ወይም የአብንን አሊያም የሌላ የፖለቲካ ኃይልን ስም በከንቱ ማጥፋት ከመሆን የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ መቆምም አለበት፡፡ እኔ በግሌ የህወሓትም፣ የአብንም፣ የኦነግም፣ የፖለቲካ መስመር አይመቸኝም፡፡ ፖለቲካቸው ባይስማማኝም የተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ ሊነዛባቸውና ስማቸው በከንቱ ሊጠፋ አይገባም ብዬ አምናለሁ፡፡ ያጠፉት ጥፋት ወይም የሰሩት ወንጀል ካለ በተጨባጭ ይቅረብና ህግ ይቅጣቸው፡፡ በሌላ በኩል፤ ከሽብርና ከሁከት ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ስማቸው እየተነሳ ያሉት አካላት (ማለትም፡- ህወሓት፣ አብን፣ ኦነግ…) ለሚወራባቸው ሃሜትና አሉባልታ፣ ለሚነዛባቸው ፕሮፓጋንዳ ሁሉ መልስ መስጠት የማይጠበቅባቸው ቢሆንም፤ ጎላ ባሉ ጉዳዮች ላይ ማስተባበያ ሲሰጡ አለመታየቱ የሚያስገርም ነው፡፡ እነሱም ቢሆኑ “ውሸት ነው፣ የለንበትም፣ በከንቱ ስማችን እየጠፋ ነው…” ሊሉን ይገባል፡፡ የእነርሱ ዝምታ በአንድ በኩል ጥርጣሬዎችን ሊያባብስ እንደሚችል ልብ ሊሉት ይገባል፡፡ ከርእሰ ጉዳዩ ጋር በቀጥታ ያልተያያዘ ሌላ ማስታወሻ ልመርቅላችሁ፡፡ በዓብይ ዘመን የታሰሩ ሰዎች ለፍርድ ይቅረቡ፣ ይለቀቁ ካልሆነ የቁም እስርም መፍትሄ ነው የትግራይ ተወላጅ የሆኑ በርካታ ወዳጆች አሉኝ፡፡ እነዚህ ወዳጆቼ በአንድ ጉዳይ ላይ ደጋግመው ይወቅሱኛል፡፡ “በአሁኑ ወቅት በርካታ የትግራይ ተወላጆች ያለ አግባብ ታስረዋል፡፡ የፍርድ ሂደቱ ሆን ተብሎ እየተጓተተ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ባለመጻፍህ አንተም ገለልተኛ አይደለህም” ይሉኛል ወዳጆቼ፡፡ በፌስቡክ ገጼ ላይ ተራ አስተያየቴን በተደጋጋሚ ጽፌያለሁ፡፡ በጋዜጣም ይሁን በሌላ አግባብ መንግስትን ለመሞገት ግን “ተጨባጭ ማስረጃ” ያስፈልጋል፡፡ በእኔ ደረጃ ያለ፣ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው በስሜት ተነሳስቶ ብዕሩን ማሾል እንደማይገባው አምናለሁ፡፡ ከዚህ በታች ያሰፈርኩትን አስተያየት የጻፍኩት ተጨባጭ ማስረጃ አግኝቼ ሳይሆን በቢሆን ( if ) እሳቤ መሆኑን ለአንባቢያን አስቀድሜ መግለጽ እወዳለሁ፡፡ ዶ/ር ዓብይ አህመድ ስልጣን ከያዙ ወዲህ ባሉት 21 ወራት በርካታ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ተጠርጥረው እንደታሰሩ ይነገራል፡፡ አንዳንዱን ሁኔታ ከመገናኛ ብዙሃን ሰምተናል፡፡ ከታሳሪዎቹ ውስጥ ፖለቲከኞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከታሳሪዎቹ ውስጥ በግልጽ የሚታወቁ የትግራይ ተወላጆችም አሉ፡፡ ይህ የሚገርም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ባለፉት 25 ዓመታት በቁጥር በርከት ያሉ የትግራይ ተወላጆች በከፍተኛ የስልጣን ቦታዎች ላይ ስለነበሩ በቁጥር በርከት ያሉ የትግራይ ተወላጆች በተለያዩ የሙስና ወንጀሎች መጠርጠራቸው የሚጠበቅ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የሆነ ሆኖ ማንኛውም ሰው በወንጀል ለምን ተጠረጠረ ልንል አንችልም፡፡ ይሁን እንጂ ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት በሀገሪቱ የህግ አግባብ ነው ወይ? በህጉ መሰረት ፍርድ ቤት ቀርበዋል ወይ? ማስረጃ ተገኝቶባቸው ከተያዙ፤ ሁለት ዓመት ሙሉ ፍርድ ሳይሰጥ መቆየቱ የፍርዱን ሂደት መጓተት አያሳይም? ይህስ ተገቢ ነው? ህወሓት መራሹን ኢህአዴግ ስናወግዝ የነበረው ይህንን መሰል ተግባር በማድረጉ አይደለም እንዴ? … እነዚህ ጥያቄዎች በአግባቡ መታየት የሚገባቸው የፍትህ ስርዓቱን እንከኖች የሚያመላክቱ እንደሆኑ አስባለሁ፡፡
Full Website