muluwold2021@yahoo.com

ልዝብ ሰይጣንነት፡ ብሄራዊ በሽታ የመሆኑ ማሳያዎች

ከሙሉቀን ወልደጊዮርጊስ

12/1/2021

ዋሽንግተን ዲሲ

ይህንን ርእስ ለመጻፍ ስጀምር ቀኑ የሚካኤል እለት በመሆኑ በዚህ ቀን እንዴት በዚህ ርእስ ትጽፋለህ ብሎ ውስጤ ሞግቶኝ ነበር፡፡ ሆኖም ስለሰይጣን ከተነሳ ሚካኤል በጦሩ ሰይጣንን ሲወጋ የሚታየውን ምስል አስታውሼ ልክ መሆኔን ለራሴ በማሳመን ከውስጤ ፈገግ በማለት መጻፌን ቀጠልኩኝ፡፡ በዛውም ልዝብም ይሁን ሙሉ ሰይጣን በደረሱበት ቦታ ሁሉ ተገኝቶ በሽታቸውን ማጋለጥ ብሄራዊ ግዴታዬ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ስለልዝብ ሰይጣን ያስታወሰችኝ እቺ ቀን ረዘም ላሉ አመታት ካልተገናኘሁት አንድ ወዳጄ ጋር በዋሽንግተን ዲሲ ተገናኝተን ሃሳብ ለሃሳብ በተለዋወጥንበት ወቅት ላይ ነበር፡፡ በ70ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ገደማ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምማርበት ወቅት አንድ እንደእኔ ከክፍለ ሀገር ከመጣ ጋር ጥብቅ ጓደኝነት መስርተናል፡፡ በክፍል እና ከክፍል ውጭ ባሉ ውሎአችን አንለያይም፡፡ በክፍል ውስጥ አጠገብ ላጠገብ እንቀመጣለን፤ ወደ ላይብረሪ አብረን እንሄዳለን፤ ተጠባብቀን ወደ ምግብ አዳራሽ በመሄድ እንመገብ ነበር፡፡ እንደዚሁም እግር ለማፍታት ከግቢ ውጭ አብረን እንቀሳቀሳለን፡፡ ታዲያ ከክፍል ተማሪዎቻችን መካከል ከአዲስ አበባ የመጡ ሁለት ተማሪዎች በመሳው ጓደኝነት ፈጥረው የኛን በጋራ መንቀሳቀስ በትኩረት ይከታተላሉ፡፡ በአጋጣሚም ይሁን በምክንያት በምንሄድባቸው ሁሉ እናገናቸዋለን፡፡ አንዳንዴም በድብቅ በሚያሳብቅ መልኩ፡፡ ታዲያ ይህ የተመለከተው አስተዋዩ ጓደኛዬ ለእነኚህ ልጆች ‘ልዝብ ሰይጣኖች' ብሎ ስም አወጣላቸው፡፡ በሗላ ላይ ስንቀራረብ የወጣላቸውን የዶቦ ስም ነግረናቸው እነሱም የኛን ባለ‘ገራገርነት' መመልከት በጣም ያስደስታቸው እንደነበረ ሲገልጹልን መሳቃችንን አስታውሳለሁ፡፡ መቸስ  በዩኒቨርሲቲ ቆይታ የአዲስ አበባ ልጆች በነሱ ቋንቋ ‘የአራዳ ልጆች' በካፊቴሪያ፤ በገላ መታጠቢያና በልብስ አጠባ ገንዳ፤ እንደዚሁም በላይብረሪ በባለ ‘ገራገሮቹ' ላይ ሲያደርጉት የነበረውን ተንኮል የታከለበት ድርጊት ቀልድ ብጤ ቢመስልም በአንዳንድ ባለ ‘ገራገሮች' የምር ሆኖ ለስነልቦናዊ ጥቃት መዳረጉ ማስታወሱ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ በአንድ ሀገርና ሀገር በሚያሰኝዋት ህዝቦች ላይ መሪዎች ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው ቢባል ትክክል ይመስለኛል፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ዲሞክራሲ ያልዳበረባቸው ሀገሮች መሪዎች በአጠቃላይ አስተዳደር፤ በኢኮኖሚና ፖለቲካ እና በባህል ረገድ ከፊት ሆኖ በመምራት የሚጫወቱት ሚና በእጅጉ የላቀ ነው፡፡ ሕብረተሰቡ የሚመሩበትን የሚቆጣጠሩበትንና የእለት ተእለት አኗኗሩን የሚወስኑ ተግባራት ይወጥናሉ፤ ይተገብራሉ፤ ይፈጽማሉ፤ ወይም በፈጠሩዋቸው ግልጽና ድብቅ መዋቅሮች አመካኝነት እንዲፈጸም ያዛሉ፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የመንግስት አስተዳደር ካላቸው ሀገሮች መካከል በቀደምትነት ከሚጠቀሱት አንድዋ እንደመሆንዋ መጠን በተለያየ ጊዜያት ያለፉና አሁን በመምራት ላይ በሚገኙ መሪዎች የግል ፍላጎት፤ ባህርይና እምነት መሰረት የየራሳቸው የሆነ ውድ ስጦታ አበርክተዋል ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌም ሚኒሊክ ወደ ተለያየ ቦታዎች በመዝመት ግዛታቸውን አስፋፍተው አንድ የማደረግ ስራ፤ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዘመናዊ ትምህርት በማሰረጽ ረገድ፤ መንግስቱ ሃይለማርያም የሶሻሊዝምን ስልተምርትና ማህበረሰብ ለመፍጠር መሞከር፤ መለስ ዜናዊ ህብረብሄራዊነትን በማቀንቀን ልማት ማስፋፋት አሁን ደግሞ ያሉት መሪ አብይ አህመድ ቀጥዬ ለማቀርበው ጽሁፌ መነሻ የሆነውን የፕሮፖጋንዳና ውሽት በማንበር ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ አራት አመት ሊደፍን ጥቂት ወራትን የቀረው የአብይ አህመድ መንግስት ለዛሬ ለመረጥኩት ርእስ የፕሮፖጋንዳና ውሸት ወረርሽኝ መስፋፋት የሚያስረዲልኝ በርካታ ሙግቶች ለማቅረብ የሚቻል ሲሆን አንዳንዴም አብይ ራሳቸው በተለያየ መድረክ የሚሰሩት ተውኔታዊ መደነቃቀፍ መመልከትና ማጤን የርእሱ ተአማኒነት ያጠናክርልኛል ባይ ነኝ፡፡ ይህ ደግሞ ፕሮፖጋንዳውና ውሸቱ በታቀደ፤ በተጠናና በተቀነባበረ መንገድ የሚከናወን መሆኑን መረዳት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የሀገሪቱ መሪ ለህዝብ በሚያደርጉዋቸው የቀጥታ ንግግርና በጋዜጠኞች የተነገሩትን ምልልሶች ላይ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው የፕሮፖጋንዳና የውሸት መድብሎች እየነቀስን ማውጣት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው የውሸት ፊሽካ የተነፋው ህዝቡ ሰከን ብሎ ባለማሰብ በግብታዊነት ሲያራግብ የነበረውን “የ27ቱ አመት የጨለማ ዘመን” ትርክታቸው ሲሆን የፀሃይ መጥለቅ መዳረሻው ወቅት የተለቀቀ አዲስ ዜማ ደግሞ በአንድ በግራር የተወረረ መሬት ላይ ከግል ጠባቂዎቻቸው በስተቀርና አንዲት በተቆፈረች ምሽግ አጠገብ ሆነው ስለተናገሩት ጉዳይ ሆኖ እናገኛዋለን፡፡ ከዚህ በሗላ የፕሮፖጋንዳና ውሸት መድብሎች ስለመቀጠላቸውና አለመቀጠላቸው ወደፊት የምናየው ሲሆን እስካሁን በሰማናቸው የውሸት አልፋና ኦሜጋ መካከል  አስነዋሪ የሆኑ በርካታ ሀገራዊ ውርደቶች፤  የብቁ አያሌ ዜጎችን አንገት የሚያስደፉ፤ ለተናጋሪው ሞገስ ለተከታዩች ደግሞ ጉርሻና ሹመት የሚታደልበት ሆኖ ሲታይ አቢይ አህመድ ለነገው ትውልድ ታሪክ ይቅር የማይለው ትምህርት እያቀበሉ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የሆነው ሆኖ ርእሱ ሰፊ መድብል የሚወጣው ስለሆነ የአልፋውን ትተን የፕሮፖጋንዳና የውሸት መደበላለቅ ሊያስረዳልኝ የሚችለውን የቅርቡን ጉዳይ ላንሳ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦር ግንባር ማምራታቸውንና በብርሃን ፍጥነት አንድ አካባቢ የሚገኝ ተራራ ማስለቀቃቸው ራሳቸው በቴሌቭዝን ብቅ ብለው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ እሱ ላይ ችግር የለብኝም፤ ያው ሄጃለሁ ያሉትም ለዛው ጉዳይ ስለሆነ፡፡ ችግር የሚሆነው የፕሮፖጋንዳውና የውሸት ሰበዙ መላለጥ ሲጀምር ነው፡፡ በጦር ግንባር ተገኝተህ ፎቶ ልትነሳ ትችላለህ፡፡ ይህ ፕሮፖጋንዳ ነው፡፡ ህዝብ ለማነሳሰት ይጠቅማሃል፡፡ ነገር ግን በሌላ ሃይል ተይዞ የነበረን መሬት በቁጥጥርህ ስር ሳታደርግ ይዣለሁ ብትል ውሸት ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም በመሬት ላይ ያለውን ሀቅ ክደህ እያወራህ ነው ያለከው፡፡ ያውም የቆምክበት ቦታ ምንም ተራራ አለመኖሩ ሲያሰብቅብህ ጉዳዩ ከፕሮፖጋንዳ ቀይ መስመርነት አልፎ ጭው ባለው የውሸት በረሃ ውስጥ ራስህን ታገኘዋለህና፡፡ በአናቱም ከውስጥ አዋቂ ተገኝ የተባለውን የዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ ሚስጥራዊ መረጃና የሌሎች አለምአቀፍ ሚዲያዎች ዘገባ ስትደርብበት የፕሮፖጋንዳውና የውሸት መደበላለቅ ፍንትው አድርጎ ያሳይሃል፡፡ የፕሮፖጋንዳውና ውሸት መለየት አለመቻሉ ሀገሪቱ ለከፍተኛ ኪሳራና ስብራት እየዳረጋት መሆኑን መረዳት የቻለ ዜጋ አለመኖሩ ወይንም በዝምታ ማለፉ እጅጉን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ በተለይም ሀገር ተረካቢ የሆነውን ትውልድ ማንነት በመቅረጽ ሚና ያላቸው ተቋሞች (የሃይማኖትና የትምህርት ተቋሞች) ፡፡ ምርምር በሚያስፈልገው ጉዳይ ለምን ይህ ተፈጠረ ብዬም አንባቢዎቼን ለጊዜውም ቢሆን አላሰለችም፡፡ ነገር ግን በሃገሪቱ አሁን እየተከናነወነ ያለው እኩይ ተግባር ለመሪው አካል የሙሉ ሰይጣንነት ካባ የሚያስደርብ እንደሆነ ቢሰማኝም ይህንን ለማየት የተሳናቸው አሁንም በርታ እያሉ ድጋፍ ለሚሰጡት ሰዎችና ተቋሞች የልዝብ ሰይጣንነት አቅም እንዳላቸው መረዳቱ አይከፋም ባይ ነኝ፡፡ ይህንን ሃቅ ይበልጥ እየተረዳን በመጣን ቁጥር በሀገር ላይ እያደረሰ ያለውን ጥልቀት ያለው ጠባሳ ባሰብን ቁጥር ልብን በእጅጉ እያደማ ያስጨንቃል፡፡ ይህንኑ መሰሪ መገንዘብ ያልቻሉ በርካታ ወገኖች መኖራቸው መመልከትም ይገርማል፤ ያሳዝናልም፡፡ ለፖሮፓጋንዳ ተብሎ በብሄራዊ መገናኛ የሚቀርቡ ምስሎችና ንግግሮች ብስልና ጥሬውን ያልለዩ ፤ እየገዘፉና የእለት ተእለት የመሆናቸው ጉዳይም ብሄራዊ ቅርጽ እየያዘ ለመምጣት ጥሩ ማሳያዎች ናቸው እላለሁ፡፡ የውሸት መድብሉ በሀገር ደረጃ ላለው ህዝብ ብቻ ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን አድማሱን በማስፋት ከአለምአቀፍ ድርጅት መሪዎች አንስቶ እሰከ የመንግስታት መሪዎች ያካተተ ሲሆን ጉዳዩ የምር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የሚያቅዱት የሚገብሩትና አፈጻጸሙን የሚከታተሉት መሪ ለረዥም ጊዜ የተጣባቸውና በልምድ የዳበረ መሆኑን እንረዳለን፡፡ እንዲህ አይነት ሰውንና ሀገርን ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረ ሰው ሲያጋጥማቸው (ውሸት በደምስሩ የተዋሃደው እንደማለት ነው) ፈረንጆች የባህርይ ማንነቱ ለመግለጽ የሚጠቀሙበት ስያሜ አላቸው (pathological liar) ይሉታል፡፡ ሰዎች አንድን ነገር እንደልምድ ለማዳበር የሚችሉበት መንገድ የሦስት ቅደም ተከተል ያላቸው ውህድ መስተጋብሮች ውጤት መሆኑን ማየት ይኖርብናል፡፡ አንደኛው የማሰብ ስራ የሚያከናውነው ጭንቅላት ወይም አእምሮ (Mind) ሊኖር ይገባል፤ ሁለተኛው የባለ አእምሮው መልካም ወይም በጎ ፈቃደኝነት/ፍላጎት (Will-decision making) ሊኖር ይገባል፤ ሦስተኛው በተደጋጋሚ እንድትሰራው የሚያበረታታህ ወይም የሚያነሳሳህ የተጋጋለ ስሜት(Emotion) ሊኖርህ ይገባል፡፡ በአጭር አረዳድ አንድን ልምድ ሊሆን የታሰበ ጉዳይ ቀጥሎ በተመለከቱት ሦስት እርከኖች ወይም ሂደት ተፀንሶ፤ ተወልዶ ከዚያም ያድጋል፡፡ በመጀመሪያ ጭንቅላት ወይም አእምሮን በመጠቀም አንድን ሃሳብ ማመንጨት ያስፈልጋል፡፡ የምንሰማቸው፤ የምናያቸውና የምንዳስሳቸው ሁኔታዎች ለሃሳቡ ማመንጫና ማጎልበቻ ጠቃሚ ግብአቶች ይሆናሉ፡፡ በሁለተኛው እርከን ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተን ደግመን ደጋግመን ባነሳነውና በጣልነው ቁጥር በአእምሮአችን የውሰጠ ህሊናው ክፍል (Sub-conscious) ተደላድሎ መኖር ይጀምራል፡፡ አንዲህ ተደላድሎ መኖር የጀመረው ሃሳብ በተፈለገ ሰአትና ባሰኘ ጊዜ በማስታወስ ለመጠቀም እድል ይኖረዋል፡፡ በሶስተኛ ደረጃም የአላሚውን የስሜት ፍላጎት ለማርካት በሙሉ ፈቃደኝነት ወደ ተግባር መተርጎም ይጀምራል፡፡ የተግባር ድግግሞሹ የደስታ ወይም የሀዘን የተጋጋለ ስሜት ውስጥ እንድንገባ ያደርጋል፡፡ ድግግሞሹ የጉዳዩ ውጤት ምን ይሁን ምን ሳያስጨንቀው ይቀጥላል፤ ይህ ደግሞ አብሮ ለሚያድገው ልምድ ለተባለው አዋላጅ፤ ለአላሚውም መገለጫ ባህርዩ ይሆናል፡፡ ልምዱም በዚህ መልክ አድጎና ዳብሮ በግለሰብ፤ በቤተሰብ፤ በማህበረሰብና በሀገር ደረጃ ለብዙ እድሎች ወይም ምስቅልቅሎች ይዳርጋል ማለት ነው፡፡ ለማጠቃለል ያህል የጥሩ ሃሳብ መዳረሻው ሰላም፤ ፍቅር፤ መተሳሰብ፤ ተስፋ፤ ልማትና እድገት የመሳሰሉት የበጎ መንፈስ ውጤቶች ሲሆን የመጥፎ ሃሳብ ማሳረጊያው ደግሞ የክፉ መንፈስ ውልጃ የሆኑትን ውስልትና፤ አታላይነት፤ መጠፋፋት፤ ክፋት፤ ተንኮል፤ ነገር ጫሪነት፤ አፈጩቤነት ይሆናል፡፡ በምሳሌነት የተጠቀምኩበት የፕሮፖጋንዳና ውሸት ወረርሽኝ በመሰረታዊ አፈጣጠሩ ሲታይ ያልሆነውን ጉዳይ እንደሆነ፤ ያልተፈጠረውን ነገር እንደተፈጠረ አድረጎ መንገር ወይም ማውራት ነው፡፡ በድግግሞሽ የፈጣሪውን ክንድ እያፈረጠመ አዳዲስ ስልቶችንና ቀመሮችን በማከል ወረርሽኙ ወደ ከፍታ እንዲመጣና አሁን እንደምናየው ብሄራዊ ችግር እስከመሆን ያደርሳል፡፡ አንዴ እዚህ ደረጃ ላይ ለደረሰ ሰው ከህመሙ ለመፈወስ ብርቱ የሆነ የባለሙያዎች ክትትል እንደሚያስፈልገው በመስኩ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ ያዳቆነ ሳያቀስስ አይቀርም እንደሚባለው በዚህ ልምድ የተለከፈ ሰው ወደ ጤናማነት ለመመለስ አታካች ቢሆንም ወደውስጥ የገባን መርዝ ጥንቅቅ አድርጎ ለማስወጣት የሚረዱ ምክረ ሃሳቦች በተመለከተ በዚህ ጉዳይ አዘውትሮ ሲናገር የሚደመጠው የዶ/ር መይልስ ሙንሮ Taking Control of Your Mind ማዳመጥ የሚረዳ ይመስለኛል፡፡ ወይንም የአገሩ በሬ በአገሩ ሰርዶ እንዲሉ “ምነው እናቴ የእንቁላሉ ጊዜ በመከርሽኝ” አባባል በእንጭጩ ለመቅጨት መካሪዎችን ከልብ ማዳመጥ የሚጠቅም እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ አቢይ አህመድ በሚድያ ብቅ ባሉ ቁጥር ውሸት መሰል ጉዳይ ጣል ሳያደርጉ አያልፉም ብለው የሚከራከሩ በርካታ ወገኖች አጋጥመውኛል፡፡ በተነጻጻሪነት ለብዝሃኑ ክፍት ባልሆኑ ስብሰባዎች ላይ ከስራ ባልደረቦቻቸው፤ ከቅርብ ረዳቶቻቸው፤ ከጎስፕል ተከታዮቻቸው፤ ከአማካሪዎቻቸውና ሚኒሰትሮቻቸው ጋር በሚያደረጉት የተለያዩ ግንኙነቶች በርካታ ውሸት ያዘሉ መልእክቶች አስተላልፈዋል ብሎ ለመከራከር የሚያበቁ በርካታ ማስረጃዎች መጠቃቀስ ይቻላል፡፡ የዚህ ድምር ውጤት ደግሞ ሀገርን በመምራት ሚና ያላቸው ሰዎችና በዙሪያቸው የሚሰባሰቡ አያሌ ሰዎች ውሸትን ያጠምቃሉ፤ ማህበረሱ ውስጥ እንዲያሰራጩ ያደፋፈራሉ በመጨረሻም የውሸት ሱስ ተገዥ እንዲሆኑ ይገፋፋሉ የሚል ማጠቃለያ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ እንዳውም የአንዳንድ ባለስልጣኖቻቸው በተግባር የአፍ ማላቀቃቸው ለተመለከተ ሀገሪቱ ወሸትን ያለሃፍረት በአደባባይ የሚለፍፉ ባለስልጣኖች በዘመንዋ እንደአሁኑ ወቅት ገጥሟት አያውቅም የሚለውን እውነትኛነት የሚያረጋግጥ ይመስለኛል፡፡ ምን ይህ ብቻ አሁን አሁንማ ነጋዴው፤ አርቲስቱ፤ አትሌቱ፤ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች በስፋት ወደ ቡድኑ ተቀላቅለዋል፡፡ በዚህ ረገድ የፕሮፖጋንዳና የውሸት ልማቱ (ልምዱ) ሀገራዊ ቅርጽ የማስያዝ ተልእኮው በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ እንዳለ አመላካች ያደርገዋል፡፡ ከሁሉም ለሰሚው ግራ እያጋባ ያለው ይህ አገራዊ በሽታና ድርቀት ከሃገር አልፎ ሌሎችም እንዲደነዝዙ የአብረን እናልቅስ ነጋሪት ጉሰማው ነው፡፡ ከጽሁፎች አንስቶ በየሶሻል ሚድያው ብሎም በሃገር ውስጥ በየኤምባሲዎቹ በር እንደዚሁም በነዳንኤል ክብረት ሳይቀር የተሰደበው ዲያስፖራ በሰላም በሚኖርባቸው አገራት የሚያደርጋቸው ሰልፎችና ካንዳንድ ሰዎች ያጋጠሙኝን ጭፍን ምስክርነት የውሸት ባህል ግንባታው ስራ ምን ያህል ስር የሰደደ እንደሆነ ማርከሻውም አርቆ እንደተቀበረ ልገነዘብ የምችልበትን አድል ለማግኘት ችያለሁ፡፡
Full Website