hidaseethiopia@yahoo.com
hidaseethiopiaa@gmail.com

ውህደት ማለት የስውር ግልፅ አሀዳዊነት ማለት እንደሆነ ተረጋገጠ

(በማር የተቀባ ዕሬት)

ታዲያ ይህ ፓርቲ የብልፅግና ወይስ የብልግና ፓርቲ?

ህዳሴ ኢትዮጵያ

ህዳር 11፣ 2012 ዓ.ም.

በኢህአዴግ ውህደት ማለት እያንዳንዱ የኢህአዴግ አባል ድርጅት እና አጋር ድርጅቶች የነበራቸውን ድርጅታዊ ህልዉና በማክሰም በአንድ ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ የሁሉም ክልሎች እንደየ ድርሻቸው መቀመጫ ያላቸው ስራአስፈፃሚ የያዘ አንድ የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ ስር መደራጀት ማለት ነው፡፡ በዚህ ጠቅላይ ፓርቲ ሲደራጅ የየራሱ ድርጅት ህልውና አብቅቶ እንደ ግለሰብ የየብሄሩ ድርሻ በመቶኛ ተሰልቶ ወንበር ይሰጠው እና በዛው ልክ ተሳትፎ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡

ከዚህ አወቃቀር መረዳት የሚቻለው፣ አንድን ክልል ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የመወሰን መብቱ ለብልፅግና ፓርቲ አስረክቧል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱ በአገር ደረጃ አንድ ብልፅግና ፓርቲ ያለ ሲሆን የአንድ ክልል ውሳኔ ያ ብልፅግና ፓርቲ ካልተቀበለው ውድቅ ይሆናል፡፡

ለምሳሌ አሁን ኢህአዴግ እያሞገሰው ያለው ውህደት ተሳክቶ የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ እውን ከሆነ፤ 3ቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እና 5ቱ አጋር ድርጅቶች ህልውናቸው ያበቃል በምትኩ አንድ ፓርቲ ወይም የብልፅግና ፓርቲ ይተካል፡፡ በያንዳንዱ ክልል የሚኖረው ፓርቲ የዚህ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ በምርጫ አሸንፎ ስልጣን ከያዘ፣ ክልሎች ህገመንግስቱ የሰጣቸው ስልጣንና ሀላፊነት ቢኖርም ይህ ፓርቲ አንድ ዉሁድ ፓርቲ እንደ በመሆኑ መጠን ህገመንግስቱ ለክልሎች የሰጠውን ስልጣንና ሓለፈነ ተቀብሎ የሚተገብረው ይህ ፓርቲ ነው፡፡ የዚህ ፓርቲ አወቃቀር ደግሞ ኦሮሚያ 34% ኣማራ 28%፣ ደቡብ 12%፣ እያለ እንደየ ክልሎች ህዝብ ብዛት ነው፡፡ ስለዚህ የኦሮሚያ ጉዳይ የሚወስነው ኦሮሞ ሳይሆን በኦሮሚያ ያለው በምርጫ ያሸነፈው የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ነው፡፡ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በአማራ፣ በደቡብም የየክልላቸው ጉዳይ የሚወስነው የየክልሉ ኖዋሪ ሳይሆን በየክልላቸው የሚገኝ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ነው፡፡ በብልፅግና ፓርቲም የሚወሰነው በተሰጣቸው ወንበር ብዛት ነው፡፡

ስለዚህ እያንዳንዱ ክልል በህገመንግስቱ መሰረት የተሰጠው ስልጣንና ሀላፊነት በየክልሉ የሚተገብር እና የሚወስን ቢሆንም፤ በተጨማሪ በያንዳንዱ ክልል በብልፅግና ፓርቲ ስም የሚመደበው አመራር የየክልሉ ተወላጅ እንደሚሆኑ ታሳቢ ቢደረግም፤ የአንድን ክልል መሰረታዊ የመብት ጥያቄ ተነስቶ ምናልባት የብልፅግና ፓርቲ የማይቀበለው ከሆነ ወይም በመብቱ ዙርያ አከራካሪና በመሆኑ የበላይ አካል መወሰን ያለበት ጉዳይ ሆኖ ሲገኝ ጉዳዩ ወደ ፓርቲው ከፍተኛ ኣካል ቀርቦ በዴሞክራሲያዊ ድምፅ ብልጫ እንዲወስን ይደረጋል፡፡ በዚህ ጊዜ ጥያቄ ያነሳው ክልል ውስጥ የሚገኝ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ አመራር ባያምንበትም በዋናው ብልፅግና ፓርቲ ኣመራር ድምፅ ውሳኔ ስለሚሸነፍ ተግባራዊ እንዲያደርግ ይገደዳል፡፡ ስለዚ የክልሉ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ሳያገኝ ይቀራል ማለት ነው፡፡ በሌላ ኣባባል መዋሀድ ማለት የራስን ህገመንግስታዊ መብት አሳልፎ ለሌላ መስጠት ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ የራስን ጉዳይ በብልፅግና ፓርቲ ስም ሌሎች ገብተው እንዲወስኑ ዕድል መስጠት ማለት ነው፡፡

ስለዚ የአፋር ፖለቲካ ድርጅት ተዋሀደ ማለት የአፋር ህዝብ መብት ለብልፅግና ፓርቲ አሳልፎ ሰጠ ማለት ነው፡፡ የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል፣ የሶማሌ፣ የሀረሬ፣ የደቡብ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ተዋሀዱ ማለት የየክልላቸው ህዝብ መብት ኣሳልፈው ለብልፅግና ፓርቲ ሰጡ ማለት ነው፡፡ ብልፅግና ፓርቲ ማለት ደግሞ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ፓርቲ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች በየራሳቸው ጉዳይ ሳይሆን በሁሉም ጉዳይ ገብተው ይፈተፍታሉ፣ ይወስናሉ ማለት ነው፡፡
Full Website