02/14/2020

ህግ ማስከበር ቀዳሚ የመንግስት ሀላፊነት ነው ። ኢትዮጵያ ምድራዊ ስላም የራቃት አገር ሆናለች ። የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆች ከኦሮሚያ ክልል ደንቢ ደሎ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በሰላም እጦት ምክንያት ትምህርታቸው አቋርጦ ተወልዶ ያደጉበት ቦታ ለመሄድ መንገድ ላይ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ስዎች እገታ ተፈፅሞባቸዋል ። እገታው ከተፈፀመ ሁለት ውር አልፎታል ። የታገቱት የደንቢ ደሎ ተማሪዎች ትክክለኛ ቁጥር ከገለልተኛ ተቋም ማውቅ አልተቻለም ። ከመንግሰት የተገኘ መረጃ 17 ተማሪዎች መታገታቸው ያመነ ሲሆን በቁጥር የሴት ተማሪዎች ብልጫ እንዳለው ጭምር ለማውቅ ተችሏል ። መንግስት ዜጋው ሲታገት፣ ሲታፈን እንዴት በቤተመንግስት መኖር ይከጅላል ? ።መንግስት ለዜጎች ጥብቅና ካልቆመ ቤተ መንግስት መከተም ምን ይፈይዳል ? ። ዜጎች በህግ አልባ ጉልበተኞች ለመኖሪያ ከተሰጣቸው ቤት ሲነቀሉ መንግስት ህግና ስርአት ማስከበር ካልቻለ ምኑ መንግስት ሆነው ? ።ንፁሃን ዜጎች በጠራራ ፀሐይ ግፍና ግድያ ሲፈፀምባቸው መንግስት ወንጀለኞች በህግ ካልጠየቀ የመንግስት መኖር ምን ይበጃል ? ።ህግና ስርአት የማስከበር የመንግስት ተግባር ሆኖ ሳለ ንፁሃን ዜጎች በስርአት አልበኞች ግፍና ስቆቃ ሲፈፀምባቸው መንግስት ፍትህ ማስከበር ካልቻለ መንግሰት ሳይሆን ስርአት አልባ መንግስት ይሆናል ። መንግስት ተጠያቂ የሚያደርግ ገለልተኛ ተቋም አልያም የፍትህ አሰራር ባለመኖሩ የዜጎች ሰብአዊ በደሎች ተባብሶ ቀጥለዋል ። የጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድ አሰተዳደር በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የዜጎች መብት ጥሰት እንዲሁም ወንጀል በታሪክ ያስወቅሳል ፣ በወንጀል ያስጠይቃል ። መንግስት በአግባቡ ህግ ማስከበር ይጠበቅበታል ።የመንግስት ሀላፊነት እና ተጠያቂነት በአግባቡ መተግበር አለበት ። በኢትዮጵያ የጎጥ አለቃ በዝተዋል ። የማህበራዊ ለውጥ አቀንቃኝ ነን ባይ ግለሰቦች ህግ ተላልፎ ወንጀል እየፈፀሙ ይገኛሉ ።በኤርትራ በረሃ የነበሩ ነፃ አውጪ ነን ባይ የነፃነት ግንባርመሣሪያ ሳይፈቱ አገራቸው እንዲገቡ መደረጉ የመንግስት ስህተት ነበር ። ማንን ነፃ እንደሚያወጡ በግልጽ ባይታወቅም አገር ቤት ተመልሶ ገንቢ ዜጋ ከመሆን የገንዘብ ተቋም የሆኑ አሰራ ስምንት ባንኮች የገንዘብ ዝርፊያ ተፈፅሟል ። በድርጊታቸው በህግ ተጠያቂ አልሆኑም ። ድርጊቱ  የሰላም መደፍረስ ከመጠቆም ባሻገር መንግስት ህግ የማስፈፀም አብይ ክፍተት እንዳለው በግልፅ ያሳያል ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ግኝታቸው ከኢህአዴግ ስርአት ሲሆን ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒሰትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን ሲረከቡ በርካታ የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፉ ተሰጥቷቸው ነበር ። ጥቂት የማይባሉ ስዎች ዶክተር  አብይ አህመድ “ ከሙሴ “ ሀይማኖታዊ ተግባራት ጋር ለማመሳሰል ጭምር የቃጡ እንደነበሩ የሚካድ ጉዳይ አይደለም ። ዶክተር  አብይን ኢትዮጵያዊ ሙሴ ለማለት የዳዳቸው እንደነበሩም አይካድም ። ደሩ ግን ዶክተር አብይ አህመድ ሙሴን መሆን አልቻሉም ። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅ የነበሩ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ዶክተር አብይ አህመድ በተመረጡ ጥቂት ወራት ውሰጥ በቀን በመስቀል አደባባይ ተገደሉ ። ቀጥሎም በብራዩ ይኖሩ በነበሩ የጋሞ ተወላጆች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈፀመባቸው ። ከሀያ የሚበልጡ የጋሞ ተወላጅ ዜጎች ለህይወተ ህልፈት ተዳርገዋል ። የዶክተር አብይ አህመድ አሰተዳደር የወሰደው እርምጃ ከድርጊቱ ጋር የሚመጣጠን አልነበረም ። የኢትዮጵያ መከላከያ  ስራዊት አዛዥ ኢታማዦር ሰአረ መኮነን ግድያ አስደንጋጭ ነበር ። ይህም የተፈፀመው በዶክተር አብይ አህመድ አሰተዳደር ጊዜ ነው ። የመከላከያ ሰራዊት ሀላፊ ምን ድክመት አልያም ወንጀል ቢኖራቸውም ነው ለሞት የታጩ ? ። ገደያቸውሰ ማን ነው ? ። ከግድያ በስተጀርባ ያለውሰ አካል ማን ነው ? ። ከትግራይ ጋር የሚያገናኝ መንገድ የተዘጋው በጠቅላይ ሚኒሰተር ዶክተር አብይ አህመድ አሰተዳደር ጊዜ መሆኑ ታሪካዊ ክሰተት ነው ። ህዝቦች የሚገናኙበት አገናኝ መንገድ መዝጋት ከወንጀል ያለፈ ትርጉም ያለው ነው ። የፖለቲካ መሪዎች ያለመግባባት ለምን የህዝብ ችግር ተደርጎ ይወሰዳል ? ። የትግራይ ህዝብ ምን በደለ ? ። የአማራ ህዝብ ምን በደለ ? ።  ድንበር ተቋራጭ መንገድ በስርአት አልባ አካል ሲዘጋ መንግሰት የጉዳዩ ተባባሪ ከመሆን መፍትሔ ማፈላለግ ነበረበት ። ድንበር ተቋራጭ መንገድ የሚሰራው በፌደራል መንግስት በጀት እንደሆነ እረዳለሁ ። በመሆኑም መንገድ የሚዘጉ የክልል አመራሮች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ስረአት የማስያዝ የማዕከላዊ መንግስት ሀላፊነት ነበር ። ሆኖም ሲሆን አልታየም ። ፍትሐዊ ያልሆነ የመንግስት አሰራር ውጤቱ ጥሩ ውድቀት እንጂ ጥሩ ውጤት አያስገኝም ። አገር ውሰጥ መንገድ መዝጋት ከፀጥታ ጋር ምንም የሚያገናኘው ጉዳይ የለም ። ማን ማንን ይጎዳል ? ። የትግራይ ህዝብ የሰላም አምባሳደር ከመሆኑም በላይ ለሰላም የሚሰጠው ክብር የላቀ ነው ። በመሆኑም ሰላም የህዝቦች ዋስትና እንዲሆን ከፀሎት ጀምሮ የሚተጋ ህዝብ ነው ። ታድያ ለትግራይ ህዝብ እንዴት መንገድ ይዘጋበታል ? ። ይህ እጅግ አስገራሚ ክሰተት ነው ። በታሪክ ተፈፅሞ አያውቅም ። ህዝብ እንዲራብ ፣ እንዲታረዝ ፣ እንዲሰደድ ፣ እንዲጎዳ ማድረግ መልካም አልነበረም ። ህዝብ መበደል የኢትዮጵያ ታሪክም ባህልም አልነበረም ። በፖለቲካ ሴራ ማህበረሰብ መበደል ተጠያቂነት ያስከትላል ። ህዝብ ከፖለቲካ ነጥሎ ማየቱ ተገቢነት ያለው ምክረ ሐሳብ ነው ። የብሔር ፖለቲካ ነጋዴዎች ለታሪክ የማይሆን የፖለቲካ ሴራ ትተው ንፁህ የሐሳብ አማራጭ ይዞ መታገል አዋጪነት ያለው ሐሳብ ይመሰለኛል ። በኢትዮጵያፖሊሲ ለውጥ ተኮር የፖለቲካ ውይይትእምብዛም የተለመደ አይደለም ። ይልቁንም የመጠላለፍ ፖለቲካ በስፋት የሚታይበት በመሆኑ ለበርካታ የሰው ህይወት እና ንብረት ሞት እና መውደም ምክንያት ሲሆን ይስተዋላል ። ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢህአዴግ ስርአተ መንግስት አፍርሶ የብልፅግና ስርአተ መንግስት የኢህአዴግ መርሐ ግብሮች ከመጠቀም በቀር የተሻለ የኢኮኖሚ ሆነ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማራጭ የላቸውም የሚሉ ተንታኞች አሉ ። የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ልማታዊ የኢኮኖሚ ስርአት በመደመር የኢኮኖሚ ስርአት መቀየር ካልሆነበቀር የበሰለ የኢኮኖሚ ለውጥ ያለመታየቱ ለበርካታ ትችቶች በር ከፍተዋል ። በእርግጥም መደመር የኢኮኖሚ ለውጥ ፖሊሲ አይደለም ። ሆኖም ለሶሻል ካፒቲል /Social Capital / መነሻ ሐሳብ ሊሆን ይችላል ። ማህበራዊ ጥምረት የገበያ ሚዛንእንዲሁም ምርታማነትን ሊያሳድግ እንደሚችል ይታመናል ። ሆኖም የመደመር ሐሳብ ለማህበራዊ ለውጥ ምክንያት ሊሆን አይችልም ። ማህበራዊ ለውጥ የምጣኔ ሀብት ፣መልካም አስተዳደር ፣ እንዲሁም የህግ በላይነት መነሻ ያደረገ በመሆኑም ማህበረሰብ ተደመረ አልተደመረ የሚያመጣ ለውጥ የለም ። የአንድ አገር ህዝብ ጥምረት በፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ የመንግስት አሰተዳደር ሲኖር ፣ የህግ በላይነት ሲረጋገጥ ፣ ዜጎች እንደየ አቅማቸው በአገራቸው በፈለጉት ቦታ ያለስጋት መኖር ሲችሉ ፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ስውን ማሰርና ማፈን ሲቆም ፣ ለህገ መንግስት ተገዢ የሆነ መንግስት ሲኖር ፣ ሰላማዊ የመንግስት የሰልጣን ሸግግር ሲኖር ፣ እንዲሁም ገለልተኛ የፍትሕ እና የደህንነት ተቋማት በተግባር ሲኖሩ ነው ። የአገር መከላከያ ሰራዊት ሀላፊዎች ለስብሰባ ጠርቶ የሚያሰር መንግስት ባለበት አገር የማህበረሰብ ድመራ ቧልት ከመሆን አያልፍም ።  ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢህአዴግ ስርአት ካፈረሱ ኢህአዴግ ይከተላቸው የነበሩ የመንግስት አሰራሮች ፣ የኢኮኖሚ ፖሊሶች ፣ የውጭ ግኑኝነት መርሖዎች ፣ የፖለቲካ መስመሮች መጠቀም አልነበረባቸውም ። ሆኖም አሁንም የሚተገበሩ የመንግስት ስራዎች በኢህአዴግ ስርአት ተግባር ላይ የነበሩ አሰራሮች ናቸው ። ከድርጅት ስያሜ ውጭ የተቀየረ የመንግስት አሰራር እምብዛም እየታየ አይደለም ።  ጉዳዩ እንዳያማህ ጥራው እንዳይጎዳህ ግፍው ነው ። ሀይማኖት እና ዘር መሠረት ያደረጉ የተቀናጁ ጥቃቶች ከመፈፀማቸው አሰቀድሞ መከላከል የመንግስት ተቋም ሀላፊነት ሆኖ ሳለ ባለመሆኑ በንፁሃን ዜጎች ላይ የሞት አደጋ  ደርሰዋል ። የቅርቡ የሞጣ መስጂድ ጥቃት እንደአብነት መውሰድ ይቻላል ። አራት መስጂዶች የእሳት ስለባ ሆነዋል ። በርካታ ሀብት ንብረት ወድሟል ። የሰው ህይወት ጠፍተዋል ። የክርስትና እምነት ቤተ እምነቶች እንዲሁ የአገር ውሰጥ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል ። ዜጎች በእምነታቸው እየተገደሉ ፣ እየተሰደዱ ፣ እየተፈናቀሉ ፣ እየተዋረዱ ይገኛሉ ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተቃርኖ የቆዩ የክርስትና ሆነ የእስልምና እምነት ተከታዮች ችግር ለመፍታት የጣሩ ቢሆንም የእምነት ግጭት በህግ ልዕልና ማስቆም አልቻሉም ። ሰው እንደ እህል በዘር በተከፋፈለበት አገር ፣ የጎጥ አለቆች ከህግ በላይ በሆኑበት አገር ፣ ሰው ከቤቱ ወጥቶ በሰላም የማይመለስበት አገር ፣ ወንጀል ፈፃሚ በህግ የማይጠየቅበት አገር ፣ የህግ ልዕልና በማይከበርበት አገር ፣ በቆየ ያደፈ ታሪክ ስህተት መተማመን ባልተደረሰበት አገር ፣ የኑሮ ውድነት ከልክ ባለፈበት አገር ፣ የሥራ አጥነት መጠን ጣራ በነካበት አገር ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች በዘር የሚጠፋፊበት አገር ፣ የሴራ ፖለቲካ በሚካሄድበት አገር ፣ በውጭ ሀይል ጣልቃ ገብነት የሚተዳደር አገር ፣ ለዜጎች ደህንነት ቅድሚያ ባማይሰጥበት አገር ፣ እንዴት ህዝብ አገር አለኝ ፣ መንግስት አለኝ ብሎ መናገር ይችላል ? ።  የኢትዮጵያ ህዝብ አገራዊ ማንነቱ ተነፍገዋል ። ህዘብ በአገሩ በሰላም እና ነፃነት መኖር ካልቻለ ለከፍተኛ እንግልት መዳረጉ አይቀርም ። ህዝብ ሳይኖር አገር አይኖርም ። የኢትዮጵያ ህዝብ ደህንነቱን የሚያሰጠብቅለት የህዝብ መንግስት ያስፈልገዋል ። በኢትዮጵያ እስከዛሬ የፖለቲካ ድርጅት ፖርቲ መሪ እንጂ የህዝብ አሰተዳደር መንግስት ሆነ መሪ የለም ።ከህዝብ ድህንነት በላይ ለፖለቲካ ድርጅት ምስረታ ቅድሚያ ይሰጣል ። ለፖለቲካ ድርጅት ምስረታ የሚሰሩ በርካታ መሪዎች አሉ ። ግን የህዝብ መሪዎች መሆንአልቻሉም ። የህግ ልዕልና ምርኩዝ ያላደረገ መንግስት አልያም የአገር መሪ የህዝብ አሰተዳደር መሪ መሆን አይችልም ። ከሁሉም በፊት እና በላይ የህግ ልዕልና በማያወላዳ ሁኔታ መከበር እና ማስከበር የግድ መሆኑ የማይስማማ ሰው ይኖራል ብዩ አልገምትም ። ከሁሉም በላይ የህዝብ ድህንነት እና ሰላም መጠበቅ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ። ኢትዮጵያ ሰፊ አገር እና በርካታ ማህበረሰብ የሚኖርባት አገር በመሆኗ የፖለቲካ አሰተዳደር የማህበረሰብ እሴቶች (Values ) መነሻ አልያም መሠረት ያደረገ መሆን አለበት ። የማህበረሰብ እሴቶች ስንል ሰብአዊነት ፣ ነፃነት ፣ እኩልነት ፣ ፍትሀዊ የተፈጥሮ ሆነ ሰው ሰራሸ ሀብት አጠቃቀም ፣ ፍትህ ፣ ደህንነትና ሰላም ያጠቃልላል ።የማህበረሰብ እሴቶች መሠረት ያላደረገ የመንግስት አሰተዳደር ለማህበራዊ ግጭቶች ምክንያት ከመሆን ያለፈ ማህበራዊ መሠረት አይኖረውም ። የፖለቲካ ንድፈ ሀሳብ ከማህበረሰብ እሴቶች ጋር በሚገባ ካልተጣጣመ ማህበራዊ ጠቀሜታ ያለው የህዝብ አሰተዳደር ሊሆን አይችልም ። የማህበረሰብ ነፃነት የማያከብር የመንግስት አሰተዳደር ጨቃኝ እና አምባገነን መንግስት ይሆናል ። የማህበረሰብ ፍትህ የማያሰፈፅም መንግስት የህዝብ መልካም አሰተዳደር መንግስት መሆን አይችልም ። የማህበረሰብ እኩልነት የማይቀበል የመንግስት አሰተዳደር የዲሞክራሲ መንግስት አሰተዳደር መሆን አይችልም ። የዜጎች ደህንነት እና ፍትህ የማያስጠብቅ መንግስት አሰተዳደር የህዝብ መንግስት መሆን አይችልም ። የማህበረሰብ ስላም እና ፀጥታ ማስፈን የማይችል የመንግስት አሰተዳደር የህዝብ አሰተዳደር ለመሆን የሚያሰችል ማህበራዊ መሠረት አይኖረውም ።ለአንድ የመንግስት አሰተዳደር የማህበረሰብ ተቀባይነት ማግኘት የቅድሚያ ጉዳይ ። በህዝብ ተቀባይነት ያገኘ መንግስት ህግና ስረአት መሠረት አድርጎ መንግሰታዊ ስራዎች ይከውናል ። የመንግስት ሀላፊነት በአግባቡ ተፈፃሚነት እንዲያገኝ የማህበረሰብ ንቃተ ህልውና (መብት እና ግዴታ ) ወሳኝ ነው ። መብቱ እና ግዴታው በሚገባ የሚያረጋግጥ ማህበረሰብ ባለበት አገር መንግስት ለዜጋው ሙሉ ትኩረት ይሰጣል ። ጠያቂ እና ፈታሻ ማህበረሰብ በሌለበት አገር የመንግስት ልጓም ልል ይሆናል ፣ መልካም አሰተዳደር ይደፈርሳል ፣ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ይጨምራል ፣ ወንጀል ይስፋፋል ፣ የአገር ሀብት በከንቱ ይባክናል ፣ ስራ አጥነት ይጨምራል ፣ የኑሮ ውድነት ይጨምራል ፣ ስደት እና ማህበራዊ መዛባት ያስከትላል ። በኢትዮጵያ የተረጋጋ የመንግስት ስርአት እንዳይኖር ከምክንያቶች እንዱ የፖለቲካ ሃሳብ ልዩነት ማስተናገድ አለመቻሉ ይመሰለኛል ። የመናገር መብት መገደብ የለበትም የሚል የሰው የሌላ ሰው የመናገር መብት ማክበር አለበት ። አንዱ ተናጋሪ ሌላው ታሳሪ መሆን የመናገር መብት ሊሆን አይችልም ። የሃሳብ ልዩነት ያለው ማንኛውም ዜጋ የገዢ መንግስት ጠላት ተደርጎ መዝለፍ የለበትም ። የሃሳብ ልዩነት ማስተናገድ የፖለቲካ ሰልጣኔ መጀመሪያ ነው ። ፖለቲካ የአስተዳደር ጥበብ እንጂ የቂም ማስተንፈሻ መሳሪያ አይደለም ። የኢህአዴግ ስርአት አንዱ ችግር በፀረ ተውኔት ሃሳብ የታጠረ ስርአት ነበር ። ከስርአቱ ጋር የሃሳብ ልዩነት የነበረው ማንኛውም ዜጋ እንደ ፀረ አገር ፣ ፀረ ልማት ፣ ፀረ ህገ መንግስት ፣ ዲሞክራሲ ሳይኖር ፀረ ዲሞክራሲ ፣ ፀረ ህዝብ ፣ ነጭ ለባሸ ፣ አንጃ ፣ ባንዳ የሚል የፖለቲካ ንግድ ታርጋ ሲለጠፍበትቆይተዋል ። አሁን የተቀየረ ነገር እምብዛም የለም ። የብልጽግና ፖርቲ የሚቃወም ፀረ ብልፅግና መባል ተጀምሯል ። በፀረ አመለካከት የተመሠረተ የመንግስት አሰተዳደር የማህበረሰብ ጠንቅ እንጂ ጠቃሚ የሆነበት ጊዜ የለውም ። በፖለቲካ ሃሳብ መለያየት መከባበር እና መቀራረብ ያመጣ እንደሆነ እንጂ መለያየትና መራራቅ አያመጣም ። ችግሩ የፖለቲካ ሃሳብ ያላቸው የፖለቲካ ስዎች ስብዕና የጎደላቸው ፣ አገራዊ ራዕይ ችግር ያላቸው ፣ በህዝብ ስም ደረቅ የሚነግዱእና የሚያሰነግዱ ስዎች መሆናቸው ነው ። በሰፊው ህዝብ ሰም የሚነግዱ የፖለቲካ ነጋዴዎች የማህበረሰብ ንቃተ ህሊና በጨመረ ጊዜ መግቢያ እና መውጫ ያጣሉ ። በህፍረት እና ውራደት ከስልጣናቸው ይወገዳሉ ። ለታሪክ የማይሆን የመንግስት ሰራ የሰሩ መሪዎች በርካታ ናቸው ። መንግስትነት ለታሪክ እና መጪው ትውልድ የሚጠቅም ተግባር ሰርቶ ማለፍ ነው ። ይህ  የሚያገኙት ደግሞ የተግባር መሪዎች ናቸው ። በኢትዮጵያ በመልካም ተግባር የሚነሱ መሪዎች በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም ከበርካታ የታሪክ ጠባሳዎች ነፃ አይደሉም ። የመሪዎች የአስተዳደር በደል እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰት ለትውልድ የሚሸጋገር በመሆኑ አገር እና ህዝብ ለማስተዳደር የሚመረጠው መንግስት በተግባር ለህግ ተገዢ መሆን የማህበረሰብ አመኔታ በቀላሉ የማግኘት እድል ይኖረዋል ። ህግ በመንግሰት ሀላፊዎች እየተጣሰ የማህበረሰብ አመኔታ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ አይኖርም ። ማህበረሰብ በመንግስት ላይ ተሰፋ ባጣ ጊዜ መንግስት የሚነቅፉ ዋልታ ረገጥ የዘር ፖለቲካ አራማጅ ድርጅቶች ለመደገፍ የሚያስገድድ ውሳኔ ይወሰናል ። ማህበረሰብ በሰላም የመኖር አማራጭ ካጣ ራሱ ዘረኛ ማህበረሰብ የመሆን አጋጣሚ ይሰፋል ። በኢትዮጵያ እየታየ ያለውም ዘረኝነት ማህበረሰብ ውሰጥ መስፋፋቱ ነው ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሰተዳደር ከኤርትራ ጋር ያለውግንኙነት ጤናማ የውጭ ፖሊሲ መሠረት ያደረገ ያለመሆኑ በሂደት የኢኮኖሚ እንዲሁም የማህበራዊ ግንኙነት ችግሮች እንዲከሰቱ መነሻ ምክንያት ይሆናል ። ግልፅነት የጎደለው ፣ የቆየ ችግር በመርህ መፍትሔ የማያመጣ የውጭ ግንኙነት ውስብስብና በቀላሉ የማይፈታ ግጭት እና ህውከት ውሰጥ የሚያስገባ ይሆናል ። በተለይ የኤርትራ እንዲሁም የትግራይ ህዝብ ግልጽነት በጎደለው የውጭ ግንኙነት በቀጥታ ተጎጂ ነው ። ምክንያቱም ችግሩ ያለበት አካባቢ የሚኖር ህዝብ በመሆኑም ጭምር ነው ። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋርአሁን ያላት የውጭ ግንኙነት ሰፊው የትግራይ ህዝብ ሆነ የኤርትራ ህዝብ ደስተኛ አይደለም ። በመሆኑም ግልፅነት በጎደለው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ምክንያት የትግራይ ህዝብ ከኤርትራ ህዝብ ጋር ይበልጥ እንዲተሳሰር ሆነዋል ። የኤርትራ ህዝብ በአገሩ እንዲሁም በወደቡ ምክንያት በሚስጥር የሚደረገው ግንኙነት በስፋት ይጠራጠረዋል ። የትግራይ ህዝብ ደግሞ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላት የውጭ ግንኙነት የትግራይ ህዝብ ያገለለ እንዲሁም የሚጎዳ ነው የሚል ከፍተኛ መጠራጠር ማዕበል ውሰጥ ይገኛል ። በትግራይ እና በኤርትራ ድንበር ያለው ችግር የመሬት ይዞታ ጥያቄ ሳይሆን የፖለቲካ ሴራ እንደሆነ በርካቶች ይስማማሉ ። በመሆኑም የወሰን ጉዳይ ሌላ አማራጭ መፍትሄ ካልተወጠነ በቀር በአልጀርስ ስምምነት መሠረት እልባት የሚያገኝ አይመስልም ።ምክንያቱም የወሰን ችግር ከፖለቲካ ሴራ አሰተሳሰብ ጋር የተገናኘ በመሆኑ አዲስ የመፍትሄ ሀሳብ መቀየስ የሚያስፈልግ ይመሰለኛል ። የትግራይ ህዝብ በጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አሰተዳደር ላይ ያለው ተቀባይነት እና እምነት እየቀነሰ መሆኑ ይገለፃል ። ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ከትግራይ ህዝብ ጋር መምከር ፣ መወያየት ፣ መግባባት ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል ። የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያ ያበረከተው አገራዊ አሰተዋጽኦ በምንም የሚለካ ፣ የሚተመን አይሆንም ። በአገሩ የማይደራደር ፣ አገር ጠባቂ ህዝብ ነው ። የዘረኝነት ዋልት ያልተጠናወተው ህዝብ ነው ። የትግራይ ህዝብ አብሮነት እንጂ ዘረኝነት የሚጠየፍ ፣ የሚጠላ ፣ የሚያወግዝ ፣ የሚታገል ታላቅ አስተዋይና ሆደ ሰፊ ህዝብ ነው ። ይህ ባይሆን ስህተቱ እየሰፍም ፣ እየከፍም ይሄዳል ። የትግራይ ህዝብ ለፅንፈኛ ፣ ጠባብ አሰተሳሰብ ተገዢ የመሆን ልምድ ሆነ ልማድ የለውም ። የህልውና ጉዳይ ከሆነ ግን አማራጭ መንገድ የመሻት ጉዳይ ይቀራል የሚል እምነት የለኝም ። በኢትዮጵያ የትግራይ ህዝብ ያላማከለ የመንግስት ፖሊሲ ለውጥ እምብዛም ፍይዳ የለውም ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሰተዳደር ውሳጣዊመረጋጋት እጦት ምክንያት ግብፅ በአባይ ግድብ ሰጣ ገባ ላይአለምአቀፋዊ ተሰሚነት እና የበላይነት እያገኘች ነው ።  የሰሞኑ በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት እና አዳራዳሪነት ሲመከርበት የቆየ ድርድር የካቲት 5, 2012 ስምምነት ላይ ሳይደረሰ ድርድሩ ተበትነዋል ። ግብፅ የውሃ ክፍፍል ድርሻ የሚል ተለዋጭ ሃሳብ በሱዳን ጎን ተቀባይነትና ድጋፍ ቢያገኝም ኢትዮጵያ ሃሳቡን ሳትቀበለው ቀርታለች ። የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ውሳኔ የሚደገፍ ነው ። የአለም የገንዘብ ድርጅት ( WFO) ተወካዮች እና የአሜሪካ አስተዳደር የግብፅ ሃሳብ በመደገፍ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ ቢሞክሩም ኢትዮጵያ በጫናው ሳትበገር ቀርታለች ። የሱዳን የሽግግር መንግስት ወታደራዊ መንግስት ሲሆን በአሜሪካ የአለም የገንዘብ ድርጅት የቀረበለት ዳጎሰ ያለወ ጥቅም ከግብፅ ጋር እንዲወግን የተገደደ ይመሰላል ። የሱዳን የሽግግር መንግስት የቀድሞ የአገሩ መሪ ኡመር ሀሰን አህመድ አልበሸር በተጠረጠሩበት ወንጀል ለአለም አቀፍ ፍርድ ቤት አሳልፎ ለመሰጠት የተስማማ ይመሰላል ። ይህ ለሱዳን ብሄራዊ ሀዘን እንጂ ደሰታ እንደማይሆን ይገመታል ። ሱዳን የቀድሞ መሪዋን አሳልፋ ከሰጠች አሜሪካ ማካካሻ ይሆን ዘንድ በሱዳን ላይ ተጥሎ የቆየ የንግ ማዕቀብ ይነሳል ። ሱዳን በአልቃይዳ ለሞቱት የአሜሪካ ዜጐች ካሳ እንደምትከፍል ይጠበቃል ። የኢትዮጵያ ውሰጣዊ ችግር እንደመልካም አጋጣሚ የምትተቀመው ግብፅ የአባይ ግደብ ለማደናቀፍ አቅሟ የፈቀደው ሁሉ በማድረግ ላይ ናት ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የውስጥ ችገሮች ለመፍታት እየተወሰዱ ያሉ የህግ ክፍተት ሆነ የፖለቲካ አመራር መስተካከል ይጠበቅባቸዋል ። የሴራ እና የጥላቻ ፖለቲካ እልባት ካልተበጀለት የኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሮች ከማባባስ ይልቅ መሻሸል ላይታይባቸው ይችላል ። የሰላም እና መረጋጋት እጦት በህግ ልዕልና መቋጫ ካላገኘ መንግስት ሆነ ስርአት ቢቀያየር የማህበረሰብ ችግሮች እስካልተፈቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ካለባት ምጣኔ ሀብታዊ ሆነ ማህበራዊ ችግር በቀላሉ መላቀቅ አይችልም ። ይሀ ደግሞ በቁም የሞሞት ያህል ጉዳይ ነው ። በመንደር አለቆች የተዘጉ የፌደራል መንገዶች ለህዝብ አገልግሎት ክፍት ማድረግ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ተግባር መሆኑ እየታወቀ ለችግሩ እልባት አለማበጀት የህዝብ ህልውና አደጋ ላይ መጣል ያህል የከበደ መሆኑ በቅጡ መገንዘብ ያሰፈልጋል ። ለታሪክ እና ለትውልድ የሚተላለፍ እንዲሁም የሚበጅ ተግባር ከመሪ ይጠበቃል ። ለኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ አይነት ቋንቋ የመንግስት መርሀ ግብር እቅድ መተላለፍ ፣ መነገር አለበት ። ከቤተመንግስት ሰብረን ፣ ነቅለን ፣ አሰወጣናቸው የሚሉ ከመሪ ልሳን የሚነገሩ አነጋገሮች ተገቢነት የላቸውም ብቻ ሳይሆን የይዘት ሆነ የአገላለጽ ችግር ጭምር እንዳላቸው የሚያነጋግር ጉዳይ አይደለም ። በኢትዮጵያ ህዝብም ቅቡልነት ያላቸው አይመሰለኝም ። ምክንያቱም ከማጥላላት የሚገኝ ትርፍ የለምና ። የመንግስት አሰራር ድክመት ቢኖርም አራሚ መፍትሄ ማበጀት እንጂ የመሪ ስረአት አልበኝነት አነጋገርበህዝብ ዘንድ አግባብነት ሆነ ተቀባይነት የለውም ። መጪው ትውልድ መልካም ስነምግባር እንጂ የጥላቻ ንግግር ማውረስ ከአንድ መሪ አይጠበቅም ። በተመሳሳይ መልኩ የውጭ መንግስት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት አካሄድ የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል እንዳይሆን መንግስት መገንዘብ ያለበት ጉዳይ ይመሰለኛል ። ከታሪክ መማር ለሁሉም የሚበጅ ይሆናል ።
Full Website