fekadubekele@gmx.de
መቼ ነው ከዕዳ የምንላቀቀው? መቼስ ነው ራሳችንን የምንችለውና ነፃ አገር ለመሆን

የምንበቃው?

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

ጥር 19፣ 2020

መግቢያ

ሰሞኑን እንደዋና መነጋገሪያ ሆኖ የሚናፈሰው ዜና ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት(IMF) የድረስልኝ ጥሪ ካቀረበች በኋላ ከገንዘብ ድርጅቱ የ 2.9 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብድር ለማግኘት ስምምነት ላይ እንደደረሰች ነው። እዚህ ዐይነቱ ስምምነት ላይ ለመድረስ የገንዘብ ድርጅቱ ተጠሪ የሆኑት ወይዘሮ ሶላኒ ጄን አዲስ አበባ ከጥቅምት 29 ጀምሮ እስከ ህዳር 8፣ 2019 ዓ.ም ድረስ እንደቆዩና ከመንግስቱ ተወካዮች ማለትም፣ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ሚኒሰተሩና የሚኒስተር ዴኤታው፣ እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስተሩ ጋር እንደተስማሙ ነው።  በታህሳስ 5፣ 2012 በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ታትሞ በወጣው መሰረት ኢትዮጵያ ለዓለም የገንዘብ ድርጅቱ የይድረስልኝ ጥያቄ ያቀረበችው „ከማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ለመላቀቅ“ ነው የሚል ነው። የገንዘብ ድርጅቱ ኤክስኪዩቲቭ ቦርድ ስምምነቱን በመቀበል የብድሩን መሰጠት ሲያፀድቅ፣ ይህ 2.9 ቢሊዮን ዶላር በአንድ ጊዜ የሚለቀቅ ሳይሆን በሶስት ዐመት ውስጥ ቀሰ በቀስ የሚለቀቅና ዕዳውም ከአስር ዐመት በኋላ የሚከፈል ነው። የኢትዮጵያ መንግስት የብድሩን ስምምነት ከፈረመ በኋላ የገንዘብ ድርጅቱ ያኔውኑ 308.4 ቢሊዮን እንድሚለቅ ቃል-ቂዳን ገብቷል።  እንደተገነገርን ከሆነ ወለዱ ወደ ዜሮ የሚጠጋ ነው። ይህንን ዐይነት ስምምነትና ኢትዮጵያም በስምምነቱ መሰረት ከላይ የተጠቀሰውን የገንዘብ መጠን በብድር መልክ ማግኘት በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያተኞች አመለካከት „አገሪቱን እስትንፋስ እንደሚሰጣትና ኢኮኖሚውም ወደ ትክክልኛው አቅጣጫ እንደሚጓዝ“ አመልክተዋል። ከዚህ በተጭማሪ „ አንድ አፍታ “ ተብሎ በሚታወቀው የዩቱብ ቻናል ላይ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ለዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ ከጋዜጠኛው ስለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ፣ የብድሩን አስፈላጊነት ሲያጠናክር፣ በተጨማሪም ምንም ጊዜ ቢሆን ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቱ ትከሻ ለመላቀቅ እንደማንችል አረጋግጧል። ከብድሩ መሰጠት ጋር የሚቀርቡ ሁኔታዎችን አሉታዊ ጎናቸውን-ለምሳሌ እንደገንዘብ ቅነሳ የመሳሰሉት የአገሪቱን የንግድ ሚዛን ለማሻሻል አለመቻል ቢናገርምና፣ አገሪቱ ያላትን ፖቴንሽያል አለመጠቀም የቱን ያህል እንደጎዳን ቢያመለክትም- በተለይም ስለቻይናና ጃፓን የተናገው ግን ትክክል አይደለም። ቻይና እ.አ.አ በ1978 ዓ.ም  የገበያ ኢኮኖሚ የጥገና ለውጥ ለማድረግ ከጀመረችበት ጊዜ ድረስ ከዓለም የገንዘብ ድርጅትም ሆነ ከዓለም ባንክ ብድር ወስዳ አታውቅም። ይሁንና ግና በአሁኑ ወቅት የሶስት ትሪሊዮን ዶላር የገንዘብ ክምችት እያላት፣ እንደዚሁም ደግሞ አንድ ቲሪሊዮን ያህል ገንዝብ አፍሳ የአሜሪካንን የመንግስት ቦንድ ብትገዛና፣ ለብዙ የአፍሪካ አግሮች ብድር ብትሰጠም፣ ከኢኮኖሚ ሎጂክ አንፃር ለመግለጽ በሚያስቸግር መንገድ ለአንዳንድ ፕሮጀክቶች ከዓለም ባንክ ብድር ትወስዳለች። የጃፓንን ጉዳይ ስንመለት ደግሞ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ እንዳለው ሳይሆን፣ እ.አ.አ በ2008 ዓ.ም በብዙ የካፒታሊስት አገሮች የፋይናንስ ቀውስ በተከሰተበት ጊዜ የካፒታሊስት አገሮች ለዓለም የገንዘብ ድርጅቱ ማስተላለፍ የነበረባቸውን የገንዘብ ድርሻ መክፍል ያቅታቸዋል። በዚህ ጊዜ የገንዘብ ድርጅቱ(IMF) ከጃፓን መንግስት $ 100 ቢሊዮን  እንደተበደረ መረጃዎች ያረጋግጣሉ። ያም ሆነ ይህ ቻይና፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ  የራሳቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመቀየስ ነው ውጤታማ ለመሆን የበቁት። በተለይም ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ከሁለቱ እህትማማች ድርጅቶች የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ የጥገና ለውጥ እንዲያደርጉ ግፊት ቢደረግባቸውም ሃሳባቸውን አሽቀንጥረው በመጣል በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተና ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ግንባታ በመከተል አመርቂ ውጤት ሊያገኙ ችለዋል። በቃለ-ጥያቄ ምልልሱ ላይ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ጋዜጠኛው ታዲያ እነዚህ አገሮች እንዴትና በምን ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ውጤታማና የተስተካከለ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የቻሉት? ብሎ አልጠየቀም። ዶከተሩም ይህንን ጉዳይ ሳይብራራ የብድርን አስፈላጊነት ብቻ ነው አስምሮበት ያለፈው። ይህ ዐይነት በደንብ ያልተብራራ ጥያቄና መልስ ብዙ አድማጮችን ሳያደናግር እንደማይቀር በእርግጥ መናገር ይቻላል። በተለይም ደግሞ የእነዚህን ድርጅቶች ሚና በደንብ ላልተከታተለና ዕውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ምን መምሰል እንዳለበት  ለማይረዳና ላላጠና ሰው የዶክተር ቆስጠንጢኖስ አባባልን አምኖ ሊቀበለው ይችላል። በተለይም ከዓለም የገንዘብ ድርጅትና ከዓለም ባንክ ትክሻ ላይ መላቀቅ አንችልም የሚለው አባባል አሳሳችና በራሳችን ላይ እንዳንተማመን የሚያደርግ ነው። የዶክተሩ አገላለጽ በሳይንስና በቲዎሪ የተደገፈ ሳይሆን የገንዘብ ድርጅቱን (IMF) መንፈስን የሚያዳክም ቅስቀሳና ግፊት የሚያጠናክር ነው። ትችታዊ አመለካከት(Crititical thinking) የጎደለውና በምድር ላይ የሚታዩ ተጨባጭ ሁኔታዎች ለምን በዚህ መልክ ሊገለጹ ይችላሉ? የችግሩስ ምክንያት ምንድነው? በማለት የእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቱን ኢ-ሳይንሳዊ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ አደገኛነት ለመመርመር የሚቃጣ አይደለም። ለማንኛውም በህወሃት መሪነት ኢሃዴግ የሚባለው አገዛዝ እ.አ.አ በ1991 ዓ.ም አገራችንን ከተቆጣጠረ በኋላ ኢኮኖሚውን ወደ ነፃ ገበያ ለማሸጋገርና ተወዳዳሪ በመሆን መዛባትን የሚያስወግድ ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር እንደሚዘረጋ እ.አ.አ ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ „ሰፋ ያለ ያለ የመዋቅር ማስተካከያ ፖሊሲ“ ተግባራዊ እንዳደረገ ይታወቃል። ይሁንና ግን  ከ28 ዐመት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሙከራ በኋላ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከድሮው በባሰ መልክ እንደተዛባና፣ በተለይም ደግሞ ከፍተኛ የስራ አጥነትና በቀላሉ ሊቀረፍ የማይችል ስር የሰደደ ድህነት በአገራችን ምድር እንደተስፋፋ እናያለን። በሌላው ወገን ደግሞ በጣም ጥቂት ሰዎች የናጠጠ ሀብታም በመሆን እዚህ አውሮፓ ውስጥ ማንም ገዝቶ ሊነዳው የማይችል መኪና ሲነዱና በኑሮ ሲንደላቀቁ ይታያል። ይህም ማለት እንደተነገረንና አምነንም እንድንቀበል በተደረገው መሰረት ተግባራዊ የሆነው ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ጥገናዊ ለውጥ ባለፉት 28 ዐመታት ብሄራዊና ውስጣዊ ኃይል ያለው፣ እንዲሁም ደግሞ እያደገና እየተስፋፋ በመሄድ አገሪቱንና ህዝባችን በፀና መሰረት ላይ እንዲቆሙ የሚያደርጋቸው ኢኮኖሚ ለመዘርጋት እንዳልተቻለ ነው። ይህንን ሁኔታ ለመረዳት በመጀመሪያው ወቅት የተደረገውን ጥገናዊ ለውጥና የዕዳውን ዕድገትና፣ ለምንስ ከውጭ በሚመጣ ብድር የአገራችንን ኢኮኖሚ ማሳደግ እንደማይቻል ለማሳየት እወዳለሁ። በተለይም የዕዳው ዕድገትና የኢኮኖሚው መዛባትና ድህነት መስፋፋት ከዚህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊና ኢ-ብሄራዊ ከሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር በጥብቅ የተያያዘ እንደሆነ ለማረጋገጥ እሞክራለሁ።

የመጀመሪያው የገበያ ኢኮኖሚ የጥገና ለውጥ!

ወያኔ ስልጣን ከመያዙ በፊትም ሆነ  ስልጣን ከያዘ በኋላም የዓለም ኮሙኒቲውን፣ በተለይም ደግሞ የአሜሪካንን ዕርዳታና ድጋፍ ለማግኘት ከፈለገ የግዴታ ከዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) ከዓለም ባንክ ጋር መስራት እንዳለበት ነው። ሁለቱ ድርጅቶችም የሚያቅርቡለትን ቅድመ-ሁኔታ ከተቀበለና ተግባራዊ ማድረግ ሲችል ብቻ ነው ዕርዳታና ድጋፍ እንደሚሰጠው የተነገረው። እንደሚታወቀውና በምዕራቡ ዓለም፣ በተለይም በአሜሪካንና፣ ባጭሩ የዓለም ኮሙኒቲው ተብሎ በሚታወቀው አመለካከት የደርግ አገዛዝ እስከወደቀ ጊዜ ድረስ በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ „ የሶሻሊስት ወይም የዕዝ ኢኮኖሚ „ ነው የሚል ነበር። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በተለይም ከ1945 ዓ.ም በኋላ በአሜሪካን የበላይነት የሚመራውንና በእሱ አቀነባባሪነት እ.አ.አ በ1944 ዓ.ም በብሬተን ውድስ ላይ የፈለቀውንና እንደመመሪያ የሆነውን  የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚፃረር እንደመሆኑ መጠን መዋጋትና፣ በሌላ ለአሜሪካንና ለግብረ አበሮቿ በሚስማማውና የእነሱንም ጥቅም በሚያስጠብቀው „ተፈጥሮአዊ በሆነው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ“ የግዴታ መተካት ያስፈልጋል ተብሎ የተደረሰበት ስምምነት ነው። በተለይም ወደ ሶቭየት ህብረትና ወደ ግብረአበሮቿ እየተጠጋ የመጣው የደርግ አገዛዝ የአሜሪካንን „የጄኦ ፖለቲካ ስትራቴጂያዊ ጥቅምና“ አገሮችን የማከረባበት ወይም በዘለዓለማዊ ውዝግብ ውስጥ እንዲወድቁ የሚያደርገውን ሴራ የሚቀናቀን ስለሆነ በደርግ የሚመራው „የሶሻሊስቱ ስርዓት“ ወድቆ የአሜሪካኖች አምላኪ፣ ጀርመኖች ደግሞ የእነሱ ጓደኛ(friendly) ብለው በሚጠሩት መንግስት መተካት እንዳለበት አብዮቱ ከፈነዳ ጀምሮ አጥብቀው የሰሩበት ሁኔታ ነው። ይህ ግባቸው እንዲሳካላቸው  የተለያየ ስም ያነገቡ የግራም ሆነ የቀኝ አዝማሚያ ያላቸውን የውስጥ ኃይሎች በማስታጠቅና በገንዘብ በመደጎም በአገራችን ላይ ከፍተኛ ዘመቻ አድርገዋል፤ ጦርነትም ከፍተዋል። በዚህም መሰረት በተለይም እ.አ.አ ከ1980 ዓ.ም በፕሬዚደንት ሬገን አስተዳደርና በወይዘሮ ቴቸር አጋዝኘነት የዋሽንግተን ስምምነት(The Washington Consensus) የሚባለው፣ በተለይም የአፍሪካን አገሮችንና ሌሎችም የሶስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ አገሮች እንዲቀበሉት የተዘጋጀው የመዋቅር ማስተካከያ ፕሮግራም(Structural Adjustment Program) ወይም የኒዎ-ሊበራል አጀንዳ ተብሎ የሚጠራው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ህወሃት ስልጣን ላይ ሲወጣ እንደ ቅድመ-ሁኔታና የአገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መመሪያ ሆኖ ቀረበለት። ፖሊሲው ከፀደቀ በኋላ ቀደም ብሎ እ.አ.አ በ1980 ዓ.ም ጋና፣ ቀጥሎ ደግሞ ናይጄሪያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተራ በተራ ተግባራዊ የተደረገ ፖሊሲ ነው። ፖሊሲው ጋና ውስጥ ተግባራዊ ከተደረገ ከጥቂት ዐመታት በኋላ ኢኮኖሚዋ እየተሻሻለና ወደ ውስጥ የማምረት ኃይሏ እያደገና የስራ መስክ እየከፈተ የመጣ ሳይሆን ይባስ ብሎ የስራ-አጥ ቁጥር እየጨመረና፣ በዚያው መጠንም የውጭው ንግድ እየተዛባና ዕዳውም እያደገ እንደመጣ ኢምፔሪካል ጥናቶች ያረጋግጣሉ። ስለሆነም የጋና ኢኮኖሚ የባሰውኑ በካካኦ ምርት ላይ ብቻ እንዲመካ በማድረግ ይህ ምርት እየተስፋፋ ይመጣል። እ.አ.አ በ1989 ዓ.ም በሶቭየት ህብረት የሚመራው የሶሻሊስቱ ግንባር ሲፈራርስ ለአሜሪካንና ለግብረ አበሮቿ ይህን  የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግና አገሮችንም በእነሱ ቁጥጥር ስር በማምጣት በቀላሉ መበወዝ የሚቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደቻለ የጊዜው ሁኔታ ያረጋግጣል። በተለይም በፍራንሲስ ፉኩያማ የርዕዮተ-ዓለም ፍጻሜ ተብሎ የተደረሰው መጽሀፍ የሚያረጋግጠው የአሜሪካንን የበላይነት የአፀደቀ እንጂ የኋላ ኋላና ዛሬም እንደምናየው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሊበራል ዲሞክራሲን ተግባራዊ ያደረገና፣ በተለይም ኋላ-ቀሩ የሚባሉ አገሮችን ወደ ብልጽግና እንዲያመሩ ያደረገና፣ የካፒታሊዝምን ስልተ-ምርት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የረዳቸው ፖሊሲ አይደለም። በአንፃሩ ይህ የኒዎ-ሊበራል ፖሊሲ ኢንፎርማል ሴክተር በመባል የሚታወቀውን የተዘበራረቀ ኢኮኖሚ እንዲፈጠር በማድረግ ግልጽነት ያለው የገበያ ኢኮኖሚና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የሚመካ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ እንዲያድግና ህብረተሰቡን እንዲያስተሳስር የሚያስችል የኢኮኖሚ ስርዓት እንዳይገነባ ያገደና የሚያግድ ነው። ወደ አገራችን ተጨባጩ ሁኔታ ስንመጣ፣ ወያኔ የተቋም ማስተካከያ ወይም የኒዎ-ሊበራል ፖሊሲውን አሜን ብሎ ከተቀበለ በኋላ በዓለም የገንዘብ ድርጅቱ „ ፍልስፍና“ መሰረት „ለነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊነት የሚያመቹና ፍቱን መፍትሄም ሊያመጡ ይችላሉ“ የተባሉት ዝርዝር መሰረታዊ ነገሮች ተግባራዊ ይሆኗሉ። ይህንን ጉዳይ በተለያዩ ጊዜያት እየደጋገምኩ ባቀርብም በአብዛኛዎቹ ዘንድ ይህን ያህልም ግንዛቤ ውስጥ የገባና፣ ዛሬ አገራችን ለምትገኝበት ውድቀትና ለህዝባችን ድህነት ተጠያቂ ለመሆኑ በጭንቅላት ውስጥ የተቀረፀ ሃሳብ  ለመሆኑ እጠራጠራለሁ። የሁላችንም አስተሳሰብ ወያኔን በመጥላትና እሱን በማስወገድ ላይ ብቻ ያተኮረ ስለነበርና አሁንም ስለሆነ ከበስተጀርባው ሆኖ የአገራችንን የእኮኖሚ ፖሊሲ ማን እንደሚያወጣና ተግባራዊም እንዲሆን የሚገፋፋው የዓለም ኮሙኒቲው በሚለው ላይ ይህን ያህልም ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ አይደለም። በተለይም አሁን በቅርቡ በዶ/ር አክሎግ ቢራራ ዕዳን ወይም ብድርን አስመልክቶ በተለያዩ ድህረ-ገጾች ላይ የቀረበው ጽሁፍ፣  ጸሀፊው ወያኔ ስልጣንን ላይ ከወጣ ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲና ያመጣውን ጠንቅና፣ የዕዳው መቆለል የመዋቅር ማስተካከያ ፖሊሲው ተግባራዊ ከመሆን ጋር የተያያዘ መሆኑን አንዳችም ቦታ ላይ በፍጹም አያመለክትም። በእሱ አመለካከትና ዕምነት የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳለ ሲያምን፣ ይህ ዐይነቱ ዕድገት ምን ዐይነትና ብሄራዊ ባህርይ ይኑረው አይኑረው፣ በሰፊና በፀና መሰረት ላይ የተመረኮዘና ተከታታይነት ያለው ወይም የሌለው ኢኮኖሚ ዕድገት ለመሆኑ ለማሳየት አልጣረም። በተጨማሪም ለዛሬው በአገራችን ምድር ተንሰራፍቶ ለሚገኘው ድህነትና ያልተስተካከለ ዕድገት፣ እንዲሁም በብዙ ከተማዎችና መንደሮች የማዕከለኛው ዐይነት አኗኗር ዘዴ መስፈን ከዚህ ዐይነቱ ሳይንሳዊ መሰረት ከሌለውና ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ሳይሆን የዓለም ኮሙኒቲውን ለመጥቀምና በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥቂት የካፒታሊስት አገሮችን የባሰውኑ በሀብት ለማዳበር ከተነደፈው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር በጥብቅ የተያያዘ መሆኑን ለማሳየት ወይም ለማብራራት አልጣረም። ለማንኛውም በመዋቅር ማስተካከያው ቅድመ-ሁኔታ መሰረት፣ 1ኛ) የኢትዮጵያ ገንዘብ ከዶላር ጋር ሲወዳደር መቀነስ (devalue)  አለበት። በዓለም የገንዘብ ድርጅት ዕምነት መሰረት የገንዘቡ መቀነስ የጠቅላላውን ኢኮኖሚ ሁኔታ የሚያንፀንባርቅ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ወደ ውጭ የምትልከውን ምርት በቀላሉ ለመሽጥና ተወዳዳሪ በመሆን የውጭ ምንዛሬ በብዛት ታገኛለች። ይህ በራሱ ደግሞ የውጭ ንግድ ሚዛኑን ጤናማ ያደርገዋል ይለናል። 2ኛ)  በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ኩባንያዎችና የንግድ ዘርፎችን ወደ ግል ማዘዋወር። ይህ በራሱ ወደ ውስጥ የአገር ውስጥ ከበርቴ ተሳትፎን ከፍ ሲያደርገው፣ በዚያው መጠንም ውድድር ይጦፋል። ስለሆነም ኢኮኖሚው በማደግ የስራ መስክም ሊከፈት ይችላል። 3ኛ) ገበያውን በገበያ ህግ መሰረት፣ ማለትም በአቅራቢና በጠያቂ ህግ መሰረት የዕቃዎች ዋጋ እንዲደነገግ  ማድረግ፣ 4ኛ) ስለሆነም መንግስት እንደማህበራዊ በመሳሰሉና፣ አገልግሎቶችና ሌሎች ቁሳቁሶች ላይ የሚሰጠውን ድጎማ ማንሳት አለበት። ወደዚያ የሚፈሰው ገንዘብ ሲነሳ ገንዘቡ ምርታማ ለሆኑ ሀብታሞች ይለቀቃል። 5ኛ) የውጭው ንግድ ልቅ  መሆን አለበት። የውጭውን ንግድ ክፍት ወይም ሊበራላይዝ ማደረግ የውጭ ከበርቴዎችን ለመሳብና በአገራችን ምድር መዋዕለ-ነዋይ እንዲያፈሱ ያበረታታቸዋል። በዚህ መልክ ለብዙ መቶ ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል ይከፈታል ይሉናል። ስለሆነም እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ነገሮች ቀስ በቀስ ተግባራዊ ከተደረጉ-ተደርገዋልም- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያድጋል፤ ኢትዮጵያም የሰለጠነው ዓለም አካል ትሆናለች፤ ህዝባችንም በደስታ ይፈነድቃል፤ ድህነትም ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ በማክተም የታሪክ ትዝታ ሆኖ ይቀራል ይሉናል። ከዚህ ስንነሳ ባለፉት 28 ዓመታት ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ አልሆነም  የሚል ካለ በግልጽ ወጥቶ መከራከር ይችላል። ለማንኛውም ከላይ የተጠቀሱት የፖሊሲ ዝርዝሮች ተግባራዊ ከሆኑ በኋላ እንደታቀደውና እንደታለመው የአገራችን ኢኮኖሚ አደገ ወይ? ህዝባችንም ከድህነት ተላቀቀ ወይ? አብዛኛውስ ህዝብ የስራ ዕድል አገኘ ወይ? የውጭውስ ንግድ ጤናማ ሆነ ወይ? ዕዳችንም እየቀነሰ ወይም እየጨመረ መጣ ወይ? እነዚህን ነገሮች ታች በዝርዝርዝር እንመልከት።
Full Website