ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓም (06-05-2020)

የአገር ህልውና አደጋ ውስጥ ሊገባ ስጋት በሰፈነበት ወቅት ማንኛውም ለአገርና ለሕዝብ የሚያስብ ዜጋ ችግሩን ለማሶገድ በሚያስችለው መንገድ ላይ መረባረብ ይኖርበታል።ከዳር ቆሞ ታዛቢ ሊሆን አይችልም።እኔም እንደዚሁ ያገራችን የኢትዮጵያ ጉዳይ ስለሚያሳስበኝና ለብዙ ዓመታትም የምችለውን ለማበርከት የተሰለፍኩበት ዓላማ ስለሆነ በዚህ ወሳኝ ወቅት ጊዜ የበኩሌን አስተያዬት ላቀርብ እወዳለሁ።ብዙ ጊዜ አለመታደል ሆኖ የብዙ ቀና አሳቢ ድምጾች በቡድንና በጉልበተኞች አሻጥር እዬተዋጠ ሰሚ ያጣ ጩኸት ሆኖ መቅረቱ የተለመደ ነው።ግን ያ ይሆናል ብዬ አሁንም ድምጼን ከማሰማት አልቆጠብም።ሌላው ቢቀር በዝምታ ሊያድርብኝ ከሚችለው ጸጸት እድናለሁ።ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ያደረኩት የፖለቲካ ተሳትፎም ለዝምታ አይዳርገኝም።ብዙ ውጣውረዶችንና ብዙ የትግል ጉዋደኞቼን ያጣሁበት ስለሆነ ለተነሳሁበት ዓላማ እስከ መጨረሻው ድረስ ለመቆም ወድጄ ቃል የገባሁበት እምነቴ ነው።ለሕዝቡዋ የምትመች፣የተሻለች፣ከአምባገነኖችና ከጎሰኞች የጸዳች  ኢትዮጵያ እንድትኖር ካለኝ ጽኑ ፍላጎት የሚያስፈልገውን ሁሉ ከማበርከት አልቆጠብም። አገራችን ለብዙ  ዓመታት ተቸንክራ ለኖረችበት የተዛባ ፖለቲካ ታሪክ መሰረቱ  ሕዝቡ በፍላጎቱ መርጦ በሰዬመው መንግሥት አለመመራቱ ነው።በተለይም ላለፉት 30 ዓመታት ለተጋረጠባት መጠነ ብዙና ሰፊ ፈተና ብሎም  የጥፋት ጉዞ ምክንያቱ ጎሳ ተኮር የሆነ “ፍልስፍና”/ህሳቤ የሚቀይሰው የፖለቲካ መስመርና እምነት  በመስፈኑ እንደሆነ ማንም አይክደውም።ይህ ጎሰኞች የተከሉት መንግሥታዊ ስርዓት በአገራችን ህልውና ላይ ብዙ ስብራት ያደረሰ በመሆኑ  በሕዝቡ ተቀባይነት አላገኘም፤ብዙ መስዋእትነት ቢከፈልበትም ከቦታው ንቅንቅ አላለም፤እንደውም በዬጊዜው ስምና መልኩንወይም መሪዎቹን  እዬቀያዬረ፣ባሳሳች ቃላት የታጀበ ስብከቱን በመንዛት የግዛት ዘመኑን ለማራዘም ጥረት አደረገ እንጂ የሕዝቡን ስሜትና ፍላጎት አድምጦ ለለውጥዝግጁ አልሆነም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እዬፈጠጠ የመጣው ምስቅልቅል ሁኔታና የሕዝብ ብሶት የወለደው  የፖለቲካ ቀውስ  በገዢው ጎራ በተሰለፉት ጎሰኞች መካከል  መደናገርና የፖለቲካ ሽኩቻ ፈጥሮ እርስ በርስ እያባላ ይገኛል።ያም ብቻ ሳይሆን እንደ ገበሎ ተደብቀው የነበሩ ቀውሰኞች ካሉበት ተጠራርተው አንገታቸውን ቀና ቀና በማድረግ በተቀጣጠለው የፖለቲካ ሰደድ ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ ተግባር ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።በዚህ የእርስ በርስ ቀውስ ላይ ዓለም አቀፉ የኮቪድ 19(ኮሮና) ወረርሽኝ መስፋፋት ሲጨመርበት ችግሩን በቡሃ ላይ ቆረቆር ወይም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል። በግርግር ሥልጣን ላይ የተቀመጠው ቡድን ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም  ቢፈልግም በውስጡ በተነሳው የሥልጣን ግብግብ የተነሳ ብሎም የሥልጣን ዕድሜውን በራሱ በሚመራበት ሕግ  ስለገደበው በሥልጣን ላይ የመቆዬት መብት የለውም።ይህንን መሰናክል ለማለፍ በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ አገራትንና ሕዝብን ያሸበረውን የኮቪድ 19(ኮሮና) ወረርሽኙን ተገን በማድረግ  ምርጫውን ላለመካሄድ የሕግ ድጋፍ ለማግኘት ሲቅበዘበዝ ይታያል።ይህም ብቻ አይደለም በወረርሽኙ ስም ብዙ የገንዘብ እርዳታ እዬሰበሰበ ይገኛል።ለሕዝቡ ጤና ይዋል አይዋል ወደፊት የሚታወቅ ይሆናል።ሆኖም ግን ኮሮና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰተ እንጂ ለመንግሥት መነሻና መውደቂያ ተደርጎ ሊቀመጥ የሚገባው ሰበብ አይሆንም።ከኮሮና በፊት በቀውስ የተነከረ መንግሥት ነበር፣ ከኮሮና በዃላም ምንነቱ አሁን ላይ የማይታወቅ መንግሥት ይኖራል።ጥያቄው የጤና ጉዳይ ስለሆነ የጤና ጥበቃ ተቋም የሚመለከት ጥንጂ የመንግሥትን መኖር አለመኖር የሚጠይቅ ችግር አይደለም።የጠንካራ ተቋማት መኖር አስፈላጊነትም መንግሥት ቀውስ ውስጥ ቢገባና ቢወገድ ሥራው እንዳይደናቀፍ ካለምንም ችግር እንዲቀጥል ለማድረግ ስለሚያስችል ነው።ለምሳሌም ጠንካራ አገራዊ መዋቅሮች ወይም ተቋማት  ባሉበት አገር መንግሥት ከሥልጣን ቢወርድ ምንም ችግር ሳይፈጠር፣ሰላም ሳይደፈርስ ያለመንግሥት ወይም ያለ ካቢኔ በተረጋጋ መልኩ አገር ሊተዳደር እንደሚችል ብዙ አገሮችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በሌላው ጠርዝ ላይ የተሰለፉት የነባሩ ወያኔ የግብር አጋሮች/አክራሪ ጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎች/ ምርጫ ወይም ሞት ብለው የመንግሥቱን አካሄድ ሕገወጥነት እዬሞገቱት ይገኛሉ፤ሙግትም ብቻ ሳይሆን የማስፈራራት ቅስቀሳና ዘመቻ ከፍተዋል።የነዚህ ቡድኖች ፍላጎት ያጡትን ሥልጣን መልሶ ለማግኘትና የጠነሰሱት አገር የማፈራረስ ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ እንጂ የሚረባና አገር ገንቢ ዓላማ ኑሮዋቸው አይደለም። ለሁለቱም የአንድ ኢሕአዴግ ቤተሰቦች ጭቅጭቅ መነሻና ከለላ የሆነው ሕዝብ ያልተሳተፈበትና ያላጸደቀው በነዚሁ ጎሰኛና ተገንጣይ ቡድኖች የረቀቀሕገመንግሥት ተብዬው  መመሪያ ነው። በሁለቱም በኩል የሚደረገው እሰጥ አገባ ለኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ የሚያፈነጥቅ ሳይሆን ጊዜና ዕድል ከተሰጠው አገራችን ኢትዮጵያን  ወደባሰ ቀውስና መናጋት ውስጥ የሚከት ይሆናል። ሕገመንግሥት በሕዝብ ተሳትፎና ፍላጎት በሥራ ላይ የሚውል ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱና እንደወቅቱ ሊሻሻል፣ሊቀነስ ወይም ሊጨመር የሚችሉ አንቀጾችን የሚያስተናግድ ሕጋዊ መዝገብ ነው።የማይነካ፣የማይቀዬርከሰማይ የወረደ የፈጣሪ ቃል አይደለም።ስለሆነም ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ ላይ ጥያቄ ካነሳ ወይም ለወቅቱ ጥያቄ መልስ የማይሰጥ ከሆነ ሊመረመርና ሊስተካከል የሚችል መሆኑን አምኖ መቀበል የግድ ይላል። አሁን ያለው መንግሥት ይቀጥል አይቀጥል፣ምርጫ ይካሄድ አይካሄድ የሚለውን ለመመለስ የሚከተሉትን ምክንያቶች ከግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ ይመስለኛል። 1 በሥልጣን ላይ ያለው “መንግሥት”የሥልጣን ዘመኑን ለመጨረስ ያለው ዕድሜ ከሶስት ወር አይበልጥም፤ከሶስት ወራት በዃላ ለተተኪው ማስረከብ ይኖርበታል። 2 ምርጫ ለማካሄድ በቂ ዝግጅትና የተወዳዳሪዎች በነጻ የመንቀሳቀስ ዕድልና መብት የለም  አልተከበረምም፤በዚያ ላይ ባለው የወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያትም እንቅስቃሴ ሁሉ ስለተገደበ ምርጫ ሊካሄድ አይችልም 3 ባለው ሁኔታ ምርጫ ይካሄድ ቢባል የከረረ ግጭትና ቀውስ ከማስከተሉ ሌላ ጥቅም አያመጣም።ምርጫስ ቢካሄድ ማን ከማን ይመረጣል?ከጅንጄሮ ቆንጆ! 4 በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ከአምስት ዓመት በላይበሥልጣን ላይ የመቆዬት ሕጋዊ  መብት የለውም።የሕገ መሻሻል ቢደረግ ወይም ተጨማሪ ጊዜያዊ አዋጅ ቢደነገግናና አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ቢቀጥል አገራችን አሁን ካለችበት የተሻለ ሁኔታ አይገጥማትም፤ምክንያቱም ላለፉት ሁለት ዓመት ተኩል የታዬ መሰረታዊ ለውጥ የለምና። ከዚህ በላይ የተመለከቱትን ገሃድ ሃቆች መነሻ በማድረግ ለአገራችን ሰላምና አንድነት የሚያዋጣው አማራጭ ሕዝባዊ የሽግግር መንግሥት መመሥረት ብቻ ነው። የሽግግር መንግሥቱ መስራች ሊሆኑ የሚችሉት የሚከተሉትን መመሪያዎችና መመዘኛዎች ማሙዋላት ይኖርባቸዋል።ወይም የቃል ኪዳን ውል ሊገቡ ይገባል።

1 በኢትዮጵያ  አገራዊ አንድነትና ልዑላዊነት ላይ የማያወላውል አቋም ያለው፣

2 በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን፣

3 ጸረ ኢትዮጵያና የሕዝብ ትስስርን የሚያላላ ዘርንና እምነትን መሰረት ካደረገ የፖለቲካ አደረጃጀትና ቅስቀሳ የራቀ፣ለሰብአዊና ለዜግነት መብት ክብርና ዋጋ የሚሰጥ

4 ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት የሚያይና የሚያሳትፍ ዴሞክራሲያዊአሠራርን የሚከተል፣

እነዚህን የጋራ እሴቶች የተቀበሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ሕዝባዊና የሙያ ድርጅቶች፣የሃይማኖት ተቋማት ፣ምሁራን፣የሕግ ባለሙያዎች፣የሴቶች፣የወጣቶች…ወዘተ ተወካዮች የሚሳተፉበት ይሆናል። ይህ የሽግግር መንግሥት ግፋ ቢል ለሁለት ዓመት ሥልጣኑን ተረክቦ የመንግሥቱን የተለያዩ ተቋማትና  ዘርፎች የሚመሩ በችሎታቸው የታወቁ ሰዎችን ይመድባል።አሁንም በቦታው ላይ ያሉ ከፖለቲካ ድርጅት ጋር ንክኪ የሌላቸውና ወንጀል ያልፈጸሙ ባለሙያዎችን በተመደቡበት ሥራ ላይ እንዲቀጥሉ ያደርጋል። አሁን የሰፈነው ስጋትና አለመተማመን ተገፎ የአገር መረጋጋት፣ሰላምና ጸጥታ፣የሕዝብ መቀራረብ እንዲሰፍን ያደርጋል። ሁሉንም ያሳተፈ ሕገመንግሥት ይነድፋል፤አገራዊ ምርጫ የሚደረግበትን ሁሉ አሙዋልቶ ምርጫ ተካሂዶ ለቋሚ መንግሥት ሥልጣኑን ያስረክባል። የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚለው የሕዝብ ጥያቄ ዛሬ የተነሳ ሳይሆን ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ሲስተጋባ የኖረ ጥያቄ ነው።ሆኖም ግን ቀደም ያሉትም ሆኑ የአሁኖቹ ከሥልጣን ስለሚያሶግዳቸው  አጥብቀው ይቃወሙታል።ሕዝብ እንደማይመርጣቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ።ስለዚህም በሽግግር መንግሥት ላይ  ልዩ ልዩ ታሪክ እዬፈጠሩ ሕዝቡን ለማታለል ይሞክራሉ።ሕዝብ ግን የእኔ በእኔ ለእኔ የሚለውን መንግሥት እንጂ በመሳሪያና በውጭ ሃይሎች ድጋፍ ሥልጣን ላይ የሚወጣን ቡድንወይም በጎሳና በሃይማኖት ከለላ ከፋፍለው ሊያጫርሱት የሚሞክሩትን  አይቀበልም።ያንንም በተደጋጋሚ አሳይቱዋል።

ይህ የሽግግር መንግሥት እንዴት ይመሠረታል?

አገራችን ሆነም ቀረም፣ተግባራዊም ሆነ አልሆነም በርእሰብሔራዊ ወይም ፕርዚዴንታዊ ማእቀፍ ወይም ስርዓት ውስጥ የምትመራ አገር ናት።ምንም እንኳን የአገሪቱ እርእሰ ብሔር የሚሆኑትሥልጣን ላይ የተቀመጠ የፖለቲካ ድርጅት ሹመኞች ቢሆኑም የያዙት ቦታ የአገሪቱን ሰላምና አንድነት በሚመለከተው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ከመስጠት የሚያግዳቸው አይኖርም።ሌላው ቢቀር የዜግነት ግዴታ አለባቸው። ስለሆነም አሁን ያገራችን ርእሰብሔር የሆኑት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደ ርእሰብሔርነታቸውም ሆነ እንደ አንድ ዜጋ አገራቸው ከገባችበት አጣብቂኝ እንድትወጣ የሚያስችል ውሳኔ ለማሳለፍ ሙሉ መብትና ሥልጣን አላቸው ብዬ አምናለሁ።በሌላውም አገር የርእሰብሔር ወይም የፕሬዚዳንቶች ሚና ከዚህ የተለዬ አይደለም።መንግሥት የማሰናበትና ሌላ እንዲቋቋም የማድረግ ሙሉ ሥልጣንና መብት አላቸው።ወይዘሮ ሳህለወርቅም እንዲሁ ቤተመንግሥት የገቡት ለናሙናና ፣እንግዳ ለመቀበልና ለመሸኘት ሳይሆን በዚህም ፈታኝ ወቅት ላይ ሊተገብሩት የሚገባ አላፊነት አለባቸው።
Full Website