አምባሳደር ወንድሙ የተጠቀመበት አገላለፅ ትግራይ ውስጥ ያለውን ስሜት በግልፅ የሚያንፀባርቅ ነው። ህወሓት ሙስናና የአስተዳደር በደል ፈፅማለች በሚል የሰራችውን ሰማንያ ከመቶ በጎ ተግባር ወደጎን በማሽቀንጠር ከያቅጣጫው የሚወረወርባት የነገር ዱላ አብሮ እየተመታ ያለው የትግራይ ህዝብ ነው። የህወሓትን አመራር ነጥሎ መምታት አይቻልም። ይህንን ሃቅ ወርዋሪዎቹ አሳምረው ያውቁታል። ይፋ የማይደረገው ውስጣዊ ኢላማቸው ህወሓትን የወለደውና ያቀፈው ህዝብ መሆኑ ለህዝቡ የተሰወረ አይደለም። ስድስት ፐርሰንት እየገዛን ነው ሲባል የኖረው ትግሬ ገዛን ለማለት እንጂ ህወሃት ገዛችን ለማለት አይደለም። ስድስት ፐርሰንት የህዝቡ የስነህዝብ ድርሻ እንጂ የህወሃት አይደለም። ህወሓት ስትታይ የኖረችው እንደ ህዝብ ተወካይ እንጂ እንደ ማንኛውም ፓርቲ አልነበረም። ከስልጣን ከተገለለች ወዲህ ግን ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ አይደሉም እየተባለ ነው። ህወሓትን ከስልጣን ለማግለል የስድስት ፐርሰንት ህዝብ ወኪል ናት ተባለ፣ ከተገለለች በኋላ ደግሞ ነጥሎ ለመምታትና የትግራይ ህዝብ በቂ መከታ የሌለው አድርጎ እንደድሮ በወኪል ለመግዛት ህወሓት የህዝቡ ተወካይ አይደለችም ተባለች። የኢትዮጵያ ፓለቲካ ራሱን የሚቃረን ሲሆንም " ልክ ነው " ይባላል። ከትግራይ ሲመጣ ልኩ ስህተት፣ ከመሃል ሲመጣ ስህተቱ ልክ ይሆናል። ሃቅ አንፃራዊ ቢሆንም በትግራይና በመሃል ባለው ግንኙነት ግን ቅጥ ያጣ ይመስላል።

Full Website