በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው ጀርመናዊው የታሪክ ፀሃፊ ሊዮፖልድ ቮን ራንኪ ታሪክ እንዴት መፃፍ እንዳለበት ሲመክር እንዲህ አለ፡- “ልክ እንደነበረው“፡፡  በህወሓት የ45 አመት ታሪክ ውስጥ፤ጥቃቅን ግን በርካታ የሆኑትን የውስጠ ፓርቲ ፍትግያዎቹን ትተን፤ ድርጅቱን ከመሰረቱ የናጡ ሁለት ሕንፍሽፍሾች ተከስተዋል፡፡ በፓርቲ ፖሊቲካ አለም ውስጠ ልዩነት ጤንነት ነው፡፡ ፖለቲካ ፓርቲ የሚመሰረተው በአበይት አቋሞች ላይ የጋራ አመለካከት ሲኖር ብቻ እንጂ አባላቱ በሙሉ በሁሉም ጉዳዮች ላይ አንድ አይነት አመለካከት ስላለቸው አይደለም፡፡ የውጩ እንጂየውስጡ ድምፅ የማይሰማ ፓርቲ በርግጠኝነት የአምባገነንነት ባሕርይ አለው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ሐወሓት ውስጥ የተከሰቱት ሁለት ዋና ዋና ሕንፍሽፍሾች የመጀመሪያው በ1969 ዓ.ም. በትግል ወቅት የተከሰተ ሲሆን ሁለተኛው ግን ከድል በኋላ በ1993 ዓ.ም. ነበር፡፡  ሁለተኛው ሕንፍሽፍሾች እኩል አቅም በነበራቸው አመራሮች መካከል የተካሄደና ሳሩ የተጎዳበት የዝሆኖች ትግል ነበር፡፡ ስለዚህ ሕንፍሽፍሽ መንስኤው ሆነ ውጤቱ በሁለቱም ጎራ አባላት በኤሌክትሮኒክና በህትመት ሚድያ በጥልቀት ተዘግቧል፤ተተንትኗልም፡፡ በህወሓት ታሪክ ወሳኝ ሚና የነበራቸው አመራሮች ድርጅቱን የለቀቁበት የሁለተኛው ሕንፍሽፍሽ በጊዜ ሂደት ድርጅቱን አዳክሞታል፡፡ ከዚህ በላቀ ደግሞ ድርጅቱን የለቀቁት አመራሮች በተቃዋሚነት ፖለቲካ ስለተሰማሩ ሰላም መልካም አስተዳደርና ልማት ግንባር ቀደም አጀንዳ መሆን በሚገባው ትግራይ ክልል ውስጥ አንዱ ባንዱ ላይ መሰናክል እያበጀ በመሆኑ ህዝቡ ግራ እየተጋባ ነው፡፡ የሁለተኛው ሕንፍሽፍሽ ዋና መንስኤ በትግራይ ውስጥ ባለ ዴሞክራሲ፤ መልካም አስተዳደርና የልማት እቅድ አፈፃፀም ሳይሆን በኤሪትርያና ኢትዮጵያ ጉዳይ ነበር፡፡ ው ማለት የ1969 ሕንፍሽፍሽ የተከሰተው ህወሓት ከተመሰረተች በቅጡ ሁለት አመት እንኳ ሳይሞላት ነበር፡፡ ነገሩ እጅግ አስገራሚ ነበር፡፡ ታጋዩ ገና በአላማ ፍቅር በስሜት ግለት ላይ እያለ፤ ያውም አምስት መቶ ያልሞላ የታጋዮች ቁጥር በያዘ ድርጅት፤ ደርግ ህወሓትን ከጅምሩ እንዳይውጣት በሁሉም ዘንድ ስጋት በነበረበትና ጥንቃቄ በሚደረግበት በዛ ከባድ ጊዜ እንዲህ አይነት ውዝግብና ይህን ተከትሎም ብዙ አሳዛኝ ክስተቶች መፈጠራቸው ታላቅ እንቆቅልሽ ነበር፡፡ ይህ ውስጠ ፓርቲ ውዝግብ የተከሰተው ዶር. አረጋዊ በርሀ (የበርሃ ስሙ በሪሁ) የህወሓት ሊቀመንበር በነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ምንም እንኳን ይህ የመጀመሪው ሕንፍሽፍሽ ከሁለተኛው ሕንፍሽፍሽ በላቀ ህወሓትን የውድቀት አፋፍ ላይ ያደረሳት ቢሆንም ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ማስመሰሉ ህወሓት ውስጥ እንደ ፖለቲካ ባህል የተቆጠረ ይመስላል፡፡ ብቻ አልፎ አልፎ በስብሰባ ላይ ወይንም በሚድያ የህወሃት የ17 አመታት ገድል ሲተረክ የ1969 ሕንፍሽፍሽ እንደዋዛ ይነሳና  “ህወሓትን ለማፍረስ በደርግ የተላኩ፤ አመራሩን እኛ ካልያዝነው የሚሉ፤ ርሃብ፡ ጥማት፡ ብርድና ሃሩር መቋቋም ባቃታቸው ግለሰቦች የተጎነጎነ ግን በጀግንነት የከሸፈ ሴራ ነበር“ እየተባለ ወደ አንድ ወገን ያጋደለ፤ንቀትና ማን-አለብኝነት በተላበሰ መንፈስ ይነገራል፡፡ ማንም ሆነ ማንም አብሮ ይሳተፍ የዛ ሕንፍሽፍሽ ሙሉ ሃላፊነት መውስድ ያለበት ዶር. አረጋዊ በርሀ ነው፡፡ ከህወሓት በራሱ የግል አለመግባበት ለቆ አውሮፓ ከኖረ በኋላ አሁን ወደ ትግራይ ፖለቲካ በተለመደው የአምባገነንነት ሰብእናው ተመልሶ ያለኔ አዋቂ የለም በሚል የበላይነት አባዜ  አዲስ አበባ ተቀምጦ የትግራይን ፖለቲካ እያመሳቀለ ይገኛል፡፡ ከዚህ በፊት ዶር. አረጋዊ በርሀን የሚመለከቱ ፅሁፎች በአይጋ ፎረም አውጥቻለሁ፡፡ በሁሉም ፅሁፎቼ ትኩረት የሰጠሁት የዶር. አረጋዊ ፖለቲካ አካሄድ ከትግራይ ህዝብ አንድነትና ሰላም ጋር የሚጣረስ ሆኖ ስላየሁት አቧራ ማጨሱን አቁሞ ለትግራይ ህዝብ ሰላም በሚደረገው ጥረት የበኩሉን የተረጋጋ ተሳትፎ እንዲያደርግ ምክር ለመለገስ ነበር፡፡ ከትግል ሜዳ በትግስት ቆይተው ደርግን አሸንፈው ለትግራይ ህዝብ አንፃራዊ ሰላም ያጎናፀፉትን እየዘለፉ የድህረ ድል አርበኛ መሆን የሞራል ዝቅጠት ነው፡፡

ባለፈው ሰኔ ወር ዶር. አረጋዊ በርሀ ትግራይ ውስጥ የፖለቲካ አልጋ ባልጋ እንዲሆንለት ሲጠብቅ “አንድ ትራስና አንድ ፍራሽ ብቻ ያለበት ክፍል ውስጥ ታሰርኩ“ በማለት ትግራይ ውስጥ ዴሞክራሲ የለም እያለ በአስሩ ሚድያ ሲያስተጋባው ከረመ፡፡  እንግዲህ አምላክ አፈር ላበደረ ጤፍ አይመለስ! ይህ አውሮፓ የፈጠረው የመርሳት በሽታ ፍራሽ ላይ ሳይሆን አፈር ውስጥ የተኙት ሰዎችንም አስረስቶ ነው? ወር ዒ ሸለቆ ውስጥ ወይኔ ልጆቼ “ እያሉ አፈር ውስጥ የገቡት ሽማግሌስ ተረሱ? ዶር. አረጋዊ መቐለ ሄዶ ድብደባ እንደደረሰበት እንደጉድ ሲናገር ነበር፡፡ ይቺ ዱላ ሌላ ሰው ሲመታባት ስሜት አትሰጥም፤ በራስ ላይ ስትነሳ ግን በጣም ታስጮሃለች፡፡ ከሽሬ ደርግ የላከው ሰላይ ነው በሚል በገመድ ታስሮ ሲደበደብ ያደረው ምስኪን የሰው ፍጡር የታሰረበት ገመድ የክንዱን ጡንቻ ዙሪያውን በጥልቀት ቆርጦታል፤ አይኑ ሙሉ በሙሉ ደም ጎርሷል፤ ሰውነቱ ወባ እንደያዘው ይንቀጠቀጣል፡፡ ያ እንዳይበቃ ዓዲ ዳ ዕሮ በነበረው ጊዜያዊ አስር ቤት ተወረወረ፡፡ ይህ ኢሰብአዊነት የማን ድርጊት ነበር ? የመቐለ ወጣቶች ድብደባ እንዳደረሱበት የተናገረው የኔን የበለጠ ትኩረት ስቧል፡፡ የመቐለ ወጣቶች ዶር. አረጋዊን ለመደብደብ ህወሓት እስክትልካቸው ድረስ ይጠብቃሉ ብየ አላስብም፡፡ በ1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽ ዶር. አረጋዊ ሚና ምን እንደነበር የሚተርክላቸው አባት፤ ታላቅ ወንድም፡ ወይንም ሌላ የደረሰበት ወይንም የሆነውን የሰማ ሰው ያጣሉ ብሎ መገመት ይቻላል? የትግራይ ምርጫ አሽንፎ መቐለ ከተማ ላይ ለመቀመጥ ማሰቡስ  ራሱ በቀየሰው የ1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽ የትግል ሞራላቸው ተሰልቦ፤ የመጣባቸው ነገር ምን እንደሆነ በቅጡ ሳይገነዘቡ ህይወታቸውን ለማዳን ከድርጅቱ የሸሹ፤ መሽሽ ሳይሳካላቸው የቀሩና የተጎዱ፤ ግራ እንደገባቸው ደርግ ፀረ-ህወሓት ሃይል አድርጎ የተጠቀመባቸውና ኋላም ወያኔ ናችሁ በማለት ራሱ ወህኒ ያጎራቸው፤ ከሕንፍሽፍሹ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ተበላሽቶ የቀሩ የእንደርታ ልጆች መራራ ታሪክ “የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም“ ነው፡፡ ከህወሓት ድል በኋላም በ እንደርታ ህዝብ ላይ መረን የለቀቁ ቃላት ሲነገሩና አሰልሳይ የሆነ የኢኮሚ ቅጣት ሲደርስበት ቆየ፡፡ ጅራፍ ራሱ መትቶ ራሱ ሲጮህ! እንዳይታገል አደረጉት ስላልታገለ ቀጡት፡፡

Full Website