ምህላ የሚደረገው ትግራይና ህወሓት ለምን አንሰራሩ ይሆን?

ኻልኣዩ ኣብርሃ 04-14-21

በኢትዮጵያ ፈጣሪያችን እጅግ ተቸግሯል፣ ልመናው ቅጥ አጥቷል። ምንም በደል ያልፈፀመ ሰላማዊ ህዝብ በእሸን ጦር በደቦ ሲዘመትበት፣ ሴቶች በሺዎች ሲደፈሩ፣ ግፉ ሞልቶ ሲፈሰም የትግራይን ደም በአማራ ሴት ደፋሪ ደም ለማጥራት ሲታሰብ፣ ጥንታዊ ገዳማት ሲፈርሱ ሲቃጠሉ መነኮሳት ሲገደሉና ሲዋረዱ፣ ብረት ያላነገቡ ንፁሃን ለአምስት ወራት በየቀኑ በገፍ ሲጨፈጨፉ፣ የህዝብ የኢኮኖሚ መሰረት ሲወድምና ሲዘረፍ፣ ህዝብ ለከፋ ረሃብ ሲጋለጥ፣ የጤና መሰረተ ልማቱ ጭራሹን ወድሞ ቀላል መድሃኒትም እያጣ ሲያልቅ፣ ህገመንግስትን ዋጋ ባሳጣ በመንግስት የተፈቀደ የግዛት ይገባኛል ወረራ በመቶ ሺዎች ህዝብ ሲፈናቀል፣ የትግራይ ህዝብ ለዚህ ውድመት የዳረገውን ወረራ "ህግ ማስከበር" የሚል የክርስትና ስም ተሰጥቶት በአብያተ ክርስትያናት ምርቃትና ድጋፍ መሸኘቱ እየታወቀ ምህላው አሁን የት ተገኘ? ለምንስ? ለአምላክ ምህላ የሚቀርበው በህዝብ ላይ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት እልቂት ሲደርስ ነው እንጂ አብያተ ክርስትያናቱ ራሳቸው መርቀውና ንሴብሆ ብለው በላኩት ጦር በክርስትያኑ ህዝብና በአብያተ ክርስትያናት ላይ ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈፀም ድምፅ አልባ ሆኖ አድፍጦ ከተቆየ በኋላ አይደለም። የትግራይን ህዝብ ያሸነፉ ሲመስላቸው ዘፈንና ወረብ፣ የተሸነፉ ሲመስላቸው ምህላ ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? አምላክ እኮ የተበዳይን እንጂ የበዳይን አቤቱታ አይሰማም። በርግጥ ቤተክርስትያን ተሂዶ "እከሌን ድብን ካደረግክልኝ" በሬ እየጎተትኩ አመጣልሃለሁ" እያሉ በመሳል አምላክን ማስቸገር የተለመደ ሃጥያት ነው። ልብሰ ተክህኖ ተለብሶ ቅዱስ ቆብ ተደፍቶ ስንት ተንኮል እንደሚሰራ ማን አጣው? ሃይማኖትን ለፓለቲካ ጠቀሜታ እያዋሉ ከፓርቲዎች ያላነሰ ሽኩቻ ውስጥ የሚገቡ አብያተ ክርስትያናቱን እንዳጎደፉና ምእመናንን መንገድ እንዳሳቱስ የማያውቅ ይኖራል? አንተም ተው አንተም ተው እንደማለትና አባታዊ ስራን እንደመስራት አንዱን ወገን ጭራቅ ሌላውን ወገን መላክ አድርገው እየሳሉ የሚያፋጁና ወገን ለይተው በአለም አደባባይ ላይ ሰልፍ የሚወጡ ሁሉ አሁን ደርሰው አምላክን በምህላ የሚያስጨንቁት ግፉ አንሷልና እንጨምር ፍቀድልን ነው? ነገሩ ግልፅ ነው፣ ይህን ያህል መላምትና ግምት መደርደር አያስፈልግም። የትግራይ ህዝብ ጭፍጨፋውን ተቋቁሞ መልሶ በማንሰራራቱና ህወሓትም ጠፋች በነነች ተብላ ከጳጳስና ፓስተር ጀምሮ እስከተራው አማኝ ድረስ ሳቅና ፌሽታ ሲጋሩ ቆይተው ወታደራዊ ድሎቿን ሲሰሙ ድንጋጤና ሽብራቸውን ለአምላክ ለማጋራት ቆርጠው ተነስተዋል። በመሰረቱ የአብያተ ክርስትያናት መሪዎችና የክርስትና ቆዳ የለበሱ የማህበረ ቅዱሳን ፓለቲከኞች፣ የአምላክን ቃል መጫወቻ አድርገውት ተውኔት የሚሰሩበት ፓስተሮች ማየትና መስማት የተሳናቸው ወራሪውን ጦር መርቀው ከሸኙ በኋላ ነው። አይናቸውና ጀሯቸው የተደፈነውም የላኩት ወራሪ በሚፈፅመው ግፍ የህዝብ ዋይታ እንዳይሰሙ ነው። ያውቁታል! እንዲህ ያለ መጠነ ሰፊ ወረራ ህዝብና ኑሮውን ሳያወድም እንደማይቀር ያውቁታል። ብቻ ህዝቡም ይዳከም ከተቻለም ይጥፋ ህወሓትንም ነፍስ እንዳትዘራ አድርጎ መምታት ነበር ዋናው ግብ። ህያው አምላክ ከመንበሩ አለና በነዚህ የሃይማኖት ቆዳ በለበሱት ሃጥአን ላይ መአት ላከባቸው። መአቱ ምን እንደሆነ ግልፅ ነው። በትግራይ ህዝብ ላይ የተፈፀመውና አሁንም የቀጠለው ግፍ አምላክ በውጪም በውስጥም በሚኖሩ የትግራይ ልጆች መንፈስ ውስጥ አድሮ ጥንካሬ ሰጣቸውና ተአምር እየሰሩ ነው። ይቺ "ሰሜን ኢትዮጵያ" በሚል ጨርቅ ታፍና አለም ያላወቃት ከአለም ስልጣኔዎች አንዷ የሆነችው ትግራይ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ የአለም የዜና ርእስ ከሆነች ወራት አልፈዋል። የራሱ ህዝብ በኮሮና እያለቀበትም ቢሆን አለም ለትግራይ የሰጣት ትኩረት የአምላክ እጅ ያለበት ለመሆኑ መጠራጠር የለብንም። ለዳዊት ጉልበትን ሰጥቶ ጎልያድን የጣለበትስ ከትግራዩ ህዝብ ሁኔታ ጋር አይመሳሰልምን? አምላክ የተጎዳውን ህዝብ በሚጠግንበት ሰአት ምህላ እየተጠራ ያለው "ህዝብን የማዳን ስራህን ተውውና የኛን የግፍ በትር አወፍርልን" ተብሎ ነው? ከወረራው በፊት "ለምነን ነበር" ለማለትና ለታቀደው የማይቀር ወረራ ማህበራዊ ድጋፍ ለማስገኘት የሃይማኖት መሪዎች ነን ያሉ ወደ መቐለ ሄደው ነበር። አጥቂውንና ህግ አፍራሹን ትተው ወደ ተጠቂውና ህግ አክባሪው ነበር "ተው" ለማለት የሄዱት። ይህ በሃይማኖት ታሪክ እንግዳ ድርጊት ነው። የትግራይ ህዝብ መንገድ አልዘጋ፣ የትግራይ ህዝብ ሌላውን እወራለሁ ብሎ አላስፈራራ፣ ወታደራዊ ትርኢቱም "እንዳትመጡብኝ" የሚል መልእክት ያዘለ እንጂ አዲስ አበባ ድረስ ልመጣባችሁ ነው የሚል መንፈስ አልነበረውም። የትግራይ ህዝብና መሪዎችስ እጃቸውን ሰብራ ካባረረቻቸው ኢትዮጵያ ምን አላቸው? እንኳንና በጉልበት ገፍተው አዲስ አበባ ደርሰው ኢትዮጵያን ሊያስተዳድሩ ቀርቶ አርባ ታቦት ተሸክማ ማሩኝ አስተዳድሩኝ ብትላቸውም የሚሞክሩት አይደለም። የትግራይ ህዝብና መሪዎች ሌላ ያዝረከረከው ቆሻሻን አፅድተው ሲያበቁ የሚባረሩ አይደሉም። ደርግ ያጋጃትን አገር አፀዱ አስዋቡ የጨለማ ዘመን የቀን ጅቦች ተባሉ፣ በጨለማ ዘመን ቀን ከየት እንደመጣ ባይታወቅም። አስተካክለው የሰጡትን የሚያበላሽና መልሳችሁ አስተካክሉልኝ እንደሚል ስርአት የለሽ ህፃን ልጅ ደርግ ተመልሶ መጥቶ የባሰ ያበላሻትን አገር  የትግራይ ህዝብና መሪዎቹ ለማስተካከል የሚገደዱት በሞራል ነው በውለታ? የትግራይ ህዝብና የመሪዎቹ ማንሰራራትና  ተከታታይ ድል በ"አጥፍተናቸዋል" ራስ ማታለል የማይመለስ መሆኑ ሲታይ ወደ ድንጋጤ አምርቶ መፍትሄው ምህላ ሆኗል:-"ሞቷል አብቅቶለታል ያልነው የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ አንሰራርተዋልና እባክህ አምላክ ሆይ ከነሱ የበቀል በትር ጠብቀን"! የትግራይ ህዝብና መሪዎቹ እየታገሉ ያሉት ራሳቸውን ከወራሪ ነፃ አውጥተው እውቀታቸውና ያካበቱት ልምዳቸው በራሳቸው አገር ግንባታ ለማዋል እንጂ እንደወራሪዉ ሃይል የበቀል ኋላቀር ባህል የላቸውም። ልዩነቱ ግልፅ ነው፣ በስልጣኔና በኋላ ቀርነት መካከል ነው። ጀግና ነህ የተባለው ወራሪ ጦር ንፁሃን ወጣቶችን እየረሸነ ገደል ይከታል፣ የቀን ጅብና ሰይጣን የተባለው ሰራዊት "ጡት ያልጠገቡ ህፃናት ጦር ሜዳ ላይ ወድቀው ሲያይ ያዝናል ያማርራል። ኋላቀሩ ወራሪ ሲቢል ሴቶችን ሲደፍሩና ሲያንገላቱ ስልጡኑ ሃይል ሴት ምርኮኞችን ይንከባከባል። "የኢትዮጵያ ህዝብ ለመግዛትም በሱ ለመገዛትም አይመችም" ላሉት ቀደምት አባቶች የትግራይ ህዝብ ጀሮውን ለግሶ ቢሆን ኖሮ ስድስት ኪሎ በአንበሳ እንደተበላው አንበሳ ቀላቢ አይሆንም ነበር። እስከ ምህላ የሚያደርስ ጭንቀት አያስፈልግም፣ ህወሓት መቐለ እንጂ አራት ኪሎ ወደተባለ የወራሪዎች ጎሬ አትመለስም። የወራሪዎችና ክርስትያናዊ አሟሟቂዎቻቸው ትግራይን አጥፍተው ከኤሪትርያ ጋር በመዋሃድ የ"ታላቋ" ኢትዮጵያ ህልማቸውን እውን ሊያደርጉ ነበር የተማመኑት። ይህ የገነቡት ካብ ድንገት ሲናድባቸው "ትግራይ ነፃ መንግስት ከሆነች ኢትዮጵያ ትፈርሳለች" የሚለው ዘፈን ተጀምሯል። የምህላውም አንዱ ምክንያት ይኸው "አተርፍ ባይ አጉዳይነት" ነው። ከወረራው በፊት ትግራይ ብትወረር የኢትዮጵያ የመጨረሻዋ መጀመሪያ ይሆናል እየተባለ ባመዛኙ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ምሁራን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢፅፉም ቢናገሩም መሳቂያና መሳለቂያ ሆነው እንደነበር አመት ያልሞላው ትውስታችን ነው። አንዴ "አትፎክሩ ለኢትዮጵያ ኢሚንት ናችሁ" ይባላል። ሌላ ጊዜ ደግሞ "ኢትዮጵያ ሰላም የምትሆነው ትግራይ ስትዳከም ወይንም ስትጠፋ ነው" በሚል እርግጠኝነት ልባቸው ተደፍኖ አቅማቸውን በሙሉ ይህን ለመተግበር ብቻ ያዋሉ እልፍ አእላፍ ናቸው። እንደ ነጠላ ሰረዝ ህወሓትን የሚያወግዙ ቃላት በየአረፍተነገሩ መሰንቀር ልማድ የሆነባቸው ጥላቻ ብቻ ሳይሆን ፍርሃትና ቅናትም እብረው ጭንቅላታቸው ውስጥ ተበርዘል። ሳሩም ቅጠሉም ህወሓት የሚመስላቸውና ኮሽ ባለቁጥር "ህወሓት መጣ" እያሉ የሚባንኑ እንዴት አድርገው ነው አገርን አረጋግተው የሚያስተዳድሩት? በአንድ በኩል ህወሓትን ለማጥፋት እየታገሉ በሌላ በኩል ደግሞ በህወሓት ዘመን የነበረውና ግን በብልፅግና ያጡትን ሁሉ እያነሱ ትንፋሽ  እስኪያጥራቸው ይተርካሉ። ህወሓት አንሰራራች ሲሰሙም ወደ ምህላ ይገባሉ። ይህ በፀበል የማይለቅ ጋኔል ነው! አጥብቆ የተጠጋውም ከሃይማኖተኞቹ ዘንድ ነው። ወረራው ተጀምሮ የ"ጁንታው" ዋና ከተማ ተያዘች ከተባለ በኋላ ታውረውና ደንቁረው የነበሩት አይናቸው የበራውና ጆሯቸው የተከፈተው በህልምም በውንም ያልጠበቁት አስደንጋጭ የትግራይ ህዝብና መሪዎች ማንሰሬቱት መልሶ ማጥቃት የመጀመሩ ዜና ጭንቅላታቸውን ሲመታቸው ነው። ስለትግራይ ህዝብ ደግነት ተወራ፣ እንርዳው እንደግፈው እናቋቁመው የሚሉ ጫጫታዎች መሰማት ጀመሩ። የፀረ ትግራይ ዘመቻ የቃላት "ደጅ" አዝማቹ ታማኝ በየነ "የትግራይ ህዝብ የኔም ነው፣ በሞኖፓል አትያዙ" አለ! ወይ ፍቅር?! ስድስት ሚልዮን የትግራይ ህዝብ ለዚህ የኪነት መድረክ አስተዋዋቂ ስድስት ሚልዮን ህፃናት መስለውት ይሆን? በፊት ትግራይን እያወገዘ ብር ሲያገኝ አሁን ደግሞ ትግራይን ለመርዳት ብር ሊያገኝ። የኢሳቶቹ ይሻሉ ይሆናል በድሮ የመረረ ጥላቻ አቋማቸው እንደ እንጨት ደርቀው የቀሩ። ከመዘላበድ እሱ ይሻላል። የሚነዳቸው የሚያጋብሱት ብር ብቻ ሳይሆን የትግራይ ጥላቻ ከደማቸው ውስጥ ስለገባም ጭምር ነው። የኢትዮ360 ፈላስፎች ደግሞ ትግራይን በሚመለከት "ብለን ነበር፣ ህወሓትም የተሻለ ነበር" እያሉ ነው። "ወረራው አብቅቷል ወልቃይትና ራያ በእማራ እጅ ገብቷል" ሲባል ሶስቱም ሆነው የሳቁት ረዥም ሳቅ ግን ከማንም አእምሮ ሊጠፋ አይችልም። አለም የትግራይን የዘር ፍጅት አወገዘ፣ ኢትዮጵያም በሃላፊነት እንደምትጠየቅ ሲነገር የሃይማኖት ቆብ የለበሱት "ግፋ በለው" ባዮች "እርዳታ" (ስድብ) ይዘው መቐለ ገቡ። ህገመንግስት ፈርሶ በ"ህግ ማስከበር" ስም ሉአላዊ ክልል በውስጥና በውጪ ሃይል ሲወረርና ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈፀም "ተዉ ብለናቸው ነበር፣ ጠግበው ነው" እያሉ መሃል አገር ተኝተው ለወራት በቆዩበት ጊዜ የትግራይ ህዝብ ግን ደመኞቹ ጠላቶቹ እነማን እንደሆኑ የመገንዘብ እድል አግኝቷል። ስቃዩ ትምህርት ሆኖታል፣ የዋህነቱን በሞት በመደፈር በመዘረፍ ሳሙና አጥቦ ጭንቅላቱን አፅድቷል። "ጌታ ሆይ! የማላውቃቸውን ጠላቶቼን አሳውቀኝ" አይደል የሚባለው። የትግራይ ጠላቶች መሽገው የነበሩት ለካ ከማይነቃበት የሃይማኖት ግምብ ውስጥ ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ የመቐለ ህዝብ እንደ ገመቱት የዋህና እየሞተ ይቅር የሚል ሆኖ አላገኙትም። አሁንም የህዝቡን ስሜት የሚጎዳ መግለጫ ከማውጣት አልተቆጠቡም። ኬኔዲ በወጣትነቱ የባህር ሃይል መኮንን ሆኖ የጀግና ሜዳልያ የተሸለመበትን ሁኔታ እንዲናገር ሲጠየቅ "ጀግና የሆንኩት ተገድጄ ነው" አለ። ለምን ሲባል "ጀልባየን ስላሰስጠሙብኝ ዋኝቼ ህይወቴን አዳንኩ" ብሎ መለሰ። ይህ ቀላል ንግግር አይደለም። በቅድሚያ ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ከተመታው ጀልባ ይልቅ የዜጋ ህይወት ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ሜዳሊያ በመስጠት የሚያረጋግጥ አገርና ህዝብ እንዳለ ነው። አክሱም ላይ የተገደለው 300 ሳይሆን 100 ነው እያሉ ወንጀልን በቁጥር ማነስና መብዛት የሚወስኑ፣ "እንኳን በወንድ ተደፈሩ፣  በሳንጃ ቢሆን ወንጀል ይሆን ነበር" ከሚባልበት አገር መፈጠር የምድር ኩነኔ ነው። የባሰው ደግሞ እንዲህ ሲባል ስሜቱ የማይነካ ቄስና ጳጳስ ከሞላበት አገር! ግፍ እያየ ምቾት እንዳይቀርበት አፉን የሚዘጋ የሃይማኖት መሪ በበዛበት አገር! ተገድጄ ነው ጀግና የሆንኩት ያለው ኬኔዲ ምሳሌነቱ ለትግራይ ህዝብ ነው። የትግራይ ህዝብ ለምእት አመታት ወራሪዎችን ያስለመዳቸው አንድ ክፉ ነገር አለ:- አስርበው ካስፈጁት በኋላ ይቅር ብሎ ይረሳል፣ ወረው ከጨፈጭፉት በኋላ ምላሳቸውን ሲያለዝቡለት ተለል ብሎ ይተዋል። ሲተውም ለቀጣይ ጥንቃቄ የሚያስቀረው እርሾ የለውም። ሁለተኛ እንዳይጋለጥ ሆኖም ራሱን አያስተካክልም። ይባስ ብሎ የወራሪዎቹ ፍቅር ይፀናበታል። ወራሪዎቹን እያጠናከረ ራሱን ያዳክማል፣ ለሌላ ወረራና የከፋ ጉዳትም ራሱን ያጋልጣል። የወራሪዎቹ አላማ እንደ መሪዎቹ የሚለያይ ሳይሆን ለዘመናት አንድ አላማ ብቻ እንደሆነ አይዞርለትም። ህዝበ ክርስትያን ወንድሙን ለማጥፋት አያስብም እያለ ሞት የተጀመረበትን የቃኤልና አቤልን ታሪክ ይረሳል። ከወረራው በፊት ማለት የወረራ ዛቻ ገኖ ከመውጣቱ በፊት የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱን ማጣት ሞት መስሎ ይታየው ነበር። አንዳንዶች እንደሚዘላብዱት ቢገነጠል የሚበላው አጣለሁ ብሎ አይደለም። የትግራይ ህዝብ አስተሳሰቡ በሆዱ እንደማይቃኝ ሁሉም ያውቃል። ኢትዮጵያዊነትን ማጣት የፈራው የባለቤትነት ስሜት ስለነበረው ነው። የሚገርመው ነገር የኢትዮጵያ ጠላቶች፣ አገሪቱን ለመበታተን ቆርጠው የተነሱ ሲባሉ የነበሩት ህወሓቶችም አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያዊነትን በበጎ አይን የሚመለከቱ ነበሩ። ከዛ በፊት ኬኔዲ በጦርነቱ ብዙ ችግር ደርሶበት ኖሮ ሊሆን ይችላል ያንን ግን አልፎ ቀጥሏል። ጀልባውን ሲያሰምጡበት ግን ህልውናውን ሊያጠፉ እንዳለሙ ገባው። ስለዚህ እንደምንም ብሎ የነሱ አላማ እንዳይሳካ ጥረት ማድረግ ነበረበት፣ ዋኝቶም ወጣ። ከዛ ቀጥለው ባሉት ዘመቻዎች ኬኔዲ ጀልባው እንዳይመታበት ተጠንቅቆ ከኢላማ ማራቅ አለበት። ይህ ምሳሌ ወደ ትግራይ ሲመነዘር እንደሚከተለው ይገለፃል:- ትግራይ በሚኒሊክ፣ በሃይለስላሴ፣ በደርግ ወረራ ተፈፅሞባት ብዙ ግፍ አስተናግዳለች። የአሁኑ ወረራ ከበፊቶቹ የሚለየው በህልውናዋ ላይ የመጣ መሆኑ ነው። ኢኮኖሚዋንና መሰረተ ልማቷን በማውደም "መርከቧን" አስምጠውባታል ከጦር ባህር ለመውጣት የሞት ሽረት ዋና እያደረገች ነው፣ እየተሳካላትም ነው። "የፍፃሜ ጦርነት ነው.." የሚል የኮሚዩኒስቶች መዝሙር ነበር። የኬኔዲ የአንድ ግለሰብ ህይወት ነው። የትግራይ ህዝብ ህልውና ግን የስድስት ሚልዩን ህዝብ ብቻ ሳይሆን የአኩሪ ጥንታዊ ስልጣኔ ታሪክ ህይወት የሚመለከት ነው። ይቅርታ ለህይወት እንጂ ለሞት አይደለም። ክርስቶስ ብቻ ነው  እየገደሉት "የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" ያለው። እሱም ቢሆን የማይሞት አምላክ በመሆኑ እንጂ ለሰው ፍጡር የሚበጅ አነጋገር አይደለም። "ጠላትህን እንደራስህ ውደድ" የሚለው ትእዛዝ ሌላ አጋች ቃል አለው:- "አትግደል" የሚል። ሁለቱም ሲገጣጠሙ የሚሰጡት ትርጉም እንዲህ ነው:- "ጠላትህን ውደድ ግን የሚገድልህን አይደለም"። ኬኔዲ ጀልባው ሁለተኛ እንዳይመታበትና ሰጥሞ እንዳይሞት (ሁለተኛ ጊዜ መትረፍ ላይሳካለት ስለሚችል) ጀልባውን ከገዳዮቹ ኢላማ አርቆ ወይንም ሰውሮ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። ትግራይ ሊያጠፏት ከቆረጡ ሃይሎች ራሷን ማሸሽ ይኖርባታል። ነፃ ትግራይ አሁን ካለችበት የተሻለ እንጂ የከፋ ህይወት አትኖርም። የከፋም ቢሆን ከመሞት ድህነት ይመረጣል። በትግራይ ቀልድ አዋቂ የነበሩት ሰው የህወሓት ጦር በ1981ዓም መቐለን ተቆጣጥሮ ሲያስተዳድር ሰላም ሰፈነና ግን በቂ አቅርቦት አልነበረም። እኒህ ቀልድ አዋቂ ለታጋዮች ሰላምታ ሲያቀርቡ "እንዴት ዋላችሁ እነ ሰላምና ድህነት" ብለው ቀለዱባቸው ይባላል። ሰውየው ሁለት ወንድ ልጆቻቸው በደርግ ካድሬዎች ታስረውባቸው ስለነበረ ከአቅርቦቱ ይልቅ የተገኘውን በልቶ በሰላም ለማደሩ ምክንትያት ለሆኑት ታጋዮች ምስጋና በቀልድ ለውሰው ማቅረባቸው ነበር። ትግራይ ከአጋም የተጠጋች ቁልቋል ሆና ስትደማ የምትኖርበት ምክንያት የለም። ስለዚህ ትግራይ መርጣው ሳይሆን ተገዳ የማይቀለበስ ውሳኔ ትወስናለች። የተወጋችው ብቻ ሳትሆን የወጋትም መርሳት የለበትም፣ ውሳኔዋን በፀጋ እንዲውጥ! ትግራይ የራሷን መንግስት ስትመሰርት ኢትዮጵያ እንድትበታተን በመመኘት አይደለም። የተበታተነ ጎረቤት ለትግራይም እንደማይበጅ የታወቀ ነው። ይህ ማለት ግን ትግራይ ኢትዮጵያ እንዳትበታተን ብላ ራሷን ለመስዋእትነት ማቅረብ አይጠበቅባትም። ግድያ የሞከረብህን ባትገድለውም ልታድነው ግን አትሞክርም። ትግራይ በአፄ ዮሃንስ ከጀርባዋ እየተወጋች ኢትዮጵያን ታድጋለች፣ ሃውልት የተስራላቸው ግን ከኋላ ወጊዎቹ ናቸው። ደርግ በግትርነት አንዲት ኢትዮጵያ ወይንም ሞት ብሎ ነፃ አውጪ ያራባባት ኢትዮጵያ በመለስ የምትመራው ህወሓት ነበረች 80 ቁርጥራጭ ከመሆን ያተረፈቻት። "ራሳችሁን ሳይሆን እኛን መስላችሁ ኑሩ" የሚሉት አሃዳዊያን በመንግስቱ ያልተሳካውን አሁን ተግባራዊ ለማድረግ ይታገላሉ። በፌደራሊዝም የዳነችውን አገር ፌደራሊዝም እየበተናት ነው እያሉ መአት በማውራት ሊበትኗት እየታገሉ ነው። የትግራይ ተወላጅ መሪዎች ኢትዮጵያ የብዙሃን አገር የመሆንዋን የመረረ  ሃቅ ተቀብላ አቻችላ እንድትኖር ብዙ ጥረት አድርገዋል። ከምስጋናው ስድቡ ቀደመ እንጂ። አሁን ወደ ሳምንት ሙሉ እግዞታ የሚያደርስ የአምላክ ምህረት ብቻ የሚፈታው የኢትዮጵያ ችግር ምንድነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ፓለቲከኞች በስልጣን ጥም ጎትተው ያመጡት ችግር ነው። መጀመሪያ ተረጋግቶ አገር ያረጋጋና ልማትን ያመጣ መንግስትን በቤተመንግስት ሴራ ተወገደ። የመንግስት ለውጥም ካስፈለገ በህዝብ ምርጫ መተካት እንጂ አገር የሚያናጋ አንድ መንግስትን በዘር ነጥሎ የሚያጠቃ እዛው በዛው የሆነ ለውጥ አይደለም። የመንግስት አንድ ነጠላ አካል ለብቻው በቀሪዎቹ አካላት ሲገለበጥ ይህ አይነት ህገወጥነት ህገወጥነትን እንጂ ህጋዊነትን አያራባም። 80 ብሄር ብሄረሰብ ለ30 አመት መብቱን አጣጥሞ በሰላም ከኖረ በኋላ አድፍጠው የቆዮ የድሮ ስርአት ናፋቂዎች ስልጣኑን ጨብጠው እንደድሮ በአንድ መስኮት ትገለገላለህ ሲሉት የማያምፅ ህዝብ አለ? አብያተ ክርስትያናቱ እነዚህን ፌደራሊዝምን እያጥላሉ ህገ መንግስቱን ለመቀየር የሚታገሉትን አደብ ግዙ ብለው እንደመገሰፅ ያለቀለትን ስርአት ለመመለስ የሚታገሉትን በጥባጮች ዱላ ማቀበል ሙያ ብለው ይዘውታል። ኢትዮጵያ ሳትፈርስ ፌደራሊዝም ስለማይፈርስ፣ ፌደራሊዝም እንዲፈርስ የሚፈልጉትም የአንድ ብሄር ብቻ ፓለቲከኞች በመሆናቸው፣ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንም በነዚህ እጅ ውስጥ በመሆኗ ጥሩ ዳኛ ገላጋይ መሆን አልቻለችም። ቤተክርስትያኗ ራሷ በአንድ ብሄር ፓለቲካ ተሰንጋ እያለች እንዴት አድርጋ ነው አብዛሃዎቹ የሚቀበሉትን ፌደራሊዝምን መደገፍ የምትችለው? አገሪቱን ከመበተን ማዳን ቀላል ነው። በታኞቹ ራሳቸው ስለብተና ቀድመው እየጮሁ ያሉት ናቸው። እነሱን ስራት ማስያዝ ነው፣ አገር ከተፈለገች። በፌደራሊዝም ክሮች የተሰፋች መልከ ብዙ አገር ፋብሪካ ወስደው አቅልጠው አንድ ወጥ ጨርቅ ሊያደርጓት ነው የሚታገሉት። ይህ የማይሆን ቅዠት ነው። ወደ እግዚአብሄር ምህላ ከማድረግ በፊት መጀመሪያ በሰው አቅም ሊሰራ የሚቻለውና አብዛኛውን ችግር ሊፈታ የሚችለውን ስራ መቼ ተሞከረና። ምርጫ ተላለፈ፣ ያልተመረጠ መንግስት በጉልበት ቀጠለ! የአገሪቱ ህዝብ ከዚህ የሚማረው ህግ አክባሪነትን ነው ህገ ወጥነትን? የባእድ አገርን ድንበር ጠብቁልኝ ብሎ ሌላ የባእድ ጦር አስተባብሮ በህግ የተከለከለ የአንድ ክልል ሌላውን የአለውረርን ጥሶ ሰላማዊ ክልልን መውረር ለአገሪቱ ህዝብ ህግ አክባሪነትን ነው ህገወጥነትን ነው መንግስት እያለማመደ ያለው? የመንግስትን ስርአት አልበኝነት ያየ ዜጋ ብረት ይዞ ያሻውን ቢያደርግና አገር ቢበጠበጥ ምህላ ነው መፍትሄው ወይስ መንግስትን መገሰፅ?። አህያውን ፈርተው ዳውላውን ቢቀጠቅጡት እኮ አህያው ለጀሮው የከበሮ ድምፅ ነው የሚሆንለት። ይህ ሃላፊነትን አውቆ የችግሩ ምንጭ በትክክል ለይቶ አካፋን አካፋ እንደማለት ችግሩን በምህላ ለእግዚአብሄር ማሸከም ከተጠያቂነት አያድንም። አገሪቱ ከምትታመስበት ጦርነት ውስጥ የተገባው አሳታፊ የሆነ የጋራ አገራዊ ጉባኤ ይደረግ ብለው አብዛኛዎቹ ፓለቲከኞች ጠይቀዋል። ይህ ነገሮች ሳይበላሹ ማስተካከል ይቻል ነበር። ህወሓት ተመልሳ ትመጣለች በሚል ተልካሻ ምክንያት ህዝብን እያስፈራሩ በጋራ ስለ አገር እንዳይመከር ሆነ። አገራዊ ምክክር እንዲደረግ ዋና አስተባባሪ መሆን የነበረባት ቤተክርስትያን ራሷ በብሄር ፓለቲካ ተነክራ ልሙጥ ባንዴራ እያውለበለበችና የቤተ ክርስትያናትን ጣርያዎች እየቀባች ከኦሮሞዎችና ሌሎች ብሄሮች ጋር በእልክ አተካሮ ውስጥ ሰጥማለች። ቤተክርስትያን በተፈጥሮዋ ብሄር የላትም። የህዝቦች ዳኛ ናት። በኢትዮጵያ ውስጥ ግን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያ ጳጳሷንም በብሄር የምትለካ አስገራሚ ተቋም ናት።
Full Website