በኮሮና መስፋፋት የዘፈቀደ ግምት ከጥቅሙ ጉዳቱ በእጅጉ ያመዝናል!!

በታደሰ በርሄ (ብ/ጄነራል) 05-04-20

በሚያዝያ 13/2020 እ.ኤ.አ በተስፋለም ወልደየስ ዘጋቢነት በ (Ethiopiainsider) በኩል ለአንባቢ የቀረበ በኢትዮጵያ ሰለሚኖር የኮሮና ቫይረስ መስፋፋት የሚያትት በባለሙያዎች የተደረገ ጥናታዊ ግምት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

- በኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ በዚሁ ከቀጠለ በሰኔ ወር መጨረሻ 33 ሚልዮን ገደማ ሰዎች በቫይረሱ እንደሚጠቁ፣

- በመጪው ግንቦት ወር ብቻ 1.94 ሚልዮን ሰዎች በቫይረሱ እንደሚለከፉ፣

- በሕብረተሰቡ ያለውን ንክኪ በግማሽ መቀነስ ከተቻለ ወደ 15 ሚልዮን ገደማ በበሽታው እንዳይያዙ መታደግ እንደሚቻል፣

- የቫይረሱ ስርጭት ወደ ወረርሽኝ በሚያድግበት ወቅት ከአዲስ አበባ ህዝብ ውስጥ 50 በመቶ ያህሉ ለቫይረሱ ሊጋለጥ እንደሚችል፣ እና

Videos From Around The World

- በአዲስ አበባ በሚያዝያ ወር በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች 250 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል፡ በቀጣይ ወር (ግንቦት) ቁጥሩ ወደ 1.4 ሚልዮን ሊያሻቅብ እንደሚችል ጥናታዊ ግምቱ ገለፆ፣ የህብረተሰቡ ንክኪ በግማሽ  ከቀነሰ ግን 872,243 ሰዎች ከመጠቃት ሊድኑ እንደሚችሉ ያስቀምጣል፡፡ (እዚህ ላይ የግምታዊ አሃዙ  ስሌታዊ እርግጠኝነት ግርምትን ይፈጥራል)፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ የጤና ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቱትዮት ባለፈው መጋቢት ወር የተዘረጋ ሌላ ሰነድ፡-

- 28 ሚልዮን ሰዎች በቫይረሱ ሊያዙ እንደሚችሉø ሆኖም የጐንደርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባለሙያዎች ሐሳብ ተጨምሮበት ይህንን አሃዝ በ5 ሚልዮን ጭማሪ ሊያሳይ እንደሚችል፣እና

- ከከተማ ነዋሪዎች አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ውስጥ 21 በመቶ በኮሮና የመጠቃት አደጋ እንዳለውና ይህም በቁጥር ሲገመት 23 ሚልዮን እንደሆነ ተገልïል፡፡

አሁን በቅርቡ በግንቦት 2/2020 እ.ኤ.አ በጤና ሚኒስቴር የጤና ነክ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ያዕቆብ ሰማን ለኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የተናገሩት ፡-

- በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር እና የከፋ ጉዳት ሊደርስ የሚችለው ሰኔ መጨረሻና ሐምሌ መጀመሪያ ቀናት መሆኑን ገልፀው፣ በሃገር አቀፍ ደረጃ አሁን የምናደርገውን ጥንቃቄ ባናደርግ ከ27 ሚልዮን በላይ ህዝብ ኮሮና ያጠቃብን ነበር፡፡ በደንብ ከተጠነቀቅን ደግሞ የዚህ ቁጥር 60 በመቶ ወይንም 16 ሚሊዮን መቀነስ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡

እርግጥ ነው በመንግስት የሚወጡ መመሪያዎችና በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክሮች  ህብረተሰባችን ተቀብሎ በጥንቃቄ ካልተገበረ በኮሮና ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ስለሆነም የቫይረሱን መስፋፋት ለመከላከል በመንግስት የሚወጡ መመሪያዎች ለተፈፃሚነታቸው መንግስት ቁጥጥሩን ማጥበቅና ህዝቡም በመንግስት የሚወጡ  መመሪያዎችና በህክምና ባለሙያዎች በመሰጠት ላይ ያሉት ምክሮችን ፀንቶ የማክበርና የመፈፀም ሃላፊነቱን በተገቢው መፈፀም ይኖርበታል፡፡ ህዝቡ አሁን ባለው በቫይረሱ የሚያዝ አነስተኛ የሰው ቁጥር በማየት የሚታይ መዘናጋትና ቸልተኝነት የሚኖር ከሆነ ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋለጥ ይሆናል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ “በጥናታዊ” ግምቱ ላይ መነሳት የሚችሉ  በርካታ ጥያቄዎች ይኖራሉ፡፡  ከነዚህ ውስጥ፡-

Ø በቁጥር ተደግፎ የቀረበው ጥናታዊ ግምት እንደ መነሻ የወሰደው ምንድ ነው?

Ø የጥናቱ አለማስ ምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎች ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በባለሙያ የሚደረግ ግምት (Estimation) በተራ ሰው በዘፈቀደ ከሚደረግ ግምት (intuitive guess) የሚለየው÷ በባለሙያ የሚደረግ ግምት ምክንያታዊነት ባለው አግባብ ተሂዶ የሚደረስ ድምዳሜ በመሆኑ በተቻለ መጠን ወደ እውነታው (Reality) የተጠጋ እና ተገቢነት ያለው ግምት ይሆናል፡፡

በአንፃሩ በዘፈቀደ የሚደረግ ግምት በአመዛኙ በግብታዊነት (Spontaneous) የሚመረኮዝ በመሆኑ ከእውነታው ጋር ተቀራራቢነት የሌለውና እጅጉን የሚራራቅ በመሆኑ ጠቃሚነቱ እስከዚህም ነው፡፡ በተጨማሪ በሱ ላይ ተመርኩዞ የሚካሄድ ተግባር የሚኖር ከሆነ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ይሆናል፡፡

በዚህ መነፅር የተነሳው የመጀመሪያው ጥያቄ ስናይ ለቫይረሱ ጥቃት ይጋለጣል በሚል የቀረቡት አሃዞች በየትኛው የምክንያታዊነት መንገድ ተሄዶ የተደረሰ ድምዳሜ ወይም ጥናታዊ ግምት መሆኑን ለመረዳት እጅግ ያስቸግራል፡፡ የቫይረሱ የመስፋፋት ባህሪ፣ የሕብረተሰባችን አኗኗር ዘይቤና እንዲሁም ግንዛቤ እና አስቀድሞ ቫይረሱ በተሰራጨባቸው ሀገራት ይሁም በአለም ደረጃ ከታየው የተጠቂ ሰው ብዛት ጋር አነፃፅሮ ያንን የተጋነነ አሃዝ ማሰቀመጥ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በዚህ ላይ አሃዙ የተምታታ ነገር አለበት፡፡ ይህም ከከተማ ነዋሪዎች አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ውስጥ 21 በመቶ በቫይረሱ የመጠቃት አደጋ እንዳለው ገልፆ፣ ይህ በቁጥር ሲገመት 23 ሚልዮን እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ከተማ የሚኖረው ህዝብ 21 በመቶው 23 ሚልዮን የሚሆነ ከሆነ እጅጉን የሚበልጠዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖረው  በገጠር ሳይሆን በከተማ እንደሆነ ያስመስላል፡፡

ሁለተኛው ጥያቄ “የጥናታዊ” ግምቱ አለማ ምንድነዉ? የሚል ነው፡፡ ከላይ በአጭሩ እንደተገለፀው በምክንያታዊነት ተመስርቶ የሚደረግ ግምት ቀጥሎ ለሚከሰት አሉታዊ ይሁን በጐ ሁኔታ በቅድሚያ ለእውነታው የሚቀራረብ ግምት በማስቀመጥ ከዚህ አንፃር መደረግ ያለበት በቂ  ቅድመ ዝግጅት ለማደረግና በድንገተኛነት ከሚሰራ የተዘረከረከ የእሳት ማጥፋት አይነት እንቅስቃሴ ከሚያደርሰው ጉዳት ራስን ሆነ ሌላውን አካል ለመታደግ ነው፡፡

በስሜት ወይም በግብታዊነት የሚደረግ ግምት ከሆነ ግን የተጠቀሰው አይነት ጥቅም የሚሰጥ አይሆንም፡፡ እንዲያውም ጉዳት ነው የሚኖረው፡፡ በዘፈቀደ የሚደረግ ግምት ወደ እውነታው ተቀራራቢ የማይሆነው በሁለት መልክ ነው፡፡ ግምቱ በጣም በማጋነን ወይም በጣም በማሳነስ ሊገለፅ ይችላል፡፡ በሁለቱም መልክ  ጉዳቱ ያው ነው፡፡ ይህንን ከውግያ ጋር በተያያዘ አብነት ወስዶ ማየት ይቻላል፡፡

አንድ ተዋጊ ሀይል በአንድ ቦታ ላይ የተቀመጠ የጠላት ሀይል ለማጥቃት ፈለገ እንበል፡፡ ማጥቃቱን ለመፈፀም የጠላት የውጊያ አቅም (ትጥቅ፣ የሰው ብዛት፣ የውጊያ ልምድና ብቃት፣ የመዋጋት ሞራል፣ የያዘው ቦታ ሁኔታና አሰፋፈሩ….) ዝርዝር ጥናት ማድረግ ይገባዋል፡፡ ይህንኑ ሰለ ጠላት የተሰበሰበው መረጃ በመተነተን ከራስ ወገን የውግያ አቅም ጋር በማስተያያት በጣም ሳያጋንን ወይም ሳያሳንስ ትክክለኛ ድምዳሜ በማስቀመጥ ውሳኔ ላይ መድረስ ይኖርበታል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የጣላት ሀይል ከተጨባጭ አቅሙ በላይ ካጋነነው ግን አቅሜ አይፈቅድም በሚል አጥቅቶ ሊያገኝ ይችል የነበረው ድል ያመልጠዋል፡፡ ወይም ደግሞ ከሚያስፈልግ በላይ የወገን ሀይል በማጥቃቱ በማሰለፍ ለአለአስፈላጊ ኪሳራና የሀይል ብክነት ራሱን በማጋለጥ ለጉዳት ይዳረጋል፡፡ በአንፃሩ የጠላት  ሀይል አሳንሶ መዝኖ ከሆነም በጠላት ተበልጦ ለሽንፈት ይዳረጋል፡፡ ስለሆነም ወደ እውነታው ተቀራራቢነት የሌለው ግምት በሁለቱም መልክ በማጋነን ይሁን በማሳነስ ጉዳት እንጂ ጥቅም አይኖረውም፡፡

በተለያየ ወቅት የቀረበው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሊጠቃ የሚችል “ጥናታዊ” ግምት በእኔ እይታ በጣም የተጋነነ እና ወደ እውነታው ተቀራራቢነት  የሌለው ነው፡፡ አገሪቱ፣ መንግስት እና የሚመለከታችሁ የመንግስት  ተቋማት በጥናታዊ ግምቶቹ የተጠቀሰው አሃዝ ይቅርና የአሃዙ አንድ ሃየኛ የሚሆን ታማሚ ለማከም ይሁን ለመንከባከብ የሚያስችል አቅም የለንም፡፡ ሰለዚህ  ድንጋጤ ፈጥሮ ወደ ተስፋ መቁረጥ የሚገፋ ነው፡፡ ገማቾቹ ባለሙያዎችም  ቢሆኑ የአቅማችን ሁኔታ ጠፍቷቸው አይሆንም፡፡ ከማንም በርቀት ሆኖ ከሚታዘብ ሰው በላይ ዝርዝር ዕውቀት ይኖራቸዋል፡፡ ጥያቄ የሚያስነሳው ለምን እንደዚያ እንደሆነ ነው፡፡ ምናልባት የተገመተውን አሃዝ ያህል ያልገጠመው፣ ልዩና ከፍተኛ ጥረት ስለተደረገ ነው በሚል ቆይቶ ለሚከተል ፕሮፖጋንዳ ታሳቢ ተደርጎ ከሆነም የጤንነት አይሆንም፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ የቀረቡ “ጥናታዊ” ግምቶች ምርጫ ቦርድ ምርጫ ለማካሄድ አልችልም የሚል ውሳኔ ላይ ለመድረስ ምን ጫና አሳድረው ይሆን? መነሳት የሚችል አገባብነት ያለው ጥያቄ ነው፡፡

*ስለ ፀሃፊው፡-

በኢፌዴሪ የሃገር መከላከያ ሰራዊት በከፍተኛ የአመራር ቦታ የነበሩና አሁን በጥሮታ ላይ ያሉ ናቸው፡፡

Full Website