መዲናችንን ለመጀመርያ ጊዜም ሆነ ተመላልሶ ለሚጎበኛት ኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ አገር ዜጋ ገና ከአይሮፕላን ማረፊያው ጀምሮ ቀልባቸውን የሚስበው እንደ ጎርፍ የሚፈሰው የሰው ብዛትና በአውራ ጎዳናዎቹ ግራና ቀኝ የተከለኮሉ ሕጻናት ብዛት ነው። የሰዎች ቁጥር መብዛት ያገሪቷ አጠቃላይ ገጽታ ሲሆን የሕጻናቱ በአውራ ጎዳና ላይ በዝቶ መታየት ግን የከተሞች ብቻ ዓይነተኛ ጠባይ ይመስለኛል። የመዲናችንን የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናትን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፣ አንደኛው ቡድን በአደንዛዝዥ ዕጽ ሱስ ተጠምደው መሄድ እንኳ አቅቷቸው የሚንገላወዱ ወይም ግድግዳን ተደግፈው አንዳቸው አንዳቸው ላይ ተደግፈው እንቅልፍ አይሉት ሰመመን ውስጥ  ያሉ የሚመስሉ ግማሽ በድኖች ሲሆኑ ሌላው ቡድን ደግሞ በሱሱ ያልተለከፉና መንቀሳቀስ የሚችሉ ትራፊክ መብራት ላይ እንደ አንበጣ አሸከርካሪዎችን በግራና በቀኝ የሚያዋክቡ ሕጻን ለማኞች ናቸው። ባጠገባቸው አንዳችም ዓዋቂ ሳይኖር እነዚህ ዕድሜያቸው ከአምስት እስከ አሥራ ሁለት ዓመት የዕድሜ ገደብ ውስጥ ያሉ ሕጻናት እንዴት አድርገው ራሳቸውን ችለው የቀን ተቀን ሕይወታቸውን በልመና ብቻ አድርገው እንደ ዓዋቂ እንደሚኖሩ ለመገመት ይከብዳል። ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ፣ በአደንዛዥ ዕጽ ሱስ የተለከፉትም ሆኑ “ጤነኞቹ” እንስት ሕጻናት እነሱም ደርሰው እዚያው ሜዳ ላይ ልጅ ወልደው አቅፈው እናት መሆናቸው ነው። ሕጻናት እናቶች!

መቼም ሰው እያረጀ ሲሄድ “ያኔ በኛ ጊዜ” “ድሮ ተማሪ በነበርንበት ዘመን” እያለ የድሮውን “ወርቃማ ዘመን” ከዛሬው ጋር አነጻጽሮ የዛሬውን ዘመን መኮነን የተለመደ ነውና እኔም አርቲስቶቻችን እንደሚሉት በትዝታ ጅረት ወደ ኋላ ፈስሼ፣ ያኔ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ዘመን በመዲናችን እንኳን ሕጻናት ይቅርና እጅግ በጣም ጥቂት ከሆኑ የአካል ጉዳተኞች በስተቀር፣ ዓዋቂ ለማኝ ማየቱ ራሱ እምብዛም ያልተለመደ እንዳልነበር ትዝ ይለኛል። ዘመኑ የጥጋብና የተድላ ዘመን ነበር ለማለት ሳይሆን፣ ያኔ ማህበረሰቡ አቅመ ደካማ አባላቱን የመንከባከብ ግዴታ ስለነበረበት ራሳቸውን የማይችሉ ግለሰቦች እዚያው እሚኖሩበት ማህበረሰብ ውስጥ ሆነው ይረዳሉ እንጂ ሰፈራቸውን ትተው ለልመና ወደ ከተማ አይሄዱም ነበር። “በዚያን ዘመን” በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ ልመናም እጅግ በጣም አሳፋሪ ድርጊት ሲሆን ሕጻናት ደግሞ ለትምሕርት ተብሎ ሰፈራቸውን ለቅቀው ወደ ከተማ ይሄዱ እንደው እንጂ ለብቻቸው ሆን ተብሎ ለልመና ወደ ከተሞች የመፍለሱ ጉዳይ ከቶውንም አይታሰብም ነበር። ያ “ወርቃማው ዘመን” ትዝ እያለኝ ነው እንግዲህ እነዚህን ለትምሕርት ሳይሆን ለልመና ወይም “ሥራ ፍለጋ” በሚል ሰበብ በዚህ ጨቅላ ዕድሜያቸው ወላጆቻቸውን ባላገር ጥለው ወደ ከተማ መጥተው ለአደንዛዥ ዕጽ ሱስና ለልመና የተዳረጉትን ዜጎቻችንን አይቼ እንዴት ከዚህ ደረስን ብዬ ራሴን ሁሌም የምጠይቀው።

በመጀመርያ ደረጃ፣ ወላጅ ገና ፍቅራቸውን በደንብ ያልጠገቡ ልጆቹን እንዴት ብቻቸውን ለዚያውም ወደማይታወቅበት አገር ጨክኖ ሊልካቸው ቻለ? በርግጥስ ወላጆች ሆን ብለው ፈልገው ነው ልጆቻቸውን ወደ ከተማ የሚልኳቸው ወይስ  ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆነ ክስተት አስገድዷቸው ነው? ለዘመናት የነበረው የማህበረሰቡ የመረዳዳት ባህልስ እንዴት ተሸርሽሮ ቢጠፋ ነው ታዳጊው ትውልድ ቄዬውን ለቅቆ ሲጠፋ ማህበረስቡ ዝም ብለው የሚመለከታቸው? መንግሥትስ ይህንን ኃላፊነት የጎደለውን የወላጆችን ድርጊት ለምን ዝም ብሎ ይመለከታል? መልስ ያላገኘሁለት የዘወትር ጥያቄዬ ነው።

ይህ ማህበረሰባዊ ችግር ዛሬ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባገራችን ዕውን ከሆነ በኋላ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ መልስ የሚያስፈልገው ጉዳይ ሆኖ ይታየኛል። ቫይረሱ የሚተላላፈው በንክኪ መሆኑና ይህንንም ለመግታት ለጊዜው ፍቱን ነው ተብሎ የተነገረለት ማስወገጃ ዘዴ፣ ማለትም እጅን በሳሙናና በሙቅ ውሃ ከመታጠብ በተጨማሪ ደግሞ ስዎች እንዳይቀራረቡ ወይም እንዳይገናኙ መሆኑ ስለታመነበት እነዚህን ውሎአቸውና አዳራቸው ጎዳና ላይ በጅምላ በመሆኑ ለቫይረሱ አደጋ እጅግ የተጋለጡትን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናትን ጤንነት ለመንከባከብ ሲባል መንግሥት መንግሥት በአስቸኳይ እርምጃ መውሰድ አለበት ባይ ነኝ። የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናትን ወደ ቀድሞ ማህበረሰባቸው መልሶ ከወላጆቻቸው ጋር የማገናኘት ተግባር በኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግም ሆነ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፋዊ ውሎች ባስቀመጧቸው “የሕጻናት ተመራጩ ጥቅም” (Best interest of the child) መስፈርቶችና ግዴታዎች መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት መፈጸም ያለበት ግዴታው ስለሆነ አፈጻጸሙ ላይ እክል ሊኖር አይችልም። ፕሮግራሙም በትክክል ከተተገበረ፣ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍን የመግደል ያሕል ይሆናል። ልጆቹ ከቫይረስ ወረርሽኝ የማምለጥ ዕድል ይኖራቸዋል፣ ተፈጥሮያዊውን የወላጅ እንክብካቤንም መልሰው ያገኛሉ። መንግሥት መውሰድ ካለበት እርምጃዎች ዋና ዋናዎቹ የምላቸው፣

ሀ) የልጆቹ ወላጆች ወይም የቅርብ ዘመዶች ያሉበትን ቦታ እንዳረጋገጠ ልጆቹን አንድ ባንድ መርምሮ ከቫይረሱ ነጻ የሆኑትን በቀበሌ አስተዳደር በኩል ወደየመጡበት ያገራችን ክፍል መመለስ እና በቫይረሱ የተጠቁ ካሉም ደግሞ እንደ ማንኛውም ዜጋ አስፈላጊው እንክብካቤ ተደርጎላቸው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው እንደ ተረጋገጠ ወደ ወላጆቻቸው መመለስ፣ ከተመለሱ በኋላም መንግሥት ባወጣው መመርያ መሠረት ቢያንስ ቢያንስ ለሁለት ሳምንት ተገልለው የሚኖሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣

ለ) ባልና ሚስት ልጆችን መውለድ ብቻ ሳይሆን የወለዷቸውን ልጆች የመንከባከብ በተፈጥሮም በምድራዊ ሕግም ግዴታ እንዳለባቸው የሚያስረዳ ግልጽ መመርያ አውጥቶ ሕዝብን ማስተማርና ይህንንም የመንግሥት መመርያ በተግባር እንዲያውል የሕጻናትና የሴቶች ጉዳይ መ/ቤት ከቀበሌ አስተዳደር ጋር በመሆን እንዲያስፈጽም ሥልጣኑን መስጠት፣

ሐ) በቀበሌ አስተዳደሩ በኩል ሕጻናት (ዕድሜያቸው ከአሥራ ስምስንት ዓመት በታች የሆኑትን ማለት ነው) ያለ ወላጅ ፈቃድ ወይም ማሕበረሰባዊ ወይም ሕጋዊ ኃላፊነት ካለው ግለሰብ ጋር ካልሆነ በስተቀር ለብቻቸው ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወሩና፣ ሕጻናትን ከወላጅ ወይም ከሕጋዊ ተወካይ ጋር ሳይሆን ለብቻቸው የሚያጓጉዟቸውን ግለሰቦችና ቡድኖችን “በሰዎች የሕገ ወጥ ዝውውር ወንጀል” ከስሶ ለፍርድ ማቅረብ መቻል አለበት። (በደፈናው ሲታይ እንደዚህ ዓይነት መንግሥታዊ እርምጃ የሕጻናትን “በነጻነት የመዘዋወር” ሰብዓዊ መብት የጣሰ ሊመስል ይችላል። ግን አይደለም። እዚህ ላይ የሚያመዝነው የልጆቹ “በነጻ የመዘዋወር መብት” ሳይሆን የወላጆች ወይም የመንግሥት “ሕጻናትን የመንከባከብ ግዴታ” ነው)። በብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ውሎችም እዚህ ላይ ልዩ ትኩረት የተሠጠው ልጆችን ሕገ ወጥ ከሆነው የሰው ልጅን ማዘዋወር (human trafficking) አደጋ ለማዳንና ብሎም ልጆቹን ለሌሎች ተጉዳኝ አደጋዎች እንዳይጋለጡ ለማድረግ ታስቦ ስለሆነ መንግሥት ይህንን እንቅስቃሴ የመግታት ግዴታ አለበት።

ለሕጻናት ከወላጅ የተሻለ እንክብካቤና ፍቅርን የሚሠጥ ምድራዊ አካል የለም። የፈለገውን ያህል ደሃ ቢሆን አንድ ቤተሰብ በድህነቱ ለልጆቹ የሚሠጠውን ፍቅር አንዳችም ምድራዊ ሃብትና ሥልጣን ሊተካው አይችልም። መንግሥትም፣ ለምሳሌ ከጥቂት ወራት በፊት እንዳየነው የመዲናችን አስተዳደር የተወሰኑ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ሰብስቦ ወደ ሆነ መጠለያ ቦታ ሲወሰዳቸው ተመልክተናል። ድርጊቱ ለልጆቹ በጎ ከማሰብ የመነጨ በመሆኑ የሚደገፍ ቢሆንም  የተወሰደው እርምጃ ግን ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ስለማያስገኝ መንግሥት በቂ ትኩረት ማሳየት ያለበት ሕጻናቱን ወደ ወላጆቻቸው መመለስ ላይ መሆን አለበት። በተሻሻለው የ 1992 ዓ/ም ኢትዮጵያም የቤተሰብ ሕግም ሆነ በ1989 ዓ/ም በተደነገገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መብት ኮንቬንሺን (Convention on the Rights of the Child) ውስጥ ሕጻናትን የመንከባከብና ልዩ ጥቅም የመጠበቅ ግዴታ በመጀመርያ ደረጃ የተጣለው በወላጆች ላይ የሆነው ያለ ምክንያት አይደለምና።
Full Website