የሰልፍ ነገር፦ መቅረትም ሆነ ማርፈድ አይቻልም

ከሙሉቀን ወልደጊዮርጊስ

12/10/2021

በአዲስ አበባ ከተማ በአይነቱ ለየት ያለ ሰልፍ ለህዳር 26/2014 ተዘጋጅቷል፡፡ የሰልፉ ጥሪ ተጋሩን የሚመለከት ቢሆንም ለማድመቅ ሲባል ተመሳስለው ሰልፉን የሚቀላቀሉ ተጋሩ ያልሆኑ በሚልዮን የሚቆጠሩ ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ስለሆነም ተጋሩ ከዚህ ስብሰባ መቅረትም ሆነ ማርፈድ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡ ከሰልፉ መቅረት ማለት የኢትዮጵያ አንድነት አለመደገፍ ነው፡፡ እኔ የማስታወቂያ ሰው አይደለሁም፡፡ እንደምታዩት ማራኪ ማስታወቂያ አልሰራሁም፡፡ ይህ ማስታወቂያ በዝነኞቹ የማስታወቂያ ሰዎች በሰራዊት ፍቅሬና በሙሉ አለም ታደሰ ቢሰራ ኖሮ ምንኛ ባማረ? ለመሆኑ አገር ምድሩ መድፍ ሲተኩስ የሚያሳይ ፎቶና፤ በየሰፈሩ ሲፎክር በሚታይበት ዘመን እነኚህ ሁለት ብርቅዬ አርቲስቶች የት ጠፉ? ያም ሆነ ይህ መልካሙን እመኝላቸዋለሁ! ከላይ በተነገረው ማስታወቂያ ትንሽ መደነቃቀፍ የደረሰባችሁ አንባቢዎቼ መካከል “በዚህ ክፉ ምእራፍ ላይ ሆነን እንዲህ አይነት ማስታወቂያ መሰል ጨዋታ ለምን ያስፈልጋል?” ብላችሁ ለምትጠይቁ ወገኖቼ ይቅርታ ይደረግልኝ እላለሁ፡፡ ያው የትግራይ ህዝብ በከፍተኛ መስዋእትነት ውስጥ እያለ እንኳን ቢሆን ድል ማጣጣም ልምዱ መሆኑን ለማስታወስ ፈልጌ ነው፡፡ ለዚህም ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በአንድ ወቅት ከፈንቅል መሪዎች መካከል አንዱ ከሆነው የተደረገው ቃለ ምልልስ ይህንኑ ያጠናክርልኛል፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ባልሳሳት ሚኪ የሚባል የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ የፈንቅል አመራር አባል አንድ ጋዜጠኛ በእንግድነት ይጋብዘዋል፡፡ ጋዜጠኛው በቃለ ምልልሱ መካከል ሚኪን ቅርቃር የሚያስገባ አንድ ጥያቄ ያቀርብለታል፡፡ “ለምንድነው በርካታ የትግራይ ወጣቶች እያለቁ ባሉበት በአሁኑ ሰአት ትንሽ ድል ተገኘ ተብሎ ማታውኑ ዲያስፖራው በዊስኪ ሲራጭ የሚያድረው? ሀዘን ላይ የተቀመጠው ህዝብ አያሳዝነውም ማለት ነው?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ የሚኪ መልስም የዋዛ አልነበረም፤ የጋዜጠኛውን ወሽመጥ ቁርጥ የሚያደርግ ነበር፡፡ “ይህ ታሪክ አለማወቅ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ በጦርነት ወቅት የሚያስመዘግባቸው ድሎች በጭፈራ ያጣጥማል” ነበር የሚኪ መልስ፡፡ በእርግጥም በያንዳንድዋ መስዋእትነት ድልን ማጣጣም ማለት ቃል ኪዳንን ለማደስ፤ ብርታት ለመሰነቅ፤ በመጨረሻም በድል አድራጊነት ለመውጣት የሚያስችለው ለየት ያለ ስትራቴጂን ለመንደፍ የሚረዳ እድል አድርጎ መጠቀም የትግራይ ህዝብ በረዥም ጊዜ ታሪኩ ያዳበረው የባህሉ አንድ አካል መሆኑ ልቦና ላለው አስተምሮ ያለፈ ትእይንት አድርጌ እገነዘባለሁ፡፡ ያልተገነዘበ ካለም አሁን መገንዘብ ይኖርበታል (If you don’t know, now you know)፡፡ በዚህ የሰልፍ ዜና እንዳዳመጥኩት ከሆነ የሰልፉ አዘጋጅ አረጋዊ በርሄ እንደሆነ ምናልባትም የብልጽግና ሰዎች እነ አብርሃም በላይ፤ ሙሉ ነጋ፤ ዛዲግ አብርሃ ወይም ነቢዩ ሊኖሩበት እንደሚችሉም ይገመታል፡፡ እነኚህ ሰዎች ለስልጣን ሲሉ መሆን ከሚገባቸው በላይ እየዘለሉ እንደሆነ በዚች ጥቂት አመታት ታዝበናቸዋል፡፡ እነኚህ ሰዎች የሗሊት ጀርባቸው ሲመረመር በህወሃት ተወልደው፤ ተምረው ያደጉ ነገር ግን በክፉ ጊዜ እናት ድርጅታቸውን የካዱ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ለምን ጥለው ወጡ ብዬ አልከራከርም፡፡ የነሱ አቋም መታየት ካለበት አሁን ካለው የትግራይ ህዝብ ከደረሰበት መከራና ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እንጂ ከፓርቲ መለየትና አለመለየት መሆን የለበትም፡፡ እናም የሰዎቹ አሁን ላይ በተጻራሪ የታሪክ ገጽ ( መገኘት በራሱ ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳባቸው መሆኑ መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ስለስልጣን ሲነሳ አንድ ነገር አስታወሰኝ፡፡ የዘንድሮ ፖለቲከኛ ምን እንደነካው አልታወቀም በልጅነቴ ህልም አይቻለሁ ባዩ በዝቷል አሉ፡፡ ሰሞኑን ደግሞ አንድ ሰው ብቅ ብሏል፡፡ ይህ ሰው በብልጽግና የተቸረለትን የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ከሚሽነርነት አንሶኛል ምክንያቱም የልጅነት ህልሜ ሚነስትር መሆን  ነበር ብሎ ማኩረፉን ከውስጥ አዋቂ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ የህልም ነገር ድሮም አልነበረም ወይስ አሁን የመጣ ክስተት ይሆን? ግን የጤና ነው እንዲህ ሰው ሁሉ ህልሜ ህልሜ የሚለው? ህልሙስ ለስልጣን ብቻ ነው እንዴ! በሌላ መስክ ተሰማርቶም እያለሙ ሀገር መገንባት ይቻላል እኮ! ወደ እለቱ ርእስ ልመለስና ሰልፍ በተለያየ ቦታና ለተለያየ አላማ ይደረጋል፤ ለምሳሌም በትምህርትቤት፤ በወታደራዊ ስፍራዎች፤ የተለያዩ አገልግሎቶች ለማግኘት ወዘተ ይከናወናል፡፡ በዘመናዊው አለም መንግስታት የሚከተሉትን አፍራሽ ፖሊሲዎች ላይ ጫና ለማሳረፍ በተለያዩ አክቲቪስቶችና ተሟጋች ቡድኖች ሰልፍ ይደረጋል፡፡ በተለይም የሰላማዊ ሰልፍ (Nonviolent protest) አቀንቃኞቹ እንደነ ማህተመ ጋንዲ፤ ማርቲን ሉተር ኪንግ፤ በነ ኔልሰን ማንዴላ የሚመራ የደቡብ አፍሪካ ታጋዮች የእኩልነትና የነፃነት መብቶች መከበር የሚጠይቁ መፈክሮች በማንገብ ስርአት አንቀጥቃጭ ሰልፎች አካሂደዋል፡፡ በቅርብ አመታትም በመካከለኛውና በሩቅ ምስራቅ አገራት  የአረብ ስፕሪንግና ብርቱካናማ አብዮት በተሰኙ ግዙፍ የተቃውሞ ሰልፎች አምባገነን መሪዎች የሚይዙትና የሚጨብጡት አሳጥቶአቸው ከስልጣናቸው እንዲወርዱ አስገድዷቸዋል፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን በቀድሞ የዩኒቨርሲቲና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የእኩልነትና የሰብአዊ መብቶች ጥያቄዎች በማስተጋባት በርካታ ሰልፎች ተደርገዋል፡፡ ለዚህም ብዙ መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡ ከሁሉ የሚደንቀው ግን ባለፉት ሃምሳ አመታት የመንግስት የ‘ይደግፉኝ ሰልፍ በርከትከት ያለበት ሀገር እንደ ኢትዮጵያ ያለ አገር የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በኢትዮጵያ የሰላማዊ ሰልፍ ታሪክ ውስጥ የ1997ቱ ሚያዝያ 29 እና 30 በመስቀል አደባባይ የተደረገው አሁን ደግሞ ልክ በ31 አመቱ እሁድ ህዳር 26 በአበበ ቢቂላ ስታዲዮም የተደረጉት ሰልፎች የሁለት አገር ወጎች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በሰልፉ የተሳታፊው ቁጥር፤ በአላማውና በአፈጻጸማቸው የተለያዩ ሆነው በታሪክ መመዝገባቸው የማይቀር በመሆኑ ለጊዜው በዚህ ልለፈው ነገር ግን በሁለቱም ሰልፎች መካከልና በተሳታፊዎቻቸው ሰፊ የሞራል ልዩነት ያለው መሆኑ ጠቅሶ ማለፍ ጠቃሚ ነው፡፡ የሚያዝያው ሁለቱ ሰልፎች በሁለት ግልጽ ሆነው በወጡ የሃገረ ግንባታ ፖሊሲዎች ዙሪያ የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን ወደ መድረክ ያመጣ፤ በሃሳብና በሃሳብ ብቻ የተመሰረተ፤ ለዲሞክራሲና ለነፃነት በነፃነት የተደረገ ፍጹም ሰላማዊ ሰልፍ ሲሆን የህዳሩ ሰላማዊ ሰልፍ ደግሞ በማስታወቂያው ላይ እንደሰፈረው መቅረትም ሆነ ማርፈድ አይቻልም፤ በሰልፉ አለመገኘት ማለት የኢትዮጵያን አንድነት አለመደገፍ ነው ተብሎ አንድን የማህበረሰብ ክፍል (ተጋሩ) በማሸማቀቅና በማሸበር እንዲሰለፍ የተደረገ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ከሶስት አመት ወዲህ በተለይም የትግራዩ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ማግስት ጀምሮ ባለው የአንድ አመት ጊዜ በተለይም በውጭ ሀገር ጎዳናዎች በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል ጎራ ተለይቶ በአንድ በኩል ለፍትህ የሚጮሁ ድምጾች በሌላ በኩል ደግሞ ፍትህ ጠያቂዎችን ለማሸማቀቅ ይልቁንስ የመጠየቅ መብት የለህም ዝም ብለህ ተረገጥ፤ ተዘረፍ፤ ሙት በሚሉ ሃይሎች እጅግ እልህ አስጨራሽ ሰልፎች ተደርገዋል፡፡ አሁንም በመደረግ ላይ ናቸው፡፡ ይህንኑ ተከትሎም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ገሚሱ ለተበደሉት ውግንናውን ሰጥቶ ጥቂቱን ደግሞ ጥቅሙን በማስላት በበዳዮቹ ጎን በመሰለፍ ገመዱን ሲጎትቱ እንመለከታለን፡፡ በዚህ በእጅጉ በተቋጠረ ጦርነት የተጠላለፉት የአለማአቀፉ ማህበረሰብ ከላይ በተጠቀሰው ዋልታ ረገጥ ጫፍ ላይ የመገኘት ሚስጥሩ ከመንግስታቱ ባህርይ የሚመነጭ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የተበዳዩን ሰቆቃ ከመጤፍ ሳይቆጥሩ ጥቅማቸውን በማስላት ረድፍ ላይ የምናገኛቸው እንደ ቻይና፤ ሩስያ፤ ኢራን፤ ሳውዲአረቢያ፤ ቱርክና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በሃገራቸው ሰልፍ እንዲካሄድ የማይፈቅዱ፤ ሰልፈኛ ቢጋያጥማቸው በላዩ ላይ ታንክ የሚያስኬዱ፤ ምርጫ አለርጂክ የሆነባቸው፤ ጋዜጠኞች የሚታሰሩባቸው፤ የመናገር የመጻፍና የመደራጀት መብትን አጥብቀው የሚኮንኑ ከመሆናቸውም በላይ እነሱ የሚያምኑበትን በሃይል አንበርክኮ መግዛትን ወደ ሌሎች ሃገሮች ኤክስፖርት ለማድረግ የሚያስችላቸውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ በማጧጧፍ ኪሳቸው የሚያሞቁ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በመሆኑም በበዳዮች ጎን የመቆም እጣ ፈንታቸው ሊደንቀን አይገባም፡፡ በአንጻሩ በትግራይና ብሎም በሀገሪቱ እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ ክስረትን አሳስቧቸው ግድያውና መፈናቀሉ እንዲቆም፤ የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ ኮሪዶሮችን ክፍት እንዲሆኑ የሚጠይቁ መግለጫዎች እጅግ በርካታ በሚባሉ ወቅቶች በማውጣት ቀሪው አለም እንዲያውቀው በማድረግ ላይ የሚገኙ አገሮች እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ መግለጫዎቹ ጠቃሚ የመሆናቸውን ያህል በተጨባጭ እርምጃ አለመደገፋቸው አንዳንዴም በሚዋዥቅ አቋማቸው በሌላኛው ዋልታ ለሚገኙ የበደል አድራሽ ደጋፊዎች የልብ ልብ በመስጠት  ያልተቋረጠ ድጋፍ እንዲያደርጉ በመበረታት በተበዳዮች ላይ የሞትና የስቃይ በትር እንዲጠናከር ማድረጉን ልብ ልንለው የሚገባን ሀቅ ነው፡፡ አሁን አሁን የአለም አቀፉ ገመድ ጉተታው ለሁሉም ግልጽ የሆነ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ለሰሚ ግራ የሚያጋባው ግን የራስህ ወገን የሆነ አንድ ማህበረሰብ ያለፍርድ ቤት ውሳኔ የኔ በሚለውና በተገዙ ወታደሮች እየተገደለ፤ ህልሙን ለማሳካት ደፋ ቀና የሚል አያሌ ወጣት ከህልሙ ተስተጓጉሎ ለፍልሰት በተዳረገበት፤ ለአመታት በላቡ ያከማቸውን ንብረትና ሃብት በወራሪ ሃይል እየተዘረፈበት፤ ለአቅመ አዳም ያልደረሰች ህጻን፤ መኖክሴዎችና አሮጊቶች በጋጠወጥ የመንግስት ወታደሮች እየተደፈረች፤ ሚሊዮን ህዝብ በራሱ መንግስት እህል እንዳያገኝ ተከልክሎ እየተራበ፤ በተቀረው አገሪቱ እንደማንኛውም ዜጋ በሰላም በመኖሩ ብቻ በራስ ወገን እየተሰቃዬ ያለን ህዝብ ሰቆቃውን አጣጥለህ ግድያው፤ መደፈሩ፤ ዝርፊያው በሌላ በኩል የህዳር 26ቱ የአበበ በቂላ ስታድዮም የተጋሩ ሰልፍ ትእይነት በንጹህ ልቦና ለመረመረ ሰው የሰልፉ ተሳታፊና የእለቱ የሰልፉ አላማ ሊያስከትል ከሚችለው ውጤት ጋር አነጻጽሮ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ሆኖ ያገኘዋል፡፡ አስተባባሪዎቹ አንድም ማሰብ የተሳናቸው ወይም በሽተኞች ናቸው፡፡ በሰልፉ ላይ አሰፈራርተው እንዲገኙ ያደረግዋቸው ሰዎች እኮ ገሚሱ ቤተሰቡ የታሰረበት፤ የተገደለበት፤ ራሱ ወይም ቤተሰቡ ከስራ የታገደበት፤  በግራና በቀኝ ስርአቱ በለቀቃቸው አስበርጋጊዎች በየእለቱ በሚያስጨንቁበት ወይም አሁን ባለው ሁኔታ ትግራይ ውስጥ የሚኖሩ የቤተሰቦቹ የደህንነት ሁኔታ ወሬ ማግኘት ያልቻለበት፤ ትግራዋይነት የሀገር ስጋት ሆኖ በመቆጠሩ የሚወዳትን ሀገሩንና ወገኑን ጥሎ የተሰደደበት፤ በአጠቃላይ በትግራዋይነቱ ፍዳ እያየና ሲኦል እየኖረ ባለበት ወቅት ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ግፍ አድራጊዎቹ ልክ ናችሁ፤ ቀጥሉበት በማለት ሰልፍ ወጥቶ እንዲደግፍ የሚጠበቀው? ይህ ግብዝነት ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ከቀሪው ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር ሲሰለፍ የሚያምርበት የአክሱም ጽዮን ክብረ በአል በጨዋ ባህሉ አብሮ በአሉን ሲያደምቅ፤ የአፍሪካ የጀግንነት ገድል ማሳያ የሆነውን የአድዋ በአል ሲያከብር እንጂ ዘመን ሰጥቶአቸው በስልጣን የሰከሩ ሰዎች ከባእድ ሀገሮች ጋር በመተባበር በህይወቱና ጥሮ ግሮ ባፈራው ንብረቱ ላይ ለአለም በሚያስገረም መልኩ የተከናወነውን ወንጀል ደግፎ ማውገዝ በተጠራው ሰልፍ ላይ መሳተፍ እንደማይሆን የሰልፉ አስተባባሪዎች ልቦና ያውቀዋል፡፡ እዚህ ላይ ሁሉም በጥንቃቄ ማስተዋል የሚገባው የተጠራው ሰልፍ ከትግራይ ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎትና እምነት የሚፃረር መሆኑ፡፡ ከትግራይ ህዝብ የረጅም ጊዜ የእኩልነት፤ የፍትህና የነፃነት እሴቱ ጋር የሚጋጭ መሆኑ ነው፡፡
Full Website