የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም እያስከተለ ያለው ጭንቀት ሁላችንንም እያሳሰበን ነው። ለሁለት ወር ኢትዮጵያ እቆያለሁ ብዬ ቲኬት ቆርጬ ገና አዲስ አበባ በደረስኩ በሁለተኛው ሳምንት ወረርሽኙ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ በሰፊው ስለተወራ የአውሮፓ ሃገራት የየብስና የአየር ድንበሮቻቸውን ከመዝጋታቸው በፊት እና የዶ/ር ዓቢይም ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ባላፈው ሳምንት ወደ ሁለተኛው አገሬ አውሮፓ ተመለስኩ። በዚህ ቀውጢ ሰዓት ኢትዮጵያ ቆይቼ ከሕዝባችን ጋር ችግሩን ለመጋፈጥ አለመፈለጌ የሚያስተዛዝብ ቢሆንም ያ እንዳይሰማኝ ኅሊናዬን ቀስ በቀስ እያደነዘዝኩ እገኛለሁ።

የአገራችን ሁኔታ፣

አገራችንን በተመለከተ ወረርሽኙ እጅግ በጣም አሳሳቢ እየሆነ ነው። የቫይረሱ ብቸኛ የማጥቃት ዘዴ በንክኪ መሆኑ፣ እንደ ሕዝባችን አጠቃላይ ኑሮው ሲያርስም መከር ሲሰብስብም እናም ሲበላም በጋራ ስለሆነ ለዚህ ቫይረስ መሠራጨት  አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር ግልጽ ነው። ለዘላለም አብሮን የኖረውን ይህንን የአብሮነት እና የጋርዮሽ፣ የመተቃቀፍና የመጎራረስ ባሕል ደግሞ በቀላሉ ማስወገድ አይቻልም። በመዲናችንም እንደ መገናኛና ሜክሲኮ፣ ገርጂና ጃሞ፣ መርካቶና ፒያሳ አካባቢ የሚታየውን የሰው ጎርፍ በዓይነ ኅሊናዬ ስመለከተው ቫይረሱ አንዴ አገራችን ከገባ ተመልሶ የሚወጣ አይመስለኝም። እጅግ በጣም ብዙው የመዲናችን ኗሪዎች ደግሞ የቀን ተቀን ኑሮአቸውን የሚገፉት በቀን ሥራ ስለሆነ፣ የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት የግድ ጧት ተነስተው በየመንገዱ ተኮልኩለው አሠሪ ፍለጋ ቀኑን ሙሉ በየመንገዱ ዳር ተሰጋስገው ይቀመጣሉ፣ በየቤታቸውም የቤት ኪራይን የመሰለ ሸክም ለመጋራት ሲባል ኑሮአቸው እንደዚሁ የተፋፈነ ነው። እነዚህን የቀን እንጀራቸው በመንገድ ላይ ብቻ የሆነባቸውን ዜጎች “ለሁለት ሳምንት ብቻ ወደ መንገድ አትውጡ” ቢባል እንኳ እቤት ተፋፍናችሁ በረሃብ ሙቱ ከማለት የተለየ ትርጉም የለውም። ለሁለት ሳምንት የሚበቃ አስቤዛ ሸምተው ማከማቸት አይችሉምና! መንግሥት ደግሞ እነዚህን በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ዜጎች በየቤታቸው እየዞረ ምግብ ሊያድልላቸው ልምዱም አቅሙም ያለው አይመስልም። እነዚህ ሥራ አጥና የቀን ሠራተኞች በየከተማው ተፋፍነን ከምኖር ወደ መጣንበት ባላገር ተመልሰን ዘመዶቻችን ግቢ ውስጥ ሰቀላ ሠርተን ዶቅማና አጋም በልተን እንኑር ብለው ወደ ባላገር መፍለስ ከጀመሩ ደግሞ ቫይረሱን በነጻ ከከተማ ወደ ባላገር ወስደው አሠራጩ ማለት ይሆናል። እጅግ በጣም ግራ የሚገባና አሳሳቢ ነገር! አገራችን በጤናው ዘርፍ ያላት ስኬት እምብዛም ነው። በመጀመርያ ደረጃ፣ የጤና ተቋማት ያላቸው ተደራሽነት እጅግ በጣም ውስን ነው። ከዚያም በላይ ደግሞ የጤና ባለሙያዎቻችን ቁጥር እጅግ በጣም ትንሽ ነው። ባለው መረጃ መሠረት ዛሬ ባገራችን ያለን የሓኪሞች ቁጥር ለያንዳንዱ ዜጋ ቢከፋፈል አንድ ሓኪም ለአሥር ሺህ (10,0000) ሰው አገልግሎት ሲሰጥ፣ ዛሬ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቋቋም የሕክምና ባለሙያዎች አጠሩን ብለው የሚጮሁት ያደጉት አገራት ግን ያላቸው የሕክምና ባለሙያ ቁጥር ለዜጋው ሲከፋፈል አንድ ሓኪም በአማካይ ለሁለት መቶ አምሳ (250) ሰው አገለግሎት ይሰጣል። የሕክምና ዕቃዎችንና መድኃኒቶችንም በተመለከተ አገራችን እዚህ ግባ የሚባል ምርት ስለሌላት ብዙውን ዕቃ የምናስገባው ከውጭ አገር ነው። ለዚያ ደግሞ የውጪ ምንዛሪ ብቸኛ መገበያያ ስለሆነ ለጊዜው ሌሎችን ሴክተሮች አስርበን በሕክምና መሣርያና መድኃኒት መግዣ ላይ ብቻ እናተኩር ቢባል እንኳ መንግሥት በቂ የውጪ ምንዛሪ እንደሌለው ደጋግሞ አሳስቦናል። ቫይረሱ ቅዝቃዜ ይመቸዋል ብለው ባለሙያዎች ነግረውናል። በአገራችን ቫይረሱ እንደ ሌሎች አገራት እስካሁን ባሰፊው ያለተሠራጨው ምናልባትም ጊዜው አሁን በጋ በመሆኑና ቫይረሱን ስለሚያቀልጠው ነው ይላሉ የጤና ባላሙያዎች። ዕውነታው ይህ ከሆነ፣ ካንድ ሁለት ወር በኋላ ባገራችን የአየሩ ሙቀት እየቀነሰ ሄዶ ግንቦት አካባቢ ስንደርስ ከላይ ያስቀመጥኳቸው ደካማ ጎኖቻችን እንዳሉ ሆነው ቫይረሱን ቁጥጥር ሥር ሳናደርግ ክረምት ከመጣ የተተነበየው የፈጣሪ መዓት ወረደብን ማለት ነው። ባለሙያዎች የሚነግሩን እጅን በሳሙና መታጠብ፣ መተቃቀፍን መሳሳምንና መጎራረስን፣ ከቦታ ቦታ መዘዋወርን፣ ከማንኛውም ዓይነት መነካካት ተቆጥበንና ለሁለት ሶስት ሳምንታት ከቤት እንዳንወጣና እና ከሌሎች ጋር እንዳንገናኝ ካልተደረገ፣ ቫይረሱ ይዞልን የመጣው መዓት ማንኛችንም ከምናሳበው በላይ የገዘፈ ሊሆን ይችላል። ትናንት፣ እንኳን ሰው ሰራሹን ከኒውክሌር ጦርነት በኋለ የሚደርሰውን ዕልቂት ይቅርና ተፈጥሮን ራሱን ቁጥጥር ሥር የማዋል ዓቅም አለን ብለው ሲፎክሩ የነበሩ ኃያላን መንግሥታት ዛሬ ይህንን በንኪኪ ብቻ የሚተላለፈውን ቫይረስ መቆጣጠር አቅቶአችው ቀኑን ሙሉ ዋይ ዋይ ሲሉ ማየቱ ዋነኛ ዋቢ ነው።

2 | P a g e

አብዛኞቹ ያደጉ አገራት አንድም በባሕላቸው የመቀራረብ፣ የመሳሳም ወይም የመነካካት ልምድ ስለሌላቸው “ድንገት መንገድ ላይ ከሆናችሁ አጠገባችሁ ካለው ሰው ሁለት ሜትር ያህል ርቃችሁ ቁሙ” ብሎ መንግሥት መመርያ ሲያወጣ ዜጎች መመርያውን ያላንዳች ችግር በተግባር ያውሉታል። ከዚያም በላይ ደግሞ የድሕነት መደቡ እንዳገራችን ያልወረደ ስላልሆነ፣ ማንኛውም ዜጋ ቢያንስ ቢያንስ ለአንድ ወር የሚበቃውን አስቤዛ ገዝቶ በሩን ዘግቶ መኖር ይችላል። ለዚህን ያህል ጊዜ የሚበቃ ምግብና የቤት ቁሳቁስ መግዛት ለማይችል ዜጋ ደግሞ መንግሥት አስፈላጊውን ዕርዳታ ያደርጋል። ለጊዜው ያለውን የሕክምና ዕቃ ችግር ለመቅረፍ ደግሞ ለሌላ ዓላማ የተቋቋሙትን ፋብሪካዎች ምርታቸውን ለዚሁ ተግባር እያዋሉ ስለሆነ ችግሩን በቅርቡ ይወጡታል የሚል ግምት አለ። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ በአውሮፓና አሜሪካ የክረምቱ ጊዜ እያለፈና ሙቀታሙ የበጋ ወራት እየመጣላቸው ስለሆነ፣ ተፈጥሮ ራሱ ቫይረሱን ያጠፋዋል የሚል ተስፋ ከሁላቸውም ፊት ላይ ይነበባል። ያገራችን ሁኔታ ግን ከላይም ባጭሩ እንደ ጠቀስኩት ከዚህ ለየት ያለ ነው። ተስፋን ከሚሠጡን ይልቅ ተስፋ የሚያስቆርጡን ብዙ ነገሮች አሉ። በተለይም የቫይረሱን መስፋፋት በዚህ በጋ ማቆም ካልቻልንና በዚሁ ትግል ላይ እያለን ክረምቱ ከመጣ ሳንወድ በግድ የቫይረሱን አስከፊ ገጽታ ለማየት እንገደዳለን ማለት ነው።

ታዲያ መፍትሄው ምንድነው? እንደ ዜጋስ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?

የሕክምና ባለሙያዎች ከመንግሥት ጋር ሆነው ሙያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ስለሆነ በዚያ መስክ ለመምከር መሞከር አስፈላጊ አይመስለኝም። መንግሥት ደግሞ የዜጎችን ጤንነት የመጠበቅ ግዴታ ስላለበት ከአገር በቀልና የውጭ አገር ጠቢባን ጋር በመሆን ቫይረሱ እንዳይስፋፋ ጥረት እያደረገ እንደሆነ በየሚዲያው እየተነገረ ነው። መንግሥታዊ የሲቪል እና ወታደራዊ ተቋማትም በቁጥጥሩ ሥር ስላሉ እቅዱን በተግባር ላይ ለማዋል የሚቸግረው አይመስለኝም። እንደምገምተው ከሆነ የመንግሥት ትልቁ ችግር፣ በተለይም በትላልቅ ከተሞች፣ ዜጎችን ለሁለት ሶሶት ሳምንት ከቤት እንዳትወጡ ብሎ ማወጅና ዓዋጁን በተግባር መተርጎም ነው። ሰዎችን በፖሊስ ኃይልም ቢሆን አስገድዶ ቤት ውስጥ ማፈን ይችላል። የዕለት ጉርሳቸውን የሚያገኙት በየቀኑ ወደ ጎዳና በመውጣት ብቻ ለሆኑ ዜጎች ግን፣ በተፋፈኑበት ጠባብ ቤቶች ያለ ምግብ ኑሩ ማለት ደግሞ ሌላ ራሱን የቻለ የሞት ዓዋጅ ማወጅ ስለሆነ መንግሥትን የሚቸግረው ይመስለኛል። ከቤት እንዳትወጡ ተብሎ መመርያ ቢወጣ የተወሰነው ሕዝባችን ክፍል አስፈላጊውን አስቤዛ ሸምቶ መመሸግ ይችላል። ችግሩ ያለው ከላይ እንዳልኩት ለዕለት ጉርሳቸው የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ለማግኘት የግድ በየቀኑ ወደ ጎዳና መውጣት ያለባቸው ጋ ነው። በኔ ግምት መንግሥት የዜጎችን ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስን ብሎም ንክኪን ለማስቆም መውሰድ ያለበት ብቸኛ እርምጃ እነዚህ ለዛሬ እንጂ ለነገ ኖረው የማያውቁትን ዜጎቻችንን ለሁለት ሶስት ሳምንታት የሚበቃቸውን ምግብ ማዘጋጀትና ምግቡ የሚዳረስበትን ተቋማት ማዋቀር ብቻ ነው። ተቋማቱን በተመለከተ ባገራችን በከተማውና በገጠሩ የቀበሌ ማሕበራት መዋቅሮችንና ሌሎችም ተመሳሳይ ባህርይ ያላቸውን ለምሳሌ ዕድርን የመሳሰሉ ተቋማትን አጠናክሮ ማሰለፍ ነው። ዋናው ችግር ለዚህ ሁሉ ሚሊዮን ሰው ለአንድ ወር የሚበቃ ቀለብ ማዘጋጀት ነው። ይህ በርግጥ ትልቅ ካፒታል ይጠይቃል! በኔ ግምት ፍላጎቱ ካለን ይህንንም እንወጣዋለን ባይ ነኝ። በመጀመርያ ደረጃ ዛሬ ባገራችን ሰፍኖ ያለውን የፖሊቲካ ውጥረት አረጋግተን ይህንን የጋራ ጠላት በጋራ ለመዋጋት የፖሊቲካ ድባቡን መቀየር አለብን። ለዚህም ዋናው ኃላፊነት ያለባቸው መንግሥት፣ የፖሊቲካ ድርጅቶችና አክቲቪሲቶች ናቸው። መንግሥት በበኩሉ ከያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል ተወካይ ጋር በመሆን አገራዊ የአደጋ ጊዜ ፖሊሲ መቀየስና ይህንንም ፖሊሲ በተግባር ሊያውሉ የሚችሉ የተለያዩ ግብረ ኃይሎችን ማቋቋም ነው። ሁለተኛው ትልቁ ኃላፊነት ደግሞ ካገር ውስጥና ከውጭ አገር መንግሥታትና ተቋማት የተቻለውን ገንዘብ ማሰባሰብ ነው። እንደሚገባኝ ከሆነ መንግሥት ይህንንም እየሠራ ነው። ሶስተኛው ደግሞ መንግሥት በፖሊሲ ደረጃ ያስቀመጠውን በተግባር ለመተርጎም የሚረዱ በአደጋ ጊዜ ዜጎችን የመርዳት ልምድ ያላቸውን አገር በቀልና ዓለም አቀፋዊ የዕርዳታ ድርጅቶችንና የሲቪክ ማህበረሰቡን አሰባስቦ ዕቅዱን በተግባር እንዲያውሉ ጥሪ ማድረግ ነው። የፖሊቲካ ድርጅቶችም ከመንግሥት እኩል ኃላፊነት አለባቸው። ለፈለገው ዓላማ ይሁን ያላቸውን የግልም ሆነ የሕዝብ የፖሊቲካ አጄንዳ ለጊዜው ወደ ጎን በመተው ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ የሚቻላቸውን አስተዋጽዖ ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለባቸው። ፖሊቲካ ከጤና አይቀድምም። ሰዎች ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጎናጸፍና ብሎም ለመደሰት መጀመርያ በሕይወት መኖር አለባቸው። አዲስ አበባን ታከለ ኡማ ስላስተዳደራት ወይም መተከል ጉሙዝ ክልል ሥር ስለሆነች ቫይረሱ በተለየ መልክ አያስተናግዳቸውም። ስለዚህ የፖሊቲካ ድርጅቶች በሙሉ የፖሊቲካ አጄንዳቸውን ወደ ጎን ትተው መንግሥት እያዋቀረ ባለው የተለያዩ ዘርፎች አባሎቻቸውን መመደብና በየሙያቸውና በችሎታቸው የሚፈለግባቸውን ዜጋዊ ግዴታ እንዲወጡ ማዘጋጀት አለባቸው ባይ ነኝ።

3 | P a g e

የኛስ የዲያስፖራውስ ሚና ምን መሆን አለበት?

ላለፉት ኸያ ዓመታት ዲያስፖራው በፖሊቲካ ቅስቀሳው ዘርፍ በቋሚ ተቃዋሚነት ከመሰለፉ ባሻገር ባገሪቷ የኤኮኖሚ ዕድገት ውስጥም ጉልህ ተሳትፎ እንደነበረው ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው። አዎ! እያንዳንዳችን የተቻለንን ያህል በየወሩ ለዘመዶቻችን ስንልክ የነበረው ዕርዳታ፣ ኑሮአቸውን በእጅጉም ባያሻሽል፣ ከመራብ እንዳዳናቸው ግልጽ ነበር። ብዙዎች ግን ይህንን የተንጠባጠበ እና ያልተማከለ የዕርዳታ መረብን ዕርዳታ ተቀባዮቹን በሞትና በሕይወት መካከል ለማኖር እንጂ ሕይወታቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለመለወጥ እምብዛም አስተዋጽዖ አላደረገም ይላሉ። የኮሮና ቫይረስን መስፋፋት “በተለመደው” የዕርዳታ መስመር ወይም ልምድ መግታት የምንችል አይመስለኝም። ቫይረሱ “ዘመናዊ” ስለሆነ እኛም ቫይረሱን ለመግደል የዕርዳታ ባህላችንን ማዘመን ግድ ይላል። ይህ ከያቅጣጫው ለዘመዶቻችን የምንልከው ገንዘብ ከላይ እንዳልኩት ተረጂውን በሞትና በሕይወት መካከል ያኖር እንደው እንጂ ጤነኛ የማህበረሰቡ አባል እንዲሆኑ አይደርጋቸውም። አንድ ቤተሰብ ከውጭ አገር በሚላክለት ገንዘብ ለጊዜውም ቢሆን ራሱን ችሎ “በቤቱ ታሽጎ ለሁለት ሶሶት ሳምንታት” መኖሩን ይወጣ እንደው እንጂ፣ ጎረቤታቸው የዕለት ጉርሱን ለመሸቀል ወደ ጎዳና የሚወጣ ከሆነ  የነሱ “ራስን ማግለል” ብቻ ከቫይረሱ ነጻ ሊያደርጋቸው አይችልም። በሽታው ጅምላ ጨራሽ ስለሆነ ትግላችንም ሁሉንም የሚያሳትፍ መሆን አለበት ማለቴ ነው። እንኳን እኛ ድሆቹ ይቅርና ያደጉ አገራት እንኳ በሽታውን ለየብቻቸው መቋቋም የማይቻል መሆኑን ስለተረዱ ከሌሎች ጎረቤት አገራት ተባብሮ ቫይረሱን ለመውጋት የጋራ ግንባር ለማቋቋም ሽር ጉድ እያየናቸው ነው። ወገኖቼ፣ ጠቢባን እንደሚነግሩን ከሆን ቫይረሱን ለመግደል ያለን አንድ ምርጫ “ንኪኪን ማቆም” ወይም “ራስን ማግለል” ነው። በቀላል አማርኛ፣ ሕዝባችንን ቢያንስ ቢያንስ ለአንድ ወር ያህል ከቤቱ እንዳይወጣና ከሌሎች እንዳይገናኝ ማድረግ ማለት ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ለምሳሌ በመዲናችን የምንታዘበውን የሰውን ጎርፍ ለዚህን ያህል ጊዜ ራሱን ካገለለ በኋላ መቀለብ መቻል ማለት ነው። ይህን ለመተግበር ደግሞ እጅግ በጣም ብዙ ብዙ ብዙ ብዙ ሚሊዮን ብር ያስፈልገናል። ስለዚህ ወገኖቼ፣ በየግላችን ለዘመዶቻችን የምንልከው ገንዘብ እንዳለ ሆኖ በተጨማሪ በሚመቸን መንገድ የምንችለውን ያህል አዋጥተን አንድ ላይ ብንልክ፣ መንግሥት ባዘጋጀው ብሔራዊ ፖሊሲ መሠረት ጠቀም ላለ ጉዳይ ይውላል ማለት ነው። አዎ ሁላችንም በየፊናችን የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት በያገሩ እየተንቀሳቀስን ነው። እጅግ በጣም የሚያበረታታ እንቅስቃሴ! ሆኖም ግን አካባቢዬ ካለው እንቅስቃሴ እንደማስተውለው ከሆነ የሚያዋጡቱ ግለሰቦች አብዛኞቹ ያው ከዚህ በፊትም ሲያዋጡ የነበሩ ናቸው። አሁን ከፊታችን የተጋረጠውን የኮሮና ቫይረስ አደጋ ግን ከተለመደው የችግሮቻችን ካታሎግ ሁሉ ለየት ያለና እጅግ በጣም አደገኛ በመሆኑ የተሳታፊዎቹ ቁጥር ከተለመደው (the usual contributors) እጅግ በጣም ሰፋ ማለት አለበት። ስለዚህ በመላው ዓለም የምንገኝ ከሚሊዮን በላይ የምንሆን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለአንድ ወር ማለትም ለተከታታይ ሰላሳ ቀናት ብቻ ዓይናችንን ጨፍነን የመጣው ይምጣ ብለን በየቀኑ አንድ አንድ ዶላር ብቻ ብናዋጣ በየቀኑ አንድ ሚሊዮን ዶላር በወሩ መጨረሻ ደግሞ ሰላሳ ሚሊዮን ዶላር ልናዋጣ እንችላለን ማለት ነው። ፍላጎቱ ካለ ሰላሳ ዶላር በወር መክፈል የማይችል ሰው ደግሞ ያለ አይመስለኝም። ወገኖቻችን ለቫይረሱ ጥቃት ሰለባ ሆነው ዳግም ላናገኛቸው ሳይሰናበቱን በቁማቸው እያሉ ብንረዳቸው ጥቅሙ የሁለትዮሽ ነው። እነሱ ከአደጋ ይተርፋሉ፣ እኛም ከኅሊና ፀጸት እንድናለን።
Full Website