ፈሪ አስሮና አፍኖ ይደበድባል

ሃይለ ሚካኤል ገሠሠ

12-10-20

ውጊያ ህግና ደንብ ብቻ ሳይሆን የጨዋነትና የጀግንነት ባህል የሚንፀባረቅበትም ነው። የድሮ ሰዎች የሰይፍ ፍልሚያ ሲያካሂዱ መሳሪያ በጋራ መርጠው፣ ተዋጊዎቹ ከውግያው ውጪ ሌላ አካላዊ ጉዳት እንዳይደርስባቸውና ለውግያው ያላቸው እኩል ዝግጁነት እንዳይዛነፍ በሁለቱም ወገን ይረጋገጣል። የማሸነፉ ጣእምና የጀግንነት ፉከራና ቀረርቶው ከውጊያ ስልት የበላይነት እንጂ ተቀናቃኙን ከሚያዳክምና ለጥቃት ከሚያጋልጥ የቅድመ ውጊያ ሸርና ተንኮል አይመነጭም። ውሃና ምግብ ከልክለው ካዳከሙት ጋር ተዋግቶ ማሸነፍ የፈሪ እንጂ የጀግና ሙያ አይደለም። "ግላድያተር" በሚባለው ታዋቂ ፊልም ላይ መንፈሰ ደካማውና ፈሪው የሮም ንጉስ እንደተቀናቃኝ ከቆጠረው ጦር አዛዥ ጋር ፍልሚያ ለመግጠም ሲዘጋጅ በትክክለኛ ፍልሚያ እንደማያሸንፍ እርግጠኛ ነበረ። ከሮም ህዝብ ፊት መዋረድ ያልፈለገው ንጉስ ጦር አዛዡን ከአደባባይ የፍልሚያው ስነስርአት አስቀድሞ ለማዳከም በጠባቂዎቹ ጎኑ ላይ በስለት እንዲወጋ አደረገ። በአደባባይ ፍልሚያው ላይ የጦር አዛዡ የተወጋው ወገቡን ይዞ እያነከሰ ሲዋጋ ብዙ ተጨማሪ ጉዳቶች ደርሰውበት መሸነፍ አፋፍ ላይ ሲደርስ ጀግና እስከመጨረሻዋ ትንፋሹ ተስፋ አይቆርጥምና ንጉሱን ክፉኛ ወግቶ ዘረረው። የፈሪና የግፈኛው ንጉስ ፍፃሜም ሆነ።

ይህ አይነት ሁኔታ በኢትዮጵያ ተከስቷል። የትግራይን ህዝብ ጀግንነት የማያውቅ ወይንም ፈርጣማ ክንዱን ያልቀመሰ የውጭ ወራሪ ሃይል የለም። ኢጣልያ በመሃል አገር ንጉስና በእንግሊዝ መንግስት ታዝላ፣ የትግራዩን ንጉስ በማህዲስቶች አስገድላ በሸርና በድጋፍ ወደ ትግራይ ዘለቀች እንጂ አሉላና ዮሃንስን በአይኗ እያየች እንኳንና አላጀ ወደ ደጋው አስመራ የምትወጣበት ድፍረትም አልነበራትም። እንግሊዝ የትግራይ ጀግኖችን የከሰላ ድል ብትሞት አትረሳውም። ግብፅም ለሶስተኛ ጊዜ ሰሜኑን ለመርገጥ እንዳትሞክር ያደረጋት የትግራይ ጀግንነት መሆኑ የታወቀ ነው። ትግራይን በጦር ማስገበር ያቃታቸው የአማራ ነገስታት ከ15ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ህዝቡን ሲያንበረክኩ የኖሩት በመከፋፈልና እርስ በርሱ በማጋጨት ነበር። መረብ ወዲህና መረብ ወድያ ብለው ለሁለት የገመሱት አልበቃ ብሎ በአውራጃና በወረዳ እየወገነ እርስ በርስ ሲተላለቅ ኖሯል። በኢኮኖሚ እንዲዳከምና የውጊያ አቅም እንዲያጣም ግብር በማብዛትና ግዛቱን እየቆረጡ ለራሳቸው በመጠቅለል፣ በድርቅ ሲራብና በአንበጣ ሲበላ "አይኔን ግንባር ያድርገው" ብለው ሲያስፈጁት የአማራ ነገስታት፣ መሳፍንትና ታሪክ ፀሃፊዎች ለአለም የሚነግሩት አማራው በጀግንነት የላቀ ሆኖ ትግራይን እንደገዛ ነበር።

Videos From Around The World

ትግራይ ግን "ድመት 12 ነፍስ አላት" እንደሚባለው ብትቀጠቀጥ የማትጠፋ፣ ብትጎድል የምትሞላ፣ ብትራብ የምትጠግብ፣ ብትጠማ የምትረካ ለጠላት የማትመች፣ ለወዳጅ ግን ወለላ ማር የሆነች የአማራ ገዢዎች የእግር እሾህ ናት። የአማራ ገዢዎች ኢትዮጵያን ዝንተ አለም ለመግዛት ላላቸው ህልም ብቸኛና ከስሩ ተነቅሎ የማይጠፋ ጋሪጣ የሆነችባቸው ትግራይ ብቻ ናት።  የተቸገሩበት የትግራይ ጀግንነት ብቻ አይደለም፣ የበላይነታቸውን ለኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያስመሰክሩበት ጥንታዊነት ያለው በትግራይ እጅ ውስጥ በመሆኑ ነው። ሶስት ሺህ አመት የትግራይ እንጂ የአማራ አይደለም። የአክሱም/ ትግራይ ሺህ አመታት የስልጣኔና የአለም አቀፍ ታዋቂነት ሲሆኑ ከዛግዌ በኋላ የነበሩት የአማራ 500 አመታት ግን የእርስበርስ ጦርነት፣ የመስፋፋትና የህዝቦችን መብት የገፈፉ የጨለማ አመታት ነበሩ። ለዚህም ነው ታሪክን ከባለ ታሪኮቹ በመቀማት የሌለ የበላይነት ለመፍጠር የሚሞከረው። የአማራ ልሂቃን ያለሃፍረት በሰው ልብስ የሚያጌጡባቸው ነገሮች ለምሳሌ: ከትግራይ:- የግእዝ ቋንቋና ፊደል፣ የያሬድ መንፈሳዊ ዜማ፣ የኦርቶዶክስና የእስልምና መነሻነት፣ እንዲሁም የአክሱም መስራችነትና ባለቤትነት ናቸው። ከላስታ/ አገውም ድንቅ የሆኑትን ውቅር አብያተ ክርስትያናት በአማራ አርማ ላይ በማካተት የታሪክ ቅሚያ ፈፅመዋል። ከአማራ እጅ ወጥቶ የኢትዮጵያ ህዝቦች በፈቃዳቸው መግባቢያ ያደረጉት አማርኛንም እንደ ግል ንብረት በመቁጠር የበላይነት ማስመስከሪያ ተደርጓል።

የትግራይን ጀግንነት በጨዋ ደንብ በጀግንነት እንደመግጠም የአማራ ገዢዎች   አንዳንድ የትግራይ መሳፍንትን አስከድተው ከጎናቸው በማሰለፍና በአገር ክህደት የእንግሊዝን የጦር አውሮፕላኖችና አብራሪዎችን በመጠቀም ቀዳማይ ወያኔን "አሸነፉ"። ይህ ሽንፈት እንጂ ማሸነፍ አይባልም። ጎራዴና ምንሽር የታጠቅ የገበሬ ጦርን ማሸነፍ ሲያቅታቸው መንግስት ያህል ነገር ከውጭ የአየር ድብደባ ድጋፍ ጠየቀ። ግፍ በዛብኝ ግብር በዛብኝ ያለውን የገዛ ወገኑን በውጭ ሃይል አስመታ። ይህ የፈሪ ተግባር ትግራይን ለጊዜው ያረጋጋ ቢመስልም ከ50 አመት በኋላ ከአላጀ የተመለሰው ወያናይ ልጆቹ አዲስ አበባ ገቡ። የብሄር ብሄረሰቦች የራስ አስተዳደር የሚያጎናፅፈውን ህገመንግስት አስፀድቀው የአማራ ገዢዎች ኢትዮጵያን አንድ አድርገው ለዘላለም ለመግዛት የነበራቸውን ህልም እስከወድያኛው አጨለሙት። በዚህ የተንገበገቡት የአማራ ልሂቃንና አይኑን ጨፍኖ የሚከተላቸው አጉል ተስፈኛ ህዝብ ትግራይን ለማጥፋትና ህልማቸው እውን ለማድረግ ቆርጠው ተነሳሱ። አሁን ግን ትግራይ ብቻዋን አልሆነችም። የፀረ-አማራ አገዛዝ መፍትሄ ስራይ የተከተቡት ቁጥራቸው ሰማንያ ያክል የሚሆኑት ብሄር ብሄረሰቦችም ጭምር ሆኑ። ይህ ግን የአማራ ልሂቃንን የነብር አይን ከትግራይ እንዲነቅሉ አላደረጋቸውም። ስጋታቸው፣ ቂማቸው፣ የበቀል ስሜታቸው ከመምህሩ እንጂ ከደቀ መዝሙሩ ላይ አልሆነም። ሌላውን ከመናቃቸው የተነሳ አውራው (ትግራይ) ከተመታ ቀሪው ገብስና አረፋ ነው ብለው አቃለሉት። ለሰላሳ አመታት በአማራ ልሂቃንና ጭፍን ተከታዮቻቸው በትግራይ ላይ የተካሄደው የማጥላላት ዘመቻ ሲከናወን የነበረውን ታይቶ የማይታወቅ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልህቀትን ለማገናዘብ ፍላጎትን ያሳየ አልነበረም። ትልቁና መልካሙ የአገር ደህንነት፣ የስላምና እድገት ስእል በትልቁ ጎልቶ የሚታይ ቢሆንም ስልታዊ በሆነና ሰፊ ሽፋን ባለው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የኢትዮጵያ ህዝቦች በችግሮች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩና  ትግራይን እንደ ዲያብሎስ እንዲቆጥሩ ጭንቅላታቸውን የማጠብ ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል። ለዚህም ነው ብሄር ብሄረሰቦች የትግራይ ህዝብ መስዋእትነት ድምፃቸው እንዲሰማና ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ የረዳቸው መሆኑን ረስተው እንደበዳይ የቆጠሩት። የህወሓት ስህተቶች ኢህአዲግን አብረው ከመሰረቱት ሌሎች ፓርቲዎች በተለየ ጎልተው እየወጡጽ የስርአት ለውጥና ለተሻለ ዴሞክራሲ ተብሎ የተካሄደው ለውጥ ተቀልብሶ በትግራይ ላይ ያፈጠጠ የአማራው ልሂቃን የዘመናት አጀንዳ ማስፈፀሚያ ሆኖ አረፈው። ትግሉን ያቀጣጠለውና ያለ ደም መቃባት ህወሓትን ከስልጣን ለማውረድ የሞከረው የኦሮሞ የለውጥ ሃይልም "አማራን ሸወድነው" እያለ  ቢንጠራራም የአማራ ልሂቃን ጉዳይ አስፈፃሚ ከመሆን ግን አልዳነም። የለውጥ ሂደቱን የጀመረው ፌደሬሽኑን የበለጠ በማጠናከር ሳይሆን የአማራ ነገስታትን ምስል በማደስ፣ ለደርግ ቅሪቶች የልብ ልብ በመስጠት እንዲያንሰራሩ በማድረግና ፌደራሊዝምን በአሃዳዊነት ለመተካት ዘመቻ በመክፈት ነው። የዚህ ዋና የጥቃት ኢላማ ደግሞ የፌዴራል አስተሳሰብ መከታ የሆነችው ትግራይ ነች። ለፌደራሊዝም መስፈን ሲታገሉ የነበሩት የኢህአዲግ አባል ድርጅቶችም በአሃዳዊነት ተጠልፈው በትግራይ ላይ በማፍጠጣቸው የራሳቸው ነፃነት አሳልፈው በመስጠት በገዛ ፈቃዳቸው ወደ ቀድሞው ባርነት የመውረድ አደገኛ ጉዞ ተያይዘውታል። በዚህ ሂደት ላይ ትግሉ የኦሮሞ ስኬቱ ግን የአማራ ሆኗል። የአማራ ስኬት የሚገለፀው ለአገዛዝ ህልሙ እንቅፋት በሆነችው ትግራይ ላይ በአስተዳደር በደል አሳቦ የኢትዮጵያን ህዝብ በማነሳሳት ነው። ይህ ህዝብን በትግራይ ላይ የማነሳሳቱ ስኬት የመጣው የአማራ ልሂቃን አምርረው የሚጠሉትና የአራዊት ህግ እያሉ ሲያሰየጥኑት የነበረው ህገ መንግስት ጥላ ከለላዎች ሆነው በመታየት ነው። "ጩኽቴን ቀሙኝ" እንደሚባለው የህገ መንግስቱ መከታዎች ፈጣሪዎቹ ትግራዮች ሳይሆኑ ህገ መንግስቱ በሌላ እንዲተካ የሚታገሉት የአማራ ልሂቃንና ተባባሪዎቻቸው ሆነው ተገኝተዋል። ምስኪን ህገ መንግስት፣ ጠባቂዎቹ ጠላቶቹ ናቸው !

ይህ የህገ መንግስት የይምሰል ጥበቃ ለኢትዮጵያ ህዝብ ፍጆታ እንጂ እውነታው ግን ህገ መንግስቱን መጠበቅ ሳይሆን መጣስ ነው። ቅራኔው ጉልህ ነው፣ ህገ መንግስቱ የሚጠበቀው ህገ መንግስቱን በመጣስ ሆኗል። ከረዥም ጊዜ ስነ አእምሯዊ ዝግጅት በኋላ የፌደራሊዝም የመጨረሻ ግን ከባድ ምሽግ በሆነችው ትግራይ ላይ ግልፅ ወረራ ተጀምሯል። ትግራይ ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ምርጫ በማካሄዷ ህገ መንግስት አፍራሽ ሆና ተፈረጀች። ይህ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ እንደ ወንጀለኛ እንድትታይ ያደርጋታል። ይህ ደግሞ ትግራይን ለማጥቃት አረንጓዴ መብራት የሚያበራ ነው። እውነት የጉልበትና የጩኸት የሚሆንበት ዘመን ደርሰናል። ሆኖም ትግራይን ለማጥቃት "በቂ ህዝባዊ ምክንያት" ይኑር እንጂ ጥቃቱ በስኬት ይጠናቀቃል የሚል እርግጠኝነት አልነበረም። የትግራይን አልበገር ባይነት በሚገባ የሚያውቀው የአማራው ልሂቅ እንደ ጀግና ትግራይን መግጠም መፍራቱ ግልፅ ነው። ፉከራውና ቀረርቶው ቢያስተጋባም፣ የስድቡ አይነት እየበረከተ ቢሄድም ስድብ ገለባ ነውና ውጤት አልባ ሆነ፣ "በጩኸት የፈረሰች ከተማ ብትኖር ኢያሪኮ ብቻ ናት"  እንደተባለው። ስለዚህ የአማራ ልሂቃን ተቀናቃኛቸውን ከውጊያ በፊት በአካል፣ በስነ ልቦናና በኢኮኖሚ የማዳከሙን የፈሪ ስልት መረጡ። ህዝብ ተባረረ፣ ተራው የትግራይ ህዝብ እንደ ባእድ ተቆጥሮ በያለበት የህልውና ስጋት እንዲያድርበት ዘመቻ ተከፈተበት፣ አውራ መንገድ ተዘግቶ ህዝብን ለማስራብ ተሞከረ፣ ተጋሩን ከስልጣን በማግለል የትግራይን የፓለቲካ አቅም ለመሸርሸር ጥረት ተደረገ፣ መብራት በማጥፋት፣ ስልክ፣ ኢንተርኔትና ባንክ በመዝጋት፣ በጀት በማገድ፣ ሰብአዊ እርዳታን በመከልከል ካዳከሙ በኋላ ጦርነትን አሸነፍኩ ብሎ መፎከርና ማቅራራት የፈሪ እንጂ የጀግና ተግባር አይደለም። የሮሙ ንጉስ ተቀናቃኙን ከፍልሚያ በፊት እንዳስወጋው አይነት ድርጊት ነው በትግራይ ላይ የተፀመው። በህግ ማስከበር ስም የውጭ ሃይል አስገብቶ የራስህን ህዝብ ማስደብደብ የመጀመሪያው ወያኔ ላይ የተደረገውን የፈሪ ድርጊት መድገም ነው። አነተኛ የጦር ዝግጅት ካለውና ቀድሞ በሸር የተዳከመው የትግራይ አቅም በውጭ እርዳታ ላይ ተደግፎ መውረር አሸናፊ አያሰኝም። ተዋጊው ኤርትራ ፎካሪው አማራ የሆነበት አስቂኝ ትእይንት እያየን ነው። በህገ መንግስቱ መሰረት የተካለለውን የትግራይ ደቡባዊና ምእራባዊ ድንበር በጦሩ ሳይሆን በአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሺያ እንዲጣስ ተደርጎ ህገ መንግስቱን በይፋ በማፍረስ፣ በምእራብ ትግራይና በደቡብ ትግራይ የአማራ ክልል አስተዳደር እየተደራጀ መሆኑ ይነገራል። ይህ ህገ መንግስቱን መጣስ ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? የህግ ማስከበሩ ዘመቻ ህግ እየተጣሰ የሚከናወን ከሆነ የዘመቻው ዋና አላማ ህወሓትን ለፍርድ ለማቅረብ ነው የሚለውን ዋጋ የሌለው ሽፋን ያደርገዋል። የፌደራል መንግስት የክልል ድንበር አከላለል በህገወጥ መንገድ ሲቀየር እያየ ዝምታን ከመረጠ በትግራይ ላይ ህግ ማስከበር የሚለው ፌዝ ይሆናል። ህገ መንግስቱ የሚከበረው በምሉእነት እንጂ አንድ ጎኑን እያስበሉ አይደለም። ህገ መንግስቱ ሊቀየር ነው የሚሉት በህገ መንግስቱ የበላይነታቸውን የተቀሙት ናቸው እንጂ ተጠቃሚዎቹ ብሄር ብሄረሰቦች አይደሉም። ገና ሊቀየር ነው በሚል ቅየራውን በህግ ጥላ ስር አስቀድሞ መተግበር ህገ ወጥነት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል። የመከላከያ አዛዦችና የአማራ ታጣቂዎች የተለያየ ነገር ይናገራሉ ግን ትግራይን አብረው ይወራሉ። መከላከያው ምእራብ ትግራይና ደቡብ ትግራይ ሲል የአማራው ታጣቂ ሰሜን ምእራብ አማራና ሰሜን አማራ ይለዋል። ህገ መንግስቱን የመጠበቅ አደራ የተሰጠው መከላከያ ህገ መንግስቱን ከሚንዱት ጎን ሆኖ ህገ መንግስቱን ከሚያከብረው ትግራይ ጋር እየተዋጋ ነው።  ምስቅልቅሉ የወጣ ታሪክ ነው፣ አንኳሩ ግን የአማራ የበላይነት እንቅፋትን የማስወገድ ዘመቻ ነው። ትግራይ ላይ በሚደረገው ጦርነት የተለያየ ባንዴራ የያዙ ሃይሎች ተሳትፈዋል። በትግራይ በኩል ህጋዊ የሆኑት የክልልና የፌደራል ባንዴራዎች የሚውለበለቡ ሲሆን ህግ አስከብራለሁ ብሎ የዘመተው ሃይል ግን ህገ መንግስቱ የከለከለውን ልሙጥ የቅድመ ፌደራሊዝም ባንዴራ እያውለበለቡ ትግራይ የገቡ እንዳሉ በስእላዊ ዜና ሪፓርቶች በግልፅ ታይቷል። ይህ የሚያመለክተው የጦርነቱ አላማ ትግራይን አዳክሞ የማንበርከክ እንጂ ህገ መንግስቱን የማስከበር አይደለም። ቢሆንማ ኖሮ ዋናው የህግ አስከባሪ ሊሆን የሚገባው ጦሩና የክልል ታጣቂ ሳይሆን የፌደራል ፓሊስ ሃላፊነት ነበር። ስለዚህ የአማራ ገዢ መደብ ሆይ ትግራይን በጀግንነት ለመግጠም የተበተብካትን ማሰሪያ ፍታላት፣ እንደፈሪ በእርዳታና ድጋፍም አትፋለማት። ይህን ካደረግህ ብትሸነፍም ጀግና ብታሸንፍም ጀግና ትሆናለህ። የምናወራው ስለሸጥከው ክብርህ እንጂ ትግራይንማ አታሸንፋትም።

Full Website