ፊንፊኔ

መስከረም 2013

አገራችን ያለችበት ሁኔታ ከኮ/ል አብይ አህመድ በስተቀር ሁሉም የውስጥም የውጭም ሐይሎች አደጋ አፋፍ መሆና ባለማወለወል የገመገሙበትና የተነተኑበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን።ኮ/ል አብይም በውስጣቸው የሚመሯት አገር በጣም አስከፊ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ተገንዝበው የሚይዙትና የሚጨብጡትን አጥተው ከሁሉም የቡዱናቸው (ቲማቸው) አባላት ጋር እርስ በርስ መበላላት ከጀመሩ ቆይተዋል። ኮነሬሉ ሁሌ ግዜ  ምንምዓይነት ሐላፊነት መውሰድ አይፈልጉም። እንደተለመደው ሁሉም ነገር በሌሎች የማላከክ የቆየ ባህሪያቸው አሁን ደግሞ በቡዱኑ (በቲሙ) አባላት ማላከክ ጀምረዋል።ስንኖር ኢትዮጵያውያን ስንሞትም ኢትዮጵያውያን ብለው የሂትለራዊና የመንግስቱ ሐይለማርያም መፈክር ያሰሙት ኮ/ል አብይ አህመድ የምንኖርባትና የምንቀበርባት አገር ኢትዮጵያ ሊያሳጡን ተግተው በመስራታቸው መንግስት አልባና የመበታተን አደጋ የተደቀነባት አገር ለመሆን በጣም አጭር ጊዜ ብቻ ቀርተቷል። የፌደራሊስት ሐይሎች ጥምረት ሰምኑን ያወጡት ሀገር የማዳን የሰላም ጥሪ ከዚህ አካያ ወቅታዊና አስፈላጊ ነው።

ይህ ሀገር የማዳን የሰላም ጥሪ ወቅታዊነቱና አስፈላጊነቱ የተረጋገጠ ቢሆንም ቅሉ ተግባራዊ መሆን ይችላል ማለት ግን አይደለም። ምቹ ሁኔታ ይፈልጋል። ለተግባራዊነቱ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ዘርዝሮ ማየትና ችግሮቹ በመፍታት እንዴት መሻገርና ጥሪዎቹ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል ብሎ መንቀሳቀስን ይጠይቃል። ስለዚህ በመጀመርያ ደረጃ የሰላም ጥሪው በራሱ ምን ያህል ተጨባጭ መፍትሔ ነው? በእውነት አገርን ከመበታተን ሊታደግ ይችላል ወይ? የሚለውን ለመመለስ ይዘቱን ብንፈትሸው አንዱ ለተግባራዊነቱ የሚወስን ጉዳይን ማየት ይቻላል።

የፌደራሊስት ሐይሎች ጥምረት ባለ አስራ አንድ ነጥብ የአገር የማዳን ሰላም ጥሪ ለመላው የኢትይጵያ ህዝቦች፣ ፖለቲካዊ ሐይሎችና በስልጣን ላለው ቡዱን አቅርቧል። መግለጫው ወደ አስራ አንዱ ዝርዝሮች ከመግባቱ በፊት አምስት አንቀፆች ያሉት መግብያ ያስቀምጣል። ኢትዮጵያ በጥልቅ ቀውስ እንደምትገኝ፣ ግንቦት 2012 መካሄድ የነበረበት ጠቅላላ ምርጫ ህገመንግስታዊ ባልሆነ መንገድ መተላለፉ፣ ምርጫ ከአምስት ዓመት በላይ ለማራዘም ህገመንግስቱ እንደማይፈቅድና ህገመንግስቱ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት ክፍተት እንደሌለው በተዘዋዋሪ በመግለፅ ይጀምርና በሁለተኛው አንቀፅ በሰላም እጦትና በጠራ ፖሊሲ ባለመመራቱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያትታል። ቀጥሎም በስልጣን ያለው ቡዱን የዲሞክራሲ ምሰሶ የሆኑትን ምክርቤቶችና ሚድያዎች በመቆጣጠር ነፃነታቸውን በመቀማት የግሉ የፖለቲካ አጀንዳ አስፈፃሚዎች በማድረግ በህዝብ ጥያቄዎች ላይ ለማፈንና ለመጨፍለቅ እየተጠቀመባቸው መሆኑን ያስረዳል። በማጠናከርም በስልጣን ያለው ቡዱን ከመሻሻል ይልቅ ይባስ ብሎ ጭቆናውን በማስፋት በህዝቡና በመሪዎቹ ላይ አሰቃቂ ግፎች በመፈፀም ሁኔታው እየተባባሰ እንደሚገኝና ይህ ሁኔታ ፈጥኖ ካልተቀለበሰ አገራችን የመፈራረስና የመበታተን አደጋ እንደሚገጥማትና ለምስራቅ አፍሪካ ይሁን ደቡባዊ ቀይ ባህር ብሎም ለዓለም ሰላምና ድህንነት አደጋ እንደሆነ በፅኑ ይሞግታል። በመጨረሻም ይህ ታሪካዊ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ህዝቦችና ፖለቲካዊ ሐይሎች በአንድ ቆመው አገር የማዳን ግዴታቸው መወጣት እንዳለባቸው በአፅንኦት ጥሪ በማድረግ ነው አስራ አንዱን ዝርዝር ነጥቦች የሚገልፀው።

በመሰረቱ ይህ መግቢያው ክፍል አሁን አገራችን ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ በጣም አጭር በሆነ አገላለፅ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ኢትዮጵያ ከዚህ የተጋረጠባት አደጋ ማውጣት የሁሉም አገር ወዳድ ግዴታ መሆኑና ወቅቱም አሁንና አሁን መሆኑን በግልፅ ያስቀምጣል። በፖለቲካ ሐይሎች ያሉ ልዩነቶች በሁለተኛ ደረጃ መታየት እንዳለባቸው ያስቀምጣል። መጀመርያ በምን መንገድ ትመራ ከሚለው የሐሳብ መስመር ልዩነት እንዴት ትመራ የትኛው ያዋጣል የምንልላት አገር ኢትዮጵያ ከመበታተን እናድናት ይላል።

የመግለጫው አስራአንዱ ነጥቦች በይዘታቸው በሶስት በመክፍል አንደሚከተለው አይቻቸው አለሁኝ።

የመጀመርያዎቹ አራት ነጥቦች የኮ/ል አብይ አህመድ መንግስት በውዴታም በግዴታም ሊፈፅማቸው የሚገባ ነጥቦች ናቸው። በንፁሓን ህዝቦች የሚደረጉ ግድያዎችና እስራት አቁሞ ለሰላም ጥሪው ዝግጁነቱ እንዲያውጅ፣ በማንኛውም የአገሪቱ ክፍል ያሉ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈታ፣ የውጭ የድህንነትና ፀጥታ አካላት ከአገራችን እንዲወጡ እንዲያደርግ፣ በየክልሉ የፈጠረው ወታደራዊ አስተዳደር እንዲያፈርስና ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ስራ እንዲሰሩ፣ የፀጥታ ስራም ፌደራል ፖሊስና የክልል ፖሊሶች እንዲፈፅሙት፣ የመከላከያ ሰራዊቱ በህገመንግስቱ በተሰጠው ስራብቻ  እንዲያተኩር አፅንኦት በመስጠት ይገልፃል።

እነዚህ ለመፈፀም የማያስቸግሩ ናቸው። ሰላም ጥሪውን መቀበል ለኮ/ል አብይ እንደ ኮ/ል ጋዳፊ መኪናቸው ውስጥ ወይም የቆሻሻ ቦይ ውስጥ በድንጋይ ተወግረው ሬሳቸው እንዳይገኝ ወይም እንደ ኮ/ል መንግስቱ ለመፈርጠት ከመከጀል የሚያድናቸው ነው። በዛውም ገና በውል ያልተፈጠረው ፓርቲያቸው ፒፒ በሽግግሩ መድረክ እንዲሳተፍም ዕድል ይሰጣል። እነዚህ አራት ነጥቦች ተግባራዊ እንዳይሆኑ ዕንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉት ኮ/ል አብይ ስልጣን ወይ ሞት ብለው ከተንቀሳቀሱ ብቻ ነው። አልቀበልም! ብለው ኣካኪ ዘራፍ ሊሉ ይችላሉ። ድርቅ ካሉ ደግሞ ይሰበራሉ። እንዳይሰበሩ ሌላ መንገድ ሊመርጡ ይችላሉ። ፈረንጆቹ አስታራቂ ሐሳብ እያሉ በተለያዩ ድርጅቶቻቸው አማካይነት ሲገልፁት የቆዩትን ተቀብያለሁ፣ የፖለቲካ እስረኞች እፈታለሁና አስቸካይ ጊዚያዊ አዋጁን አንስቻለሁ ብለው እሺ እንደራደር ሊሉ ይችላሉ። በስልጣናቸው ሁነው መደራደርን ሊመርጡ ይችላሉ። ተገደው የፈቷቸውን ፖለቲካ እስረኞች በራሳቸው በጎ ፍቃድ እንደፈቱ ሊከውኑ ይችላሉ። በፖለቲካ እስረኞች አፈታትም ግማሹን ፈተው እንትና በሽብርተኝነት ስለሚጠየቅ እንትና በሙስና ወይም የክልል አስተዳደር ነው የከሰሱት እኔ ጣልቃ ገብቼ ፍቱ ማለት አልችልም ወደሚል ጨዋታም ሊገቡ ይችላሉ።

ሁለተኛው ክፍል ሦስት ነጥቦች የያዘው ክፍል ሆኖ አምስት ስድስትና ሰባት ላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች ያካተተ ነው። የሰላምና አገርን የማዳን ዓላማ ያነገበ ከሁሉም ብሄር ብሄረስቦች የተወከሉ ሁሉም የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ፓርቲዎችና ማህበራት የሚሳተፉበት ኮንፍረንስ እንዲዘጋጅና በዚህ ኮንፍረንስ በአገሪቱ ያሉ ሁሉም የፖለቲካ ችግሮች የሚፈቱበት ስትራተጂ የሚነድፍበትና ነፃና ፍትሓዊ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሚካሄድበትን ሁኔታ መክሮ መፍትሔ ማዘጋጀት በተጨማሪም ስድስተኛው ነጥብ የአገር ሽማግሌዎቹ ከሁሉም ህዝቦች የተውጣጡ የተባለውን ኮንፍረንስ እንዲያመቻቹና በሰባተኛው ነጥብም ገለልተኛ የሆነ የባለሞያዎች የባለ አደራ መንግስት ከሁሉም የብሄር ብሄረሰቦችን የሚያንፀባርቅ መንግስታዊ አስተዳደር እንዲመሰረትና ምርጫ ተካሂዶ ህጋዊ አስተዳዳሪ እስኪመሰረት እንዲያስተዳድር የሚል ይገኝበታል።

ይህ ለኔ ለኮ/ል አብይም ለፀረ ህገመንግስት ለሆኑ ሐይሎችም በተወሰነም ለውጭ ሐይሎች/ሁሉም ላይሆኑ ይችላሉ/ የሚከብዳቸው ይሆናል። ይህን የሰላም ጥሪ መቀበል እውነተኛ ኢትዮጵያዊ መሆንን ይጠይቃል። በምላስ ኢትዮጵያዊነት ለሚሰብኩት ወሳኝ ፈተና ይሆናል። በቁጥር ሲሰሉ እነዚህ በጣም ጥቂቶች ናቸው። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሊህቅ ኢትዮጵያ እየፈረሰች ማየት እንደማይፈልግ መገምገም ይቻላል። ሆኖም መፈለግና እንዳይሆን ማድረግ/መፈፀም ለየቅል ነው። በውጤቱ አተኩሮ ሀገር ማዳኑን ሳይሆን ከማዳን በኃላ ያለው የስልጣን ገበጣ እያሰበ መፍርስ የማይመኝላትን አገር ሊያፈርሳት የሚችል ተግባር ሊፈፅም ይችላል። ይህ አንዱ ተግዳሮት ነው። ኮ/ል አብይና የውጭ አለቆቹ ያመጡት ለውጥ ተብየ እንዲህ መውደቁ ብቻ ሳይሆን አገር የሚበትን የሚያፈርስ መሆኑን እያዩም በሌላ መንገድ ሌላ ኣማራጭ ይዘውና በዚህ የሰላም ጥሪ ተመርኩዘው ሌላ የነሱን ጥቅም የሚያረጋግጥ በተጨባጭ ግን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚጎዳ መደራደርያ በማምጣት ሊያደናቅፉትና የመበታተኑ የእልቂቱ አደጋ እንዲቀጥል ሊያደርጉ ይችላሉ። ኮ/ል አብይም ስልጣን ወይ ሞት ብለው ምርጫ ይደረጋል ከፈለጋቹሁ በምርጫ ጣሉኝ ብለው እስካሁን በጥሪው ላይ አስተያየት እንዳልሰጡትና እንዳይሰጥበትም በሚቆጣጠሩት ሚድያ እንዳደረጉት ሊቀጥሉ ይችላሉ። ይህ ደግሞ አገር ወዳዶች አሁን በመላው አገሪቱ እየተቀጣጠለ ያለውን ትግል ከፍ አድርገው የአብይን መንግስት ሊያወድቁ ተጨማሪ መስዋእትነት በመክፈል አገርን ከመፈራረስ ለመታደግ የሚያስገድድ ይሆናል። የሚቻልም አማራጭ ነው። ይህ ክፍል የኮ/ል አብይን መንግስትና በየክልሉ ያሉ የስልጣን ዕድሜያቸው በህገመንስቱ መሰረት መስከረም ማገባደጃ ሲያበቃ ከስልጣን እንዲወርዱ በሰላም በፍቃደኝነት ወይም በሐይል ስለሚያደርግ ከትግራይ በስተቀር በሁሉም ክልሎች የባለአደራ መንግስት መመስረትን ይጠይቃል። የሁሉም ህዝቦች ተሳትፎና ክትትል የሚጠይቅ ስራ ስለሆነ ከባድም ቢሆንም ሊፈፀም የሚችል ነው። የህዝቦች ተደራጅተው ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጡ ጉዳይ ወሳኝ ያደርገዋልና።

የመጨረሻው ክፍል ለሰላም ጥሪው ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ በጣም አስፈላጊ የሆኑ አራት ነጥቦችን ያካተተ ነው። የመጀመርያው ነጥብ በኢህአዴግ ዘመን ተፈፀሙ የሚባሉትን ወንጀሎችና በዚህ ግዜ በኮ/ል አብይ ዘመን እየተፈፀሙ ያሉ ወንጀሎችን የሚያጣራና ለህዝብ ይፋ የሚያደርግ ገለለተኛ ቡዱን እንዲደራጅ ይጠራል። ሚድያ በህገመንግስቱ አጥር ውስጥ ሁነው እንዲሰሩና ትኩረታቸው አገር የማዳን ስራ ላይ እንዲያደርጉ የማመቻቸት ስራም እንዲሰራ ጥሪ ይደርጋል። ዓለም አቀፍ አጋሮች ለዚህ አገር ማዳን ስራ እንዲደግፉ በማለት መጨረሻ የሚያጠቃልለው ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ብሄር ብሄረስቦችና የመከላከያ እና የፀጥታ ሃይሎች የፖለቲካና የማህበረሰብ ድርጅቶች ይህን ታሪካዊ ሀገር የማዳን ጥሪ የሰላም ጥሪ እንዲደግፉ ይላል።

ይህኛው ክፍል የቀደሙት ሁለት ክፍሎች ተግባራዊ መሆን የሚችሉበት ሁኔታ ከተፈጠረ ለማጠናከር የሚረዱ ቁልፍ ነጥቦች ናቸው። ይጣራ የተባለው የአብይ ቡዱን ሊቀበለው የሚከብደው ቢሆንም ከስልጣኑ በፍቃዱም ያለፈቃዱም ከወረደ በኃላ የሚፈፀም ስለሆነ የሚያሰቸግር አይሆንም። የውጭ ሐይሎች በጠቅላላው የሚደግፉበት ሁኔታ ተለይቶ ካልተሰጠ በውስጥ ጉዳያችን መፈትፈታቸው ስለማይቀር አፍራሽ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ድጋፋቸው የማይፈለግ አገሮችና ድርጅቶችም መለየት አለባቸው። ይህም ሆኖ የዓለም አቀፍ ተሳትፎ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም። የፈረሰ አገር ማየት አይፈልጉም። የፈረሰ አገር ጥቅማቸውን በቀጥታም በተዘዋዋሪም መጉዳቱ አይቀርም። ድጋፋቸው ግልፅነት ያለውና አገር ለማዳን ለምናደርገው እንቅስቃሴ የሚረዳ መሆን አለበት። የህዝቦች ድጋፍ ሲባል ፖለቲኮኞች ጉዳዩን ፈትፍተው ለህዝቡ እንዲያቀርቡ ማለት አይደለም። ህዝቦች አገር በማዳን ሚናቸው ጥሪው እውን እንዲሆን ከማድረግ ጀምሮ የሰላም ሀገር የማዳን ሂደቱ ተሳክቶ ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ እስኪረጋገጥ በቀጥታ የሚሳተፉበትና ሁሉም ሂደት ከህዝቡ ያልተደበቀና በየወቅቱ የሚገለፅበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ህዝቦች ይህ የሀገር እናድን ይህ የሰላም ጥሪ የራሳቸው የትግል ጥሪ ነው። ወሳኝ ሚናቸውን የሚጫወቱበት ጉዳያቸው ነው። የመከላከያና ሌሎች የፀጥታ አካላትና ፖለቲከኛችም ማህበራትም ድጋፋቸው የማይተካ ተራ እንዳለው አውቀው መሳተፍ አለባቸው። ይሳተፋሉም። በምንም መንገድ ጥሪው መደናቀፍ እንደለሌበት ይገነዘባሉ ብየ አስባለሁ።
Full Website